Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣ በንግድ ምክር ቤቱ ታይተዋል የተባሉ ግድፈቶች ሊጠየቅ ይገባል ተብሎ፣ የንግድ ምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ላይ የኦዲት ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ማሳለፉ ተቆመ፡፡

የንግድ ምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ከቦርዱ ዕውቅና ውጪ የተለያዩ ሕገወጥ ተግራትና ከንግድ ምክር ቤቱ የአሠራር ፖሊሲ ውጪ ሲፈጸሙ ነበር የተባሉ ግድፈቶችን በመዘርዝር፣ ጽሕፈት ቤቱ የኦዲት ምርመራ እንዲካሄድበት ቦርዱ ውሳኔ ያስተላለፈው በዚሁ ጉዳይ ላይ በተጠራ አስቸኳይ ስብሰባ ነው፡፡ በቦርዱ ውሳኔ መሠረት የኦዲት ምርመራውንና ሌሎች የማጣራት ሥራዎችን የሚሠራ ኮሚቴ የተቋቋመ መሆኑን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡  

ከሪፖርተር ምንጮች ማረጋገጥ እንደተቻለው፣ የጽሕፈት ቤቱ አመራር ፈጽመዋል ተብለው ከተጠቀሱት ግድፈቶች መካከል በዋናነት የንግድ ኅብረተሰቡ ሀብት እንዲባክን አድርገዋል የሚል ነው፡፡

ከዚህም ሌላ ቦርዱ የማያውቃቸው የውጭ ጉዞዎች መካሄዳቸውንና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንዲባክን ተደርጓል በሚል በአሃዝ የተደገፈ መረጃ ጭምር እንደቀረበ ተጠቅሷል፡፡

በተለይ ዋና ጸሐፊው ያልተፈቀደ፣ በበጀት ያልተያዘና አላስፈላጊ የውጭ ጉዞዎች በማድረግ ውስን የሆነውን የንግድ ምክር ቤቱንና የአገርን የውጭ ምንዛሪ አባክነዋል የሚል ጥቆማ እንደቀረበባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

በምክር ቤቱ የተፈጸሙም ቅጥሮች፣ የደረጃ ዕድገቶች፣ ዝውውሮች፣ እንዲሁም ያለ ቦርዱ ዕውቅና ከውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ካሉ ተቋማት ጋር የተካሄዱ የጋራ ስምምነቶችና ትልልቅ ግዥዎች ላይም ቅሬታ እንደቀረበባቸውና በምርመራውም እንዲካተቱ ውሳኔ እንደተሰጠባቸው ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ዋና ጸሐፊው ቦርዱ በጠቅላላ ጉባዔ ከተሰየመ ከ2015 ዓ.ም. መጀመሪያ ጀምሮ እስካሁን አላስፈላጊ፣ ቦርዱ ያላወቃቸውና በበጀትም ያላፀደቃቸው የተባሉ ከ15 በላይ የውጭ ጉዞዎች ራሳቸውና ሌሎች እንዲሳተፉበት አመራር በመስጠት፣ በመቶ ሺሕ የሚገመት የውጭ ምንዛሪ ወጪ እንዲሆን በማድረግ፣ የንግዱን ማኅበረሰብ ሀብት እንዲባክን አድርገዋል የሚል ጥቆማ በመረጃ እንደወጣባቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ከውጭ ጉዞዎች ጋር የተያያዙ ወጪዎች የንግድ ምክር ቤቱን የፋይናንስ ፖሊሲ የተፃረረ ነው በሚል ጭምር ቅሬታ የሚያቀርቡ ወገኖች፣ እንዲህ ዓይነት ጉዞዎች የውጭ አገር ሥልጠናዎችና የልምድ ልውውጦች በሚል በምክር ቤቱ የተያዘና የፀደቀ አንዳችም በጀት እንደሌለም ይጠቁማሉ፡፡

በንግድ ምክር ቤቱ የተከናወኑ አዳዲስ ቅጥሮችና የደረጃ ዕድገቶች በውድድር ላይ ያልተመሠረቱ፣ የምክር ቤቱን የማቋቋሚያ አዋጅና የምክር ቤቱን የሰው ሀብት ልማትና አስተዳደር ፖሊሲን ያልተከተሉ ናቸው የሚለው ቅሬታ በቦርዱ ትኩረት የተሰጠው መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ መመርመር አለባቸው ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ ተጠሪነቱ ለዳይሬክተሮች ቦርድ ሆኖና ላለፉት ሁለት ዓመታት በሥራ ላይ የነበረው የንግድ ምክር ቤቱ የውስጥ ኦዲት አገልግሎት ሥራ አስኪያጅን ያለ ቦርዱ ዕውቅናና ሥልጣን በዋና ጸሐፊው እንዲሰናበት መደረጉ ነው፡፡ ይህም የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እንዲነሳ ማድረጉንም በመጥቀስ እንዲጠራ ተጠይቋል ተብሏል፡፡

በንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 341/95 መሠረት የቦርዱ ሥልጣንና ተግባራት አንዱ የምክር ቤቱን ዓላማ ከግብ ለማድረስ አስፈላጊ የሆኑ ተግባራትን ከማከናወን ባለፈ፣ ከዋና ጸሐፊው በሚቀርብለት የመምርያና አገልግሎት ኃላፊዎች ቅጥርና ስንብት ላይ ውሳኔ ይሰጣል ይላል፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ ቅጥሮችና ደረጃ ዕድገቶች፣ እንዲሁም ስንብት ላይ የቦርዱ ሚና ምን እንዲሆን ተደርጓል የሚል ቅሬታም ቀርቧል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከ15 ሺሕ በላይ አባላት ያሉት ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በጥንካሬያቸው ከሚገለጹት የንግድ ምክር ቤቶች በዋናነት የሚቀመጥ ነው፡፡ ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያጋጠሙት ነው የተባሉ አንዳንድ ችግሮች ተጠረቃቅመው አሁን ላይ ጥያቄ እንዲነሳባቸው እያስገደደ ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡

አባላትን እንደ ዘርፋቸው ከመጥቀምና የዓለም አቀፍ የገበያ ትስስር ከመፍጠር አንፃር፣ እንዲሁም ከሌሎች የውጭና የአገር አቀፍ ተቋማት ጋር አጋርነት ዙሪያ ግልጽነት የማይታይ መሆኑ እንደሆነ ከአሠራር ጋር የተያያዘ ቅሬታ የቀረበበት ጉዳይ ሆኗል፡፡  

የንግድ ምክር ቤቱ ወቅታዊና አጠቃላይ አሠራር በዚህን ያህል ደረጃ ቅሬታ እንዲቀርብበት ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ፣ የንግድ ምክር ቤቶችን እንዲቆጣጠሩ በአዋጅ ሥልጣን የተሰጣቸው እንደ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ተገቢውን ክትትል ያለማድረጋቸው ነው የሚል አስተያየት እየተሰጠ ነው፡፡  እንዲህ ዓይነት ችግሮች ከመከሰታቸው በፊትም ይሁን ከተከሰቱ በኋላ፣ አፋጣኝ የማስተካከያ ዕርምጃ ሲወስዱ አለመታየታቸውን እንደ ችግር ይጠቅሳሉ፡፡

 ለቦርዱ የደረሰው ጥቆማ በአጣሪ ኮሚቴው እንዲያጣራለትና ለቦርዱ እንዲያቀርብ ውሳኔ መተላለፉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ቦርዱ እንዲህ ያለውን ውሳኔ ካሳለፈም በኃላ ተከታታይ ስብሰባዎችን ያደረገ ሲሆን፣ ቦርዱ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ጉዳዩን በዋናነት እንዲያቀርብ ካደረጉት መካከል የንግድ ምክር ቤቱ ምክትል ፐሬዚዳንት አቶ ፋሲካው ሲሳይ በጉዳዩ ላይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጉዳዩ እንዲህ በቀላሉ የማይታይና በሕግ እስከመጠየቅ የሚሄዱበት ጉዳይ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

ከአሠራር ግድፈት ጋር የተያያዙ በርካታ ቅሬታዎች ተነስተዋል፡፡ እነዚህን ቅሬታዎች በዝርዝር በመጥቀስ ማጣራት እንዲደረግ፣ ለዚህም አጣሪ ኮሚቴ እንዲቋቋም ቦርዱ በአብላጫ ድምፅ ውሳኔ እንዳሳለፈም አቶ ፋሲካው አረጋግጠዋል፡፡

ቅሬታው በዋናነቱ የቀረበባቸው ዋና ጸሐፊው አቶ ሺበሺ ቤተ ማርያምና ፕሬዚዳንቷ ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ ናቸው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ሥራውን የሚመሩትና የሚያስተባብሩት እነሱ በመሆናቸው በዋናነት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ንግድ ምክር ቤቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች በንግድ ምክር ቤቱ የአሠራር ክፍተቶች ሲፈጠሩ ለቦርዱ ማሳወቅ የነበረባቸው ቢሆንም፣ ቦርዱ ምንም የሚያውቀው ነገር ባለመኖሩ በቀረበባቸው ቅሬታ ላይ ከአንድ የቦርድ አባል በስተቀር ሁሉም ምርመራው እንዲካሄድ ውሳኔ ሊያሳልፉ መቻላቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ይህም በቃለ ጉባዔ ተዘርዝሮ የተቀመጠ ሲሆን፣ ይህንን ቅሬታና አጠቃላይ ታዩ የተባሉ የአሠራር ግድፈቶችን በሙሉ የሚያጣራ የኦዲት ኮሚቴው እንዲያውቅ መደረጉንም ከአቶ ፋሲካው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

 በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሠንበት ሸንቁጤና የንግድ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ሺበሺ ቤተ ማርያም፣ ተፈጠሩ የተባሉ ችግሮችን በተመለከተ ቦርዱ እንዲጣራ ስለመወሰኑ አረጋግጠዋል፡፡ ይሁን እንጂ የቀረበው አቤቱታና ቅሬታ ትክክል አለመሆኑንና ንግድ ምክር ቤቱ ሕግና ሥርዓትን ጠብቆ እየሠራ መሆኑንም በበቂ መረጃ ማሳየት ይቻላል ብለዋል፡፡

በተለይ ወ/ሮ መሰንበር ስለጉዳዩ ሲያብራሩ፣ በምክትል ፕሬዚዳንቱ የቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ቦርዱ ምርመራ ይካሄድ ብሎ የሰጠው ውሳኔ ችግሩ በመኖሩ ሳይሆን፣ በቀረበው ጥያቄ መሠረት ይጣራ ተብሎ ጥያቄ ሲቀርብ ይህንን ማስፈጸም ኃላፊነት ስላለበት ነው ብለዋል፡፡ ጉዳዩ እንዲህ ተጋንኖ መቅረቡ አግባብ አለመሆኑን ጭምር የሚሞግቱት ወ/ሮ መሰንበት፣ ውሳኔው ከተላለፈ በኋላ ጉዳዩን በይበልጥ እንዲያጣራ እስካሁን በነበሩ የኦዲት ኃላፊ ምትክ አዲስ ኦዲተር ተቀጥሮ የማጣራት ሥራውን እንዲሠራ ስምምነት ላይ መድረሱንም አመለክተዋል፡፡   

አቶ ሺበሺም ቢሆኑ ንግድ ምክር ቤቱ በተገቢው መንገድ ሥራውን እየሠራ ሲሆን፣ አሁንም በሚቀጠረው ኦዲተር በኩል የማጣራት ሥራው እንዲሠራ የሚደረግ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ተፈጠረ የተባለው ችግር ያለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ የውጭ ጉዞን በተመለከተም የንግድ ምክር ቤቱ አሠራር በሚፈቅደው መሠረት የሚከናወን በመሆኑ ግድፈት ተፈጥሯል በሚለው ሐሳብ ላይ የማይስማሙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም አሠራሩ ሕጋዊ ስለመሆኑ ማሳየት ይቻላል ይላሉ፡፡ ከውጭ ጉዞ ጋር በተያያዘ ወጣ የተባለው የውጭ ምንዛሪ ወጪ ግን ተጋንኖ የቀረበ በመሆኑ ጉዳዩ ሲጣራ እውነታው ሊታወቅ ይቻላል ብለዋል፡፡

‹‹ይጣራ የተባለው አጠቃላይ አሠራርና የኦዲት ሥራ ተጠናቅቆ ከቀረበ በኋላ በሚገኘው ውጤት መሠረት ተጠያቂ የሚሆን ካለ ተጠያቂ እንዲሆን ይደረጋል፤›› ያሉት ወ/ሮ መሰንበት፣ በተለይ የውጭ ምንዛሪ ብክነትን በተመለከተ የቀረበውን ቅሬታ እሳቸውም የማይቀበሉት ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ ወጣ የሚባለው የውጭ ምንዛሪ መጠን እጅግ የተጋነነ ነው ይላሉ፡፡  

አቶ ፋሲካው በበኩላቸው፣ ምርመራውንና የኦዲት ሥራው በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ ውጤቱን ማወቅ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡ ተጠያቂ መሆን ያለበት ሰው ተጠያቂ እንዲሆን በማድረግ ንግድ ምክር ቤቱ የጠራ አሠራር ኖሮት እንዲጓዝ የሚሹ ሲሆን፣ የኦዲት ሥራውም ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት እንዲከናወን መደረግ አለበት ብለዋል፡፡ ነገሩን በማድበስበስ የሚሠራ ከሆነ ጉዳዩን ወደ ሕግ ለመውሰድ የሚገደዱ መሆኑን ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች