Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየዓድዋ ጦርነትና በዋዜማው የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ሁኔታ

የዓድዋ ጦርነትና በዋዜማው የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ሁኔታ

ቀን:

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

የኢትዮጵያ ሁኔታ

የዓድዋ ድል ከተገኘ እነሆ 128 ዓመታት አስቆጠረ፡፡ ሆኖም ስለድሉ ሲወሳ እንጂ ከድሉ በፊት ስለነበረው ሁኔታ ሲነገር ብዙም አይሰማም፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ይህን ክፍተት ኢምንት ያህልም ቢሆን ለመሙላት ነው፡፡ ስለሆነም ስለወቅቱ የኢትዮጵያ ሁኔታ ሲወሳ ኢትዮጵያ ከዘመነ መሣፍንት ተላቃ አንድነቷን ካስከበረች ገና በአሠርት ዓመታት ውስጥ እንደነበረች መጥቀሱ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ጊዜ ሲጠቀስም የሕዝቡ ሥነ ባህሪያዊ አመለካከት ከአፄ ቴዎድሮስ፣ ከአፄ ዮሐንስና ከአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጋር እንደሚያያዝ አያጠያይቅም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛት ለማድረግ የተደረገ ጦርነትና ስምምነት

ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛት ለማድረግ የተደረጉት ጦርነቶች ከጥንት ከግብፅ፣ ከዚያም ከኦቶማን ኢምፓየር፣ ቀጥሎም የስዊዝ ካናል መከፈትን ተከትሎ አፍሪካን እስከ መቀራመት ዘመቻ ያለው የታሪክ ጉዞ ሲታይ በእጅጉ ብዙ ነው።  ሆኖም ሁሉንም ማቅረብ ስለማይቻል ኢትዮጵያንና ኤርትራን ባፈራቀቁት ጦርነቶች ላይ በቅድሚያ እንመልከት፡፡

በዓድዋ ጦርነት ዋዜማ የቱርክና የግብፅ ወረራ

የኦቶማን ሥርወ መንግሥት እየተባለ የሚጠራው የቱርክ መንግሥት፣ ከጥንት ጀምሮ የቀይ ባህርን የንግድ መስመር ከሜዲትራንያን ባህር ጋር ቀላቅሎ ለመያዝ በነበረው ብርቱ ፍላጎት፣ ከኢትዮጵያ ጋር ግን ያልተቋረጠ ጦርነት አድርጓል። በዚህም መሠረት እ.ኤ.አ. በ1557 የምፅዋ በቱርክ ኡስማናውያን መያዝ ባህረ ነጋሹንና በአጠቃላይም መላውን የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ሥጋት ላይ ጣለው። ወደ አገር ውስጥ በመዝለቅ በኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ጣልቃ ለመግባት ሞከረ። ይህም ወራሪዎች ከሰሜኑ ጠረፍ ወደ ውስጥ እየመጡ ኢትዮጵያን ለመውጋት ካደረጉት አያሌ ጥረት የመጀመሪው ሙከራ ነበር። ይሁን እንጂ የአፄ ሠርፀ ድንግል ዜና መዋዕል እንደሚያስረዳው የሐማሴን ሕዝብ ወራሪዎቹን ወዲያውኑ በቆራጥነት ተቋቁሞ መልሷቸዋል። በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ1636 አዲስ መናገሻ መዲና በጎንደር ከተመሠረተ በኋላ፣ የመሃሉ መንግሥትና አሁን ኤርትራ የምትባለዋ ግዛት አንድነት በይበልጥ ተጠናከረ። ቀደም ሲል በጨረፍታ እንደቀረበው ሁሉ ከጎንደር ነገሥታት ልቀው የታወቁት ታላቁ ቀዳማዊ ኢያሱ ዜና መዋዕላቸው እንደሚያስረዳው የሰራዬዋን ወለተ ጽዮንን አገቡ። ከዚያም ቱርኮች በምፅዋ በኩል በሚወጣውና በሚገባው ንግድ ላይ በምንም ዓይነት ጣልቃ እንዳይገቡ ለማገደድ እ.ኤ.አ. በ1693 ወደ ባለቤታቸው የትውልድ ሥፍራ ኤርትራ እየተጓዙ ያስገብሩ ነበር። ከእዚህ የንጉሠ ነገሥት ዜና መዋዕል ለመረዳት እንደሚቻለው በእሳቸው ዘመን ብዙ መኳንንት ዓመታዊ ግብራቸውን ለመክፈል፣ እንዲያም ሲል ለመሾምና ለመሸለም ወደ ጎንደር ይመላለሱ ነበር። በ17ኛው ምዕተ ዓመት የንጉሠ ነገሥት ሱስንዮስ ዜና መዋዕል ውስጥ ከትግራይ (ኤርትራን ይጨምራል) እና ከሌላው ግዛት የተገኘውን ግብር ዝርዝር መዝግቦት ይገኛል።

አሁን ‹‹ኤርትራ›› እየተባለች በምትጠራውና ከእርሷም ደቡብና ምዕራብ ባለው ክልል መሃል ያለው አንድነት ተዛምዶ እንዴት እንደነበረ፣ በ18ኛው ምዕተ ዓመት መገባደጃ ገደማ በተነደፈ የትግራይ ካርታ ላይ በግልጽ ተመልክቷል። በስምንተኛው የኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባዔ ውጤት ውስጥ በተካተተው የአሉላ ፓንክረስት ጥናት ውስጥ የኢትዮጵያ ቤተ ክህነት መዲና ከነበረችው አክሱም በኋላ የኤርትራ ክፍል የሆኑትን ሰራዬን፣ ሐማሴንና ቡርን ከሰሜን በመጨመር በጠቅላላው 12 አውራጃዎች እንደነበሯት ያስረዳል። እ.ኤ.አ. በ1810 ገደማ ግብፆች ሱዳንን በጦር ኃይል ከያዙ በኋላ በምዕራብ ኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ መታየት ጀመሩ። የኃይል ሚዛኑን በማየት ወረራ ለማካሄድ አልቻሉም። እ.ኤ.አ. በ1828 ግን ወልቃይት ላይ ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር ጦርነት ገጥመው ድል ሆኑ። በወልቃይት በኩል ሽንፈት ሲገጥማቸው እ.ኤ.አ. ከ1832 እስከ 1834 ድረስ በነበረው ጊዜ ከኤርትራ እስከ ወለጋ ድረስ ባለው የኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ሰላምና ፀጥታን ሲያደፈርሱ ቆይተዋል። በ1879 ዓ.ም. በተጠቀሰው የኢትዮጵያ ግዛት ድንበር አካባቢ በደጃች ክንፉ የተመራው የኢትዮጵያ ጦር በወራሪው የግብፅ ጦር ላይ ድልን ተቀዳጀ። ይሁንና ቀደም ባሉት ዘመናት በተለይም ፈረንሣዮች ሰሜኑን የኢትዮጵያ ክፍል ለመቆጣጠር የሚያስችላቸው ስምምነት ከኢትዮጵያ በኩል ለማግኘት ለረዥም ጊዜ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀረ።

በ1847 ዓ.ም. የጎንደሩ ካሳ ኃይሉ በኋላ አፄ ቴዎድሮስ ተብለው ሲነግሡ ከግብፆችና ከቱርኮች ጋር ተደጋጋሚ ጦርነት እንዳካሄዱ ሲታወቅ ቴዎድሮስ በ1860 ዓ.ም. በእንግሊዞች ተሸነፉ። ሆኖም ግብፆች በአፄ ቴዎድሮስና በሥልጣን ተቀናቃኞቻቸው ይደረግ በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ክፍተት ስላገኙ ግብፆች እ.ኤ.አ. በ1864 ከረንን ይዘው እንደነበር አይዘነጋም። ዳሩ ግን አፄ ዮሐንስ ከአፄ ቴዎድሮስ ቀጥሎ ሥልጣኑን ይዘው ስለነበር በህዳር ወር 1868 ዓ.ም. በጉንደት ላይ ጦርነት በመግጠም ድል አደረጉ። በየካቲት ወር 1868 ዓ.ም. ጉርአ ላይ ለሦስት ቀናት በተደረገው ጦርነት የግብፅን ጦር ደመሰሱ። ከከረን በቀር ሌላውን የኤርትራ ክፍል በቀላሉ በቁጥጥራቸው ሥር አዋሉ።ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የኦቶማን ቱርኮች ፈለግ ተከትለው የመጡት ግብፆች እ.ኤ.አ. ከ1832 እስከ 1834 ድረስ በነበረው ጊዜ ከኤርትራ እስከ ወለጋ ድረስ ባለው የኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ሰላምና ፀጥታን ሲያደፈርሱ ቆይተዋል። ግብፅ በኢትዮጵያ ከፈጸመችው ወረራ አንዱ በወርነር ሙዚንገር የተደረገው ወረራና በዓፋር ሕዝብ ቆራጥ ተጋድሎ የተገኘው ድል አንዱ ሲሆን ይህም እንደሚከተለው ቀርቧል።

ወርነር ሙዚንገር ጆስፍ ሙዚንገር የተባለ የስዊስ ፌዴራል ምክር ቤት አባል ልጅ ሲሆን፣ ኦልተን በሚባል ሥፍራ ተወልዶ ሳይንስና ታሪክን በበርን ዩኒቨርሲቲ አጠና። ከዚያም ወደ ግብፅ እ.ኤ.አ. በ1852 በመምጣት ካይሮ ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል በመቀመጥ የዓረብኛ ቋንቋ ችሎታውን አዳበረ። በአንድ የፈረንሣይ የንግድ ድርጅት ውስጥ በመግባትም በተለያዩ የቀይ ባህር ዳርቻ ወደቦች በመዟዟር የንግድ ሥራውን ማከናወን ጀመረ። በ1855 ዓ.ም. ተቀማጭነቱን በምፅዋ በማድረግ የፈረንሣይ ምክር ቤት አገልጋይ ሆነ። ከዚያም ወደ ከረን በመዛወር ለስድስት ዓመታት ተቀምጦ የቦጎስን አካባቢ ሁሉ እየተዘዋወረ አጠና። እ.ኤ.አ. በ1861 ማዕከላዊ አፍሪካን ለመጎብኘት ፍላጎት የነበረውን ቴዎዶር ቮን ሄግሊን ከተባለ ሰው ጋር ለመሥራት ፈቃደኛ ሆኖ ጉዞ ጀመረ። ዳሩ ግን በጋሽና አትባራ (ተከዜ) በኩል አድርጎ ወደ ካርቱም ከሚወስደው ሥፍራ ተለየው። እዚያም ቮን ሄግሊንን በመተካት የጉዞው መሪ በመሆን እ.ኤ.አ. በ1862 ኮርዶፋ ደረሰ። ዳሩ ግን ዳርፉርና ዋዳይ ከተባለው ሥፍራ ለመድረስ አልቻለም።

ከዚያም እ.ኤ.አ. በ1863 ወደ አውሮፓ ተመልሶ ጥቂት ቆይቶ በመመለስ በሰሜንና ሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ ዳርቻዎች መኖር ጀመረ። ወርነር ሙዚንገር 1865 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ድንበር ላይ የነበረውን የእንግሊዝ ቆንስላ አባል በመሆን ቢያገለግልም ከምፅዋ አልወጣም ነበር። እንግሊዝ ኢትዮጵያን እ.ኤ.አ. በ1868 ስትወር ግን የፈረንሣይ ቆንስላ ሆነ። እዚያም የሐማሴን የጦር መሪ የሆነው የደጃዝማች ወልደ ሚካኤልን ሴት ልጅ አገባ። ደጃዝማች ወልደ ሚካኤልንም ሐማሴንን ለፈረንሣይ እንዲሰጥ ይወተውት ጀመር። ዓላማው ሲሳካለትም ወደ ፈረንሣይ ተመለሰ። የፍራንኮ ፕራሺያ ጦርነት ሲጀመርም እ.ኤ.አ. በ1870 ወደ ምፅዋ ለመመለስ ዝግጁ ሆነ። ዳሩ ግን የፈረንሣይ የትኩረት አቅጣጫ ወደ እዚህ ትልቅ ጦርነት በመቀየሩ ምክንያት ወርነር ሙዚንገር ከፈረንሣይ ቆንስላነት ወደ ምፅዋ መምጣቱ ቀርቶ ፊቱን ወደ ግብፅ አዞረ። በማዞሩም በወቅቱ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ወደ ነበረችው ግብፅ ሄደ። በዚያን ጊዜም የግብፅ መሪ ከዲቭ ኢስማኤል ነበር። ከዲቭ ኢስማኤልም የከረንና የምፅዋ ገዥ አደረገው። በሥልጣን ላይ ሲቀመጥም ከደጃዝማች ወልደ ሚካኤል ጋር በመነጋገር በፈረንሣይ ሥር እንድትሆን አድርጓት የነበረችውን በጎስን በግብፅ ሥር እንድትሆን አደረጋት። እ.ኤ.አ. በ1875 ዋርነር ሙዚንገር ግብፅ በሦስት አቅጣጫ ኢትዮጵያን ለመውረር ካሠማራችው ጦር የአንደኛው ክንፍ መሪ በመሆን በታጁራ ክንፍ ተሠለፈ። በዚህም ግንባር ተሠልፎ ሲዋጋ ታጁራ ላይ በተለይም ገመሪ ተብሎ በሚጠራው ሐይቅ ዳርቻ በአውሳው ሡልጧን በመሐመድ ኢብን ሐንፈሬ (ዒሊልታ) የሚመራ ጦር ገጠመው። ጦርነቱም በአውሳው ሡልጧን ሙሐመድ ኢብን ሐንፈዴ ድል አድራጊነት ተጠናቀቀና ወርነር ሙዚንገር፣ ወልደ ሚካኤል፣ ሚስቱና ልጁ ተገደሉ።

ከዲቭ ኢስማኤል ፓሻ በቱርክ የበላይነት ሥር ያደረው የግብፅ አስተዳደር መሪ የነበረ ሲሆን ስመ ገናና እንደነበረ ከታሪኩ መረዳት ይቻላል። ከዲቭ ኢስማኤል የግብፅና የሱዳን ፓሻ (የቱርክ ሹመኛ) ሆኖ ማገልገል የጀመረው እ.ኤ.አ. ከ1863 እስከ 1879 በነበረው ጊዜ ነበር። የአያቱን፣ የሙሐመድ ዓሊ ፓሻን አርዓያነት የተከተለው ከዲቭ ፓሻ ‹‹አገሬ ከእንግዲህ አውሮፓዊት እንጂ አፍሪካዊት አይደለችም። ስለሆነም አሮጌውን የአኗኗር ሕይወት አሽቀንጥረን በመጣል አዲሱን ሥርዓት መከተል አለብን፤›› የሚለውን አመለካከት ያራምድ የነበረ ሲሆን ከብሪታንያ ከፍተኛ ብድር በመበደር አገሩን ለዕዳ የዳረገም ሰው ነበር። ግብፅ በታላቋ ብሪታንያ እጅ የወደቀችበትም ምክንያት ይኸው ሰው በከተታት ዕዳ ምክንያት ነው። ይህም ሆኖ ኢስማኤል ግዛቱን ከዓባይ ባሻገር ያሉት አገሮች ብሎም መላው አፍሪካንና የቀይ ባህርን ድንበር ሁሉ ለመግዛት የቀን ሕልም ያልም ነበር። ይልቁንም በማዕድን ሀብት የበለፀገችና የደለበ ለም የእርሻ አፈር ያላትንና በአፄ ዮሐንስ አራተኛ ትመራ የነበረችውን ኢትዮጵያን ለመውረር ታጥቆ ተነሳ። የበላይ ጠባቂዋ ኦቶማን ኢምፓየርም ምፅዋንና ሱዋኪን ጠቅልሎ እንዲገዛ አደረገችው። የቱርክንም ይሁንታ በማግኘት ወደ ሐማሴን ግዛት ሰርጎ ገባ። የምሥራቃዊ ሱዳንና የቀይ ባህር ዳርቻ ገዥ አድርጎ የሾመውን ወርነር ሙዚንገርንም በእሱ በራሱ የሚመራ ጦሩን በታጁራ በኩል አሠማራ። ሆኖም ራሱ ከዲቭ ኢስማኤል በሰሜን በኩል የነበረው የአፄ ዮሐንስ ጦር ጉራዕ ላይ ሲያሽመደምደው ልጁ ሐሰን ኢስማኤልም ተማረከ።

የግብፅ ወታደሮች በከፊል በአውሮፓና በአሜሪካ መኮንኖች ይመሩ የነበር ቢሆንም እ.ኤ.አ. በ1875 ጉንደት ላይ በ1876 ጉራዕ ላይ በተከታታይ በወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ በነበሩት በአፄ ዮሐንስ አራተኛ ጦር ድል ሆነዋል። ዮሐንስም ‹‹የአገሬ ድንበር ከባህር ይጀምራል፤›› በማለት በየጊዜው ይገልጹ ነበር። በሌላ አቅጣጫ ግብፆች ምፅዋን ለቀው እንዲወጡ ለማድረግ ‹‹የኢትዮጵያ አለወደብ መኖር ፍትሕ የጎደለው መሆኑን፤›› ለመንግሥት ቪክቶሪያ የሚያስረዳ መልዕክተኛ እ.ኤ.አ. በ1873 ወደ እንግሊዝ አገር ልከዋል። የምፅዋን ወደብ ደሴት ለማስለቀቅ አዳጋች ቢሆንባቸውም ግብፆች አብዛኛውን የኤርትራ ክፍል በቀላሉ በቁጥጥራቸው ሥር ለማዋል በቅተዋል። በመካከሉ አፄ ዮሐንስ ከኦርቶዶክስ ሩሲያ ጋር ግንኙነት ለመመሥረት ፈልገው መልዕክተኞች መላካቸው የእንግሊዝን መንግሥት ሥጋት ላይ ጣለ። የሩሲያ ቀይ ባህር አካባቢ መግባት ጥቅሟን የሚፃረር መስሎም ስለታያት ለአፄ ዮሐንስ የገባችውን ቃል አፍርሳ ኢጣሊያ የምፅዋን ወደብ እንድትይዝ ገፋፋች። ስለሆነም በ1877 ዓ.ም. ገደማ ጣሊያን ምፅዋን ያዘች።

በዓድዋ ጦርነት ዋዜማ የደርቡሾችና የጣልያኖች አመጣጥ

ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ከተገደሉ በኋላ አፄ ዮሐንስ አራተኛ ግዛታቸውን በማስፋፋት በነበሩበት ጊዜ በባህር በራቸው መጠቀም የሚያስችላቸው መንገድ ተከፈተ። ይኸውም እ.ኤ.አ. በ1880 መባቻ ላለ በድርቡሾች አመፅ የተነሳ በሱዳን ውስጥ የተከበቡትን የእንግሊዝና የግብፅ የጦር ሠፈሮች ለማስለቀቅ የኢትዮጵያን ዕርዳታ ማግኘት አማራጭ የሌለው ዓብይ ጉዳይ ሆኖ ስለተገኘ ነበር።

በመሆኑም እንግሊዝ የኢትዮጵያን ዕርዳታ ጠየቀች። አፄ ዮሐንስ ሲዋዋሉ በአፀፋው ግብፆ በጊዜው የያዙትን የኢትዮጵያ ምድር ለቀው እንዲወጡና ምፅዋንም እንዲያስረክቡ ጠየቁ። እንግሊዞች የመጀመሪያውን ጥያቄ ሲቀበሉ ወደቡን በሚመለከት ረገድ ግን (የቅኝ ገዥ ስለሆኑ ለአንድ ነፃ አፍሪካዊ አገር ያላቸው ስሜት እምብዛም ስለነበር) የጦር መሣሪያዎችን ጭምር ሸቀጣ ሸቀጥ ‹‹በእንግሊዝ ጥበቃ ሥር›› በነፃ የመተላለፍ ፈቃድ እንዲያገኙ እንደሚያደርጉ ቃል በመግባት ተስማሙ። እነዚህን መሠረተ ጉዳዮች ያቀፈው ውል እ.ኤ.አ. ጁን 3 ቀን 1884 ተፈረመ። ውሉም የሚፀናው በሁለቱ ተፈራራሚዎች መካከል ብቻ ሳይሆን በወራሾቻቸውና በትውልድ ትውልዶቻቸው ላይ ጭምር ነበር። በዚህ ስምምነት መሠረት ራስ አሉላ ሱዳን ውስጥ በደርቡሾች ተከበው የተያዙትን ስድስት የወታደር ሠፈሮች ወዲያውኑ በመድረስ ተዋግተው አስለቀቁ። የእንግሊዝ መንግሥት በድርቡሾች የተያዘበት ሠራዊት በአፄ ዮሐንስ ሠራዊት ነፃ ከወጣ በኋላ ክህደት ተፈጸመበትና እ.ኤ.አ. ፌብሯሪ 5 ቀን 1885 ጣልያን ምፅዋን እንድትይዝ ተደረገ።

አንድ ወቅት ላይ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ካውንስለር የነበረው ኤቢዋይልድ የዘመኑን የገዛ የአገሩን መንግሥት መሰሪነት ለመግለጽ በመጽሐፉ እንግሊዝ እ.ኤ.አ. በ1884 ከዮሐንስ ጋር ያደረገችውን ስምምነት አፍርሳ እንደካደች ሂስ አካሂዷል። በመጽሐፉም፣ ‹‹እስቲ ተመልከቱ በንጉሥ ዮሐንስ ላይ የፈረምነውን አድራጎት። በማንኛውም መልኩ ቢመለከቱት አንዳችም የልብ ቅንነት ፍንጣቂ አያሳይም። በእኔ አዕምሮ ውስጥ እንደሚጉላላው ከሆነ በአፍሪካ ላይ ከፈጸምነው የድለላ ሥራ ወንጀል መካከል ይኸኛው ምንጊዜም ሥርየት ሊያገኝ የማይችል ከባድ በደል እንደሆነ በሰቀቀን ይሰማኛል። እንግሊዝ ዮሐንስን ከተጠቀመችባቸው በኋላ ምንም እንዳላበረከቱ ዓይነት ለተባባሪዋ ለኢጣሊያ ግዳይ በመጣል ተወዳጀችባቸው። ጣልያኖች በእኛው ድጋፍ ምፅዋን እንዲይዙ አደረገች። ዮሐንስ የውሉን ድንጋጌ አክብረው ቃል ኪዳናቸውን በመጠበቅ ድርሻቸውን በቅንነት ከተወጡ በኋላ እንግሊዝ ግን ቃል ኪዳኗን አፍርሳ ምፅዋን ለጣሊያኖች በማስረክበ እሷ የተዋዋለችውን ቃል ኪዳን ጣልያኖች እንዲያፈርሱ አድርጋለች። ይህ እውነታ ለእንግሊዝ ሕዝብ ሥውር ነበር። እንደ እኔ ምኞት ለእኛ ስም ሲባል ነገሩ ሐሰት በሆነ ደስ ባለኝ ነበር። ግን ዕድላችን ሆኖ የተፈጸመው የበደል ድርጊት ሀቅ ነው። ይህ በ18ኛው ምዕተ ዓመት የእንግሊዝ መንግሥት በአፍሪካም ሆነ በእስያ ከፈጸመው ሌላ ወራዳ የክህደት ተግባርና ወንጀል ይልቅ እንግሊዞችን የቅሌት ማቅ አልብሶ የታሪክ መሳለቂያ አድርጎን ዘለዓለም ሲነበብ ይኖራል፤›› በማለት አትቷል።

ወደቡን በያዙ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ መሀል አገር ለመግፋት ቢሞክሩም እ.ኤ.አ. በ1887 ከወደቡ 24 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ በሚገኘው በዶጋሊ ላይ ከራስ አሉላ ጋር በተደረገው ውጊያ ድል ተመትተው ወደ መጡበት ተመልሰዋል። ይህም የኢትዮጵያ ድንበር እስከ ቀይ ባህር ድረስ የተንጣለለ መሆኑን በትክክል ያመለክታል። አፄ ዮሐንስ አራተኛ ከእንግሊዞች ጋር ባደረጉት ስምምነት በሱዳን ውስጥ በደርቡሾች የተከበበውን የእንግሊዝና የግብፅ ጦር ነፃ ባወጡበት ወቅት ደርቡሾች አምርረው ተቀይመው ነበር። ይህን ለመበቀል፣ ደርቡሾች ከሁለት ዓመት በኋላ ኢትዮጵያን ወረሩ። አፄ ዮሐንስ እ.ኤ.አ. ማርች 1889 ከደርቡሾች ጋር ሲዋጉ አለፉ።

በዓድዋ ጦርነት ዋዜማ የማህዲዎች አመፅ

በመሠረቱ ማህዲ ማለት ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በነብዩ ሙሐመድ (ሱዓወ) የሕይወት ዘመን እንደነበረው ንፁህ እምነት ይኖረው ዘንድ በአንዱ ፈጣሪ ብቻ የሚመራ የተመረጠ ማለት ሲሆን፣ የማህዲ ንቅናቄ የተነሳበት መሠረታዊ ምክንያት የኦቶማን ኢምፓየር ሥርወ መንግሥት እንደራሴ በነበረው በመሐመድ ዓሊ ፓሻ (1769 እስከ 1849 ኖረ) መሪነት ሱዳንን በቅኝ ግዛትነት ያዛት በነበረችበት ጊዜ፣ በኢስላም የምዕራባውያን አገሮችን የግብር ሥርዓት የተከተለ ግብር ስለጣለችባቸው ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወታደሮችን እየመለመለች በሌሎች አገሮች ለምሳሌ በኢትዮጵያ ታሠልፍ ስለነበረ አመፁ ከዚህም ጋር የተያያዘ ነበር፡፡

በዓድዋ ጦርነት ዋዜማ በየቦታው አመፅ የነበረ ሲሆን፣ በተለይም የማህዲያውያን አመፅ በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር በሁለት መሠረታዊ ግንኙነት አለው፡፡ ሱዳኖችን በላቀ ሁኔታ ያበገናቸው ደግሞ ግብፅ የክርስትና እምነት ተከታዮች የሆኑና በአንድ በኩል የባሪያ ንግድን እየተቃወሙ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የራሳቸውን ሕዝብ ባሪያ አድርገው የሚገዙ  ምዕራባውያን አገሮች ወደ አገራቸው ይዛ በመምጣቷ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት መሐመድ አህመድ የተባሉ የሱዳን ከፍተኛ የሃይማኖት አባት ራሳቸውን ‹‹ማህዲ›› ብለው በመሰየም እ.ኤ.ኤ በጁን 29 ቀን 1981 ወታደራዊ ኃይል አዘጋጅተው በግብፅ ላይ የጅሃድ ጦርነት አወጁ፡፡ በዚህም መሠረት እ.ኤ.አ. በ1882 ኤል ኦቤድ የነበረውን የግብፅ ወታደራዊ ሠፈር ድል አድርጎ ያዘ፡፡ ብሪታንያ ግብፅ ስዊዝ ካናልን ስትከፍት ከፍተኛ ብድር አበድራት ስለነበርና ያንን ዕዳ በወቅቱ ለመክፈል ስላልቻለች፣ በውሏ መሠረት የንግድ መስመሩን ለመቆጣጠር በሚል ሰበብ ግብፅን በ1882 ያዘች፡፡ ብሪታንያ ግብፅን ቅኝ ግዛት አድርጋ ለመያዝ በመቻሏም ሱዳንንም ለማጠቃለል ስለቻለች በኮሎኔል ዊልያም ሂክስ የሚመራ 8,500 ብዛት ያለው ታጣቂ አዘመተች፡፡ ይህም ሠራዊት በዘመኑ የታወቀውን የጦር መሣሪያ የታጠቀ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ማህዲስቶቹ በረሃማ ወደ ሆነው ሥፍራ ሲገቡላቸው ከበው መንቀሳቀሻ አሳጧቸው፡፡ በዚህም ምክንያት የብሪታንያ ጦር ወረራው ሳይሳካለት ቀረና በሸይካን ጦር ሜዳ ድል ሆነ፡፡ 

የዓድዋ ጦርነት ዋዜማና የሔዊት ስምምነት

የሔዊት ስምምነት እየተባለ የሚጠራው ስምምነት በአፄ ዮሐንስ አራተኛና በሪር አድሚራል ዊልያም ሔዊት መካከል እ.ኤ.አ. ጁን 3 ቀን 1884 የተፈረመ ስምምነት ነው፡፡ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በአንድ በኩል በግብፅና በሱዳን ማህዲስቶች፣ በሌላ በኢትዮጵያና በግብፅ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ከፍተኛ ጦርነት የነበረ ሲሆን፣ በአራቱም አቅጣጫዎች የቅኝ ግዛቷን ለማስፋፋት ምኞት የነበራት እንግሊዝ ገለልተኛ ለመምሰል ጥረት ያደረገችበት ጊዜ ነበር፡፡ ግብፅ እ.ኤ.አ. ከ1880 ጀምሮ የእንግሊዝ ቅኝ በመሆኗም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከሱዳንና ከኢትዮጵያ ጋር የምታካሂደው ጦርነት ከራሷ ጋር የተያያዘ ነበርና የግብፅ ጉዳይ እንደሚመለከታት አያጠያይቅም፡፡ ስለሆነም የግብፅ ሠራዊት እስከ ደቡብ ሱዳን ዘልቆ ሲገዛ የማህዲስቶች አመፅ ተነሳበት፡፡ ይኸው የማህዲስቶች አመፅ  ጭካኔ የተሞላበት ከመሆኑም በላይ በእንግሊዝ የሚደገፈው ጦር ሊቋቋመው ስላልቻለ መፈናፈን በማይቻልበት ሁኔታ ላይ ወደቀ፡፡ የግብፅን ጦር ለማስወጣት የነበረው አንድ አማራጭ መንገድ በምዕራብ ኢትዮጵያ በኩል ማስወጣት ነበር፡፡ ግብፅ በወቅቱ ከኢትዮጵያ ጋር የመረረ ጦርነት አካሂዳ በጉንደት፣ በሰሐጢና በሌሎቹም ቦታዎች ድል ያልቀናት ቢሆንም ሰንኮፏ ተነቅሎ አልወጣም ነበርና የለየላት ጠላት ነበረች፡፡ ቢሆንም እንግሊዝ በአንድ በኩል ገለልተኛ መስላ የመቅረብ ባህሪ ስለነበራት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በመቅደላ ጦርነት የሰጠቻቸውን የጦር መሣሪያ እንደ ውለታ በመቁጠር የአፄ ዮሐንስን ትብብር ለማግኘት በሪር አድሚራል ዊልያም ሔዊት የሚመራ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ ላከች፡፡ ሪር አድሚራል ዊልያም ሔዊትም ጥሩ ወዳጅ በመምሰል ከአፄ ዮሐንስ ጋር ቅኝ ግዛቱ የሆነችው ግብጥ የገጠማትን ችግር አዋያቸው፡፡ አፄ ዮሐንስም የጦር መሪውን ሐሳብ አዳምጠው ግብፅ የሰሜኑ የአገራቸው ክፍል እንደያዘች፣ ወደ መሀል ለመግባት ባደረገችው ጥረትም ብዙ የሰው ሕይወት እንዳለፈ፣ በወቅቱ ምፅዋን ይዛ እንደነበር በመግለጽ የጠየቀውን ትብብር መፈጸም እንደሚያስቸግራቸው ገለጹ፡፡ ሪር አድሚራል ዊልያም ሔዊትም ወደ እሳቸው የመጣበት መሠረታዊ ምክንያትም በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል የነበረውን ችግር ለመፍታት ጭምር መሆኑን አብራርቶ በማህዲ ጦር የተከበበው ጦር በኢትዮጵያ በኩል አልፎ ወደ ምፅዋ እንዲያልፍ፣ ቀጥሎም ግብፆች ከሰሜን ኢትዮጵያ ግዛት ለቀው እንዲወጡ ለማድረግ እንደሆነ አብራራ፡፡ በዚህም መሠረት

ሀ. የግብፅ ወታደር እስኪጓዙ በምዕራብ ኢትዮጵያ በኩል አድርጎ ወደ ምፅዋ በነፃ እንዲያልፍ፣

ለ. በቦጎስና በሌሎች የጦርነት ሥፍራዎች የደረሰው ጉዳት እንዲካስ፣

ሐ. ኢትዮጵያ ግብፃውያን ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲያልፉ፣

በዚህም መሠረት ግብፆች አንዳች እንከን ሳይገጥማቸው በኢትዮጵያ በኩል አለፉ፡፡ እ.ኤ.አ. በሴፕቴምበር 1884 በግብፅ ተይዞ የነበረው የቦጎስ አውራጃን መልሰው ተቆጣጠሩ፡፡ ፊታቸውን ወደ ሱዳን በማዞርን የጀመረችውን ጦርነት ቀጠለች፡፡ በዚህም መሠረት በራስ አሉላ አባ ነጋ የሚመራው ጦር እ.ኤ.አ. ሴፕቴምበር 23 ቀን 1885 ኩፊት ላይ በተደረገው ጦርነት ድል አደረጉ፡፡ ሆኖም እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 1886 ተመልሶ ደንቢያን ያዘ፡፡ የባህበረ ሥላሴ ገዳምን በማቃጠል ወደ ጭልጋ ተጠጋ፡፡ ሆኖም የጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 1887 እስከ ጋላባት ድረስ አባረሩት፡፡ የማህዲ ጦር እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 1888 ተመልሶ በመምጣት የንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን ጦር ሣር ውኃ በሚባለው ሥፍራ ድል አደረገና ጎንደርን ተቆጣጠረ፡፡

እንግሊዝ ግብፅን በገባችው መሠረት ምፅዋንና የተቀረውን ግዛት ለኢትዮጵያ ማስረከብ ሲገባት፣ እንዲያውም ይባስ ብላ ኢጣሊያ ኤርትራን እንድትይዝ አደረገች፡፡ የኢጣሊያ ወታደሮችና በኢጣሊያ የሠለጠኑ ኤርትራውያን አስቃሪዎችም በማህዲስቶች ላይ ዘመቻ አካሄዱ፡፡ ከ1890 ዓ.ም. ጀምሮም አቁርደት ላይ ጦርነት አካሂደው ድል አደረጉ፡፡ ሆኖም ማህዲስቶች ከ10,000-12,000 የሚገመት ሠራዊት ይዘው እንደገና ተጠናክረው መጡ፡፡ በዚህ ጊዜ በኮሎኔል አሪሞንዲ የሚመራው አስካሪሱን ጨምሮ 2,400 ያህል ጦር የነበረው ዘመናዊ የኢጣሊያ ሠራዊት በ1895 ዓ.ም. በከሰላ ጦርነት ወሳኝ ድል ተጎናፀፉ፡፡ ሆኖም ወደፊት በስፋት እንደምንመለከተው በ1896 ዓ.ም. በዓድዋ ጦርነት ሲሸነፉ ከሰላን ለእንግሊዝ ሰጥተው ወደ ኤርትራ ተመለሱ፡፡

በጦርነቱ ዋዜማ የተከሰተ ረሃብ

በዓድዋ ጦርነት ዋዜማ የአውሮፓውያን ወረራ ብቻ ሳይሆን እጅግ አስከፊ ረሃብም ደርሶ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ከደረሱት በጣም ትልቅ የድርቅና የረሃብ ዘመናት አንዱ ከ1888 እስከ 1892 ዓ.ም. ማለትም አፄ ዮሐንስ በሞቱበት ጊዜ የነበረው መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡ በዚህ ጊዜ የነበሩት የሮም ሚሽነሪዎች እንደመዘገቡት የአየሩ ሁኔታ ባልተለመደ ሁኔታ ሞቃት ሆነ፡፡ ይህም የአየር ንብረቱን አዛባው፡፡ እንደሰደድ እሳትም መላውን አጥለቀለቀው፡ የአየር ንብረቱ መዛባት ለሶማሊያና ለደቡባዊ አገሮችም ተረፈ፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያን የጎበኘ ማርቲ የተባለ ግለሰብ ስለድርቁ በሰፊው አትቶታል፡፡

በዓድዋ ጦርነት ዋዜማ አፍሪካን እንደ ቅርጫ የመከፋፈል ተግባር

የዓድዋ ወረራ በ1888 ዓ.ም. ሲካሄድ የአውሮፓ ኢምፔሪያሊዝም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት መሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህ የአውሮፓ አገሮች ኢንዱስትሪ ዕድገታቸው ጋር የተያያዘ ፍላጎታቸውን ለማርካት ማለትም ርካሽ የሰው ጉልበት ለፋብሪካዎቻቸው አስፈላጊ የሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን በገበያ ማግኘት ለህልውናቸው አስፈላጊ እንደነበረም ማስተዋል አስፈላጊ ነው፡፡ አውሮፓውያን አገሮች አንዳቸው ከሌላቸው በኢንዱስትሪ ዕድገታቸው ልቀው መገኝት ስለነበረባቸው ይህንን የበላይነት ለማረጋገጥ በየፊናቸው መሯሯጥ ነበረባቸው፡፡ ታላቋ ብሪታንያና ፈረንሣይ ከደቡብ እስከ ሰሜንና ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ቅኝ ግዛታቸውን ለማስፋፋት ሲፈልጉ፣ ጀርመንም በምሥራቅና በምዕራብ አፍሪካ አንዳንድ ቅኝ ግዛት አገሮች አግኝታ ነበር፡፡ ቤልጅየም ኮንጎን ይዛለች፡፡ የአውሮፓ አገሮች ሥዕል ይህንን ይምሰል እንጂ ርካሽ የሰው ጉልበት ጥሬ ዕቃና ገበያ መፈለግ ጉዳይ በእስያና በአሜሪካም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ነበር፡፡ ለምሳሌ ጃፓን ኮሪያን ይዛለች፡፡ ሩሲያም ግዛቷ ወደ ምሥራቅ አስፋፍታለች፡፡ የአዲሲቱ አሜሪካ ግዛትም እንደዚሁ በፍጥነት እያደገ ነበር፡፡

ለመሆኑ ያኔ የኢጣሊያ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? ነገሩን የበለጠ ግልጽ ለማድረግ ይረዳ ዘንድ ከሥር መሠረቱ እንደሚከተለው እንመልከት፡፡ ስዊዝ ካናል እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 17 ቀን 1869 ሲከፈት የሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ ጂኦ ፖለቲካዊ መልኩን እንዳለ ለውጦታል፡፡ ከፈርኦኖች ዘመን ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜም ከሜዲትራንያን ባህር ወደ ቀይ ባህርና የኤደን ባህረ ሰላጤ በቀላሉ በጀልባ አቋርጦ ለማለፍ ተችሏል፡፡ የስዊዝ ካናል ህልውና ማግኘት ከሜዲትራንያን ባህር ወደ ቀይ ባህርና ኤደን ባህረ ሰላጤ በቀላሉ ለማቋረጥ ማስቻሉ ታላቅ ነገር ቢሆንም፣ ከአሥር ዓመታት በኋላ ደግሞ ሌላ ጠቀሜታ እንዳለው አመለከተ፡፡ በመሆኑም ብሪታኒያና ፈረንሣይ በግብፃዊው ብሔርተኛ መሪ በዑራቢ ፓሻ አነሳስ ሥጋት ስላደረባቸው እ.ኤ.አ. ጁላይ 11 ቀን 1882 አሌክሳንደሪያን በቦምብ ደበደቡ፡፡ ይህም ‹‹ለጊዜው›› በሚል ስም የካይሮን በብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ ሥር መውደቅን አስከተለ፡፡ ይኸው ለጊዜው ተብሎ ለግማሽ ምዕተ ዓመት የቀጠለ የቅኝ ግዛት መንገድም የሌሎችንም የአውሮፓ አገሮች ግዛት የማስፋፋት ሕልም አነሳሳ፡፡ ነገሩ ሕልም መሆን ሳይቀር የአፍሪካን መከፋፈል (መቀራመት) አስከተለ፡፡

ይህም አፍሪካን እንደ ቅርጫት የመከፋፈል ተግባር፣ ብሪታንያ ግብፅን በያዘች በሦስተኛው ዓመት፣ ማለትም እ.ኤ.አ. ጁን 26 ቀን 1885 ‹‹በኃያሉ ፈጣሪ ስም›› በተፈረመው በበርሊኑ አጠቃላይ አዋጅ መሠረት ሕጋዊ ሆነ፡፡ ከሁሉም አውሮፓውያን ኃይሎች ደግሞ የሰሜን ምሥራቅ አፍሪካን ለመያዝ የላቀውን ፍላጎት ያሳየችው ኢጣሊያ ነበረች፡፡ ለዚህ ተግባር ያመቻት ዘንድ የመልክዓ ምድራዊ ጥናት ተመራማሪ ባለሙያዎችንና አሳሾቿን መላክ ጀመረች፡፡ እነዚህም ባለሙያዎች አብዛኛውን ጊዜ የቅኝ ግዛት ምኞቷን ሊያሳኩ የሚችሉ ሌሎች ባለሙያዎች ይከተሏቸውና ያጅቧቸው ነበር፡፡ የበርሊን አጠቃላይ አዋጅ በተፈረመ በጥቂት ዓመታት ውስጥም ለዘመናት ነፃነቷን ጠብቃ ከቆየችው ኢትዮጵያ በስተቀር፣ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች በአውሮፓውያን ቅኝ ገዥ ኃይሎች ግዛቶች ተዋሀዱ፡፡

ስለሆነም ኢጣሊያም ያኔ ገና ወጣት ነፃ አገር ነበረች፡፡ አፍሪካን በመከፋፈል ውስጥ የመሠለፍ ጉዳይ ከሌሎች የአውሮፓ አገሮች አንፃር ሲታይ ለየት ያለ ነው፡፡  አካሄዷም እንደዚሁ ለየት ይላል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ኢጣሊያ የራሷን አንድነት ከማደራጀት አልፋ፣ ሌሎችን አገሮች ለመውረር የሚያስችል አቅምም ልምድም ስላልነበራት ነው፡፡ ኢጣሊያንም ለማዋሀድ የታገሉ አርበኞቿን ውለታ መመለስ ቢኖርባትም በወቅቱ የነበራት የኢኮኖሚ ዕድገት ደካማ ስለሆነባትም ዜጎቿ አንድም ወደ ላቲን አሜሪካ እንዲሰደዱ፣ ያለበለዚያም የነበረውን ችግር እንዲያቃልል መንግሥት ማፋጠጣቸው አልቀረም፡፡ የቅኝ አገዛዙ ኅብረት አገሮች አባል በመሆኗ አንዳንድ ክፍሎች በአፍሪካ ቅኝ ግዛት የሚሆን አገር እንዲፈለግና ዜጎቿ እዚያ እንዲሠፍሩ መወትወታቸው ደግሞ እውነት ነበር፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የመንግሥት ተቀናቃኝ ፓርቲ አባላት የቅኝ ግዛት ሐሳብ ፋይዳ እንደሌለው በመግለጽ አጥብቀው ይከራከሩ ነበር፡፡ ይልቁንም ኢትዮጵያን በመውረር የሚገኘው እንደ ናይጄሪያና ሴኔጋል ያሉ አገሮችን በመውረር ከሚገኘው ጥቅም ጋር ሲነፃፀር የማይመጣጠን በመሆኑ፣ ጥቅም ይገኛል ቢባልም ደግሞ ከፍተኛ ጥረትን ማድረግ የሚያስፈልግ ስለሆነ የዓድዋን ዘመቻን አጥብቀው መቃወማቸውን ቀጠሉ፡፡ የቅኝ አገዛዝ ጦርነት ከማካሄድ ይልቅ ሌላ የዕድገት መንገድ እንዲፈለግ ወተወቱ፡፡ በዶጋሊ የደረሰው ሽንፈት ትምህርት ሊሆን እንደሚገባም አሳሰቡ፡፡ አሉላንም እንደ ጋሪባልዲ ጀግና መሆኑን እየገለጹ ጦርነት እንዳይካሄድ በቅኔ ጭምር ቅስቀሳ ጀመሩ፡፡ ከዚህም ሌላ ደግሞ በወቅቱ በኢጣሊያ በነበረው ችግር ምክንያት የተጎዱት ኢጣሊያውያን ገበሬዎች ወደ ኢትዮጵያ ተሰደው መሬት ሊያለሙ የሚችሉበት አቅም ስላልነበራቸው፣ የቅኝ ግዛት መመሥረቱ ተቀባይነት እንዳያገኝ ጥረት ለሚያደርጉ ወገኖች አመች ሁኔታን ፈጥሮላቸው ነበር፡፡ በሌላ በኩልም የዘውዱ አገዛዝ የቅኝ አገዛዝን ማስፋፋት ለችግሩ እንደ ዓይነተኛ መፍትሔ አድርገው ወሰደው፡፡ ትምክህተኛነቱም የቡርዥዋ አስተሳሰብ የቅኝ ግዛት ማፋፋት ፍላጎቱን ገፋፋው፡፡

እዚህ ላይ ሌላው መታወቅ ያለበት ጉዳይ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ለማድረግ በተነሳችበት ጊዜ ደሃ አገር ብትሆንም እንኳን እንደ አውሮፓ አኅጉር አባልነቷ ከኢትዮጵያ በማንኛውም መንገድ የተሻለች ነበረች፡፡ ይልቁንም ኢትዮጵያ አንድነቷን ለማጠናከር ጥረት በማድረግ ላይ ነበረች፡፡ ኢጣሊያ ደግሞ አንድነቷን ካጠናከረች ሃያ ሰባት ዓመት ያሳለፈች ነበረች፡፡ ይህንን በቀላል አገላለጽ እንኳን ብናየው የ27 ዓመት ወጣትና የአሥር ዓመት ሕፃንን ማወዳደር ይሆናል፡፡ የሆነው ሆኖ የኢጣሊያ ዘውዳዊ አገዛዝ የውስጥ ችግሩን ለማስወገድ የቅኝ ግዛት ማግኘትን እንደ አማራጭ መፍትሔ ያዘ፡፡ በዚህ ወቅት ቀደም ሲል እንደተገለጸው፣ እንግሊዝ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ካይሮ የባቡር ሐዲድ መስመር ለመዘርጋትና በነዚህ አገሮች መካከል የሚገኘውን ሕዝብ ለማስገበር ብርቱ ፍላጎት አደረባት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ፈረንሣይ ከምዕራብ አፍሪካዊቷ ጎልድ ኮስት እስከ ጂቡቲ ድረስ የባቡር ሐዲድ ለመዘርጋትና በእነዚህ አገሮች መካከል አገሮች ለመያዝ ፍላጎት ስለነበራት በሁለቱ ተስፋፊዎች መካከል የጥቅም ግጭት መነሳቱ አልቀረም፡፡ በተለይም እንግሊዝ የፈረንሣይ ዕቅድ እንዳይሳካ ለማድረግ ውላ አድራ የምታስወግዳትን ደካማዋን ኢጣሊያ መሣሪያ ለማድረግ ፈለገች፡፡ ነገርን ከሥሩ ውኃውን ከጥሩ እንደሚባለው ሀቁን ከሥር መሠረቱ ስንመለከተው፣ በዚህም መሠረት ኢጣሊያም ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛቷ እንድታደርግ ግፊት አደረገች፡፡ ኢጣሊያ የእንግሊዝ ቀኝ ክንድ ተንተርሳ ኢትዮጵያን አጠቃልላ ለመያዝ ታጥቃ ተነሳች፡፡ ኢትዮጵያ የዓድዋ ጦርነትን የገጠመችው በዚህ ሁኔታ ነበር፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...

የአገሪቱ ባንኮች የመጭበርበር ተጋላጭነት እየጨመረ መሆኑን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ

በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ2 ቢሊዮን ብር መጭበርበሩን ገልጿል ቀሲስ በላይ...