Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በዓይናችን ሕይወት ሲለወጥ አይተናል›› ወ/ሮ ሙሉ ግርማይ፣ የላይፍ ኢትዮጵያ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ

ላይፍ ሴንተር ኢትዮጵያ በ2005 ዓ.ም. የተመሠረተ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን ላለፉት 11 ዓመታት ወላጅ አልባ ሕፃናትንና መበለቶችን ሲደግፍ የቆየ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ ወላጆቻቸውን ላጡና ለችግር ለተጋለጡ ሕፃናት መሠረታዊ የኑሮ ፍላጎታቸውን በማሟላት፣ የተረጋጋ ሕይወት ይኖራቸው ዘንድ በትምህርትና በጥሩ ሥነ ምግባር ተኮትኩተው ለራሳቸው፣ ለቤተሰባቸውና ለአገራቸው ጠቃሚ ዜጋ እንዲሆኑ በመቅረፅ ላይ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ ከ300 ለሚበልጡ ወላጅ አልባ ሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ፣ ልብስ፣ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችና የመሳሰሉትን በማቅረብ፣ የሕይወት ክህሎት ሥልጠናና የምክር አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው፡፡ በተጨማሪም ከ400 በሚበልጡ መበለቶች መሠረታዊ የቢዝነስ ሥልጠናና የተዘዋዋሪ ብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነው በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ተግባራት ተሠማርተው የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ኑሮ እንዲያሻሽሉ በማድረግ ላይም ይገኛል፡፡ ላይፍ ሴንተር ኢትዮጵያ እስካሁን ስላከናወናቸው ተግባራትና ወደፊት ሊሠራቸው ያቀዳቸውን ሥራዎች በተመለከተ የማነ ብርሃኑ የድርጅቱን መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሙሉ ግርማይን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱን እንዴት አቋቋሙት?

ወ/ሮ ሙሉ ግርማይ፡- ድርጅታችንን በ2005 ዓ.ም. የተመሠረተበት ዓላማ ወላጅ አልባ ሕፃናትንና መበለቶችን ለማገዝ ነው፡፡ እኔ ራሴ እንደ አንድ ግለሰብና እንደ አንዲት ኢትዮጵያዊት፣ ዛሬ ድርጅታችን እንደሚደግፋቸው ችግረኞች ያለ ሕይወትን ያሳለፍኩኝ ሴት ነኝ፡፡ ባለቤቴ አቶ ታምራት ላይኔ 12 ዓመታትን በእስር ቤት ሲያሳልፍ፣ ልጆቼን ብቻዬን አሳድጊያለሁ፡፡ ስለዚህ እናት ብቻዋን ልጆችን ስታሳድግ የሚገጥማትን መከራ ሁሉ አልፌያለሁ፡፡ ልጆቼን ይዤ ለሦስት ዓመት በስደት ኬንያ ኖሬያለሁ፡፡ በስደት ኑሮዬም ቤት አልባና ዘመድ አልባ ሆኜ እንድኖር ተገድጃለሁ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2003 ወደ አሜሪካ ከሄድኩኝም በኋላ ልጆቼን የማሳድግበት አቅም አልነበረኝም፡፡ ብቻዋን ልጆች እንደምታሳድግ እናት ልጆቼን በድህነት ሳሳድግ ቆይቻለሁ፡፡ አባት ሳይኖር እናት ብቻዋን ልጆቿን በማሳደግ የሚገጥማት ፈተና ሁሉ ደርሶብኛል፡፡ በራሴ ብቻ ሳይሆን ልጆቼ ያለ አባት ሲያድጉ የጎደለባቸውን ነገሮች ሁሉ አይቻለሁ፡፡ ስለሆነም ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆችንና፣ ልጆቻቸውን ብቻቸውን የሚያሳድጉ ቤተሰቦችን ሕይወት እንዳስብ የራሴ ሕይወት መነሻ ሆኖኝ ይህን ድርጅት ለማቋቋም ችያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ወላጅ አልባ ሕፃናትን እንዴት ነው የምትቀበሉት?

ወ/ሮ ሙሉ፡- ወላጅ አልባ ሕፃናትን የምንቀበላቸው ከወረዳ መስተዳደር ጋር በመነጋገር ነው፡፡ በወረዳ ጽሕፈት ቤት የሚገኙ የመንግሥት አካላት ልጆቹና ቤተሰቦቹ ስለሚገኙበት ሁኔታ ዝርዝር መረጃ ስለሚኖራቸው ከእነሱ ጋር በመሆን የልየታ ሥራ እንሠራለን፡፡ በዚህ ሥራ ውስጥም ልጆቹ የእውነት ወላጅ አልባ ናቸው የሚለውን እናረጋግጣለን፡፡

ሪፖርተር፡- ማዕከላችሁ ለልጆቹ የሚያደርግላቸው ድጋፍና እንክብካቤ ምን ይመስላል?

ወ/ሮ ሙሉ፡- እኔ በመጀመሪያ ላይፍ ሴንተርን ስመሠርት ያደረግኩት ነገር ቢኖር እኔ ይዤ ከተነሳሁት ዓላማ ጋር ተመሳሳይ ሥራ የሚሠሩ ድርጅቶችን መጎብኘት ነበር፡፡ በዚህም የተረዳሁት ልጆችን አንድ ላይ ሰብስቦ ማሳደግ ለልጆች አስተዳደግ እንደማይጠቅም ተረዳሁ፡፡ ስለሆነም የወሰንኩት ልጆቹ ከኅብረተሰቡ ሳይነጠሉ ቤታቸው ሆነው እየረዳናቸው እንዲያድጉ ነው የፈለግነው፡፡ ስለዚህም ሞዴላችንን ሆም ቤዝድ እንለዋለን፡፡ ልጆቹን በያሉበት ሆነው ነው የምንረዳቸው፡፡ ዘመድ ከሌላቸው ለምነንም ቢሆን የሆነ ሰው ኃላፊነት ወስዶ እንዲያሳድጋቸው እናደርጋለን፡፡ ከአሳዳጊዎቻቸውም ጋር አጋር ሆነን እንንከባከባቸዋለን፡፡ አንድ እናት ወይም አንድ አባት ካለም የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ በቤታቸው ሆነው እንዲያገኙ ነው የምናደርገው፡፡

ሪፖርተር፡- በማዕከላችሁ ለልጆች የሚደረገው ድጋፍ ምን ምንን ያካትታል?

ወ/ሮ ሙሉ፡- ማዕከላችን ለሚደግፋቸው ልጆች በየወሩ ለምግብ፣ ለትምህርትና ለጤና የሚሆን ለእያንዳንዱ ልጅ 1,400 ብር እንሰጣለን፡፡ ከዚያ ውጪ ቤት ውስጥ የሚጎድላቸውን ነገር በማዕከላችን ለመሸፈን እንሞክራለን፡፡ ለምሳሌ ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ቤት ውስጥ የቤት ሥራ የሚያግዛቸው የለም፡፡ ስለሆነም ሦስት አስተማሪዎች ቀጥረን አምስቱንም ቀን (ከሰኞ እስከ ዓርብ) ከትምህርት በኋላ መድበን በግሩፕ ይማራሉ፡፡ የኮምፒዩተር ትሬኒንግ እንሰጣለን፡፡ የምክር (የካውንስሊንግ) አገልግሎትም ያገኛሉ፡፡ ለወላጆቻቸው ስለልጅ አስተዳደግ ትምህርት እንሰጣለን፡፡

ሪፖርተር፡- ማዕከላችሁ ሌሎች የሚሠራቸው ሥራዎች ካለ ቢጠቅሱልን?

ወ/ሮ ሙሉ፡- አቅም የሌላቸው እናቶች (መበለቶች) ሠርተው ኑሮአቸውን እንዲያሻሽሉና ሕይወታቸውን እንዲለውጡ የቢዝነስ ክህሎት ሥልጠናና የብድር አገልግሎት መስጠት ሌላው የምንሠራበት መስክ ነው፡፡ የምንሰጠው የክህሎት ሥልጠና ሴቶች ‹‹እችላለሁ፣ ሠርቼ ኑሮዬን ማሻሻልና ሕይወቴን መለወጥ እችላለሁ፤›› በሚል ተስፋን እንዲሰንቁ የሚያደርግ ነው፡፡ ሥልጠናውን ከወሰዱ በኋላ ንግድ እንዴት ይሠራል? ትርፍ እንዴት ይገኛል? የሚለውን ከተረዱ በኋላ ለመነሻ የሚሆናቸውን ገንዘብ እናበድራቸዋለን፡፡ የእኛ ድርጅት ገንዘብ በጥሬ አይሰጥም፡፡ ለፕሮጀክት የሚሆናቸውን ማቴሪያል ገዝተን ነው የምናስረክባቸው፡፡ ለምሳሌ በማዕከላችን የቢዝነስ ክህሎት የወሰደች ሴት ፕሮጀክቷ እንጀራ መጋገር ከሆነ ምጣድና ሌሎች የሚያስፈልጉ ነገሮችን አብረን ገዝተን እናስረክባታለን፡፡ ቤት ድረስ በመሄድም ሥራዋን እንከታተላለን፣ ሲደክማትም እናበረታታለን፣ በምክርም እንደግፋታለን፡፡ ገንዘብ በጥሬ የማናበድራቸው ገንዘቡ ይጠፋል፣ ይባክናል ብለን ስለምናስብ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ እስካሁን ለ590 ሴቶች 4.3 ሚሊዮን ብር የሚደርስ የብድር አገልግሎት ሰጥተናል፡፡ በዚህም ኑሮአቸውን የለወጡ በርካታ እናቶችን አፍርተናል፡፡ በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ፣ በዶሮ እርባታ፣ በፈሳሽ ሳሙና፣ በልብስ ስፌት፣ በሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅና በሌሎችም የንግድ ዘርፎች ተሠማርተው ከራሳቸውና ከቤተሰቦቻቸው ሆድ አልፈው ለሌሎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ በርካታ ሴቶችንም አግኝተንበታል፡፡ በዓይናችን ሕይወት ሲለወጥ አይተናል፡፡ ምንም ነገር የሌላቸው እናቶች በእኛ ድጋፍ ኑሮአቸው ተሻሽሎና ለሌሎች ተርፈው ስመለከት እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡  

ሪፖርተር፡- ወደ ማዕከሉ ስንገባ ጋዋን ለብሰው የተመረቁ የወጣቶችን ምሥል ተመለከትኩ፡፡ እንደ ነገሩኝ ላይፍ ሴንተር ከተመሠረተ ደግሞ ገና አሥራ አንድ ዓመቱ ነው፡፡ ልጆቹን ከስንት ዓመታቸው ጀምሮ ብትደግፏቸው ነው ለዚህ ማዕረግ የበቁት?

ወ/ሮ ሙሉ፡- አንዳንዶቹ ድርጅቱ ከተመሠረተ ጀምሮ ከእኛ ጋር የቆዩ ናቸው፣ ከእኛ ጋር አሥር፣ ዘጠኝም፣ ስምንት ዓመትም የቆዩ አሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ እኛ ረድተናቸው ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ አሥራ ሦስት ልጆች አሉ፡፡ ይህ ማለት እኛ ማዕከሉን ስንመሠርት ስምንት ዓመት የነበረች ሴት፣ በእኛ እንክብካቤ ሥር ሆና ኮሌጅ ያጠናቀቀች አለች ማለት ነው፡፡ ይህንን ለምሳሌ አነሳሁ እንጂ ሌሎች በርካታ ኮሌጅ ያሉ የምንረዳቸው ተማሪዎች አሉ፡፡ ማዕከላችን ለልጆች የትምህርት ቁሳቁስ ከማሟላትና ገንዘብ ከመስጠት ባሻገር በካውንስሊንግ ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ሥልጠናውን ደግሞ የመልካም ባሕርይ ግንባታ (ጉድ ካርካተር ብዩልዲንግ) እንለዋለን፡፡ ይህም ልጆቹ ከኅብረተሰቡ የወጣ {ያፈነገጠ} ባህሪ እንዲያዳብሩ፣ ጎዳና እንዳይወጡ፣ እንዳይባልጉ፣ ቤተሰብ እንዳያስቸግሩና የአገር ሸክም እንዳይሆኑ ከሥር ከሥር እናሠለጥናቸዋለን፡፡ ኦርፋን (ወላጅ አልባ) የሚባል አስተሳሰብ እንዳይኖራቸውና በራስ መተማመን እንዳያዳብሩ ከትምህርት ጎን ለጎን ብዙ ሥራዎች እንሠራለን፡፡ እኛ ልጆችን ለማብላት፣ ለማጠጣት ብቻ ሳይሆን ጥሩ ዜጋ ሆነው ለሌላው በረከት እንዲሆኑ ዓላማ ይዘን እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማዕከላችሁ ምን ያህል ሠራተኞች አሉት? ከአዲስ አበባ ውጪስ የሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ይኖራል?  

ወ/ሮ ሙሉ፡- በብድር፣ በካውንስሊንግ፣ በትምህርትና በልጆች ዲፓርትመንት ውስጥ ሃያ ሁለት ሠራተኞች አሉን፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ፣ በአማራ ክልል ዋግህምራ ሰቆጣ እና በኦሮሚያ ክልል መቂ ከተማ ላይ እየሠራን እንገኛለን፡፡ አሁን ዕቅዳችን ቅርንጫፎቻችንን ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለማስፋትና ድጋፍና ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ሁሉ በምንችለው ልክ ለመድረስ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማም ባልደረስንባቸው ወረዳዎች ገብተን የመሥራት ዕቅዱ አለን፡፡ በምንሰጠው አገልግሎት እናቶችም፣ ልጆችም ሲጠቀሙ ስላየን ይህንን አገልግሎታችንን ይበልጥ ማጠናከር አለብን ብለን በማመን ትኩረት ሰጥተን በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ማዕከላችሁ በቀጣይ ሊተገብራቸው ያቀዳቸው ዕቅዶች ምንድናቸው?

ወ/ሮ ሙሉ፡- ማዕከሉ በቀጣይ ሊሠራቸው ያቀዳቸው ሥራዎችን በተመለከተ አሁን ልጆቻችን እያደጉ ነው፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ሥራ የማያገኙበት አጋጣሚ አለ፡፡ እነሱን በቢዝነስ (በንግድ) እንዲሠማሩ እንሠራለን፡፡ ላይፍ ሴንተር እስካሁን የሠራቸውን ሠናይ ተግባራት በተለያዩ ቦታዎች ማስፋት ሌላው ዕቅዳችን ነው፡፡ ማዕከላችን ባልደረሰባቸው አካባቢዎች በመሄድ ሕዝባችንን ማገዝ እንፈልጋለን፡፡ በውኃ፣ በጤና፣ በትምህርትና በሌሎችም ማኅበራዊ ዘርፎች ላይ በመሳተፍ ከቀድሞ በተሻለ መልኩ ማኅበረሰቡን ለማገዝና ለመደገፍ ዓላማ አድርገን በመንቀሳቀስ ላይ ነን፡፡

ሪፖርተር፡- ማዕከላችሁ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ከእነማን ጋር በቅንጅት ይሠራል? የሥራ አጋሮቻችሁ እነማን ናቸው?

ወ/ሮ ሙሉ፡- ከመንግሥት አካላት ጋር በፓርትነር አብረን እንሠራለን፡፡ የመሥሪያ ፈቃድ የሰጠን መንግሥት ነው፡፡ በወረዳ የሚገኙ የመንግሥት አካላት መጥተው ይመዝናሉ፡፡ እንዴት እንደምንሠራ ይገመግማሉ፣ ፕሮጀክታችንን እነሱ አፅድቀው ነው የምንሠራው፡፡ በተለያዩ ነገሮች ላይ እየመጡ ያግዙናል፡፡ በተረፈ ገንዘብን በሚመለከት በሕይወት አጋጣሚ እኔ በአሜሪካ ስለምኖር መቶ ፐርሰንት በሚባል ደረጃ ለምኜ ነው የማመጣው፡፡ መንግሥትን የምንጠይቀው ነገር ቢኖር ማዕከላችን በየወሩ ለቤት ኪራይ ወደ 80 ሺሕ ብር እያወጣ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ የድሆችን ሕይወት ሊለውጥ የሚችል ገንዘብ ነው፡፡ ስለሆነም ይህንን ሠናይ ዓላማ ለመደገፍ ለድርጅት የሚሆን ቦታ በመስጠት ሊተባበረን ይገባል እላለሁ፡፡ ሌላው እያንዳንዱ ግለሰብ አምስት ብር ቢያዋጣ ተጠራቅሞ ቁም ነገር ስለሚሠራ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተቀደሰ ዓላማውን በገንዘብ መደገፍ ይኖርበታል፡፡ እነዚህ ልጆች ከእኛው ኢትዮጵያውያን አብራክ የተገኙ ልጆች ናቸው፡፡ ስለሆነም እያንዳንዱ ግለሰብ በሚችለው አቅም ሁሉ እንዲህ ዓይነት ሕፃናትና እናቶችን የመርዳት የዜግነት ኃላፊነት ስላለበት የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በአሁኑ ወቅት ከ21 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ሰብዓዊ ዕርዳታ ይፈልጋል›› አቶ አበራ ሉሌሳ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ምክትል ጸሐፊ

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ላለፉት 89 ዓመታት በመላ አገሪቱ የሰብዓዊነት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በድርቅ፣ በበሽታና በግጭት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የምግብ፣ የመጠለያ፣ የመድኃኒትና የ24 ሰዓት...

ከቢሻን ጋሪ እስከ ዶባ ቢሻን እንክብል

ዶባ ኢንዱስትሪያል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሦስት ዓመታት በላይ ጥናትና ምርምር ያደረገበትንና ለገበያ ያበቃውን ዶባ-ቢሻን እንክብል የውኃ ማከሚያ...

ለሴቶች ድምፅ ለመሆን የተዘጋጀው ንቅናቄ

ፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በፆታ እኩልነት፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲሁም የሴቶችን ማኅበራዊ ችግር በማቃለል ዙሪያ በተለያዩ ክልሎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ...