Sunday, April 21, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ካሪቡ አፍሪካ፡ ኢትዮጵያ ‹የአፍሪካ እናት ናት› ስንል በምክንያት ነው

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ ደስታ

  • የኢትዮጵያ ዘውዳዊ መንግሥት በየወሩ ለታንዛንያው የነፃነት ታጋይ ለጁሊየስ ኔሬሬ ደመወዝ ትከፍላቸው እንደነበር የምናውቅ ስንቶቻችን ነን፤
  • የኬንያው የነፃነት አባት ለጆሞ ኬንያታ ሴት ልጅስ ኢትዮጵያ በየወሩ 250 የኬንያ ሽልንግ ተቆራጭ በማድረግ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን እንድትጨርስ ማድረግዋንስ፤
  • አገራችን ኢትዮጵያ ለናሚቢያ ነፃነት ዘጠኝ ዓመት በዓለም ፍርድ ቤት ጠበቃ አቁማ መከራከሯንስ . . .፤

ለደቡብ አፍሪካ፣ ለዚምባቡዌ፣ ለጋና ነፃነት ያደረገችው ውለታዋ… ሌላም… ሌላም… እናት ኢትዮጵያ ለአፍሪካና ለአፍሪካውያን ያደረገችው ተዘርዝሮ የማያልቅ ውለታ . . .!!

‹‹ኢትዮጵያ የአፍሪካ እናት›› ሲባል እንዲሁ ለንግግር ማሳመሪያ ወይም ለጉራ አይደለም፡፡ በርግጥም አገራችን ኢትዮጵያ- ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ‹ተቆርቋሪና ደግ እናት› መሆኗ በታሪክ መዛግብትና በታላላቅ ሰዎች አንደበት ጭምር ተደጋግሞ የተመሰከረለት፤ ሊካድ የማይችል የታሪክ ሐቅ ነው፡፡

ለአብነትም፣

ከሰሞኑን የአፍሪካ ኅብረት በ37ኛው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለታዋቂው ፓን-አፍሪካኒስት፣ የታንዛኒያ የነፃነት ታጋይና መሪ – በአፍሪካ ኅብረት የሰላምና የጸጥታ ሕንፃ ፊት ለፊት የታነጸው የመታሰቢያ ሐውልት ከሰሞኑን በክብር ተመርቋል፡፡ ለመሆኑ ኢትዮጵያ  ለእኚህ የነፃነት ታጋይ የወር ደሞዝ ትቆርጥላቸው እንደነበር የምናውቅ ስንቶቻችን ነን…?!

ለታንዛንያው የነፃነት አርበኛ ለጁሊየስ ኔሬሬ ከኢትዮጵያ መንግሥት የወር ደመወዝ ተቆርጦላቸው ይከፈላቸው ነበር፡፡ ከዚህ የኢትዮጵያውያን ውለታ የተነሳም ታንዛንያውያን ነፃነታቸውን ከተጎናጸፉ በኋላ የውጭ አገር ሰዎች ከታንዛንያ ሲባረሩ ስድስት መቶ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ቤተሰቦች ከኪሊማንጃሮ ተራራ አጠገብ በግብርና የመኖር መብታቸው ተጠብቆላቸው በክብር እንዲኖሩና ከአገር እንዳይወጡ ተደርጎ ነበር፡፡

ከ60 ዓመታት በፊት የኬንያው ‹‹የማኦ ማኦ›› ሕቡዕ ነፃ አውጭ ድርጅት መሪ የነበሩት ጆሞ ኬንያታ ለሰባት ዓመት ያህል በእንግሊዝ መንግሥት ታስረው ነበር፡፡ በወቅቱም የኢትዮጵያ መንግሥት ትምህርቷን በዩኒቨርሲቲ ትከታተል ለነበረችው ለጆሞ ኬንያታ ሴት ልጅ፣ በየወሩ ሁለት መቶ ሃምሳ የኬንያ ሽልንግ በኢትዮጵያ መንግሥት ጄኔራሌ ቆንሲሌ አማካይነት ይሰጣት ነበር፡፡ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥት ኬንያ ላይ ደርሶ ለነበረው ረሃብ ዕርዳታ የሚውል በኬንያ የብሪታንያ ተወካይ በነበሩት በሰር ሃምፍሬይ በኩል ሁለት መቶ ሃምሳ ሺሕ ሽልንግ ለኬንያ ዕርዳታ ልግስና አድርገዋል፡፡

የኬንያው የነፃነት አባት ጆሞ ኬንያታ ከእስር እንደተፈቱም የአገራችንን ውለታ በማሰብ ከሴት ልጃቸው ጋር በአገራችን ይፋዊ ጉብኝት አድርገው ነበር፡፡ በወቅቱም በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ልደት አዳራሽ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ላደረጉላቸው ውለታ ከፍ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ይህ ኢትዮጵያ ለአፍሪካና ለሌሎች የዓለም ሕዝቦች እናት የመሆኗን እውነታ ከታሪክ መዛግብት ብናገላብጥ የምናገኘው የታሪክ ሐቅ ነው፡፡ ለአብነትም ከመጽሐፍ ቅዱስ እስከ ቅዱስ ቁርኣን፣ ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.)፣ ከግሪካውያኑ ጠቢባን፣ ፈላስፋዎች እና የታሪክ ምሁራን ከሔሮዱተስ እስከ ሆሜር፣ ከጥቁር ሕዝቦች መብት ታጋዮች እና ፓን አፍሪካኒስቶቹ- ከማርከስ ጋርቬይ እስከ ዊሊያም ኤድዋርድ ቡርግሃርድ ዱ ቦይስ፣ ከጋናው የነፃነት አባት ከዶ/ር ክዋሜ ንኩርማህ እስከ የኬንያው የነፃነት አባት ጆሞ ኬንያታ፣

ከደቡብ አፍሪካው የነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ እስከ ኦሊቨር ታምቦ እና ታቦ እምቤኪ፣ ከዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ እስከ ሴኔጋላዊው ሴዳር ሴንጎር… ወዘተ. ያሉ ታላላቅ ሰዎች፤ አገራችን ኢትዮጵያ ‘‘የአፍሪካ እናት’’፤ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ የአፍሪካዊነት/የጥቁር ሕዝቦች ነፃነትና ብሔራዊ ኩራት፣ የታሪክና የሥልጣኔ፣ የባህልና የቅርስ መሠረት መሆኑን ደግመው ደጋግመው መስክረዋል፡፡

ይህን የታሪክ እውነት የፀረ አፓርታይድ ታጋይ፣ የነፃነት አርበኛ እና የዓለም ሰላም ኖቤል አሸናፊ የሆኑት ኔልሰን ማንዴላ፣ Long Walk to Freedom በተባለ መጽሐፋቸው፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት- በደቡብ አፍሪካውያንና በአፍሪካ ሕዝቦች ዘንድ የነበረውንና ያለውን ታላቅ ክብርና ስፍራ በተመለከተ እንዲህ ሲሉ ነበር በአጭር ቃል የገለጹት፤

‘‘Ethiopia always has a special place in my imagination & the prospect of visiting Ethiopia attracting me more strongly trip to France England & America combined, I felt I would be visiting my own genesis.’’

(ኢትዮጵያ በልቤ ውስጥ ሁልጊዜም ልዩ ቦታ አላት፤ የፈረንሳይን፣ እንግሊዝንና አሜሪካን በጥምር ከምጎበኝ ወደ ኢትዮጵያ ሄጄ ኢትዮጵያን መጎብኘት የበለጠ ይስበኛል፣ ትልቅ ደስታንም ይሰጠኛል፡፡ ይህም የራሴን [የአፍሪካዊነቴን] የታሪክና የሥልጣኔ መሠረት፣ ሰው የመሆን ነፃነትንና ክብር ዓርማ የሆነች አገርን የጎበኘሁና ያገኘሁ ያህል ሆኖም ይሰማኛል)፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንጸባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles