Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ የሚይዙትና በተለምዶ ‹‹ሚኒባስ›› የሚባሉ ታክሲዎች አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

በአንድ ወቅት የእነዚህ ታክሲዎች ቁጥር ከ15 ሺሕ ይልቅ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ዛሬ ላይ ግን ብዙዎቹ ከመስመር ወጥተዋል፡፡ ከሚኒባስ የታክሲ አገልግሎት ጋር ተያይዞ አስገራሚው ነገርም እንዲህ ባለው የሚኒባስ የታክሲ አገልግሎት ከስመር የሚወጡትን ለመተካትም ሆነ ለማብዛት አለመቻሉ ነው፡፡ ወደዚህ ቢዝነስ የሚገቡ ግለሰቦችም ሆኑ ኩባንያዎች ፍላጎት የማጣታቸው ጉዳይም እንቆቅልሽ ሆኗል፡፡

በእርጅናም ይሁን በሌላ ምክንያት ከመስመር የሚወጡ ታክሲዎች በአዲስ አይተኩም፡፡ እየበዛ ከመጣው የትራንስፖርት ተገልጋይ አንፃር ቁጥራቸው ሊጨምር ይገባቸው የነበሩ ማኒባስ ታክሲዎች በተቃራኒው ቁጥራቸው እየተመናመነ የመምጣቱ ነገር በእርግጥም የሚያነጋግር ነው፡፡ ይህ ክፍተት ደግሞ የከተማዋን የትራንስፖርት አገልግሎት የበለጠ አወሳስቦታል ማለት ይቻላል፡፡

አሁን በሥራ ላይ ያሉትም ቢሆኑ አብዛኞቹ እርጅና የተጫናቸው ለተገልጋዩ ምቾት የማይሰጡ ናቸው፡፡ ይህም ሆኖ በትራንስፖርት ችግር የሚሰቃየው የኅብረተሰብ ክፍል አማራጭ ስለሌለው ተዛዝሎባቸው ጭምር ይጠቀምባቸዋል፡፡

እነዚህ ታክሲዎች ይብዛም ይነስም የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር በመታደግ ረገድ ያላቸው ጠቀሜታ የሚታወቅ ቢሆንም አገልግሎቱ እንደ አንድ የማይነጥፍ ቢዝነስ ዕድገት የማይታይበት ሆኖ መገኘቱ ያሳዝናል፡፡ ወደዚህ ቢዝነስ የሚገቡ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ለምን ጠፉ? ለሚለው ጥያቄ በራሱ መልስ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡

ተጓዦች እየበዙ ባሉበት በዚህ ወቅት የትራንስፖርት ቢዝነሱም አብሮ ሊያድግ ሲገባው ጭራሽ ያሉትም ከመስመር እየወጡ መሆን መቼም ጤናማ ሊሆን አይችልም፡፡

በተለይ ሥራና መውጫና መግቢያ ሰዓት ያለው ችግር ማንም የሚታዘበው ፈጦ ያለ ነገር ነው፡፡ ችግሩ ይቀላል ተብሎ በሚታሰብበት ሰዓትም ቢሆን ተገልጋዮች የማያጣው የታክሲ አገልግሎት የሚነግረን የበዛ ተገልጋይ መኖሩን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ገበያ አለ ማለት ነው፡፡ ቢዝነሱ አለ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ገበያ ባለው ቢዝነስ ውስጥ ሰዎች ተበረታትው ለምን አልገቡም የሚለው ጉዳይ በእርግጥም እንቆቅልሽ ነው፡፡

መንግሥት እንደ አንበሳ ባስ ባሉ ድርጅቶቹ በኩል የሚያሰማራቸው ተሽከርካሪዎቹም ቢሆኑ የከተማዋን የትራንስፖርት የፍላጎት የሚመጥን አለመሆኑ በግልጽ እየታወቀ የሚኒባስ ታክሲ አገልግሎት ላይ ያለውን ችግር ከግምት በማስገባት ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጥ ሲገባው ያለመደረጉ የከተማ አስተዳደሩ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ይሆናል፡፡ የችግሩን ስፋት ተገንዝቦ ብዙ አማራጮችን መመልከት ሲገባው ይህንን ባለማድረጉ ተገልጋዮች እንዲቸገሩ ብዙ ጊዜያቸውን በትራንስፖርት ጥበቃ እንዲያሳልፉ አድርጓል፡፡

በአገር ወቅት የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር ያቀላል ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት መገለጫ ይሆናሉ የተባለው ቀላል ባቡር ያተረፈልን ዕዳ ብቻ ነው፡፡

ከተማዋን ለሁለት ከፍሎ መስመሩ የሚያልፍ አካባቢዎችን ቢዝነስ መግደሉ ሳይንስ በቅጡ አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑ አለመሆኑ በግልጽ እየታወቀ የሕዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ የግል ዘርፉን ተበረታቶ ወደ ሥራ እንዲገባ አለማድረግ ተገቢ አይሆንም፡፡

ወደ መስመር ከሚገቡት ይልቅ የሚወጡ ባሶች፣ የቀላል ባቡር ፉርጎዎችና ሚኒባሶች እየበዙ ከሆነ በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ያለው ልዩነት የበለጠ እየሰፋ ነውና ጉዳዩን ዝም ብሎ መመልከት ችግሩን እያባባሰው ነው፡፡

በአጠቃላይ ዛሬ ላይ በአራቱም የከተማው አቅጣጫዎች በየመንገዱ ትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት አሰልቺ ሠልፎችን ይዞ የምናየው ተገልጋይ እየተንገላታ የሚታይበት አንዱ ምክንያት በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ወደ ቢዝነስ እንዲገቡ አለመደረጉ ነው፡፡

ስለዚህ የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ችግር ሥር እየሰደደ በመሆኑ መንግሥት ችግሩን ከመቅረፍ እንደ አንበሳ ባስ ባሉ ድርጅቶቹ ብቻ መቅረፍ የማይችል መሆኑን መረዳት አለበት፡፡ ከዚህም በኋላ ፍላጎቱ እያደገ የሚሄድ ከመሆኑ የግል ዘርፉ ወደዚህ ቢዝነስ እንዲገባ ዕገዛ ሊደረግለት ይገባል፡፡ በተለይ የሚኒባስ ታክሲዎች ቢዝነስ አዋጭ እንዲሆን የሚያስችል አሠራር ተዘርግቶ ቁጥራቸውን ማበራከት እስካልተቻለ ድረስ ችግሩን መቅረፍ አይችልም፡፡

ከዚህ አንፃር ሰሞኑን በአንድ የግል ባለሀብት ኩባንያ ተገጣጥመው የወጡ ናቸው የተባሉ ሚኒባሶች ለሙከራ የታክሲ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑ መሰማቱ ምናልባት ለሌሎችም ወደዚህ ቢዝነስ ለሚገቡ ባሀብቶች በር ከፋች ሊሆን የሚችል ከሆነ እየሰየው ነው፡፡

ወደ 20 የሚደርሱት እነዚህ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ሚኒባሶች አገልግሎቱን እንዲሰጡበት የታፈቀደበት መንገድ እንደተጠበቀ ሆኖ እንዲህ ባለ በተደራጀ መልክ የግል ዘርፉ የሚገባበት አሠራር ከተፈጠረ ችግሩን ማቃለል ይቻላልና ይህንን አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ግን የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ እንዲዘምን ጥሩ ዕድል ይሰጣል፡፡

ተጠቃሚዎች ከታሪፍ በላይ እንዳይከፍሉ ተሽከርካሪዎች ከመጫን አቅማቸው በላይ እንዳይጭኑ ለማድረግም ቢሆን በተደራጀ መልኩ ወደ ቢዝነስ የሚገቡ ግለሰቦችና ድርጅቶችን ማብዛት ጠቃሚ ነው፡፡

ይህ አሠራር ግን ሁሉንም በእኩል ሊያስተናግድ በሚችል መልኩ ሊተገበር የሚገባው ነው፡፡ ማበረታቻ ካስፈለገ መስጠትም ይገባል፡፡ የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር ከማቃለል አንፃር እንደ አንድ መፍትሔ መታሰብ ያለበት ኩባንያዎች ለሠራተኞቻቸው ሰርቪስ ማዘጋጀት ነው፡፡ ቢቻል ግዴታ ሆኖ ቢሠራበት ካልተቻለ ሠራተኛው ወጪውን በመጋራት አገልግሎት ቢሰጥ ለድርጅቱም ለሠራተኛውም ጠቃሚ ነው፡፡

ነገር ግን አንድ ወይም ሁለት ተሽከርካሪዎችን በማዘጋጀት የመፍትሔ አካል መሆን የሚችሉ አቅም ያላቸው ኩባንያዎች ሳይቀር ይህንን ሲያስቡ አይታይምና ይህ ሐሳብ ዳብሮ ሥራ ላይ የሚውልበት መንገድ ቢፈለግ አዋጭ ሊሆን ይችላል፡፡ በጥቅል ሲታይ ግን የከተማውን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል ሁሉንም አማራጮች መመልከት የግድ ይላል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት