Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በቤት አስቤዛ ዋጋ ላይ ሰሞኑን የታየው ቅናሽ ዘላቂነት እንዲኖረው መሠረታዊ ምክንያቱ ቢጠና የተሻለ ነው!

በናታን ዳዊት

ሽንኩርትና ቲማቲም ታሪካዊ የተባለ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎባቸው ሲቸበችቡ ሰንብተው ነበር፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለተወሰነ ጊዜ የአንድ ኪሎ ሽንኩርት እስከ 150 ብር ሲሸጥ ነበር፡፡ ቲማቲም ደግሞ በኪሎ 60 ብር ድረስ ዋጋ ተሰጥቶት ሲሸጥ መቆየቱ ምን ያህል ሸማቹን ሲያማርር እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በተደጋጋሚ እንደምንገልጸው ኢትዮጵያን በሚያክል ትልቅ አገር የሽንኩርትና ቲማቲም ዋጋ የሸማቾች ራስ ምታት ሆኖባት በተደጋጋሚ ስለዚሁ ችግር ማውራት በራሱ ያሳምማል፡፡ ለሽንኩርትና ለቲማቲም ምርት ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የግብርና ምርቶች ምቹ የሆኑ መልክዓ ምድር ያላት አገር በምግብ ራሷን ባለመቻል ስሟ ሲነሳና በተደጋጋሚ የዋጋ ንረቶች ሸማቾች የሚማረሩባት ሆና መቀጠሏን ከማየት በላይ ምን ሊያስቆጭ ይችላል?

ከሰሞኑ ብዙ ስናማርርበት የነበረው እንደ ሽንኩርትና ቲማቲም ያሉ ምርቶች ዋጋቸው በግማሽ በሚባል ቀንሶ ስናይ ደግሞ ሸማቾች አንፃራዊ ዕፎይታ ሰጥቷል፡፡ እስከ 150 ብር ሲሸጥ የነበረ አንድ ኪሎ ሽንኩርት በብዙዎቹ ገበያዎች ከ75 እስከ 80 ብር እየተሸጡ ነው፡፡ ከ50 እስከ 60 ብር ሲሸጥ የነበረው አንድ ኪሎ ቲማቲምን አሁን ከ20 እስከ 25 ብር መሸጥ ተጀምሯል፡፡ ድንች በኪሎ 30 ብር ቀይ ስር 20 ብር ድረስ እየተሸጡ ነው፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከነበረው ዋጋ ጋር ሲነፃፀር እስከ 100 በመቶ ቅናሽ ማሳየት ችሏል፡፡ በእርግጥ ይህም ዋጋ ቢሆን ትክክለኛው የገበያ ዋጋ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ አንድ ሰሞን በተጋነነ ዋጋ ሲሸጡ የነበሩት በተለይ እንደ ሽንኩርትና ቲማቲም ያሉ ምርቶች ዋጋቸው በግማሽ ቀንሶ ለገበያ መቅረባቸው ትልቅ ነገር ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንድ የቲማቲም አምራቾች ያመረቱትን ቲማቲም በኪሎ ሦስት ብር የሚገዛን ጠፋ እስከማለት መድረሳቸውንም ሰምተናልና አሁን ቀንሶ እየተሸጠበት ያለው ዋጋ ትክክለኛ የገበያ ዋጋ አይደለም የሚል እምነት እንድንይዝ ሊያደርገን ይችላል፡፡

በአንፃሩ የዋጋ መወደድ የሚፈጥረውን ችግር ያህል የተመረተ ምርትን በአግባቡ ለገበያ አለማቅረብ ወይም ‹‹በሞተ ዋጋ›› የሚገዛን አጣን የሚባል ከሆነ ይህም ትልቅ ችግር መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ውስጥ ለዋጋ ንረት እንደ መንስዔ ከሚጠቀሙ በርካታ ስብራቶች መካከል የግብይት ሥርዓታችን በዘልማድ የሚከናወን በብልሹ አሠራሮች የተተበተበ ጭምር መሆኑ ነው፡፡ አምራቾች እናተርፍበታለን ያሉትን ምርት በሦስት ብር መሸጥ አልቻልንም ማለታቸው የሚነግረንም የግብይት ሥርዓታችን ብልሽትና የተደራጀ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ባለመቻሉ ነው፡፡ ይህም ክፍተት ገበያውን ደላሎች እንዲፈነጩበት ዕድል ሰጥቷል፡፡

በወሳኝነት የግብይት ትስስር ጉዳይ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ብርቱ ምርኩዝ የመሆኑን ያህል አልተሠራበትም፡፡

ለማንኛውም በግብይት ሥርዓታችን ውስጥ ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ ከሰሞኑ ሽንኩርትና ቲማቲምን ጨምሮ በተለያዩ ምርቶች ላይ የታየው ዋጋ ቅናሽ ሸማቹን በተወሰነ ደረጃ ዕፎይታ የሰጠ ቢሆንም ዘላቂነቱ ላይ ግን ጥርጣሬ አለው፡፡  

በመሆኑም በጥቂት ሳምንታት ወይም በወራት ጊዜ ውስጥ እነዚህ ምርቶች የተጋነነ ዋጋ የተሰጣቸው ለምን ነበር? በአንዴስ ዋጋቸው በግማሽ ቀንሶ ለገበያ የቀረቡበት ምክንያት ምን እንደሆነ በመፈተሽ የሚገኘው ትክክለኛ መረጃ የተረጋጋውን ገበያ ለማስቀጠል ያስችላል፡፡ ምክንያቱም ከዚህም በኋላ እነዚህ ምርቶች ያልተጠበቀ የዋጋ ጭማሪ እንዳይታይባቸው ለማድረግ አሁን የታየውን የዋጋ ለውጥ ያመጣው ምንድነው የሚለው ጥያቄ በጥናት ላይ የተመሠረተ ምላሽ ካገኘ ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘትም ዕድል ሊሰጥ ይችላል፡፡ ለሰሞኑ የዋጋ መረጋጋት ምርት እንዲጨምር ተደርጎ ከሆነም እንደ ጥሩ ልምድ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ዋጋው ቢያንስ አሁን ካለው ዋጋ እንዳይጨምር መንግሥት የሠራው ሥራ ካለ ይህንን መግለጽና በሌሎች ምርቶችም ላይ መተግበር ይቻላል ማለት ነው፡፡

እስካሁን ግን ለሰሞኑ ዋጋ መረጋጋት ይፋዊ መረጃ ባይሰጥበትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ከተለያዩ ክልል ተወካዮች ጋር አድርገውት በነበረው የውይይት መድረክ ላይ ጠቆም ያደረጉት ነገር መጠነኛ ፍንጭ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ነገሩን በዝርዝር ባይገልጹትም ጉዳዩን የኑሮ ውድነት እያስከተለ ያለውን ጫና በማብራራት ነበር የጀመሩት፡፡ ‹‹የኑሮ ውድነት የዓለም ችግር ነው፡፡ እኛ ጋር ደግሞ የነበርንበት ሁኔታና የሕዝባችን ብዛት የማምረት ልምዳችን ተደማምሮ በጣም ከፍተኛ የሆነ ችግር አለ፡፡ በተለይ ደሃው ላይና በመንግሥት ሠራተኛው ላይ ያለው ጫና ከፍተኛ ነው፤›› ያሉት ጠቅላል ሚኒስትሩ፣ ይኼ የሚፈታው በማምረት ብቻ እንጂ ሌላ መንገድ የሌለው መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

አያይዘውም ‹‹ቲማቲም ውድ ነበር፡፡ አምርታችሁ አሁን ገበያው ላይ ያለውን ለውጥ ተመልከቱ፡፡ ሽንኩርት ችግር ነበር፡፡ ጎመን ችግር ነበር፡፡ አሁን ገበያውን እያቀዛቀዘው ነው፡፡ ይህንን በሁሉም ምርቶች ማስቀጠል አለብን›› ለታየው ቅናሽ ተጨማሪ ምርት በመመረቱ እንደሆነ ያስገነዝበናል፡፡ እውነታው ይህ ከሆነ ይህንኑ አሠራር እያበረታቱ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥም ዋጋን ለማረጋጋት የዋጋ ንረትን ለመቀነስ አቻ የማይገኝለት ቀዳሚ መፍትሔ ምርት መጨመር ነው፡፡

ምርት ካለ ገበያ ይረጋጋል፡፡ ችግሩ ግን ይህንን ምርት የማሳደግ ሥራ በዕውቀትና በመረጃ ላይ የተመሠረተ አሠራር ዘርግቶ ማስቀጠል ላይ ነው፡፡ ለሽንኩርትና ለቲማቲም ዋጋ መቀነስ ምርት እንዲጨምር ተደርጎ ከሆነ ሌሎች ምርቶችንም በዚሁ መንገድ ማስኬድ የማይቻልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ይህ ደግሞ በጥናት ላይ የተመሠረቱ አሠራሮች ሲዘረጉና አስቸኳይ የሆኑ ፖሊሲዎች ሲኖሩ ውጤቱ የበጠ ይሆናል፡፡ መልሶ ገበያው እንዳይግልና የደላሎች መጫወቻ እንዳይሆን ይህንን አጋጣሚ መነሻ በማድረግ መሥራት ሊያመልጥ የማይገባ ዕድል ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡

ከዚህም ሌላ እጥረት ያለበትን ምርት ለማምረት የተበረታታ አምራች ያመረትኩትን ምርት የሚገዛኝ አጣሁ በማለት የሚያሰማውን እሮሮ ለማስቀረት አምራቹና ሸማቹ በቀጥታ የሚገናኙበትን አሠራር መዘርጋት ነው፡፡ ይህንን ለማስፈጸም ያልተቋረጠ ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ከተደረገ የተጋነነ ዋጋን ለመቀነስና የተረጋጋ ገበያ እንዲኖር በማስቻል የሸማቹን ጫናም በተወነ ደረጃ ማቃለል ይቻላል፡፡ፍፈስሰበደ

ሰሞናዊ ዋጋ ቅናሽ የታየባቸው ምርቶች በዚህን ያህል ደረጃ ለመቀነሳቸው ትክክለኛው ምክንያት መታወቅ አለበት የምንልበት ሌላው ቁልፍ ጉዳይ አሁን ቀነሰ ተብሎ እየተሸጠ ባለበት ዋጋ መሸጥ የሚቻልበት ዕድል መፍጠር ስለሚያስችል ነው፡፡

ምክንያቱም አንድ ኪሎ ሽንኩርት በተለያዩ ገበያዎች ውስጥ እስከ 150 ብር ሲሸጥ 25 ብር ሲሸጥ የነበረ ድርጅት ነበርና ቀድሞም ቢሆን ዋጋው የተሰቀለው ያለአግባብ መሆኑን ስለሚጠቁመን ነው፡፡

ዘላቂ መፍትሔው ግን በእነዚህ የመፍትሔ ሐሳቦች ብቻ የሚመለስ አለመሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ በዋናነት የግብይት ሥርዓቱን መስመር ለማስያዝ ተግቶ መሥራት የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ዕርምጃ መሆን አለበት፡፡ አሠራርን ማዘመመን እያንዳንዱን ምርቶች በየከተማው የፍጆታቸውን ልክ ማወቅና መተንተን በዕቅድ ለማምረትና ገበያን ለማረጋጋት ከፍተኛ ዕገዛ ያደርጋል፡፡

በተለይ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችን ቢያንስ ተቀራራቢ የሆነ የፍላጎት መጠኑን ማወቅ በልክ እንዲመረት ያስችላል፡፡ በዘፈቀደ ወይም አንድ ሰሞን እንዲህ ያለው ምርት ተወደደ ተብሎ በዘመቻ ለማምረት ዘው ብሎ መግባት ጉዳት አለው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለውን ሁሉ ያገናዘበ መረጃ ማሰባሰብና በዚሁ መረጃ ላይ ተመሥርቶ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የሚሠሩ ሥራዎች ላይ በትጋት ከተሠራ የዋጋ ንረቱን ለመቀነስና ሸማቹን ለመታደግ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ በኃላፊነት የሚሠራ ራሱን የቻለ ተቋም ይኑረን አይኑረን ባናውቅም ይህንኑ ብቻ የሚሠራ ተቋም ቢኖረን ደግሞ የበለጠ ውጤታማ ሊሆን ይችላል፡፡

በእርግጥ ለሰሞኑ የዋጋ መቀነስ በአምራቹ ተነሳሽነትም ሆነ በመንግሥት አስገንዛቢነት ምርት እንዲጨምር በመደረጉ የተገኘ ውጤት ከሆነ ይህንን ማስቀጠሉ ላይ መበርታት ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ ዋጋ ለማረጋጋት ቀዳሚው መፍትሔ ምርት መጨመር ብቻ መሆኑ በፍጹም ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ምርት ለማሳደግ ደግሞ ምቹ አሠራር ይኑር፡፡ በተለይ ተረጋግቶ ለማምረት ሰላም ወሳኝ ነውና በዚህ ላይ መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት ማስታወሱ ተገቢ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ውጤታማ ሊሆን የሚችል አሠራር ብንዘረጋ ሰላም ከሌላ መደነቃቀፍ የማይቀር በመሆኑ ነው፡፡

ለማንኛውም ገበያውን ሊያረጋጉ የሚችሉ ሥራዎች ሊበረታቱ ይገባል፡፡ ዋጋቸው የሚቀንሱ ምርቶች ይበርክቱልን፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት