Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የግብይት ሥርዓቱን ለማዘመንም ሆነ መስመር ለማስያዝ ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል!

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ከግብይት ሥርዓት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ሰሞኑን ማብራሪያ ሰጥተው ነበር፡፡ በዚህ ማብራሪያዎች የግብይት ሥርዓቱን ለማሻሻል የተወሰዱ ዕርምጃዎችንና ተገኘ ያሉትንም ውጤት ምሳሌዎችን በመጥቀስ ጭምር ገልጸዋል፡፡ 

ካነሷቸው ነጥቦች መካከል ከግማሽ ምዕት ዓመት በኋላ የአገሪቱ የንግድ ሕግ መሻሻል የግብይት ሥርዓቱን እያዘመነው ነው የሚለው ይገኝበታል፡፡

በእርግጥ የግብይት ሥርዓቱን ለማዘመን የንግድ ሕጉ መሻሻሉ ጠቀሜታ እንዳለው አይካድም፡፡ ነገር ግን የንግድ ሕጉ መሻሻል ብቻውን ግብ አይደለም፡፡ በተለይ የንግድ ሕጉን በትክክል ወደ መሬት ለማውረድ የሚያስፈልጉ መመርያዎችና ተያያዥ ማስፈጸሚያዎች ባልወጡበት ሁኔታ የንግድ ሕጉ ተሻሽሎ መውጣት ብቻውን በተባለው ልክ የግብይት ሥርዓቱን አዘምኖታል ማለት ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ወደፊት አይቻልም፡፡ መሬት ላይ ያለው እውነትም የሚነግረን ይህንኑ ነው፡፡ 

የንግድ ሕጉ መሻሻል በኢትዮጵያ የተንሠራፋውን ብልሹ የግብይት ሥርዓት እያስተካከለ ነው ተብሎ የተገለጸበት መንገድም ቢሆን ችኮላ የተቀላቀለበት ነው ሊባል ይችላል፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ በተለይም በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ያለው አጠቃላይ ሒደት እጅግ የከፋ ብልሽት ያለበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተሠሩ የተባሉት ሥራዎችና የተወሰዱ ዕርምጃዎች ገና ሙከራ ላይ ያሉ ናቸው ሊባል ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓት ችግርና አጠቃላይ የንግድ ሥርዓቱ ብልሽት እንዲህ ቀላል ባለመሆኑና በግልጽም የሚታይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በተወሰኑ ያውም ጊዜያዊ በሚባሉ ዕርምጃዎች ሊፈታ ይችላል ተብሎ አይታሰብም፡፡ የግብይት ሥርዓቱን ለማሻሻል በተለይ በቀጥታ ከሸማቾች ጋር የተያያዙ አሠራሮችን በተመለከተ የእሑድ ገበያን ከማስፋፋት ጋር እየተሠራ ያለው ሥራም ቢሆን መሠረታዊ የሚባለውን ችግር አይፈታም፡፡ በተወሰነ ደረጃ ዋጋን የማርገብ ሁኔታ እንዲፈጠር ቢያስችልም ይህም ቢሆን በተቀናጀ መልክ የበለጠ ሊሠራበት የሚገባ ነው፡፡ 

ለኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓት ብልሽትና ግድፈት በርካታ ምክንያቶች የሚጠቀሱ ሲሆን ተደጋግሞ የሚነሳው ደግሞ የደላሎች ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የግብይት ሥርዓቱን ለማሻሻል ወስጃቸዋለሁ ካላቸው ዕርምጃዎች መካከል ከሦስት ሺሕ በላይ ደላሎች የንግድ ፈቃዳቸው እንዳይታደስ ማድረጉን በዚሁ ሰሞናዊ ማብራሪያ ላይ ተገልጿል፡፡ በእርግጥም ደላሎች የአገሪቱን የግብይት ሥርዓት በማፋለስ ቀዳሚውን ሥፍራ እንደሚይዙ ይታመናል፡፡ በየትኛውም ቢዝነስ ውስጥ ደላሎች ተሰግስገው ገበያውን መዘወራቸው ሕጋዊ የግብይት ሥርዓት ላይ የፈጠሩ ጫና እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ሚኒስትሩ ከዚህ አንጻር ከሦስት ሺሕ በላይ የሚሆኑ ደላሎችን ፈቃድ ደግሞ እንዳይታደስ ማድረጉ ትልቅ ስኬት ተደርጎ መጠቀሱ በራሱ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ 

በድፍን ኢትዮጵያ ያሉ ደላሎች በተለይ መሠረታዊ በሚባሉ ምርቶች ላይ ገብተው ያሻቸውን የሚያደርጉ ደላሎችና ተባባሪዎቻቸው ሲታሰቡ ግን ተወሰደ የሚባለው ዕርምጃ ከቁጥር የሚገባ አይደለም፡፡ እንዲህ ባለው ዕርምጃም ደላሎችን መንቀል አይቻልም፡፡ 

ደግሞም በድለላ ውስጥ አሉ የሚባሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ሥራ ያን ያህል በመንግሥት ዕውቅና የሚሰጠው ሆኖ ነው ወይ? ፈቃድ ሲሰጣቸው የነበረው የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ ችግሩ ጥቂት ፈቃድ በማገድ የሚፈታ አለመሆኑ ግን ሊሰመርበት ይገባል፡፡ አሁን ገበያው እየታመሰ ያለው እኮ ምንም ፈቃድ በሌላቸው ደላሎች መሆኑን ስናስብም የሚኒስትሩ ዕርምጃ ሥር ነቀል ለውጥ ለሚያስፈልገው የግብይት ሥርዓት እየወሰደ ያለውን መፍትሔ ኢምንት ያደርገዋል፡፡ 

በግብይት ሥርዓት ውስጥ ፈርጠም ያለ ጡንቻ ያላቸው እነዚህ ደላሎች ምናልባት የሚሠሩት ሥራ በትክክል ቢታወቅና በየጊዜው በእነሱ ጉልበት የሚሸጥ፣ የሚለወጠው ምርትና ንብረት ቢሰላ ምን ያህል ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር እንዳለ ያመለክታል፡፡ ከእያንዳንዱ ግብይት በኮሚሽን ስም የሚወስዱት ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ ቢንቀሳቀስ ከዚህ ብቻ መንግሥት የሚያገኘው ግብርም ሲታወስ ያስቆጫል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓት ብልሽት መለጫዎች የሆኑ ደላሎችን ለመቆጣጠርና ከግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ለማውጣት ፈቃድ ከማገድ ባለፈ በእያንዳንዱ ቢዝነስ ውስጥ ያሉ ፈቃድ የሌላቸው ደላሎችን ማስወጣት ይጠይቃል፡፡ ይህም አምራችና ሸማቹን በቀጥት የማገናኘት አሠራርን ሁሉ የሚጠይቅ በመሆኑ ይህንኑ ማጠንከር ግድ ይላል፡፡ ሥራውም የሌሎች ተቋማት ትብብር የሚጠይቅም ነው፡፡  

ገበያውን የሚያምሱ ደላሎች ፈቃድ የሌላቸው ምናልባትም የሆነ ቢዝነስ ንግድ ፈቃድ ይዘው በቀጥታና በተዘዋዋሪ ግብይቱን የሚዛወሩ በመሆናቸው እነዚህ ላይ ካልተዘመተ የግብይት ሥርዓቱ ፈጽሞ ማሻሻል አይቻልም፡፡ 

የግብይት ሥርዓቱን ለማሻሻል ንግድ ሚኒስቴር ሠራው ያለውን ሥራ እንቀበል ቢባል እንኳን ለግብይት ሥርዓቱ ብልሽት ሌላ ማሳያ የሚሆነው የኮንትሮባንድ ንግድ እጅግ ገንግኖ ባልወጣ ነበር፡፡ ሚኒስትሩ የግብይት ሥርዓቱ እንዲሻሻል እያደረገ ነው የሚለውን መግለጫ በሰጡበት አንድ ሳምንት ብቻ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛያቸው የሚነግረን ይህንኑ ክፍተት ነው፡፡

የግብይት ሥርዓቱ እየተሻሻለ ነው ከተባለ ከመቼውም ጊዜ በላይ እያደገ የመጣው የኮንትሮባንድ ንግድ ሊቀንስ ይችል እንደነበር ይታመናል፡፡ ሆኖም የምናየው ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው፡፡ 

ስለዚህ የግብይት ሥርዓቱን ለማዘመን እየወጡ ያሉ ሕጎች መልካም ቢሆኑም የኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓት መስመር ለማስያዝና የተረጋጋ ገበያ እንዲኖር ከተፈለገ አሁን ተወሰዱ ከተባሉ ዕርምጃዎች በላይ ሊታሰብ ይገባል፡፡ አዳዲስ ሕግጋትን ማውጣት ከብልሹ አሠራሮች እጅን መሰብሰብና በቅንጅት መሥራቱን ሁሉ ይጠይቃል፡፡ 

አሁን እየተስፋፋ የመጣውን የኮንትሮባንድ ለመከላከል፣ ደላሎችን ትርጉም ባለው መንገድ ከገበያ ለማውጣት የሚሠራው ሥራም ዘለቄታ ሊኖረው ይገባል፡፡ የግብይት ሥርዓቱን የበለጠ ለማዘመንም ሆነ ለማሻሻል በፖሊሲ ደረጃ አዲስ አሠራርና የቁጥጥር መንገድ በመቅረጽ ጭምር ካልተደገፈ ሥር የሰደደውን ችግር መንቀል አይቻልም፡፡ ምናልባትም በብቁ ባለሙያዎች የተደራጀ ጠንካራ ራሱን የቻለ ተቋም ያስፈልጋል፡፡ 

ልንተማመንበት የሚያስፈለገው ዋና ነጥብ ግን ከችግሩ ስፋትና ውስብስብነት አንፃር የአገሪቱን የግብይት ሥርዓት ለማሻሻል ብሎም ለማዘመን በአንድ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አቅም ብቻ የሚፈታ ያለመሆኑን ነው፡፡ ለዚህም ነው ለግብይት ሥርዓቱን ለማዘመንም ሆነ መስመር ለማስያዝ ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል የሚባለው፡፡ የግብየት ሥርዓቱ መስመር አለመያዝ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ዕቅዶችን በአግባቡ ለመፈጸም የማያስችል በመሆኑ ጉዳዩ በልዩ ትኩረት ሊሠራበት ይገባል፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት