Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኤርትራ መንግሥት ‹‹ወታደሮቼ በኢትዮጵያ ምድር የሉም›› አለ

የኤርትራ መንግሥት ‹‹ወታደሮቼ በኢትዮጵያ ምድር የሉም›› አለ

ቀን:

  • ሕወሓት 270 ሺሕ የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ አላስፈታም ሲልም ከሷል

በለንደን የሚገኘው የኤርትራ፣ የእንግሊዝና የአየርላንድ ኤምባሲ የካቲት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የኤርትራ ወታደሮች በሉዓላዊ የኤርትራ ግዛቶች ውስጥ መሆናቸውንና በኢትዮጵያ ምድር አይገኙም በማለት አስታወቀ፡፡

ለመግለጽ አስቸጋሪ ባልሆኑ ምክንያቶች የተወሰኑ ተንታኞችና ‹‹የሕወሓት ቅጥረኛ ጥቅም አራማጆች›› በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት እ.ኤ.አ. ከኅዳር 2020 እስከ 2022 ድረስ በተካሄደው ጦርነት፣ ተመሳሳይ ትረካዎችን በተደጋጋሚ እያሰሙ ነው ሲል በመግለጫው ወቀሳውን ሰንዝሯል፡፡

የኤርትራ መግለጫ እንደሚያስረዳው፣ መልሶ መላልሶ ትረካው በይበልጥ የተገለጸው፣ በቅርብ ጊዜ “The Statesman; Gray Dynamicsና World Peace” Foundations በተባሉ ድረ ገጾች ላይ በወጡና በሰፊው በተመሳሳይ ዕትሞች ላይ በቀረቡ መጣጥፎች፣ ኤርትራ ‹‹በትግራይ ክልል በርካታ አካባቢዎች ወታደሮቿን አሥፍራለች›› በሚል በውሸት መከሰሷን ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሪፖርተር የትግራይ ጊዜዊ አስተዳደርና የሕወሓት ከፍተኛ ሥራ ኃላፊዎችን በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

የኤርትራ መግለጫ እውነታዎቹ ምንድናቸው? በሚል አምስት ጉዳዮችን ያስቀመጠ ሲሆን፣ በዚህም በመጀመሪያ የተገለጸው፣ ለሁለት ዓመታት የተካሄደው አስከፊና ዋጋ ያስከፈለ ጦርነት ነው፡፡ ሕወሓት በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ላይ እ.ኤ.አ. ኅዳር 4 ቀን 2020 የማጥቃት ጦርነት በከፈተበት ወቅት የተቀሰቀሰውና ዓላማ ብሎ የጀመረው ስለመሆኑ አስረድቷል፡፡

ጦርነቱ ሁለት ዓላማዎች እንደነበሩት ያስታወሰው መግለጫው፣ ሕወሓት በኢትዮጵያ የተመሠረተውን አዲስ መንግሥት የማስወገድና ኤርትራን ወደ ትግራይ መጠቅለል የሚል ዕቅዱን ማሳካት እንደነበረው አስታውቋል፡፡ ይሁን አንጂ ጦርነቱ ስለወታደራዊ ብቃቱ ኃላፊነት የጎደለው የሕወሓትና በውጭ አጋሮች የተነገረው የተሳሳተ ሥሌት ውጤት ነው ብሏል፡፡ 

በተጨማሪም እ.ኤ.አ. ሐምሌ 2018 ኤርትራና አዲሱ የኢትዮጵያ መንግሥት ታሪካዊ የሰላም ስምምነት ሲፈራረሙ የተፈጠረውን ቀጣናዊ ሰላም ወደኋላ ለመመለስና ለማደናቀፍ ባለው ፍላጎት የተነሳ ስለመሆኑ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

 በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል  የሰላም ስምምነት የተፈረመው፣ ሕወሓት የጦርነት ዓላማዎቹና ጀብዱዎቹ፣ እንዲሁም በአብዛኛው በመኸር ወቅት የከፈታቸው ሦስት ጥቃቶች ሙሉ በሙሉ በከሸፉበት ወቅት ነው ብሏል፡፡

ከሳምንት በፊት በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ ሞሊ ፊ እና የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር (አምባሳደር) ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በትግራይ በነበራቸው ውይይት፣ የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ የሚፈጸምበትን ሁኔታ በተመለከተ ምክክር ማድረጋቸውን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረው ነበር፡፡

ከጥቂት ቀናት በፊት የትግራይ ጊዜዊ አስተዳደር ኮሙዩንኬሽን ኃላፊ ለሚዲያ በሰጡት መግለጫ፣ የፕሪቶሪያ ስምምነት አለመፈጸም በትግራይ ሕዝብ ላይ ከፍተና የሆነ ችግር እየፈጠረ መሆኑን አስታውቀው ነበር፡፡ ስምምነቱ እንዲፈጸም ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ጋር ምክክር እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

‹‹በጊዜያዊ አስተዳደሩና በፀጥታ ኃይሉ ላይ የተጀመረውን የተባበረ ስም ማጥፋት እናወግዛለን፣ ሕዝቡ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ሊሠራ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

የኤርትራ መግለጫ እንደሚለው የማይሻሩ እውነታዎች እንዳሉ ሆነው፣ ሕወሓት በፕሪቶሪያ ስምምነት ላይ የተቀመጡትን ሁሉንም ድንጋጌዎች በቅን ልቦና ከመፈጸም ይልቅ፣ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን በትግራይ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የኤርትራ ወታደሮች መኖራቸውን በመጥቀስ ያልተገባ ተንኮል ይዘው የመጡ ይመስላሉ ብሏል፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህ ውንጀላዎች የውሸት ብቻ ሳይሆኑ የሕወሓትን ያልተቋረጠ አቋም በድጋሚ የሚያመላክቱ፣ ባድመንና ሌሎች የኤርትራ ሉዓላዊ ግዛቶችን ለሁለት አሠርት ዓመታት ያህል ይዞ መቆየት የድንበር ኮሚሽንን ውሳኔ መጣስ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ሕወሓት አሁንም ‹‹የፕሪቶሪያን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ወሳኙ መንገድ ትግራይ ከጦርነት በፊት ወደ ነበረችበት አስተዳደራዊ ድንበሯ መመለስ ነው፤›› ሲል ማስታወቁን የገለጸው የኤርትራ መግለጫ፣ 270 ሺሕ የቀድሞ ታጣቂዎችን እስካሁን ትጥቅ አላስፈታም ብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የባህርና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ክፍያ አንፈጽምም ያሉ የመንግሥት ተቋማትን እንዲያግባባለት ለፓርላማው ጥያቄ አቀረበ

ዋና ኦዲተር ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ አለመሰብሰቡን አስታውቋል የቀድሞው ሜቴክ...

የገቢና የወጪ ንግድን ጨምሮ በጅምላና በችርቻሮ የሚሳተፉ የውጭ ባለሀብቶች የሚያሟሉት የካፒታል መጠን ይፋ ተደረገ

ሰባት ተቋማት የተካተቱበት ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ይደራጃል ተብሏል ከዚህ ቀደም ለውጭ...

የፓዌ ወረዳ ነዋሪዎች ከአማራ ክልል ተሻግረው በሚመጡ ታጣቂዎች ጥቃት እየደረሰብን ነው አሉ

ከአማራ ክልል አዋሳኝ ድንበር አካባቢ በምትገኘው ፓዌ ወረዳ ውስጥ...

የሞጆ ደረቅ ወደብ ጥበቃ ሠራተኞች የጦር መሣሪያዎቻቸው ተወስደውባቸው በዱላ እየጠበቁ ነው ተባለ

የአገሪቱን 90 በመቶ ደረቅ ጭነት የሚያስተናግደው የሞጆ ደረቅ ወደብ...