Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየውጭ አገር የሥራ ሥምሪት አገናኝ ኤጀንሲዎች የመቶ ሺሕ ዶላር ዋስትና ግዴታ መደረጉን...

የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት አገናኝ ኤጀንሲዎች የመቶ ሺሕ ዶላር ዋስትና ግዴታ መደረጉን ተቃወሙ

ቀን:

የኢትዮጵያ የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት አገናኝ ኤጀንሲ አሠሪዎች ፌዴሬሽን አባላት፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ለዋስትና አንድ መቶ ሺሕ ዶላር ወይም ተመጣጣኝ መጠን ያለው ገንዘብ በቴሌ ብር እንዲያስገቡ በደብዳቤ ያስተላለፈውን ትዕዛዝ ተቃወሙ። 

የፌዴሬሽኑ አባላት ተቃውሟቸውን ያሰሙት ማክሰኞ የካቲት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት የስብሰባ አዳራሽ፣ በፌዴሬሽኑ በተጠራ ጉባዔ ላይ ነው። 

ፌዴሬሽኑ የኤጀንሲዎች ባለቤት የሆኑ አባላቱን ለጉባዔ የጠራው በቅድሚያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኤጀንሲዎች ወደ ውጭ አገር ለሚልኳቸው ዜጎች፣ የአደጋ ጊዜ ዋስትና የሚሆን አንድ መቶ ሺሕ ዶላር ወይም ተመጣጣኝ መጠን ያለው ገንዘብ በቴሌ ብር ይግባ በሚል ያሳለፈው ውሳኔ እንቀበል? ወይስ በአዋጁ መሠረት ባለው አሠራር እንቀጥል ለሚለው የመወያያ አጀንዳ መሆኑን አስታውቋል፡፡ 

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ፌዴሬሽኑ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በሚያደርገው ድርድር ኤጀንሲዎች በአንድ ሠራተኛ የሚቀበሉት የኮሚሽን ክፍያ መጠን ምን ያህል ይሁን የሚለውም ለአባላቱ አስተያየት የቀረበ ጥያቄ ነው። 

ከጉባዔው ተሳታፊ የኤጀንሲ ባለቤቶች መካከል አንድ አስተያየት ሰጪ፣ ‹‹ይህ ስብሰባ የህልውና ጉዳይ ነው። በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር መሽቶ በነጋ ቁጥር አዳዲስ ሕጎች እየወጡ፣ አዳዲስ ማስታወቂያዎች እየተለጠፉ በገዛ አገራችን የሥራ ነፃነታችንን አጥተናል፤›› ብለዋል። 

ተሳታፊው አክለውም፣ ‹‹መቶ ሺሕ ዶላር በቴሌ ብር አስገቡ የሚል ማስፈራሪያ ከደረሰን በኋላ፣ የማኅበሩ አባላት ሌሊት እንቅልፍ አጥተን ስንወያይ አንግተናል፣ ጉዳዩ አሳሳቢ ነው። ሲጀመር መቶ ሺሕ ዶላር በቴሌ ብር የማስያዝ አቅም አለን ወይ? ደግሞስ የፋይናንስ ተቋም ያልሆነ ድርጅት ከዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር በላይ ተሰብስቦ የሚገባለት ለምንድነው?›› ሲሉም አክለዋል፡፡ 

‹‹ፌዴሬሽኑን አጠንክረን አደራጅተን መብታችንን ማስከበር ግድ ነው። አዋጅ እያለ በየቀኑ በብጣሽ ወረቀት መብታችን ሊጣስ አይገባም፤›› ሲሉ ተናግረዋል። 

ስለሥራና ሠራተኛ ማገናኘት አገልግሎት የወጣው አዋጅ ቁጥር 623/2009 ስለዋስትና ገንዘብ አስፈላጊነት በሚለው አንቀጽ 23 ከ(ሀ) እስከ (ሐ) ዘርዝሮ ያስቀመጠው ድንጋጌ፣  ከኤጀንሲዎች የሚጠበቀውን የዋስትና ገንዘብ መጠን በግልጽ ያስቀምጣል። 

በዚህም መሠረት ሠራተኛን ወደ ውጭ አገር የሚልክ ማንኛውም የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ለሠራተኛው መብት ዋስትና ማስከበሪያ የሚውል እስከ 500 ለሚደርሱ ሠራተኞች 30 ሺሕ ዶላር፣ ከ501 እስከ 1,000 ለሚደርሱ ሠራተኞች 40 ሺሕ ዶላር፣ ከ1,001 በላይ ለሆኑ ሠራተኞች 50 ሺሕ ዶላር ወይም ተመጣጣኙን የኢትዮጵያ ብር ሃምሳ በመቶ የገንዘብ መጠን በዝግ ሒሳብ በባንክና ሃምሳ በመቶ ከታወቀ የገንዘብ ድርጅት የተረጋገጠና የማይሻር የዋስትና ወረቀት ማስቀመጥ አለበት ይላል። ንዑስ አንቀጽ ሁለት ከሦስት አገሮች በላይ የሚልክ ኤጀንሲ ተጨማሪ ገንዘብ ማስያዝ እንደሚኖርበት ይደነግጋል። 

ለፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ መዝገቡ አሰፋ ሪፖርተር መቶ ሺሕ ዶላር ወይም ተመጣጣኝ መጠን ያለውን ብር በጥሬ ገንዘብ በቴሌ ብር አስገቡ የሚለው ትዕዛዝ ከሚኒስቴሩ መቼ እንደተላለፈ ላቀረበው ጥያቄ፣ ‹‹ሰኞ የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ነው አንድ ማስታወቂያ የወጣው። እዚህ ስብሰባ እንዳለን ስላወቁ ይሁን አጋጣሚ ይሁን አላውቅም፣ ግን ሰኞ የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ነው ማስታወቂያው የወጣው። በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚወጡ ማስታወቂያዎች ትልቁ ችግር ማኅተም ይደረግባቸዋል፣ አንዳንዴ ፊርማ ይኖራል፣ አንዳንድ ጊዜ አይኖርም፣ ማን ፈርሞ እንዳወጣውም አይታወቅም። በእነሱ ድረ ገጽ በእነሱ ሲስተም ላይ ስለተለቀቀ ያው እነሱ ናቸው የለቀቁት ብለን እንወስዳለን እንጂ፣ በትክክል ደብዳቤውን ያወጣው ማነው ብለን ሄደን የምንጠይቀው? ማን ይሁን ማን አይታወቅም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። 

አቶ መዝገቡ፣ ‹‹የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አዲስ ዲጅታላይዝ እያደረገ ያለው ሲስተም በጣም ሥራ አቅልሎልናል፡፡ እዚያ አካባቢ ያሉ አንዳንድ እንከኖችን ግን በውይይት መፍታት አለብን ብለው ነው የተነጋገርነው፤›› ብለዋል። 

ነገር ግን ማክሰኞ የካቲት 19 ቀን የጉባዔ ጥሪ የተደረገለት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አንድም አመራር ለውይይት እንዳልተገኘ ፌዴሬሽኑ አሳውቋል፣ ሪፖርተርም ተመልክቷል። 

በማክሰኞ ዕለቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ጉባዔ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ አባል በበኩላቸው፣ ‹‹ኤጀንሲዎች እዚያ መሥሪያ ቤት ያለን ክብር በጣም የወረደ ነው። ፌዴሬሽኑ እንዴት ነው ከሚኒስቴሩ ጋር እየሠራ ያለው? እኛን ብቻ ነው የማያከብሩት ወይስ እናንተንም ነው?›› ሲሉ ጠይቀዋል። 

አስተያየት ሰጪው የፌዴሬሽን አባል አክለውም፣ ‹‹ሚኒስቴሩም በአዋጅ መሠረት ነው የተቋቋመው፡፡ እኛ ኤጀንሲዎችም በሕግና በአዋጅ የተሰጠንን መብታችንን ተጠቅመን ነው የተቋቋምነው። የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሲስተም አበልፃጊነት ኃላፊነትና ሥልጣን የተሰጠው በማነው? በአዋጁ መሠረት ማን ምን እንደሚያደርግ ይታወቃል። በቴሌ ሚኒስቴር ብርና በጥሬ ገንዘብ ክፈሉ የሚባለው ከአዋጁ ውጪ ከየት የመጣ ነው? ፌዴሬሽኑስ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን በሕግ መጠየቅና ይህን ትዕዛዝ ማሳገድ ያልቻለው ለምንድነው?›› ሲሉ የፌዴሬሽኑን አመራሮች ምላሽ እንዲሰጡ ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል። 

የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህን ትዕዛዝ ለምን አስተላለፈ ተብሎ ለምክትል ፕሬዚዳንቱ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹አሁን የዕድሳት ጊዜያችን ደርሷል። ኤጀንሲዎች በሙሉ ፈቃድና ብቃት ማረጋገጫ የሚያድሱበት ጊዜ ደርሷል። በዚህ ወቅት እኛ የባንክ ዋስትና ገንዘቡን ገቢ አድርገናል። ለማስገባታችን የማረጋገጫ ሰነድ ተሰጥቶናል። አሁን ደግሞ በጥሬ ገንዘብ እንቁጠር የሚል ነገር ነው ከሚኒስቴሩ የመጣው። ያ ደግሞ አጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱን የሚተላለፍ አካሄድ ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። 

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት በበኩላቸው የሕግ አማራጮችን ለመመልከት ፌዴሬሽኑ የገንዘብ አቅም እጥረት እንዳለበት ገልጸዋል። የፌዴሬሽኑን የገንዘብ አቅም ለመገንባት ከአባላት አሥር ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ አቅዶ ከስምንት ወራት በፊት ኮሚቴ ቢቋቋምም፣ ከ700,000 ብር በላይ መሰብሰብ ሳይቻል እንደቀረና ሥራው እንደቆመም ተነግሯል። 

በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በጥሬ ገንዘብ የተጠየቀውን ዋስትና አስመልክቶ አስተያየት የሰጡ የአንድ ኤጀንሲ አባል፣ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ንግድ ተቋማት ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ዋስትና ሲጠየቁ ከባንኮች ጋር ነው የሚሠሩት። ይህ በእኛ ኤጀንሲዎች ላይ በተለየ የሚደረገው ለምንድነው?›› ሲሉ ጠይቀዋል። 

ሌላ አባል ደግሞ፣ ‹‹መቶ ሺሕ ዶላር አስይዙ የሚለው ጉዳይ በቴሌ ብር መሆኑ ሳይሆን፣ ዋናው ጥያቄ በባንክስ ቢሆን አስይዙ ብንባል እንችላለን ወይ የሚለው ነው። በብድር የመንቀሳቀስ መብታችንን ነው እየተነፈግን ያለነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ መዝገቡ ለምንድነው የዋስትና ገንዘቡ በጥሬ ገንዘብ እንዲገባ የተፈለገው የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው፣ ‹‹እሱን ነው ያልተረዳነው። በዚህ ጉዳይ ገና የበለጠ መነጋገር ያስፈልጋል፤›› ብለዋል። 

አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ የኤጀንሲ ባለቤት፣ ‹‹ሕግን ከማስከበርና የዜጎችን ደኅንነት ከማስከበር አንፃር ኤጀንሲዎች ችግር ስላለብን ነው አሁን መብታችንን ማስከበር የከበደን። የውጭ ምንዛሪ የመንግሥት ዋነኛ ጉዳይ ነው። አስፈላጊነቱን ሁላችንም እናውቃለን። የሚኒስቴሩን ተወካዮች ዛሬ ጠራናቸው ለምን አልመጡም? ዛሬ ተወያይተን መሄድ ያለብን ፌዴሬሽኑን እንዴት ነው የምናሳድገውና መብታችንን ማስከበር የምንችለው የሚለውን ነው። ካልሆነ የፌዴሬሽኑን አመራሮች በቃ አልቻላችሁም ብለን መቀየርም እንችላለን፤›› ሲሉ ተናግረዋል። 

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት የኤጀንሲዎች ሕግን አክብሮና የዜጎችን መብትና ደኅንነት አስከብሮ ከመሥራት አንፃር ስላሉ ችግሮች ሲናገሩ፣ ‹‹ሁለት አገር የላችሁም፡፡ ይህችን አገርና ራሳችሁን መጥቀም በምትችሉበት ሁኔታ ፌዴሬሽኑ የኮሚሽን ዋጋ ቆርጦ ተወያይቶ ሲስተም ውስጥ በሰው 900 ዶላር ኮሚሽን እንዲገባ አድርጎ እያለ የእኛም አባል ልትሆኑ ትችላላችሁ፣ ሌላውም ሊሆን ይችላል፣ ማስረጃዎቹ በእጃችን አሉ። ሌሎች ለሚመለከታቸው አካላት ብቻም ነው የምንሰጠው። እኛ ጋ ግን ማስረጃዎች ከእነ ፎቶግራፋችሁ ከእነ ድምፃችሁ አለን፤›› ብለዋል። 

አሉ ስላሉዋቸው ማስረጃዎች ማብራሪያ ሲሰጡም፣ ‹‹ለምን ለዓረብ ዜጋ ይቀራል? ለዚህች ደሃ አገር ምን አለ የውጭ ምንዛሪው ቢገባ? ከዚያ በላይ ለእናንተ ነው ገቢው፣ ለመንግሥት ግብር ብትከፍሉበት ነው ግፋ ቢል። ስለዚህ ከዋጋ በታች በመሆን ዜጎቻችን የፊሊፒንስና የኢንዶኔዥያ ዜጎች ተከብረው በሚሠሩበት አገር ኢትዮጵያ ተወደደች ብለን፣ ባለው አቅም መንግሥትም ግለሰቦችም ዜጎችን በማሠልጠን እየላካችሁ ባላችሁበት ወቅት የእናንተን ገበያ ለመሻማት ብቻ ሁኔታውን ለመግለጽ ቋንቋው አይመችም (ዜጎች ናቸው የሰው ልጅ ክብር አለው) “Buy One Free One” ‹‹አንድ ግዥ አንድ ነፃ›› እስከሚባል ደረጃ ድረስ ለዓረቦች ዋጋ አውርዳችኋል። የ900 ዶላር ኮሚሽኑን 450 ሆኖ አንድ ስጦታ ነው፣ አንድ ደግሞ በገንዘብ እስከሚባል ደርሷል፤›› ብለዋል።

ጉዳዩን አስመልክቶ አስተያየት የሰጡ ሌላ አባል በበኩላቸው፣ ‹‹አንዳንድ ኤጀንሲዎች ዘንድ 15 ሰው እልክልሃለሁ አምስቱን በነፃ እጨምርልሃለሁ እያላችሁ የምትደራደሩ እንዳላችሁ እናውቃለን፤›› ብለዋል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አያይዘውም፣ ‹‹ይህ ተግባር ከዛሬ ጀምሮ የማይቆም ከሆነ ከዘርፉ በፈቃዳችሁ መውጣት ብቻ ሳይሆን፣ የሕግ ተጠያቂነት እንዳለም አውቃችሁ በፈቃዳችሁ ከዚህ ተግባር ውጡ፤›› ሲሉ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። 

የውጭ አገር ሥራ ሥምሪት አዋጅ 923/2016 አንቀጽ 19 የሥራ ሁኔታዎችን ለመወሰን የወጣው ድንጋጌ በቅድሚያ እንዳስቀመጠው፣ በተቀባይ አገር መነሻ ክፍያ ተብሎ ከተወሰነው ኢትዮጵያና ተቀባይ አገር ባደረጉት የሠራተኛ ቅጥር ሁለትዮሽ ስምምነት መነሻ ክፍያ ተብሎ ከተደረሰው ሁለቱ አገሮች ባፀደቁት ዓለም አቀፍ ስምምነት ከተመለከተው አነስተኛ የደመወዝ መጠን የማያንስና የተሻለ ጥቅም የሚሰጥ፣ የደመወዝና መደበኛ የሥራ ሰዓትና የትርፍ ሰዓት ክፍያ አያያዝ ያለው በሚኒስቴሩ የተዘጋጀ ሞዴል የሥራ ውል መጠቀም እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ 

የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት አገናኝ ኤጀንሲ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት፣ ‹‹አላሠራ ያሉን ብዙ ነገሮች አሉ። በዚያ ላይ አብረን የምንሠራበትና የምንታገልበት ብዙ አለ፡፡ እኛ ንፁህ እንሁንና ማን እንደሚያሸንፈን እናያለን፣ እኛ ከተደራደርንላችሁ ከ900 ዶላር ኮሚሽን በታች አታውርዱ፤›› ብለዋል። 

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርን የመቶ ሺሕ ዶላር ወይም ተመጣጣኙን በጥሬ ገንዘብ አስገቡ ትዕዛዝን በተመለከተም ከአባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ፣ ‹‹ባንኩ በዝግ አካውንት አስቀምጬለታለሁ ካለ፣ ሁሉም ኤጀንሲ አሥር በመቶ ለባንኩ ሰጥቶ፣ ባንኩ የዋስትና ማረጋገጫ ከጻፈ ወዲያ፣ ያለህን ንብረት ሸጠህ ስትሞት ካላየሁህ የሚለው አጉል ነው አንቀበልም፤› ብለዋል። 

ከሚኒስቴሩ በኩል ሕገወጥ የባንክ የዋስትና ማረጋገጫ ከተገኘ የሚል ጥያቄ እንደቀረበላቸው የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹ሕገወጥና ፎርጅድ የባንክ ማስረጃ ያቀረበ ኤጀንሲ ፈቃድ ይሰረዝ ብቻ ሳይሆን፣ በሕግ ተጠያቂ ተደርጎ ይታሰር ብለን መልሰናል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ (ክፍል አንድ)

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...