Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የጋራ ድላችን!

ከፒያሳ ወደ ቄራ ልንጓዝ ነው። ለበርካታ ደቂቃዎች ሠልፍ ይዘን የጠበቅነው ዶልፊን ሚኒባስ ላይ ተሳፍረናል፡፡ በከዘራቸው አጋዥነትና በድጋፍ ጭምር የተሳፈሩ አዛውንት፣ ‹‹የዛሬው የታክሲ ሠልፍና ጥበቃ ቢያናድደኝም የጥንቷ ውቢቱ አራዳ ላይ ይህንን የመሰለ የታሪክ መታሰቢያ ተሠርቶ በዓይኔ በማየቴ ግን እጅግ ደስ ብሎኛል…›› እያሉ አጠገባቸው ለተቀመጠች ኮረዳ ሲናገሩ አዳመጥናቸው፡፡ ጠይሟ ኮረዳ እየተቅለሰለሰች፣ ‹‹አባቴ እኔማ ውስጡ ገብቼ ያየሁትን ውጭ ስሰማው ከነበረው ጋር ሳነፃፅረው እጅግ በጣም ነው ድንቅ ያለኝ…›› ስትልም አዳመጥናት፡፡ መጨረሻ ወንበር ጥግ ላይ የተቀመጠ ለግላጋ ወጣት ደግሞ፣ ‹‹ፒያሳ የጣሊያን ወረራ ውርስ የሆኑ ቅርሶችን ታቅፋ ዕድሜዋን ከመግፋት ውጪ፣ እንዲህ ያለ ቁምነገር ይሠራባታል ብዬ አስቤም አላውቅም…›› እያለ መናገር ሲጀምር፣ ‹‹እንዴት ነው ነገሩ ጎበዝ፣ እኛ እኮ በዩቲዩብና በቲክቶክ የሚነገረን ሌላ እናንተ የምታወሩት ሌላ…›› ከማለቱ አንዱ ከመሀል መቀመጫ፣ ‹‹አንተ አታፍርም እንዴ፣ ሰዎቹ በዓይናቸው ያዩትንና የተደመሙበትን ሲነግሩን አንተ የስማ በለው ወሬ ታርከፈክፍብናለህ እንዴ…›› ብሎ ከጋቢና ኮስታራ ጎልማሳ በንዴት ሲናገር የሁላችንም ጆሮ ተቀሰረ ማለት ይቻላል፡፡ ተገኝቶ ነው እንዴ!

‹‹የእኛ ዘመን ሰው ዕርግማን ያለበት ይመስል በሁሉም ነገር ምን እንደሚያወዛግበው ነው ግራ ግብት የሚያደርገው…›› የሚለው ወያላችን ነው፡፡ ‹‹የወሬ ወፍጮአችን ነፍስ ዘርቶ የሚንቀሳቀሰው በውዝግብ እንጂ በመስማማት ማዕቀፍ ውስጥ አይደለም…›› ብሎ ይመልሳል ሌላው። ‹‹ስማ አንተ፣ ምን ለማለት ፈልገህ ነው?›› አንድ አፉን ያዝ የሚያደርገው ኮስታራ ጎልማሳ ወያላው ላይ አፈጠጠበት። ‹‹ምን አልኩ ጋሼ?›› ወያላው ጎልማሳው ስለምን እየጠየቀው እንደሆነ ስላወቀ ከሸረኛ ሳቅ ጋር መለሰለት። ‹‹ያልሰማሁ መስሎህ እንዳይሆን፣ እንኳን ይኼንን የዝንብ ጠንጋራም እናውቃለን…›› አለ ጎልማሳው። ወያላውም፣ ‹‹ጉድ እኮ ነው፣ የቲክቶኩን አደን ሳትጨርሱ ታክሲ ተራ ገባችሁ?›› ብሎ ያስነሳውን አቧራ የባህር ማዕበል አስመስሎት አረፈ። ‹‹ስለልማደኛው ውዝግባችን እየጠየቅከኝ ከሆነ ለአንተ በቃ ውዝግቡን ላላ እናደርግልሃለን፡፡ ታዲያ ይኼንንም በጉልበት ከምትወስደው በፀባይ፣ በመልካምነት፣ ከሰው ጋር በማደርና አገርን በቅንነት በማስተዳደር ቢሆን ይመረጣል…›› አለው። ነገር ሊጀመር ነው!

ጉዟችን ቀጥሏል። በታክሲያችን የሬዲዮ ድምፅ ማጉያ በኩል ነፍሱን ይማረውና ጌታቸው ካሳ፣ ‹የብዙኃን እናት ኢትዮጵያ የሚሏት… አገሬን አትንኳት› ይላል። መጨረሻ ወንበር ካሉ ተሳፋሪዎች ሁለቱ ስለመጪው ቅዳሜ ምሽት ሲጨዋወቱ ይሰማሉ። ‹‹እኔ ግርም የሚለኝ የዓድዋ ጀግኖቻችን በከፍተኛ ወኔ በሚታወሱበት በዚህ ሳምንት እናንተ አሸሼ ገዳሜ መቼ ነው ቅዳሜ ትባባላላችሁ…›› ይላል አንደኛው። ‹‹ጉድ እኮ ነው ዘንድሮ…›› ይለዋል አንዱ። የቅዳሜ ባለቀጠሮዎች እንደ ማፈር ብለው ዝም ሲሉ ወሬው ቀጠለ፡፡ ‹‹ይህች አገር እኮ በትውልድ ቅብብሎሽ እዚህ መድረሷን አንርሳ፡፡ የዓድዋ ጀግኖች ሲያልፉ ከዚያ በኋላም ለአገራቸው ግንባራቸውን ለጥይት ደረታቸውን ለጦር የሰጡ በርካታ ሰማዕታት ውድ ሕይወታቸውን መገበራቸው አይዘንጋ…›› ሲል ለግላጋው ወጣት፣ ‹‹ልጄ ልክ ብለሃል፣ ቅብብሎሹ ባይኖር እኮ አገር አትኖረንም ነበር፡፡ ትውልድን በደቦ ከመውቀስ ስህተቱን እያሳዩ ማስተማር ነው መልካሙ ነገር…›› ሲሉ ነገር በረደ፡፡ ይሻለናል!

‹‹መልካም ምላስ ቁጣን ታበርዳለች የሚለውን ምሳሌ በጣም ነው የምወደው አባባ…›› ስትል ያቺ ጠይም፣ ‹‹የእኔ ልጅ በጣም ትክክል ነጥብ አነሳሽ፡፡ ንግግራችን ሁሉ በጨዋነትና በስክነት ሲሆን እኮ እርስ በርስ ስንተዛዘን ልብ እንነካለን፡፡ ጨዋነቱ ጠፍቶ በተራና ባልተመረጡ ቃላት ስንዘራረጥ ደግሞ ጦሱ ለምስኪኖች እየተረፈ ስንቶች አለቁ መሰለሽ ልጄ…›› እያሉ በሐዘን ሲያቀረቅሩ ራሳቸው ልብ ይነኩ ነበር፡፡ ኮስታራው ጎልማሳ ከወደ ጋቢና፣ ‹‹አባታችን እንዳሉት መወቃቀሱ ጥቅም ባይኖረውም እኔ ግን በዚህ ዘመን ትውልድ ላይ ቅሬታ አለኝ፡፡ ዘመኑ በዕውቀትና በቴክኖሎጂ የበለፀገ ሆኖ ሳለ ብዙኃኑ ወጣት ማንበብ ሞት መስሎ ይታየዋል፡፡ ቲክቶክና ፌስቡክ ላይ ከሚባክነው ጊዜ ሩቡ ለንባብና ለዕውቀት ሸመታ ቢውል ኖሮ፣ ማንም እየተነሳ እየነዳው እሳት ውስጥ አይከተውም ነበር፡፡ እርግጥ ነው ለፍትሕ፣ ለነፃነትና ለእኩልነት መታገል ታላቅ ተግባር ነው፡፡ ነገር ግን በግለሰቦች ቅስቀሳ ዘውግን ተከትሎ መንጎድ ግን ለእኔ ድንቁርና እንጂ ምንም ሊባል አይችልም…›› ሲል ሁላችንንም ሊባል በሚችል ሁኔታ አንገታችንን አስቀረቀረን፡፡ እ…ህ…ህ…ህ… አትሉም ታዲያ!

ወያላው ሒሳብ ይሰበስባል። በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተሰናበተው ጌታቸው ካሳ፣ ‹አገሬን አትንኩ› ዘፈን አልቆ ‹እመኛለሁ› በሚለው ተተክቷል፡፡ ጌታቸው ‹እመኛለሁ› በሚለው ዘመን አይሽሬ ዘፈኑ፣ ‹…አልሳካ ያለኝ ኑሮና ብልኃቱ እየተጫነኝ ነው ከበላይ ዳገቱ…› እያለ በዚያ እንከን አልባ ድምፁ ሲያንጎራጉር ወይ የዘመን ግጥምጥሞሽ እያልን የምናዳምጥ እንኑር አንኑር ባይታወቅም፣ ለአፍታም ቢሆን ሁላችንም በለሆሳስ አብረነው ሳናዜም አልቀረንም፡፡ ዘፈኑ ተጀምሮ እስኪያልቅ ወጋችን ቆሞ ነበርና፡፡ ዘፈኑ ተጠናቆ በሌላ ሲተካ፣ ‹‹አይ ወንድሜን ነፍሱን ይማረውና ምርጥ ምርጥ ሙዚቃዎችን ነው ትቶልን ያለፈው፡፡ እኔ መቼም የእሱ ሙዚቃ ሲከፈት በተለይ ‹አዲስ አበባ…› የሚለው ዘፈኑ ልቤን ትርክክ ነበር የሚያደርጋት…›› የሚለው ኮስታራው ጎልማሳ ሲሆን፣ ‹‹እኔስ ብትል ‹ሳይሽ እሳሳለሁ› እና ‹የከረመ ፍቅር› የሚባሉት ዘፈኖቹ ልቤን ነበር ጥፍት የሚያደርጉት…›› ሲሉ አዛውንቱ ሳቅ በሳቅ አደረጉን፡፡ ‹‹እናንተ ዛሬ እርጅና ቢጫነኝም እንደ እናንተ እኮ ወጣት ነበርኩ…›› ብለው ሲስቁ አብረን ሳቅን፡፡ ትዝታ ደስ ሲል!

መንገዳችን ወደ መገባደዱ ነው። ከፒያሳ የጀመረው መንገዳችን የዓድዋ ሙዚየምን መነሻ አድርጎ በርካታ ወጎችን እያስኮመኮመን፣ ገነት ሆቴልን አሳልፎ ቡልጋሪያ አካባቢ አድርሶናል፡፡ አካባቢው ትናንትን በትዝታ ዛሬን ባለው ገጽታ ነገን ደግሞ በማናየው ምናብ ውስጥ ሆኖ ሲታይ፣ የትውልድ ቅብብሎሽ የሚባለው እውነታ ቁልጭ ብሎ ይታያል፡፡ ‹‹ትናንት የነበሩት ባላቸው ዕውቀት፣ ክህሎትና የአገር ሀብት የሚመስላቸውን ሠርተው አልፈዋል፡፡ የዛሬዎቹም ዘመኑ ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ አኳያ የመሰላቸውን ለማድረግ ጥድፊያ ላይ ናቸው፡፡ የነገዎቹ ደግሞ ተራቸውን መጠበቃቸው አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል ግን የራሳቸውን ዛሬ ሳይሠሩበት ትናንት ላይ ተቸክለው ውዝግብ ካልፈጠሩ በስተቀር የሚኖሩ የማይመስላቸው መብዛታቸው ግን ድንቅ ይላል፡፡ ከቡልጋሪያ እስከ ቄራ ያለው ጉዞ በዚህ ዕይታ ውስጥ ሆኜ ሳየው ድንቅ ይለኛል…›› የሚለው ያ ለግላጋ ወጣት ያለ ጊዜው መብሰሉ ያስታውቃል፡፡ ታድሎ!

‹‹አንተ መልካም ልጅ እውነት በዚህ አያያዝህ በዕድሜም ሆነ በዕውቀት ትንሽ ገፋ ስትል ተስፋህ እንደሚጎመራ ይታየኛል….›› ሲሉ አዛውንቱ፣ ‹‹ሁሉንም ነገር አውቃለሁ እያሉ ከሚዘባርቁ ምሁርና ልሂቅ ተብዬዎች እንዲህ ዓይነቱ ለግላጋ አስተዋይ ነው ለአገር የሚጠቅመው…›› ብሎ ኮስታራው ጎልማሳ የድጋፍ ሐሳብ አቀረበ። ‹‹ልጆቼ የዓድዋ ድል በዓልን ስናከብር ያለፉት የከፈሉትን መስዋዕትነት በክብር እየዘከርን፣ አሁን ያለነው ደግሞ እኛ በጋራ ታሪክ የምንሠራበትን አንድነት እየገነባን፣ የነገው ትውልድ የራሱን ታሪክ እንዲሠራ የምታስችለው ጠንካራ አገር እንድትኖረው ዕድሉን እያመቻቸን ይሁን፡፡ እኛ እዚህ ደረጃ ደርሰን የምንነጋገረው የጥንቶቹ ለአገራቸው ክብርና ህልውና በከፈሉት ወደር የሌለው መስዋዕትነት መሆኑን ተገንዝበን የጋራ ድላችንን በጋራ ስሜት እንዘክረው…›› ሲሉንና ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ብሎ በሩን ሲከፍተው እኩል ሆነ። አዛውንቱ ከዘራቸውን ተደግፈው እየወረዱ መንገዳቸውን ሲጀምሩ ለግላጋው ወጣት ጠጋ ብሎ፣ ‹‹ወዴት እንሚሄዱ ይንገሩኝና ልሸኝዎት…›› ሲላቸው፣ ‹‹እነዚያ ልጆች እኔን ነው እየጠበቁ ያሉት፣ ልጄ ፈጣሪ ያሳድግህ…›› ብለው ተሰናበቱን፡፡ በውስጣችን ግን ‹‹የጋራ ድላችንን በጋራ እንዘክረው…›› የሚለው አባታዊ ምክራቸው እያስተጋባ ነበር፡፡ መልካም ጉዞ!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት