Saturday, April 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የጀግኖቹ የሞራል ልዕልና አይዘንጋ!

የታላቁ ዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲዘከር፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚመጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በዓድዋ ከወራሪው ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር ተፋልመው ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ አይረሴ አሻራ ያሳረፉ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በዚህ ዘመን ሲታወሱ፣ የእነሱን የአገር ፍቅር ስሜትና የሞራል ልዕልና የሚመጥን ካልሆነ የዘመኑ ትውልድ የታሪክ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ጀግኖቹ የታላቁ የዓድዋ ድል ባለቤቶች በዳግማዊ ምኒልክና በእቴጌ ጣይቱ መሪነት ዓለምን ያስደነቀ ተጋድሎ ያደረጉት፣ በዘመኑ የነበሩ ውስጣዊ ሽኩቻዎችንና አለመግባባቶችን ከአገር ፍቅር ስሜት በታች በማድረግ በአንድነት ለመቆም በመቻላቸው ነው፡፡ ይህንን የመሰለ አርቆ አሳቢነትና አስተዋይነት የነበራቸው ጀግኖቹ የዓድዋ ድል ባለታሪኮች፣ ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ከእናት አገራቸው በታች መሆኑን ለመገንዘብ የሚያስችል ከፍተኛ ሞራላዊ ልዕልና ስለነበራቸው ነው፡፡ የዚህ ዘመን ትውልድ አባላት አገር ከሚመሩ ግለሰቦች ጀምሮ እስከ ተርታው ዜጋ ድረስ፣ የዓድዋ ጀግኖችን የሞራል ከፍታ ለመጎናፀፍ የሚያስችል የአገር ፍቅር ስሜት ሊኖራቸው ይገባል፡፡

ታላቁ የዓድዋ ድል ዘወትር እንደሚባለው የኢትዮጵያውያን ወይም የአፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን፣ የመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦችና በቅኝ ገዥዎች ሲረገጡ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች ጭምር የሚጋሩት ነው፡፡ ይህንን የመሰለ አንፀባራቂና ተምሳሌታዊ ፀረ ኮሎኒያሊስት ድል ባለቤት የሆነች አገር ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ ልሂቃን፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የተለያዩ ማኅበረሰቦች አባላት ራሳቸውን በቅጡ መመርመር ይኖርባቸዋል፡፡ ታላቁ የዓድዋ ድል ከአራቱም ማዕዘናት የተሰባሰቡ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በጋራ ያስገኙት ድል ነው፡፡ እነዚያ አርቆ አሳቢ ጀግኖች እስከ አፍንጫው ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን ከታጠቀ፣ በቂ የሎጂስቲክስ አቅርቦት ከነበረው፣ ዘመናዊ የትራንስፖርትና የግንኙነት አውታር ከዘረጋ፣ በጦር ሥልቶች ዘመናዊ ሥልጠና ካገኘና በአጠቃላይ በሁሉም መመዘኛዎች የበላይነት ከነበረው አውሮፓዊ ኃይል ጋር ተፋልመው አሸናፊ መሆን የቻሉት ከራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት በላይ አገራቸውን በማስቀደማቸው ነው፡፡ ታላቁ ድላቸው በአውሮፓም ሆነ በመላው ዓለም ሲሠራጭ ከባድ ድንጋጤና መገረም የተፈጠረው፣ በወቅቱ ጥቁር ሕዝብ ነጭን ለማሸነፍ የሚያስችል ብቃት የለውም ተብሎ ስለሚታመን ነበር፡፡

የጀግኖቹ አገር ወዳድነት ግን የማይቻለውን እንዲቻል አደረገ፡፡ የአገር ፍቅር ስሜት እንዲህ ዓይነቱን ታላቅ ድል ኢትዮጵያን አቀዳጅቶ በዓለም አደባባይ ስሟን በኩራት ሲያስጠራ፣ የዚህ ዘመን ትውልድ አባላት እከሌ ከእከሌ ሳይባባሉ ለምን እንደዚያ ዘመን ጀግኖች በአንድነት ለመቆም አቃተን ማለት ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከተለመደው ክስ፣ ወቀሳ፣ ጥላቻ፣ ክፋት፣ ሴራ፣ ቂም በቀል፣ ሐሜትና አሉባልታ ውስጥ ሊያስወጡ የሚችሉ ተግባራት ላይ ማተኮር ይጠበቅባቸዋል፡፡ እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት መሰናክሎች እንዲወገዱ በአገር ደረጃ ተቀምጦ ለመነጋገር የሚያስችል ዓውድ መፈጠር ይኖርበታል፡፡ በትንሹ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠሩ ቅሬታዎችና ቅራኔዎች የኢትዮጵያን አየር ስለሞሉት፣ በቅንነትና በጨዋነት ሊያነጋግሩ የሚችሉ መድረኮችን ለማመቻቸት የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ይተኮር፡፡ አንዱ ሌላውን እያሳጣና እየወነጀለ፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ እንደ ጠላት እያሳደደና ሕዝብና አገርን ምስቅልቅል ውስጥ የሚከቱ የጥፋት ድርጊቶች ውስጥ ተነክሮ ሰላም ማስፈን አይታሰብም፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ጠላትነት ውስጥ ተዘፍቆ ታላቁን የዓድዋ ድል መዘከር ቀልድ ነው፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ውጥንቅጥ ሊወገድ የሚችለው እንደ ጀግኖቹ የዓድዋ ትውልድ ለአገር በአንድነት ለመቆም የሚያስችል ወኔ፣ የአገር ፍቅር ስሜት፣ አርቆ አሳቢነት፣ አስተዋይነት፣ ቅንነት፣ ሥነ ምግባር፣ የሞራል ከፍታና ጨዋነት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ የዓድዋ ጀግኖች ወራሪውን ኮሎኒያሊስት ኃይል ለመፋለም ጥሪ ሲደረግላቸው ያለ ምንም ማንገራገር በአንድነት የተመሙት፣ በመንግሥት አስተዳደር ሁሉም ደስተኞችና የተመቻቸው ሆነው ሳይሆን ልዩነታቸውን ወይም ቅሬታቸውን አለዝበው አገራቸውን በማስቀደማቸው ነበር፡፡ በዚህ ዘመን ግን የፖለቲካ ሥልጣንም ሆነ ጥቅም ከአገር በታች ሊሆን ባለመቻሉ፣ በትንሹም ሆነ በትልቁ ጉዳይ ልዩነት ሲፈጠር ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ ጦር መነቅነቅ የዘወትር ሥራ ከሆነ ቆይቷል፡፡ ይህ ችግር ድፍን ሃምሳ ዓመት ከሞላው የየካቲት 1966 ዓ.ም. አብዮት ጋር ይያያዛል፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘውዳዊ ሥርዓት በአብዮቱ አማካይነት ከተገረሰሰ በኋላ ኢትዮጵያ የደም ምድር የሆነችው፣ ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ አስተናግዶ ለአገር በጋራ መሥራት ባለመቻሉ ነው፡፡

በወቅቱ መንግሥታዊ ሥልጣኑን በተቆጣጠረው ደርግ፣ መኢሶን፣ ኢሕአፓና ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የተስተዋለው ፈር የሳተ አካሄድ ለአንድ ትውልድ ዕልቂት፣ እስር፣ ሥቃይ፣ ስደት፣ እንዲሁም ለፖለቲካዊ ባህል ብልሽት ዳርጎ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ ይህ ጉዳት ከሥርዓት ወደ ሥርዓት እየተሸጋገረ እዚህ ደረጃ ደርሶ በኢትዮጵያ ምድር መራር የሆነ መጨካከን ፈጥሯል፡፡ ለመስማት የሚዘገንኑ ግድያዎች፣ ማፈናቀሎች፣ ዘረፋዎች፣ ውድመቶች፣ ዕገታዎች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የመሳሰሉ አስከፊ ድርጊቶች የዚህ ዘመን መገለጫ ከሆኑ ዓመታት እየተቆጠሩ ነው፡፡ የዓድዋ ጀግኖች ከዛሬ 128 ዓመት በፊት ከነበሩበት የሞራል ከፍታ የወረዱ አሳፋሪ ድርጊቶች በስፋት ሲስተዋሉ፣ የዘመኑ ትውልድ የግልም ሆነ የወል ተጠያቂነት እንዳለበት መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ በፍጥነት ተወጥቶ እንደ ዓድዋ ጀግኖች የሞራል ከፍታውን መያያዝ ካልተቻለ፣ ታላቁን የዓድዋ ድል ለመዘከር መንደፋደፍ ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡ በቅርቡ ተገንብቶ ለዕይታ የቀረበው የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ታሪክ ዘካሪ ብቻ ሳይሆን፣ የዘመኑን ትውልድ በአንድነት የሚያስተሳስር የጋራ እሴት መሆን ካልቻለ ሐዘኑ ከባድ ነው፡፡

የጀግኖቹ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ሲዘከር ይህ ትውልድ ከላይ እስከ ታች በሕግ የበላይነት ለመተዳደር ፍላጎት ማሳየት፣ በፍትሕ፣ በነፃነትና በእኩልነት ማመን፣ ብልሹ አሠራሮችን መፀየፍ፣ ከዝርፊያና ከሌብነት መፅዳት፣ አድሎአዊነትን ማስወገድ፣ ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት የሚሆኑ ድርጊቶችን በጋራ መታገል፣ ለልዩነት ዕውቅና መስጠት፣ መከባበር፣ ለመነጋገርና ለመደራደር ፈቃደኛ መሆን፣ ከሴራና ከተንኮል መታቀብ፣ ለፍትሕና ለርትዕ ጠበቃ መሆንና ሌሎች ጠቃሚ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ አሁን በስፋት እንደሚታየው በብሔር፣ በእምነትና በሌሎች ጉዳዮች ኢትዮጵያውያንን በመከፋፈል ግጭት እየቀሰቀሱ ማፋጀት መቆም አለበት፡፡ ከአገር የበለጠ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ፍላጎትና ጥቅም እንደሌለ መተማመን ያስፈልጋል፡፡ የዓድዋ ጀግኖች ከያሉበት ተጠራርተው አገራቸውን ከአውሮፓ ኮሎኒያሊስት ኃይል ለመከላከል የተፋለሙት፣ ከአገራቸው የሚያስቀድሙት ምንም ነገር እንደሌለ ጥብቅ የሆነ ዓላማና የሞራል ከፍታ ስለነበራቸው ነው፡፡ ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር ይህ የሞራል ልዕልና እንዳይዘነጋ አደራ መባል አለበት!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...