Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትአልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለፋና ቲቪ በሰጡት ባለ ሁለት ክፍል ቃለ መጠይቅ ውስጥ፣ ‹‹አገር የሚያጠፋ ባለጌ ስድብ፣ የማጋጨትና የማዋጋት ክፉ ሐሳብ ከምን መጣብን!? ተዋጋን ተዋጋን! መቼ ነው የሚበቃን!…›› በሚል መልክ የሰላም ማጣት እንቆቅልሻችንን ደጋግመው አንፀባርቀው ነበር፡፡ ፊልድ ማርሻሉን ግራ ያጋባቸውንና አልፈታ ያለ ጉድ ያፈራነው እኛው ነን፣ ትናንትና የነበርንና ዛሬ ያለን ሰዎች፡፡

1) ገታራነት፣ ጀብደኝነት፣ አለመፍራትና አለማፈግፈግ ከጉብዝና ጋር መዛመዱ፣ ጥፋትን ተረድቶ አጥፍቻለሁ ማለትና ትክክል ሲባል ከነበር የስህተት መንገድ ለመውጣት መሞከር፣ ተሰሚነትንና ተከባሪነትን ከማሳነስ ጋር መዛመዱ የቆየ ቅርሳችን ነበር፡፡ ይህ የአስተሳሰብ ሙሽት በ1960ዎቹ ትውልድ ትግል ላይ ተፅዕኖውን አሳድሯል፡፡ ‹‹ተራማጅነት›› የመታወቂያ ፈርጅ ከመሆን አልፎ፣ ስህተቶችንንና ጥፋቶችን በትግል ልምድ ውስጥ እየመረመሩ፣ እየለዩና እያረሙ የመጓዝ ባህርይ ለመሆን አልቻለም ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ግልጽ የወጡ ጥፋቶችን ማረም ተስኗቸው ትግላቸው ከተሰባበረ በኋላ፣ ‹‹ትግል›› የሚባል ነገር ወዲያው ያስወረዳቸው ፖለቲከኞች ወደ ፆመ ሃይማኖተኝነት ዞሩ፣ ቀድሞ ወደ ነበራቸው አስተሳሰብ ለመመለስና ትግልን ለመርገም/መሳለቂያ ለማድረግ/‹‹ማረን ኢምፔሪያሊዝም›› ለማለት ተቻኮሉ፡፡ ‹‹የመላ ኢትዮጵያ ጠጪዎች ማኅበር (መኢጠማ) አባላትን ነን›› እስከ ማለት ድረስ ለዝቅጠት ጉዞ እጅ የሰጡም ነበሩ፡፡ ትግል በቃን ባይሉም፣ ቁዘማ ውስጥ የገቡም ጥቂት አልነበሩም፡፡ ፖለቲካን የቅጥቀጣ መሣሪያ እስከ ማድረግ የሠለጠነው ደርግ፣ የትኛውም ዝንባሌ ውስጥ የነበሩትን ተሸናፊዎች ዝም ብሎ አልተዋቸውም፡፡ ‹‹የበደሉትን አብዮት›› በመካስ ተግባራት ውስጥ (በመንግሥታዊ የአፈና ቢሮክራሲው ውስጥ፣ በፓርቲ ሥራ ውስጥ፣ በርዕዮተ ዓለም – ፖለቲካ ቱልቱላ ነፊነት ውስጥና በአጨብጫቢ ኪነት ውስጥ ሁሉ) አሰማርቶ እንደ ቅሪላ እያሸ የትግል ስሜታቸው ዳግም እንዳያግት አድርጎ የማኮላሸት ሥራ አካሂዷል፡፡

የደርግ አጋዥ ከነበሩትና ከደርግ መንጋጋ ተርፈው ደርግን በማገልገል የቀጠሉትም ‹‹ተራማጆች›› የጌታቸውን ማንነትና የእነሱን ሎሌነት በደንብ አውቀው ሽር ያሉ ነበሩ፡፡ አሁን በ2014 ዓ.ም. ‹‹የሻምላው ትውልድ›› የተሰኘ መጽሐፍ የጻፈው ፋሲካ ሲደልል ይህንን ባይክድም፣ ሃምሳ ዓመት ሊሞላው ትንሽ ከቀረው የጊዜ ቆይታ በኋላ እንኳ፣ የደርግ ባለሥልጣን ሎሌ በነበረበት ዘመን ‹‹የሶሻሊስት አብዮት››ን ስለማካሄዳቸው ማውሳቱ፣ እዚህ አገር ውስጥ ምን ያህል እውነታን በትክክል የማስተዋልና የመረዳት ችግር እንደሠለጠነ የሚመሰክር ነው፡፡

ፋሲካ ሲደልል በመጽሐፉ ስለጊዜው ትምህርትም እንዲህ ይለናል፣ ‹‹… በእኛ ዘመን ትምህርት የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማፋጠን የሚያግዙ ሙያተኞችን ብቻ ሳይሆን፣ በርዕዮተ – ዓለም ዕውቀታቸው፣ በፖለቲካ አመለካከታቸው የሶሻሊስት ሥርዓት ለመገንባት የሚካሄደውን ትግል የሚያጠናክሩ፣ አብዮታዊ ወጣቶች የሚመረትበት የፖለቲካ መድረክም ሆኖ ነበር፡፡ ከዚህ አጠቃላይ እምነት በመነሳት … የመማር ዕድልን ለማስፋፋት… ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡›› ይህንን ብሎም የተማሪዎችን ቁጥርና የትምህርት ቤቶችን የቁጥር ዕድገት እየደረደረ ዕድገቱን ሊያሳምነን ይሞክራል (353-4)፡፡ በመማርያ ክፍል የነበረው የተማሪ ቁጥር ሥርጭት ምን ያህል ለመማር አዋኪ እየሆነ እንደሄደ፣ ካድሬያዊና ፕሮፓጋንዳዊ ሥራዎች የትምህርት ባለሙያዎችንና ተማሪዎችን ከትምህርት ተግባር ላይ ምን ያህል ያጓድሉ እንደነበረ አይናገርም፡፡ በተጓደለ ትምህርት ላይ የምዘና ብልሽትና በግፊት/በኮታ ማሳለፍ ስላደረሰው በደል ትንፍሽ አይልም፡፡ ከዚህ በላይ ሰፊ ትችት ውስጥ የመግባት ፍላጎት የለኝም፡፡ አንድ ነገር ግን በጥቅሉ ልናገር፣ በመንግሥቱ ኃይለ ማርያም መሪነት ሥር ሆነው እነ ፋሲካ ሲደልል ያካሄዱት ‹‹አብዮት››፣ በኢትዮጵያ ታይቶ የማይታወቅ የሰብዕናና የተቋማት የሥራ ባህል ውድቀትን እንደ ወረርሽኝ ያስፋፋ የዝቅጠትና የንቅዘት፣ የአድፋፊነት፣ የአጨብጫቢነት፣ የፍርኃትና የግለሰብ አምልኮ ‹‹አብዮት›› ነው፡፡ ሶሲዮ ኢኮኖሚው፣ ወጪና ገቢ ንግዱ፣ ክፍፍሉና ጠቅላላ የማኅበራዊ ኑሮው ሥርዓት፣ (የፀጥታ፣ የፍትሕ፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የመጓጓዣ፣ ወዘተ. ዘርፉ ሁሉ በፖለቲካዊ ቢሮክራሲያዊ ዋጤነትና ምጥመጣ፣ በልሽቀትና በእጥረት፣ (በአድልኦ ሥራ፣ በጉቦ ሥራ፣ በሥውር ሥራ፣ በውጣ ውረዳዊና ደጅ ጥናታዊ እንግልትና በድንፋታ) የተወረረ ነበር፡፡ እንዲህ ያለው ለሥነ ምግባር፣ ለህሊና፣ ለሥራና ለሙያ መታመን ውልቅልቁ የወጣበት እውነታ፣ ሰውነትንና የትግል ፍላጎትን እየላሰ ይበላል እንጂ የትግል መለምለሚያ አይሆንም፡፡

ከትግል ሽንፈት በኋላ ጫካ/በረሃ ተሰደው የብሔርተኛ ትግልን የተቀላቀሉ ታጋዮች ዞሮ ዞሮ ከአገራዊና ከኅብረ ብሔራዊ ታጋይነት መስመር የተሰናበቱበት ሒደት ውስጥ ነውና የገቡት፣ ያለፉ ጥፋቶችን ያረመ ትግልን ከሌላ ማኅፀን እንደማይወልዱት ግልጽ ነው፡፡ ወደ ውጭ የተሰደዱ ከ‹‹ተራማጅ›› ቡድኖች የተራረፉ መሪዎች ውለው አድረው ስለትግላቸው ታሪክና ግምግማ ቢጽፉ የአገሪቱን የትግል ታሪክ መሠረታዊ ችግሮች ብትንትን አድርጎ የሚያሳይና ለመጪው ትግል መማርያ የሚሆን ታላቅ ሊባል የሚችል ሥራ ሊወጣቸው አልቻለም፡፡ የሞካከሩት ሥራ በአያሌው ወደ ቡድናቸው ያደላና የጥፋት ግምገማቸው ከአገም ጠቀም ያልራቀ ነበር፡፡ እናም በ1960ዎች ትግልና በተከታዩ የደርግ ዘመን አገዛዝ ምንነት ላይ የተጻፈ፣ ማንም ንቆ ሊገፋው የማይችልና የኋለኛውን ትውልድ የሚያንፅ ቅርስ ሥራ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ የተሞካከሩትን ይዞ የተሻለ ግንዛቤ የፈጠረ ልሂቅ ብቅ አይል ነገር፣ አንድ ለእናቱ ዩኒቨርሲቲያችን በደርግ ኢሠፓ መዋቅርና ፕሮፓጋንዳዊ መረብ ታንቆ የደርግን መንግሥታዊ የጥፍነጋ ሥርዓት የሶሻሊስት አብዮትና የሶሻሊስት ኢኮኖሚ ብሎ የሚያስተምር እስረኛ ነበር፡፡ በዚያ ላይ ነባሩም አዲሱም ትምህርት ቀመስ ሁሉ የፖለቲካ ፆመኛነት የበረታበት ነበር፡፡ የፖለቲካ ፆመኛነት የሰፈነበትን ጊዜ እርከን እናወጣለት እንደሆን እንጂ፣ ከ1971 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. የመጋቢት ለውጥ ድረስ የተራዘመ ነበር፡፡

በ1980ዎች መጀመሪያ አካባቢ ከባህር ማዶ ኢህዲአ (EPDA) የሚባል ድርጅት በሬዲዮ ሥርጭቱ፣ ‹‹ለውጥ ከእንግዲህ ሊመጣ የሚችለው ከወታደሩ ነው…›› እያለ የወታደራዊ መንግሥት ግልበጣ እንዲካሄድ ሕዝብም ይህንኑ እንዲጠብቅ መቀስቀሱ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝብ የተንገሸገሸበትን ሥርዓት ተንትኖ ሕዝብን ለማነቃነቅ የሚችል ፖለቲካ የሞተበት የፆም ዘመን መሆኑን ያንፀባረቀ ነበር፡፡ የመንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ወታደራዊ ቢሮክራሲያዊ አገዛዝ በዚያ ጊዜ ከፍተኛ የሕዝብ ጥላቻ ውስጥ ወድቆ ሳለ፣ የ‹ኢህዲአ›ን ቅስቀሳ ተከትሎ በግንቦት 1981 ዓ.ም. የተካሄደው በጭራቃ ወታደራዊ የግልበጣ ሙከራ በጊዜው ለነበረው ባዶነት ሌላ ማሳያ ነው፡፡ ሕወሓት ከበረሃ ሆኖ ማሌሊት፣ ኢማሌሃ፣ ምንትስ እያለ ስለማርክሳዊ ሌኒናዊነት፣ ስለቡርዧዊነትና ስለባላደራዊነት ይደረድር የነበረውም ቅብጥርጥር የፖለቲካን ማንሰራራት የሚያሳይ ሳይሆን፣ የፖለቲካ ምድረ በዳነትን ያሳየ (የከረመ ሬሳ ታቅፎ ‹አልሞተም! በሕይወት አለ!› እያሉ ለማሳመን ከመሞከር ዓይነት ሥራ ያልተሻለ) ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ‹‹ዋናው ቅራኔ የብሔሮች ቅራኔ ነው… የብሔሮች መብት እስከ መገንጠል ድረስ…›› የሚል ነገርም እውነታን ዘቅዝቆ ያየ/ የመደብ ጭቆና አንድ ቅርንጫፍን ዛፍ አድርጎ ያቀረበ መንሸዋረር ነበር፡፡  እናም በወታደራዊ አምባገነንነት ፍዳ እየቆጠረ ለነበረ ሕዝብ (ለልሂቁ ጭምር) የማይገባ እንቆቅልሽ ከማውራት የማይሻል ነገር ነበር፡፡ እውነትን ግሽልጥ አድርገን እናውጣት ከተባለም፣ ‹ለውጥ ሊመጣ የሚችለው ከወታደሩ ነው፣ ለውጥን ከወታደሩ ጠብቁ› ብሎ የባህር ማዶው ‹ኢህዲአ› የቀሰቀሰበት ጊዜና በአንፃሩ የበረሃው ሕወሓት ‹የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒንስቶች፣ ወዘተ› እያለ ይዘላብድ የነበረበት ጊዜ ‹የአልሞትኩም ብዬ አልዋሽም› ፖለቲካ (የፖለቲካ መሞት) በኢትዮጵያ ጣሪያውን የነካበት ጊዜ ነበር፡፡

ሕወሓት ኢሕአዴግነትን ለብሶና ከሻዕቢያ ጋር ሆኖ በደርግ ላይ ድል የመቀዳጀቱም ነገር ለኢትዮጵያ ሕዝብ የለውጥ ብርሃን ሆኖ ደርግን በፖለቲካ ድል የመምታት ጉዳይ አልነበረም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በደርግ የ17 ዓመት የደነቆረበትን ስለከበርቴ ጠላትነት የሚያወራ ርዕዮተ ዓላማዊ ቁርበት የሚያንቋንቋ ቡድን ነበር፡፡ ወታደራዊ ድሉም በሬሳው የቀረው ደርግ በግድ ድል ካላደረግከኝ ብሎ የሰጠው ስጦታ ነበር፡፡ ከከሸፈው የግንቦት 1981 ዓ.ም. የመንግሥት ግልበጣ በኋላ፣ ደርግ የከሰረ ሥርዓቱን ጠግኖ የሕዝብና የሠራዊቱን ድጋፍ ለማደስ የነበረውን ዕድል ከመጠቀም ፋንታ በግልበጣው ውስጥ የተሳተፉትን የማጨድና የመቅጣት ዕብደት ውስጥ ገብቶ ሕዝብንና ሠራዊቱን ማሳረር ነበር የተያያዘው፡፡ የሠራዊቱን መከፋት ለመቆጣጠርም በሹም ሽርና በፕወዛ የማይተማመኑ ሰዎችን እያገናኘ ማጣመዱን አጥብቆ የሠራዊቱን ቅሬታ አባሰው፡፡ ተስፋ መቁረጥ፣ የውጊያ ፍላጎት ማጣትና ዕንቢኝ ባይ የአመፅ ስሜት በሠራዊቱ ውስጥ እንደተስቦ ተባዛ፡፡ ሌላ አታጋይ የፖለቲካ ኃይል ባዶ በነበረባት ኢትዮጵያ፣ ሠራዊቱ ቢያኮርፍ ቢያምፅ (አመፁን በመሸሽና በገፍ እጅ በመስጠት ቢገልጽ) ከሕወሓት/ኢሕአዴግ ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረውም፡፡ ደርግ ራሱን በራሱ እየበላ ራሱን ለሽንፈት ያመቻቸውም ይህን ያህል በሆነ ጥልቀት ነበር፡፡

2) በሕወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን ላይ ደግሞ ትንሽ እናትኩር፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግ በሬዲዮው የፈለገ ፕሮፓጋዳ ቢነፋ ፕሮፓጋንዳው የኢትዮጵያን ነባራዊ እውነታና የሕዝብ ህሊና የተቆናጠጠ አልነበረምና አዲስ አበባ ሲገባ በፖለቲካ የማያውቀው ሕዝብና ከተማ ውስጥ ከመግባት የተለየ አልነበረም፡፡ ከገባም በኋላ ዋና ቅራኔ ያለውን የብሔር ጉዳይ ‹‹የመፍታት›› ነገርና ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲን›› የመገንባት ነገር የኢትዮጵያን ሕዝቦች ችግሮች የመፍታት ሥራ ሳይሆን፣ አዲስ ችግር የመትከል ነበር፡፡ ቻርተር/ሕገ መንግሥት በማፅደቅና ‹‹ዲሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት››ን በማስረፅ/በማስፋፋት የተከናወነውም ይህ ነበር፡፡

ቻርተሩም ሕገ መንግሥቱም ኢትዮጵያን ማናቸውም ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች በፈለጉ ጊዜ ሊነጠሉ የሚችሉባት በፈቃደኝነት የተቋቋመች አገር አደረጓት፡፡ የዘመነ ዘመናት የግንባታ ታሪክ ያላት አገር በተፈለገ ጊዜ ልትሸረፍ/ልትበተን የምትችል እንጥልጥል አገር ሆነች፡፡ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት›› እና ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› የሚባለውም ፖለቲካ ይህንኑ የእንጥልጥል አገርነት የሚሰብክ (እያንዳንዱ ብሔር የኢትዮጵያ አካልነቱ በፈቃደኝነት ላይ የሚቆይ ስለመሆኑ፣ እያንዳንዱ ብሔር ለብሔሩ መሥራት እንዳለበት፣ ብሔሩ የሠፈረበት ሥፍራም ይዞታው እንደሆነ የሚያስተምር) ነው፡፡ በአጭሩ ይዘቱ፡- ዋና ቀልብህንና መታመንህን በየብሔርህ ውስጥ አድርገህ ለየብሔርህ እየሠራህ ኢትዮጵያዊ ሆኖ መቀጠል ፈቃድህ እስኪሆነ ደረስ ከሌሎች ብሔሮች ጋር አብረህ ‹‹በመከባበር›› ኑር፣ ይህንን አመለካከት የሚቃወም ጥቅምህን፣ መብትህን የሚቃወም/ሊጨቁንህ የተነሳ ነው፣ ሕገ መንግሥቱና አብዮታዊ ዴሞክራሲ የእያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ የህልውና ጉዳይ ነው የሚል ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱና ፖለቲካው ብሔር ብሔረሰቦች በፈቀዱ ጊዜ መነጠል መብታቸው ስለመሆኑ ከመናገር ባሻገር በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነትም ይጠቅማቸዋል ባይ ነው፡፡ ይህ ተጠቃሚነታቸው የሚቀጥለው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ እስከተመሩ ድረስ  ነው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲም የሕወሓት/ኢሕአዴግ ፖለቲካና ድርጅታዊ መዋቅር ነው፡፡ እናም የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አመራር እስካለ ድረስ ልነጠል ማለት የሕዝብ ጥቅምን መፃረር/ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጋር መጣላት ይሆናል፡፡ ማለትም ኢሕአዴግ ሕወሓትና አመራሩ በሥልጣን እስካለ ድረስ መነጠል የተፈቀደ አይደለም በተግባር፡፡ ለዚህም መጠበቂያ አለው፣ ሥርዓቱን የሚመሩት የሕወሓት/ኢሕአዴግና አጋር ፓርቲዎች በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚመሩ ናቸው፡፡ የታጠቀ ኃይሉ አውታር በሙሉ በሕወሓት ፖለቲካና ዕዝ ቁጥጥር ነው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲን መጠበቅ — የሕወሓት ኢሕአዴን ሥልጣን መጠበቅ — ለፀጥታ አውታሩ ተልዕኮው ነው፡፡ በእንጥልጥል ያለችው ኢትዮጵያ የምትበተነው ደኅንነቱንና መከላከያውን በዕዙና በርዕዮቱ የሚቆጣጠረው ሕወሓት/ኢሕአዴግ መበተኗን በፈለገ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ በተቀረ በሕወሓት/ኢሕአዴግ ፍላጎት ላይ የተንጠለጠለ ህልውና ይዛ 27 ዓመታት በኖረችው ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔረሰቦች ጭቆና ተባዛ እንጂ አልተቃለለም፣ የግለሰብ መብቶች ረገጣም እንደዚሁ፡፡

ይህንን ሁሉ እውነታ በርብሮና ተንትኖ ከእነ መፍትሔው ያሳየ ፖለቲካም ተፈልቅቆ አልወጣም ነበርና፣ ሕወሓት/ኢሕአዴግ የሚያናፍሰው ፖለቲካ ብዙዎችን እንዳደናገረና እንዳወዛገበ ህሊናንም እንደሰረቀ ቆየ፡፡ ብዙ መሸካከርና በየሠፈር የተከፋፈለ ዕይታ ተባዛ፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግና ሌሎች ብሔርተኛ ቡድኖች ያባዙትን ብሔርተኛ ክፍልፋይነትን ለመጋተር የሞከረ ፖለቲካ ቢኖር የአንድነት ድፍን ፖለቲካ ነበር፡፡ ድፍን ያልኩት፣ በዚያም በዚህ እያለ ሕገ መንግሥቱንና እነ አንቀጽ 39ን ቢቃወምም፣ ለኢትዮጵያ አንድነት እታገላለሁ በሚል ሦስት ቃላት ሊነገር ከሚችል ያለፈ ይዘት የሌለው ስለሆነ ነው፡፡ በፕሮግራም ደብተሮች ላይ ማኅበራዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ  ዕቅዶች መኮልኮል የሁሉም ፓርቲዎች ደንብ ነው፡፡ ደንባዊ ከሆነው ወገኝነት አልፎ በኢትዮጵያ ነባራዊና ህሊናዊ እውነታ ውስጥ ያሉ ጉዳቶችን ዕጦቶችን ድቀቶችን እየበረበሩ ማስረዳት ግን ባንዳቸውም አልታየም፡፡

አለመታየቱም አያስደንቅም፡፡ በደርግ ጊዜ የነበሩ ተራማጆች ተሰባብረው ከሞት የተረፉት ፖለቲካ ዕርም ወደ ማለት ወርደዋል ወይም ወደ ብሔርተኛነት ዞረዋል፡፡ ከእነሱ በኋላ የመጣውን ትውልድ ደግሞ ሕወሓት ኢሕዴግና ሌሎች ብሔርተኞች በብሔር ፖለቲካ ህሊናውን ባያሌው በጣጥሰውታል ወይም አደናብረውታል፡፡ ለይቶለት ‹‹ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ!›› የሚለው ከብሔርተኛ ሙሽት የተራረፈው አዛውንትና ውስን ወጣት ብቻ ነው፡፡ የሕወሓት ኢሕአዴግ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› እና ‹‹ዴሞክራሲያው ብሔርተኝነት›› የኢትዮጵያን ችግሮች ከመጨመር በቀር እንዳልፈታ ሁሉ ‹‹ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ! አንድነት አንድነት!›› ባይነት ከመፈክር ያላለፈ (ፖለቲካ ሊባል የማይችል) ነበርና፣ በጥቅሉ የፖለቲካ ባዶነት እውነታው አልተቀየረም፡፡

በደርግ ጊዜ፣ ሰውና ተቋማዊ አውታራት በመንግሥታዊ ቢሮክራሲ ዋጤነትና አዛዥነት ተሰንገው፣ የልሽቀት የድቀትና የቡጥቦጣ ወረርሽኝ ደረሰባቸው፡፡ የትም ቦታ ሰው አክባሪነት፣ ምግባር አክባሪነት፣ ሥራና ሙያ አክባሪነት ተንኮታኮተ፡፡ ደርግ ለሕወሓት/ኢሕአዴግ ባቀበላት ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ፣ በብሔርተኛ ቡድኖች የበላይና የበታች ገዥነት አማካይነት በተፈጠረ የይዞታ ቅርምት በኩል የሚካሄደው መቃቃር ያመርት የነበረው ጭቆናና ቡጥቦጣው አገር እስከ መስረቅ ድረስ ወሰን የጠፋው ነበር፡፡ ይህንን አስተውሎ የሚገዳደር አቅም ብቅ አይል ነገር ህሊና ራሱ ተሰርቆ ነበር (በተበጣጠሰ ያስተሳሰብ ሙሽት)፡፡

ሕዝብን ይዞ የሚታገል የፖለቲካ ትግል ብቅ ብሎ ነበር ቢባል፣ በ1997 ዓ.ም. ቅንጅትና ኅብረት የሚባሉ የትብብር ቡድኖች እንቅስቃሴ በመጣበት ጊዜ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ፣ እነዚህም ቡድኖች ቢሆኑ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ዘንድ የነበሩትን ጥንድ ፍላጎቶች (ማለትም የብሔር የቋንቋ የባህል መከበርንና ፍትሐዊ አያያዝንና እንደ አንድ አገር የመቀጠልን ፍላጎቶችን) በቅጡ አግባብቶ የሸረበ ፖለቲካ ማፍለቅ አልቻሉም ነበርና በሁለት ጎራ በኩል የነበረው ፍጥጫ መቃለያ አልነበረውም፡፡ በጊዜው ጎልቶ የወጣው ፖለቲካ የዜግነትና የግለሰብ መብት ከብሔር መብት ጋር ግጥሚያ የያዘ ነበር፡፡ ከዚያም በላይ፣ ተቀዋሚዎቹ ካለፋት ትግሎች ተጠማምዶና ተከፋፍሎ አቅምን የማዳከም ጥፋቶች፣ በአግባቡ አልተማሩም ነበር፡፡ የቆሙበት ምድር ሕወሓት ኢሕአዴግ አድራጊ ፈጣሪ መሆን የሚችልበት መሆኑን አውቀው፣ ፍላጎታቸውንና ዕርምጃቸውን በጥንቃቄ አልመሩም፡፡ ኳስ ጨዋታ አቋርጠው ለዓመታት የቆዩ ሰዎች በተሳሰረ (ቅልጥፍናና የቴክኒክ ብቃት ባላካበተ) ሰውነት ከልክ በላይ እንጫወት ሲሉ በራሳቸው ላይ ጉዳት እንደሚያስከትሉ ሁሉ፣ ቅንጅትና ኅብረትም ሕወሓት/ኢሕአዴግ የሚባለውን ወፍራም ድብ፣ ጥግ ድረስ ተዳፍረውና አስቆጥተው ተሰባበሩ፡፡ የሕወሓት ኢሕአዴግ አዛዥ ናዛዥነትና ቅጥቀጣ ከበፊቱ ይበልጥ ጠነከረ፣ የፖለቲካ መፈራገጫ ሜዳው ይበልጥ እሾሃማ ሆነ፡፡ ብልጭ ብሎ የነበረው ሰደዳማ የተቃውሞ ትግል ተጠምጥሞበት የነበረውን የመላ ኅብረተሰብ ድጋፍ አሳቅቆ ጠፋ፡፡ የፖለቲካ ትግል ኦናነት እንደገና ሠፈነ፡፡

መፈረካከሱ፣ መታሰሩና መፈታቱ ሁሉ ከተካሄደ በኋላ፣ የተወሰኑት ወደ ስደት እየሮጡ በጎረቤት አገር መሽጎ ትጥቅ ትግል የማካሄድ አሮጌ የትግል ሥልት ውስጥ ገቡ፡፡ አገር ቤት የቀሩት ወደ ድሮ አናሳ የፖለቲካ ቡድንነት እየወረዱ በድሮ የብሔርተኛ ኢብሔርተኛ የጎራ ሠልፋቸው ውስጥ ገቡ፡፡ ከተወሰነ መፍተልተል በኋላ ደግሞ ከድቆሳና ከውድቀት ትምህርት የተወሰደ የሚመስሉ ነገሮች ተከሰቱ፡፡ የዜግነት ፖለቲካ አለኝ በሚለውና ተፈረካክሶ የመሰባሰብ ውጤት በሆነው ‹አንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ› በሚባል ቡድን ውስጥ ነጋሶ ጊዳዳና ስዬ አብርሃ (ከኢሕአዴግ የወጡ) ገቡ፡፡ ወደፊት እስከ መዋሀድ የመሄድ ተስፋን በፈነጠቀው ‹‹…መድረክ››  ውስጥ የብሔር ፖለቲከኞችና የዜግነት ፖለቲከኞች (አረና ትግራይ ‹‹አንድነት›› ኦፌኮ….) ተጎዳኙ፡፡ የዚህ ጉድኝት መፈጠር የቡድንና የግል መብቶችን መፋጠጫነት ሰብሮ፣ የሁለቱንም የዴሞክራሲ መብቶች አካልነት በቅጡ ተንትኖና አስጢኖ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል አዲስ አሰባሳቢ አመለካከት ያቀዳጀ፣ ስብስቡን አበራክቶም በወጥ አደረጃጀት ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ልሳን ይሆናል ተብሎ ተጓጉቶም ነበር፡፡ ሆኖም የፖለቲካ ዕድገትና ብስለት አልነበረምና የየጎራ ግጥሚያን ለመሻገር መሞከር ‹‹የማይቀላቀሉ›› መርሆችን ለማቀላቀል መሞከር ተደርጎ እየተወገዘ፣ በዚያ ላይ የእነ ሕወሓት ሠርጎ ገብ ሴራ በአሉባልታና በጥርጣሬ መተማመንንና መስማማትን እያነከተ የመድረክ ስብስብን ቀናነሰ፣ አንድነት የሚባለውንም ቡድን አምሶ ፈረካከሰ፡፡ የማይኳኋኑ ነገሮች ተዳበሉ በሚል ነቀፋና ስላቅ፣ የመድረክን ጉድኝት እንዳይሰምር በመታገል ረገድ፣ የልደቱ አያሌው ኢዴፓና መኢአድ አልሰነፉም ነበር፡፡ ተስፋ የተደረገበትም ጉድኝት አስወርዶት ወደ ተለመዱ የጎራ መደቦቹ ተመለሰ፡፡

የዚህን ሁሉ የእንዘጭ እንቦጭ የተወሰኑ ምክንያቶች ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ አንደኛው ሕወሓት/ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ ጊዜ አንስቶ የሥልጣን ተጋፊ የፖለቲካ ኃይል ብቅ እንዳይልበት የፖለቲካ ቡድኖችን በተለያየ ውንጀላ እያጠመደ፣ በሚቆጣጠረው የፀጥታና የፍትሕ አውታርም በኩል ሆነ በምርጫ ቦርድ በኩል ከመምታት ባሻገር፣ በውስጣቸው ሰላዮችና ነገር ሠሪዎች እያሰረገ በአንጃ ሽኩቻ በማመስ፣ በአንጃዎች ቆራርሶ በማካሰስ፣ የማይበገርለትን አንጃ በሕገወጥነት እያሰረዘ ለእሱ ታዛዥ የሆነውን በሕጋዊነት እያስቀጠለ መካን ቡድን በማበራከት ሲያጠቃ ኖሯል፡፡

ሁሉም ውድቀት ግን  በሕወሓት/ኢሕአዴግ ጥቃት የሚመካኝ አይደለም፡፡ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ ለመምሰል በሞከረበት ጊዜ ውስጥ፣ ቅንጅትና ኅብረት የሚባሉት ስብስቦች (በተለይ ቅንጅት) ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍና ተሰሚነት አግኝተው ነበር፡፡ ተቃዋሚዎች ሁሉም መንግሥታዊ መዋቅር በሕወሓት/ኢሕአዴግ ቁጥጥር ውስጥ መሆኑን ሳይዘነጉ፣ ዓላማቸው ሕወሓት ኢሕአዴግን ማሰናበት ሳይሆን ከመጠማመድ የራቀ የዴሞክራሲ ልምምድ ጥሩ ጅምር እንዲያገኝ ስለመሆኑ የሚናገሩና የሚናገሩትንም የሚያምኑበት ቢሆን ኖሮ፣ የኢትዮጵያን ፖለቲካና የዴሞክራሲ ዕድል አንድ ዕርምጃ ሊወስዱት ይችሉ ነበር፡፡ ይህ ግን ከዕይታ አቅማቸው ውጪ ነበር፡፡ ስለትልቁ የዴሞክራሲ ጉዳይ አልሞ የማሰብ አቅም ለድርጅት ደኅንነትና የሕዝብ ድጋፍ የመጠንቀቅን አስተዋይነት ዘሎ አይመጣም፡፡ ቅንጅትና ኅብረት ከስላቅም አልፈው እያደር በእልህ እልህ እየተመነጠቁ የማገጠ ቅስቀሳ ውስጥ መግባታቸው፣ ስለህልውናቸው እንኳ ይጠነቀቁ እንዳልነበር የሚናገር ነው፡፡ ግዙፍ ሸፍጥን የሚያከሽፉበት የትግል ሥልት ዝግጅት ባላደረጉበት ሁኔታ፣ ስለማሸነፋቸው እርግጠኛ ሆነው መቀስቀሳቸውም በዚያች ዓመት የምርጫ ውድድር ላይ የይለይልን ቁማር የማካሄድ ነገር ነበር፡፡ እናም የተቃዋሚዎች ድክመትም የውድቀታቸው አንድ ምክንያት ነበር፡፡

በአጠቃላዩ ድክመት ውስጥ፣ ልዩ ልዩ ቡድኖች በሒደት ያሳዩት ነገረ ሥራም አስተዛዛቢ የሚል አገላለጽ የሚያንሰው ነበር፡፡ መሰሪነት፣ ቅጥረኝነት፣ የፖለቲካ ሽባነት፣ ከአፍንጫ አይርቄነት፣ ድርጅቴ ርስቴ ባይነት ሁሉ ነበር፡፡ ከደርግ አንስቶ ለዓመታት የተካሄደ ቅጥቀጣ የረባ ልሂቅ እንዳይኖራት አድርጓል፡፡ ይህ አጠቃላይ ጉዳት የአገሪቱን የትምህርት ቅስም እስከማዳቀቅ ሥር ያበጀም ነበር፡፡ እና የፖለቲካ ልሂቃኑ ችግር ሥርዓታዊ የማኅፀን ችግርም የነበረበትም ነው፡፡

3) ከ2006 – 2010 ዓ.ም. የተካሄደ/እየተጠራቀመ የሰፋና በመስዋዕትነት የቀለመ የሕዝብ እምቢታ፣ ያዋለደው የለውጥ ብልጭታ ሕዝብ የሳሳለትና አፍጥጦ ይጠብቀው የነበር ነበር፡፡ የኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሥልጣን የመልቀቅ ጥያቄ በኢሕአዴግ ውስጥ ከነበሩት የለውጥ አድቢዎች ጋር የተገናኘ ቋጠሮ ይኑረው አይኑረው እስካሁን ተፍታቶ የወጣ መረጃ የለም፡፡ ሕዝቡ ግን መጪው የጠቅላይ ሚኒስትር ምርጫ ከሕወሓት፣ ከብአዴን ወይም ከደኢሕዴን ቢሆን የሕወሓት ታማኝ ታዛዥ ይቀመጥብናል ከሚል ግምት ጋር ተመራጩ ከኦሕዴድ የመሆኑን ነገር አቆብቁቦ ይጠብቅ ነበር፡፡ በሕዝባዊ እምቢታው ውስጥ ጉልሁን ሥፍራ ይዞ የነበረውም የኦሮሞ ወጣቶች ሚና፣ ‹‹በኦሮሞ በኩል ያለውን የሕዝብ እምቢታ ለመሸንገል ኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መምረጥ ይበጃችኋል፣ አለዚያ ግን!…›› የሚል ማስፈራሪያ  በሕወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ላይ ደግኖ ነበር፡፡ የዚህ ማስጠንቀቂያ ጫና ለለውጥ ያደባውን የቡድን ስብስብ አግዟል፡፡ አንድ ላይ ተቀናብረው የሕወሓትን ሌላ ሰው የማጨት ፍላጎት ተጋፍተው ዓብይ አህመድን እንዲያጩ ሕወሓቶችም በድምፅ ብልጫ ለተበለጡበት ምርጫ እጅ እንዲሰጡ ረድቷል፡፡

ዓብይ አህመድ በበዓለ ሹመቱ ሥነ ሥርዓት ላይ ያደረገው ንግግር የለውጡን አቅጣጫ የጠቆመ ብቻ ሳይሆን፣ የሕዝብን ስሜት ኮርኩሮ ከመነሻው የለውጡ ቡድን በሕዝብ ድጋፍ እንዲታጀብ ያስቻለ ነበር፡፡ ከዚያ ንግግር በኋላ የመጡ ውሳኔዎቹና ዕርምጃዎች የሕዝብ ድጋፍን አጠቃላይ እስከ መሆን ማባዛት የቻሉም ነበሩ፡፡ የለውጡ ቡድን ‹‹የለማ መገርሳ ቡድን›› እየተባለ መጠራቱ ሕወሓቶች ንቁ የለውጥ ተሳትፎ እንዳልነበራቸው በውስጠ ታዋቂ ይጠቁም ነበር፡፡ የታጠቀው ኃይል ከደኅንነት እስከ መከላከያና ፖሊስ ድረስ በሕወሓታዊ የዕዝ ስንሰለት ውስጥ መሆኑ ደግሞ ለማንም ሥውር አልነበረም፡፡ እናም የለውጥ ቡድኑ ሰዎችና የለውጡ ደጋፊ ፖለቲከኞች፣ ለውጡ ሥውር ሸፍጥ/የእጅ ጥምዘዛ እንዳያገኘው መመከቻ የማበጀት ተግባር ፊታቸው ተድቅኖ ነበር፡፡ ወታደራዊ ቅልበሳ ቢሞከር፣ ለውጡ የነበረው የብዙኃን ድጋፍ የታጠቀው አካል ድረስ የዘለቀ ነበርና ወታደራዊ የግልበጣ ሙከራን የመቃረንና የማክሸፍ እንቅስቃሴ ከሲቪሉ ሕዝብ ባሻገር ከታጠቀው ሠራዊትም አካባቢ ይመጣ እንደነበር ይገመታል፡፡ ይህ ከሰፊ ድጋፍ የመጣ ግምት በራሱ የወታደራዊ ግልበጣ ዕድልን ያሸማቅቃል፡፡ ሌሎች ሻጥሮች ግን በመላ ሕዝብ ድጋፍ ብቻ የሚሸማቀቁ አልነበሩም፡፡ በሕዝብ ድጋፍ ብቻ እንደማይሸማቀቁም፣ ሰኔ 16 አብዮት አደባባይ ትዕይንት ላይ፣ የተደረገ የግድያ ሙከራ የማስገንዘቢያ መልዕክት አስተላልፎ ነበር፡፡ መልዕክቱን ሰምቶ ሸፍጥ ለማክሸፍ የሚበቃ የመከታ ሥራ ግን ማን ሊሠራ!

የአገዛዝ በደል ተጠያቂነትን በአጠቃላይ የኢሕአዴግ አድርጎ መውሰድን፣ ሕወሓቶችን ወደ ንቁ የለውጥ ተሳታፊነት መሳብን፣ ሕወሓትን ነጥለው የሚወነጅሉ ቅስቀሳዎች እንዲለዝቡ ማድረግን፣ በአጭር ጊዜ መርሐ ግብር በመንግሥት ደረጃ ለውጡን የሚመሩ ሰዎችንና የለውጡን መላ ደጋፊዎች ማስተሳሰርን፣ በዚህም ትስስር አማካይነት ሕዝብን በለውጥ እንቅስቃሴ ተሳትፎና ሸፍጦችን ነቅቶ በመታገል ተግባር ማደራጀትን ለውጡ ይፈልግ ነበር፡፡ እነዚህን ተግባሮች አቀናብሮም ሆነ በተናጠል እያነሱ በማስጨበጥ ረገድ በጊዜው የኢትዮጵያ ለውጥ ምሁራዊ የአቅም ክፍተት ነበረበት፡፡ ‹‹የለማ መገርሳ ቡድን›› ይባል የነበረው ቡድን የጥቂት ግለሰቦች ቡድን ነበር፡፡ ግለሰቦቹ በፖለቲካ አስኳልነት ደረጃ የተደራጁ የፖለቲካ ሐሳቦችንና ተግባሮችን የሰነቁ አልነበሩም፡፡ የወጣቱ ዓብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ መውጣት ለውጡን በመንግሥት ደረጃ የመምራትን ኃላፊነት ያሸክማል እንጂ፣ ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችን አስቀድሞ እያስተዋሉ በፖለቲካ ሐሳቦችና ትልሞች ለውጡን የመምራት አቅምን አያቀዳጅም፡፡ ይህ ወሳኝ ተግባር ምሁራዊ ዕገዛን ይጠይቅ ነበር፡፡ ዕገዛው ፓርቲ ልሁን ማለት ሳያፈልግ ለውጡን ጉዳዬ ያሉ ማዕከሎች እየፈጠሩና ነገሮችን በየፈርጁ እያጠኑ በተከታታይነት በሚዲያ በማውጣትም ሊሟላ ይችል ነበር፡፡ ይህን ምሁራዊ ክፍተት የሞላ አልነበረም፡፡

ቀደም ብለውም ሆነ በስተኋላ ከወጡ ትንታኔዎች የተወሰነ የሐሳብ ዕገዛ ማግኘት ቢቻልም፣ እንዲህ ያለው ነገር የለውጥ ኃይሎችን አስተባብሮ የጋራ የጉዞ ካርታ/ትልም ማውጣትንና ያንን ለማሳካት አብሮ መንቀሳቀስን የሚተካ አልነበረም፡፡  የጋራ ተግባርን አውቆ አንድ ጋር መንቀሳቀስም፣ የነበረን መንግሥት፣ በሽግግር መንግሥት መቀየርን የሚጠይቅ አልነበረም፡፡ ከለውጡ መንግሥት ጋር ተቀራርበው ለለውጡ መሥራት ይሹ የነበሩም ምሁራንና ፖለቲከኞችም ይህንን በግልጽ ማሳወቅ ነበረባቸው፡፡ ለውጡን በመንግሥትነት እየመሩ የነበሩ ሰዎችም ያለባቸውን ውሱንነት ተቀብለው የትብብር ጥሪ ማድረግ ነበረባቸው፡፡

ከሁለቱም በኩል ለለውጡ መሳካት የሚገባውን ያህል ስሱነት ፈክቶ አልወጣም፡፡ ከመንግሥት ውጪ በነበረው ፖለቲካ ውስጥ እነ ዓብይን ወደ ሽግግር መንግሥት የመቀየር፣ ከዚያ በመለስ በእነ ዓብይ መንግሥት ውስጥ የመሾም ዓይን አፋር ፍላጎቶች ነበሩ፡፡ ዝም ብሎ ተመልካች በመሆንም ውስጥ የፈዘዙ ነበሩ፡፡ ለዶክተር ዓብይ አህመድ ገና ከመጀመሪያው የጎረፈለት ‹‹ሙሴ/የኢትዮጵያ አምላክ ስጦታ›› እስከመባል ሰማይ የወጣ ውዳሴና ግለሰቡ እጅጉን ተጣጥመው ነበር፡፡ ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ ያከታተላቸው ዕርምጃዎች የተሰደዱ ፖለቲከኞችን ከመጥራት፣ እስረኞችን ከመፍታትና ከመሳሰሉት አልፎ የእምነት አባቶችን እስከማስታረቅ ድረስ መርዘማቸው ለውጡን የጠቀሙትን ያህል ግለሰቡን የለውጡ አብሪ ኮኮብ ያደረጉም ነበሩ፡፡ ይህ ዝና በምላሹ ግለሰቡ አቅሞቹን እያተባ ያልተጠበቁ የሥራ ውጤቶች በማሳየት ግርምትና መደነቅን እንዲያንቦገቡግ የሚቆሰቁስ ነው፡፡ የለውጡና የግለሰብ አብሪ ኮኮብነት በዚህ አኳኋን መጎዳኘት ደግሞ ለውጡ ከሚሻው የለውጥ ኃይሎች ትብበር ጋር የሚገፋፋም ነበር፡፡

የለውጥ አጋዦች ለውጡ ያሉበትን ውስንነቶች አስተውለው፣ የትግል ኅብረት መፈጠርን ከመንግሥት ሳይጠብቁ ራሳቸውን አሰባስበው የጠቅላይ ሚኒስትሩን መሪነትና አስተዋፅኦ እያሞካሹ ከእነሱ ኅብረት ጋር እንዲሠራ ያደፋፈሩበት፣ በሕወሓት ላይ የሚካሄድ የኃጢያት ድፍዳፋ ለለውጡ የማይበጅ ስለመሆኑ እያሳወቁ በዕርቅ መንፈስ አብሮ ለለውጡ መሥራትን ያጎሉበት ሚና ከኢሕአዴግ ውጪ ካሉ ኃይሎች በኩልም አልመጣም፡፡ ለዚህ ዓይነት ጉድለት ሞይነት የሚሆን ፈጣን አስተዋይነት አልነበረም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባለ የለውጥ አመጣጥ (ማለትም የለውጡ ብቅታ በመንግሥት ውስጥ ከመጣ የአመራር ሽግሽግ ጋር የተያያዘ በሆነበትና ሕዝብ የለውጥ ጉጉቱን አዲስ መጡ አመራር ላይ ባሳረፈበት ሁኔታ፣ መንግሥታዊ አመራሩ ከሕዝብ ድጋፍ በቀር፣ የታጠቀውን አውታር በማዘዝ ረገድ ከመንሳፈፍ ብዙም ያልራቀ በሆነበት ሁኔታ)፣ ምሁራን/ፖለቲከኞችና ሕዝብ በተቃቀፉበት ሥምረት ለውጡን አጅቦ ከሻጥሮች እየተከላከሉ ወደፊት ከማስኬድ የተሻለ አማራጭ አልነበረም፡፡

የለውጥ እንቅስቃሴው ከመንግሥት ውጪ በሆነ ተቃዋሚ ፓርቲ የሚመራና የመላ ሕዝብ ድጋፍ ከዚህ ፓርቲ ጋር የሆነበት ሁኔታ ውስጥ የነበር ቢሆን ኖሮ፣ እንደ ሁኔታዎች አበሳሰል ጥያቄዎችን እያቀረቡ ሠልፉንም፣ አድማውንም፣ ድርድሩንም እየተጠቀሙ የለውጥ ማሻሻያዎች ማካበት በተቻለ ነበር፡፡  የለውጥ ጅምርና ዕድገት ሥር ካላበጁ አዲስ የመንግሥት መሪዎች ጋር ተዛምዶ ሲመጣ ግን በሰፊ ድጋፍ ከመንከባከብ ፈንታ ነቀፋ መደርደር፣ ሠልፍ ልውጣ ማለት፣ በጥያቄዎች ማዋከብ ይቅርና በዝምታ ማየት እንኳ ለውጡን መበደል ይሆናል፡፡ ለውጡን አቅፎ ለማጠናከር ራስን በፍኖተ ካርታ በማስተባበር ፈንታ፣ በባይተዋር ርቀት ውስጥ ሆኖ ‹‹ከተቃዋሚ ጋር ፍኖተ ካርታ አውጣ!›› እያሉ መጮህ የማስደንበር ሚና ከመጫወት ያነሰ አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲከኞች አካባቢ ምን ያህል ድፍን ቅልነት እንዳለ አንዱ ማሳያ የኢሕአፓ ትራፊዎች በለውጡ አፍላ ሰሞን (ዓብይ አሜሪካ ሄዶ በነበረበት ጊዜ) የሽግግር መንግሥት ተሳትፎ መጠየቃቸው ነበር፡፡ ኢሕአፓዎች ከሕወሓት ጋር የሚወራረድ ሒሳብ አለን የሚሉ ባለ ቁርሾዎች ሆነው፣ እነሱና ሕወሓት በሽግግር መንግሥት እንዲገናኙ መፈለግ ወይም ሕወሓት የተቀነሰበትና እነ ኢሕአፓ የተካተቱበት ሽግግር እንዲፈጠር መፈለግ ምን ያህል ለለውጡ መቀጠል ደንታ የሌለው ቀውስ ደጋሽነት እንደሆነ አስቡት!! እውነት እንናገር ከተባለ የትጥቅ ትግልን አቋርጠው የመጡትን ግንቦት ሰባቶችንና በኋላ የተከተሉትን ኦብነጎችን ያህል ለለውጡ ንቁ ድጋፍ ያሳየ (በተቃውሞ ሠፈር ውስጥ ከነበሩ ቡድኖች) አልነበረም፡፡ ብዙዎቹ ከተማ ለከተማ የቆዩ ቡድኖች ከባይተዋር አይሻል ነበሩ፡፡ የዓብይን መንግሥት በድጋፍ አጅቦ መጓዝ ለእነሱ ፓርቲነት የማይመጥን፣ አጨብጫቢነት ውስጥ ገብቶ መቅለል እንጂ ለውጡን የመንከባከብና የማገዝ ሥራ ሆኖ ለብዙዎቹ አይታያቸውም ነበር፡፡ የእነሱ ፓርቲያዊ ኃላፊነት ፈንጠር ብሎ መተቸት፣ መቃወም፣ ግንባር ወይም የጥምር መንግሥት እንዲፈጠር መጠየቅ፣ ምርጫ ሲመጣ ደግሞ ለሥልጣን መወዳደር ነው፡፡

ዕውን ሥልጣን ላይ ወጥቶ አገር ለመምራት የሚያበቃ የዕውቀትና የክህሎት ስንቅ አለን? የሚለው ጥያቄ ብዙዎቹን የኢትዮጵያ ስንጥርጣሪ ቡድኖች አያሳስባቸውም፡፡ የአቅም ጉዳይ ማንን እንዳሳሰበ እነሱን ያሳስባቸዋል!? የመንግሥት ቢሮዎች ያቅም የለሾች መምነሽነሻ መሆን እንግዳ ነገር አይደል፣ ሌላ እንደሆነው እየሆኑ እነሱም የሥልጣን ሲሳይን ለመቋደስ አያንሱም፡፡ ፓርቲ የማደራጀት ነገር አማረኝ አሰኘኝ ሲሉ ሊደረግ የሚችል ነው፡፡ በሆነ ቁጭት ነገር ምላስን አሥልቶና ደንቡ የሚፈልገውን ያህል ሰዎች አሰባስቦ ከሌሎች ፕሮግራሞች የተኮረጀ ‹‹አዲስ›› ፕሮግራም ጽፎና አፅድቆ ቢሮ መክፈት ነው፡፡ አበቃ፡፡ ለዴሞክራሲ መታገል ማለትም ‹‹ለዴሞክራሲ ቆሜያለሁ! ለዴሞክራሲ እታገላለሁ!›› እያሉ በየደረሱበት መለፍለፍ ነው፡፡ ዴሞክራሲን መኖር ደግሞ እንዳሻ መቀባጠር፣ በትንሽ በትልቁ መንግሥትን ማብጠልጠልና መቃወምን እንደ ሥራ መያዝ፣ በትንሽ በትልቁ ሠልፍና ሕዝባዊ ሰብሰባ የመደገስ ‹‹ዓለምን ለመቅጨት›› መሞከር ነው፡፡ ዴሞክራሲን የመኖር ትርጉም እነሱ በተቃዋሚነት እስካሉ ድረስ ይህ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን፣ እነሱ ከሚመሩት ፓርቲ ውስጥ የሚመጣ ትችትን በበጎ የሚያይ ሆደ ሰፊነት በአያሌው የሚቸግራቸው/ጥቃት በእነሱ ላይ እንደመጣ የሚሸታቸው ናቸው፡፡  ዴሞክራሲ፣ በነፃነትና በገደብ/በመብቶችና በግዴታዎች ውስጥ የመኖር ባህርይን ተለማምዶ፣ ለሕዝብ ልማት ለፍትሕና ለመልካም አስተዳዳር እሽክርና መግባት መሆኑ ከቅስማቸው ጋር አልተዋሃደም፡፡ የዚህ ዓይነት ተግባርም ከሁከትና ከግርግር ይልቅ የተረጋጋ ምክክርና የሐሳብ ልውውጥን እንደሚሻ፣ የዚህም ባህል መኮትኮት የሚጀምረውና የሚገነባው ከትግል ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ አይረዱም፡፡

እንደዚህ ያሉ ጉድለቶች የዴሞክራሲ አዋላጅ ለመሆን አያስችሉም፡፡ ጅምር ለውጥን ወደ ዴሞክራሲ ከመውሰድ ይልቅ እንዲወለካከፍ ያጋልጣሉ፡፡ አወላካፊም ይሆናሉ፡፡ ቀደም ብሎ እንደተገለጸው፣ በኢትዮጵያ ከታየው ዓይነተኛ የለውጥ ጉዞ አኳያ፣ ለዴሞክራሲ መሳካት መታገል ጠባብ ሩጫዎችን፣ ሁከትን፣ ግጭቶችን፣ ትርምሶችን፣ ጠመንጃ አናቂነትን ገና ከዝንባሌያቸው ጀምሮ እየተቃረኑና አጥፊነታቸውን እያጋለጡ፣ የለውጡ መንግሥትም የደንበር ገተር ቆፈን እንዳይዘው —  ወደ ዴሞክራሲ መሄድን እንዳይፈራ — ወደ አምባገነንነት እንዳያጋድል፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ለውጥ ወዳዶች አይዞህ ባይነትን እያሞቁ መራመድን ይጠይቅ ነበር፡፡ ይህ ተግባር አቤት አቤት እንዳለ ተልኮስኩሶ ቀረ፡፡

በዚህም ጉድለት የእነ‹‹ኢሳት›› እና የ‹‹ኦኤምኤን›› ሕወሓትን የሚዘለዝል ፕሮፓጋንዳ አራሚ አጥቶ ሕወሓት ዘርፈ ብዙ ጥፋት ወደ መደገስ ተጓዘ፡፡ የዳውድ ኢብሳ ኦነግ፣ በጠራራ ፀሐይ ሰላም ባለበት ድባብ ውስጥ የትጥቅ ቡድኖች ሊያረባ ተፈቀደለት፡፡ በየአቅጣጫው ሰላም ነሺ ተግባራት እየተፈጸሙ፣ መላ የአገሪቱን ኅብረተሰብ ባዳረሰ ስፋት አበሳ ተባዛ፡፡ ሕዝብ ቁምስቅሉን ካየም በኋላ የእኛ አልባሌ የፖለቲካ ቡድኖች የረባ ትምህርት ከጥፋት ልምዳቸው ቀስመው አልታረሙም፡፡ ዛሬም የለውጡ ዕድል ኢትዮጵያን እየመራ ካለው ፓርቲ ጋር ሆኖ ሳለ፣ ከማንኛውም በኢትዮጵያ ካለ ቡድን በላይ የሕዝብ ድጋፍ ያለውና የኢትዮጵያን ኅብረተሰብ ከዳር ዳር አያይዞ ኢትዮጵያንም ለማስቀጠል የሚችል ብቸኛ ፓርቲ እሱ ሆኖ ሳለ፤ ከዚህ ፓርቲ ውጪ ያሉት ብሔርተኞችም ሆኑ ‹‹ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ!›› የሚሉ ቁንጥርጣሪዎች አንድ ላይ ቢሰባሰቡ እንኳ፣ የኢትዮጵያን ኅብረተሰብ ለማያያዝ የሚችል የጋራ አጀንዳ ማበጀት የማይችሉ ሆነው አገር አቁሞ ያለውን መንግሥት ‹‹አምባገነን! የአንድ ብሔር!…›› ወዘተ እያሉ በሆነ ወጀብ እንዲወድቅላቸው የሚሻ ጉጉታቸውን ደብቀው ይቁለጨለጫሉ፡፡ አንዳንዶቹ ‹‹አልቻልክበትም! ሥልጣን ልቀቅ!›› የሚል ጩኸት ያሰማሉ፡፡ ከዚህ አለፍ ያለ የፖለቲካ ‹‹ሙቀት›› የሚሰማቸው ቡድኖች፣ ‹‹ተደራድረህ ሰላምን አምጣ››  በሚል ሽፋን ሊቆጣጠሩት የማይችሉት ሠልፍ በአዲስ አበባ ከተማና በሌሎች ከተሞች ሊዘረግፉ ይሞክራሉ፡፡ እንዲህ ያለ የአደባባይ ውርጭት አገሪቱን ምን ያህል ለአደጋ እንደሚያግልጣት ግን አይታያቸውም፣ ያውም አደጋው አፍንጫቸው ሥር ሆኖ!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...