Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ባንኮች በሕግ የተደገፈ ማበረታቻ ይኑራቸው!

በኢትዮጵያ በባንኩ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ የሚባለውን የተበላሸ የብድር መጠን በማጻፍ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ስሙ ሲነሳ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ከአምስት ዓመታት በፊት ባንኩ ተሸክሞት የነበረው የተበላሸ ብድር መጠን 40 በመቶ ደርሶ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የባንክ ታሪክ የተበላሸ የብድር ምጣኔው እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰ ባንክ ባለመኖሩ፣ ‹‹ባንኩ በኪሳራ ይዘጋል›› ወደሚል መደምደሚያ ተደርሶም ነበር፡፡

በእርግጥም ባንኩ የተበላሸ የብድር ምጣኔው እዚህ ደረጃ በመድረሱ ቢሊዮን ብሮችን አክስሮታል፡፡ ደግነቱ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በመንግሥት ባለቤትነት የሚተዳደር በመሆኑ፣ ከገባበት ቀውስ እንዲወጣ የመንግሥት ድጋፍ ተችሮት፣ ተጨማሪ ካፒታል እንዲመዘገብ ተደርጎ ነፍስ እንዲዘራ ሆኗል፡፡

ባንኩ ከነበረው አጣብቂኝ ወጥቶ በሁለት እግሩ እንዲቆምና አሁን ለደረሰበት የዕድገት ደረጃና አትራፊ ሆኖ እንዲቀጥል ያስቻለው በመንግሥት በተሰጠው ካፒታል ብቻ አይደለም፡፡ በአዲስ ስትራቴጂክ ዕቅድ ወደ ሥራ እንዲገባና ከኪሳራ ወጥቶ ወደ አትራፊነት እንዲሸጋገር ያስቻሉት፣ የባንኩ አዳዲስ አመራሮችና ሠራተኞች ብርቱ ትግል ጭምር ስለመሆኑ አለመግለጽ ተገቢ አይሆንም፡፡

ባንኩን ከኪሳራ አውጥቶ ወደ አትራፊነት ለማሸጋገር የተቀረፀው የአምስት ዓመታት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ በእርግጥም ውጤት አምጥቶላቸዋል፡፡ የተበላሸ የብድር መጠኑ 40 በመቶ እስኪደርስ ምን ሲጠበቅ ነበር እንዳልተባለ፣ ይህንን ታሪኩን ቀይሮ የተበላሸ የብድር መጠኑን ወደ ሰባት በመቶ አውርዷል፡፡ በአራት ዓመታት ውስጥ የሚሰጠውን የብድር መጠን በአራት እጅ አሳድጓል፡፡ በ2016 የሒሳብ ዓመት መጨረሻም ዓመታዊ የትርፍ መጠኑን 6.3 ቢሊዮን ብር በማድረስ፣ ከኢትዮጵያ በአትራፊነታቸው ከሚጠቀሱ ሦስት ባንኮች መካከል አንዱ ለመሆን እስከመቻል ደርሷል፡፡

የመንግሥት ቀጥተኛ ድጋፍ ተደርጎለትም፣ እየተደረገለት ቢሆን፣ እንዲህ ያለው አፈጻጸም በመልካምነቱ የሚጠቀስ ነው፡፡ ከልብ ከተሠራ ውጤት የሚገኝ ስለመሆኑም የሚያመለክት ነው፡፡ ሊያዋጣ የሚችል የአገልግሎት አሰጣጥና ዕቅድ መዘርጋቱንም የሚያመለክት ነው፡፡

ከሰሞኑም ባንኩ የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸሙን የሚያሳው ሪፖርቱ፣ አሁንም በብዙ መለኪያዎች አጥጋቢ ውጤት አስመዝግቧል ተብሏል፡፡ ከብድር አመላለስ ጋር በተያያዘ ግን ያልተጠበቀ ተግዳሮት እንደነበረበት ተጠቅሷል፡፡ በስድስት ወራት ውስጥ 7.8 ቢሊዮን ብር ብድር ለመሰብሰብ አቅዶ፣ አፈጻጸሙ ግን 6.1 ቢሊዮን ብር መሆኑንም አስታውቋል፡፡

አኃዛዊ መረጃው ባንኩ ባቀደው ልክ መሰብሰብ አለመቻሉን ያመለክታል፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ የተሰጠው ማብራሪያ ደግሞ ትኩረት የሚስብ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ከሪፎርሙ በኋላ ውጤታማ ሆኜበታለሁ ብሎ የሚጠቅሰው ብድር የማስመለስ ሥራው፣ በዘንድሮው ግማሽ ዓመት ባሰባሰበው ልክ ያላሰባሰበው አንድ ነገር በማጓደሉ ነው፡፡ ይህም ይሰጥ ከነበረው ማበረታቻ ጋር ይያያዛል፡፡

ባንኩ ከሪፎርሙ በኋላ ከፍተኛ የተባለውን የተበላሸ ብድር ወደ ሰባት ሊያወርድ የቻለው ባለፉት አራት ዓመታትም የሰጠውን ብድር ከዕቅዱ ብዙም ባልራቀ ሁኔታ በተገቢው መንገድ ሊሰበሰብ የቻለበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ለተበዳሪዎች የተለያዩ ማበረታቻዎችን ይሰጥ ስለነበረ ነው፡፡

ይህ ማበረታቻ በተለይ በአምራች ዘርፉ ለተሰማሩ ተበዳሪዎች ለሚያስፈልጋቸው ጥሬ ዕቃና መለዋወጫ ዕቃዎች መግዣ የውጭ ምንዛሪ በማቅረብ የሚገለጽ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ማበረታቻ ተበዳሪዎችን በማካተት ብድራቸውን በአግባቡ እንዲከፍሉ ዕድል በመስጠቱ ያቀደውን ብድር በዕቅዱ ልክ ወይም ተቀራራቢ በሆነ አፈጻጸም ለማስመለስ አስችሎታል፡፡ ይህ የሚያሳየው እንዲህም ባለው ዘዴ ደንበኞችን መደገፍ፣ ብድርም በጊዜው እንዲሰበሰብ ማስቻሉን ጭምር ነው፡፡

ይህንን ሁኔታ በተመለከተ የባንኩ ፕሬዚዳንት የሰጡት ማብራሪያ በ2016 ግማሽ ዓመት ግን ይህንን ማበረታቻ ለመስጠት የሚያስችለው የውጭ ምንዛሪ ማቅረብ  አልቻለም፡፡ 

በግማሽ ዓመቱ ብድር ከማስመለስ ሥራቸው ጋር ተያይዞ የገጠማቸው ትልቅ ተግዳሮትም ይኼው እንደ አንድ የአሠራር ሥልት ሲከተለው የነበረው ማበረታቻ መቋረጥ ነው፡፡ የተለመደው አሠራር መቅረቱ የብድር አመላለሱ ላይ ችግር መፍጠሩንም የፕሬዚዳንቱ ገለጻ አመላክቷል፡፡

ከዚህም በኋላ ቢሆን ማበረታቻው አስፈላጊ ስለመሆኑ የሚያስገኛቸውን ኢኮኖሚዊ ጥቅሞች ጭምር ጠቃቅሰዋል፡፡ ስለዚህ መንግሥትም ዕገዛ ቢያደርግላቸው ውጤታማ ነበር የተባለውን አሠራር በማስቀጠል ብድሩን በአግባቡ ማሰባሰብ እንደሚቻልም ጠቆም አድርገዋል፡፡

እንዲያውም እንዲህ ያለውን አገልግሎት ለማስቀጠል የሚያስፈልጋቸው የውጭ ምንዛሪ ከ150 ሚሊዮን ዶላር የማይበልጥ መሆኑንም በግልጽ ተናግረዋል፡፡ እዚህ ላይ ማበረታቻው ባንኩ ብድር ለማስመለስ ብቻ ይጠቅመኛል ብሎ የዘረጋው አሠራር እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ማበረታቻውን መስጠት ትልቅ ትርጉም ያለው ነው፡፡ ማበረታቻው ባንኩ ብድር ለማስመለስ ብቻ ይጠቅመኛል ብሎ የዘረጋው አሠራር እንዳልሆነም ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ስለዚህ ባንኩ ቀይሶት የነበረው አሠራር ውጤት ያስገኘ፣ ለባንኩንም ሆነ ለተበዳሪዎች፣ ከዚያም በላይ ኢኮኖሚው ላይ የራሱ የሆነ ጠቀሜታ ካመጣ  አሠራሩን ማስቀጠል የተጠየቀውንም ድጋፍ መስጠት አስፈላጊ ይሆናል፡፡

ነገር ግን ለጥሬ ዕቃ መግዣ የውጭ ምንዛሪ ካልቀረበልኝ ያለብኝን ብድር በወቅቱ አልከፍልም የሚል አንድምታ እስካላመጣና በተገለጸው ልክ እየተሠራበት ከሆነ አሠራሩን ለልማት ባንክ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ባንኮችም እንዲጋሩት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ባንኮች ጤናማ የፋይናንስ እንቅስቃሴ እንዲሠርፅ ተበዳሪዎችን የበለጠ አምራችና ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ ማበረታቻዎችን በማቅረብ አገልጋይነታቸውን በተግባር ማሳየት የሚጠበቅባቸው ከሆነ እንዲህ ያለው አሠራር መለመድ አለበት፡፡ ዛሬ በበርካታ ባንኮች ጥቂት የማይባሉ ተበዳሪዎች ቢዝነሳቸውን ማስቀጠል ያልቻሉበት አንዱ ምክንያት በአገልጋይነት ስሜት ተበዳሪዎችን በመደገፍ ወደ መስመር እንዲገቡ ባለማድረጋቸው ጭምር መሆኑ አይካድም፡፡ ባንኮች ብድራችን አልተመለሰም ብለው ገንዘባቸውን ለማግኘት በመያዣ የያዙትን ትልልቅ ኩባንያዎች በጨረታ የሚሸጡበት በተበዳሪዎች ችግር ብቻ አይደለም፡፡ ስለዚህ ንብረቱን ሸጦ ገንዘባቸውን ከማግኘት ባለፈ፣ የኩባንያዎች ቀጣይነት ላይም የራሳቸውን አሻራ ሊያሳርፉ ይገባል፡፡ ኩባንያዎችን ለማዳንም ሆነ ተሰብሳቢ ብድሮችን በአግባቡ ለማግኘት ያስፈልጋል የተባሉ ማበረታቻዎች ላልተፈለገ ዓላማ እስካልዋሉ ድረስ ሊበረታታ ይገባል፡፡ ለጥሬ ዕቃና መሰል ወጪዎች የሚያስፈልጉ የውጭ ምንዛሪ በማቅረብ፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እስካላጣ ድረስ የማበረታቻ ዓይነቶችም የውጭ ምንዛሪ በማቅረብ ብቻ ሳይሆን፣ ሌላም መንገድ ሊኖር ስለሚችል ይህንን አጥንቶ መተግበር የጋራ ተጠቃሚ መሆን ያስችላል፡፡ ከዚህ አንፃር እንደ ልማት ባንክ 150 ሚሊዮን ብር ስላጣሁ ብድሬን በአግባቡ ለማሰባሰብ አልቻልኩም ሲባልም ለጥያቄው ጆሮ መስጠት ተገቢ ይሆናል፡፡  

ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ ግን ባንኩ ይህንን ስላለ ብቻ መንግሥት የጠየቀውን የውጭ ምንዛሪ ዝም ብሎ አንስቶ ይሰጥ ማለት አይደለም፡፡ በእርግጥ ይህንን በማድረግ ሊገኝ የሚችለው ጥቅም የተባለውን ያህል ነው ወይ? ብሎ ማጣራትን ይጠይቃል፡፡ ይህ ከሆነ በባንክ ብድር ቢሊዮን ብሮች ፈሶባቸው የሚገነቡ ፕሮጀክቶች ብድራቸው ሳይከፈል የሚቀርበትን ሁኔታ ያስቀራል፡፡ ተበዳሪዎቹ ግለሰቦች ቢሆኑም፣ የሚበደሩት የሕዝብ ገንዘብ ነውና ሮጦ ንብረቱን በሐራጅ ከመሸጥ ውጤታማ ሆነው እንዲሠሩ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የበለጠ ውጤት የሚያመጡት ደግሞ ተጠያቂነት ያለበት የሕግ ማዕቀፍ ሲኖራቸው መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት