Thursday, May 30, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሰብዓዊነት አይዘንጋ!

ሰላም! ሰላም! አንዱ ሳምንት አልፎ ሌላው ሳምንት ሲተካ በሰላም ተገናኝቶ ወግ መሰለቅ መልካም ነገር ነው፡፡ ሰላም ከሌለ ያው እንደምታዩት ሞት፣ መፈናቀል፣ ምግብና መጠለያ ማጣትና ለሰው ልጅ የሚከብዱ መከራዎች እንደ አሸን ይፈላሉ፡፡ በቀደም ምን ሆነ መሰላችሁ አንዱ ድንገት አጠገቤ ደርሶ፣ ‹‹ሰማህ አንበርብር ምን ጉድ ነው የምንሰማው እባክህ…›› ብሎ አፈጠጠብኝ። እኔ ደግሞ አርዕስት የሌለው ወሬ ስለማይገባኝ፣ ‹‹ስለምን እንደምታወራ አውቄ ነው መልስ የምሰጥህ?›› ብለው፣ ‹‹ተው አንበርብር እያወቅከው ለምን ታስለፈልፈኛለህ…›› እያለ ሰቅዞ ሲይዘኝ፣ ‹‹ወንድሜ አንተ በሆድህ አምቀህ የያዝከውን ጉድ ባውቅ ኖሮ ይኼኔ ከእነ መጣህበት ጉዳይ ጨረታ አቅርቤህ እሸቅልብህ ነበር…›› ስለው በመጣበት ፍጥነት ጥሎኝ እብስ አለ፡፡ ‹‹ስንቱን አሳለፍኩት…›› አለ መሐሙድ አህመድ በዚያ ወርቃማ ድምፁ። ቆይ ግን እንዲህ በፍርኃት አጣብቂኝ ውስጥ ሆነን ለምን ይሆን ሆዳችን ውስጥ ያለውን ሌላው እንዲዘረግፍልን የምንዋትተው? ልብ አድርጉ እንግዲህ እኛም እኮ እንዲህ ከሌላው ስንቃርም ነው ፈሪ ሆነን የቀረነው ማለቴ ነው። እርግጥ ነው ሆድ ውስጥ ያለን ነገር ከወዳጅ ዘመድ ጋር ፈር አስይዞ ሐሳብ መለዋወጥ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ድንገት በየደረሱበት ከሌላው እየቃረሙ ‹‹ሰበር ዜና›› ለመሥራት መጣደፍ ግን የጤና አይደለም፡፡ በየሥርቻው የአገር ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ዲፕሎማሲና ሌላውም ነገር ‹‹ተንታኝ›› ለመሆን በሌሎች ትከሻ ላይ መመርኮዝ ውግዝ መሆን አለበት፡፡ አይደል እንዴ!

በቀደም ዕለት ከብሔራዊ ቴአትር ወደ ፒያሳ የሚያወጣውን ጎዳና ይዤ ስራመድ ትግላችን ሐውልት ሥር ሰዎች ሲርመሰመሱ አየሁ፡፡ ምን ይሆን የሚሠሩት ጠጋ ብዬ ስቃኝ ለካስ የካራማራ ድል አክባሪዎች ነበሩ፡፡ ሞት ይርሳኝና ያንን የመሰለ የጀግንነትና የመስዋዕትነት መታሰቢያ ቀን በመዘንጋቴ ራሴን ክፉኛ ወቀስኩ፡፡ ‹‹ራስን መውቀስ አርቆ ለማሰብ ይጠቅማል…›› የሚለውን የወዳጄን ምሁሩ የባሻዬ ልጅ አስተምህሮ እያስታወስኩ በሐሳብ ጭልጥ አልኩ፡፡ ለእናት አገር ሲባል በከፍተኛ ወኔ፣ ፅናት፣ ጀግንነትና ተጋድሎ ታሪክ ያቆዩ ወገኖቼን እያሰብኩ በሕይወት ያሉትን ቃኘት ሳደርግ ሳላውቀው ዕንባዬ በጉንጮቼ ላይ ተንጠባጠበ፡፡ በቀድሞ ሠራዊት ወታደራዊ ዩኒፎርሞች አጊጠው አሁንም የበረሃ አንበሳ የመሰሉ ትንታግ የቀድሞ መኮንኖችንና የበታች ሹሞችን ሳያቸው፣ እውነተኛ የጦር ሰው ግርማ ሞገሳቸው ልቤን ሰቅዞ ያዘው፡፡ ስንቱን ችግርና መከራ ተቋቁመው ዛሬም ለእናት አገራቸው የከፈሉትን የጀግንነት ታሪክ ሲዘክሩ፣ እኔስ ማን ነኝ እያልኩ ራሴን ስመረምር የሥነ ሥርዓቱ መጠናቀቂያ ተበስሮ በፍቅር ስንለያይ ውስጤ በሐሴት እየረሰረሰ ነበር፡፡ ዕፎይ ያሰኛል!

እስኪ ወደ ሰርክ ወጋችን እንመለስ፡፡ መቼም እንደ መፍረድ ቀላል ነገር የለም። ‹ከበሮ በሰው እጅ ያምር ሲይዙት ግን ያደናግር…› ይላል የአገሬ ሰው፡፡ ድሮ ነበር እንጂ በከበሮ መደናገር ዛሬ በሰው እጅ ስናየው እያደናገረን ያለው ገንዘብ ብቻ ሆኗል፡፡ ‹ከየትና እንዴት ተገኘ? ትናንት የማኪያቶ እኔ እየከፈልኩለት አልነበር እንዴ?› የሚያስብለን አንዳንዱ ‹ኦቨርናይት› የሚያሳየው ለውጥ እንዲያው ምን ይባላል? ከበሮን ገንዘብ ይኑር እንጂ ከፍሎ ማስደለቅ ይቻላል፡፡ አይቻልም እንዴ? አስደላቂዎችን እዩ ከተጠራጠራችሁ፣ ጊዜው ተቀይሯሏ፡፡ ‹ገንዘብ፣ ገንዘብ፣ ገንዘብ፣ ገንዘብ ካለ ጠፈር ላይ ቫኬሽን› አለ፣ ዕድሜ ለገንዘብ። አሁን ይኼን ሁሉ ያመጣሁት መፍረድ ቀላል ነው ብዬ ነው አይደል? አዎ። ልብ ብላችሁ ስሙኝ ታዲያ። መቼም በፕሮፓጋንዳ ጋጋታ ከሚያጠነዙዋችሁ ‹ዳያስፖራም ሆኑ አገር በቀል› ፖለቲከኞች የእኔ ይሻላችኋል። ለራስ አልቆርስ ብለን ዳቦው እያለቀ ጠኔ እንዳይገድለን እንጂ፣ ይኼ ገንዘብ የሚሉት ምትሃት ነገር ብዙዎችን ከሰው ተራ እያወጣቸው ነው፡፡ የፖለቲካውም ሆነ የኢኮኖሚው መዳረሻ ሥልጣንና ጥቅም መሆኑ ቢታወቅም፣ የዘመኑ ገንዘብ ግን ከደም ጋር እየተለወሰ ብዙዎችን ለትዝብት እየዳረገ መሆኑን ለማወቅ ቲክቶክ፣ ፌስቡክና ዩቲዩብ በቂ ምስክሮች ናቸው፡፡ በደም ገንዘብ ያበዱ በዙ ለማለት ነው!

‹‹ለሰው ልጅ የውድቀቱ ሁሉ መነሻው ቁንፅል ዕውቀት ነው…›› የሚሉኝ አዛውንቱ ባሻዬ ናቸው፣ እውነታቸውን ነው። ባይሆን ኖሮ ምልክቶቹን አናይም ነበር። ከምልክቶቹም አንዳንዶቹ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ በትግልና በዕርዳታ ማሰባሰብ ስም ባልና ሚስት ሳይቀሩ አሜሪካና አውሮፓ ሆነው በአደባባይ ሲሰዳደቡ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ወይም ኢትዮጵያዊት ወንድማቸውን ወይም እህታቸውን በፌስቡክ ኮሜንቶች ስድብና ዛቻ፣ በቲክቶክ ስላቅና በዩቲዩብ ማስፈራሪያ እንዳይሸጡ እንዳይለወጡ አድርገው ትርምስ መፍጠራቸውና ብዙ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ታዲያ ጥፋቱ የሚብሰው ትንሽ ማወቃችን ሳያንሰን ከእኛ በላይ የለም ብለን አገር ይያዝልኝ ስንል መዋላችን ጭምር ነው። ለምሳሌ በቀደም፣ ‹‹ኧረ ይኼ ነገር ልክ አይደለም…›› ይለዋል አንድ ላብ አደር የአንድ ሀብታም ቅንጡ አውቶሞቢል ጎማ እየቀየረ። ቀያሪው እኮ ላብ አደሩ ነው። ያ አፈር አይንካኝ ባዩ ሀብታም ፌስቡክ ላይ ከዘጠና ሰዎች ጋር ቻት እያደረገ በመሀል በመሀል ‹‹ገልብጠው… የለም…  አሁን ነው የምታስረው?›› እያለ ጣልቃ ይገባል። እኔ ኮንዶሚኒየም ቤት ላሻሽጥ ደንበኛዬን እየጠበቅኩ ቆሜ እታዘባለሁ። ሥራዬ ብለው ከታዘቡ እኮ ስንት ያለ ቦታው የተቀመጠ ዕቃ ትታዘባላችሁ መሰላችሁ፡፡ በጣም ብዙ!

እኔ እየታዘብኩ ነው ብያችኋለሁ። ጎማው ተገልብጦ ነው የታሰረው። ልጁ የሚያደርገው ጠፍቶት ከባለቤቱ አላውቅም ብሎ ዝም ብሎ ገጥሞታል። በዚያ ላይ ብሎኖቹን በጣም አታጥብቅ ስለተባለ እንደ ነገሩ ሰካክቷቸዋል። ባለመኪናው ጎማው ገጥሞ ሲያይ ሃምሳ ብር ወርውሮለት ሊያሽከረክር ገባ። በዚህ ቅፅበት ሃምሳ ሜትር ርቀት ላይ ሙሽራ እስኪመስል ሽቅርቅር ብሎ የለበሰ ጎልማሳ ጥጉን ይዞ ሽንቱን ይሸናል። አንድ መንገደኛ፣ ‹‹ምናለበት እንደ አለባበስህ አስተሳሰብህን ብታሳምረው?›› ብሎት አለፈ። ‹‹አንተ አትሸናም? በመንፈስ ነው የምትኖረው?›› ጎልማሳው እየተሳደበ ሳይጨርስ ያ ፊት ለፊቴ ቆሞ የነበረ መኪና በቅጡ ያልተገጠመውና ያልታሰረው ጎማ መብረር ሲጀምር ሾፌሩ የሚያደርገው ጠፍቶት ሲደነባበር፣ መሪውን ወደ አልሆነ አቅጣጫ አዞረውና ጎልማሳው ላይ ወጣ። ወጣ ማለት እንደ ዘበት የሚነገር መሆኑ የገባኝ ይህን ጊዜ ነው፡፡ ጎማው ላዩ ላይ ተከመረበት ማለት ይቀላል፡፡ እንዲያ ነው!

ዓይኔ እያየ ጎልማሳው በዚያው አንቀላፋ ብላችሁ ታምኑኛላችሁ? የነገሮችን አነሳስ ሳይ ስለቆየሁ ደንግጬ ራሴ ሲዞር ለወሬ ከተሰበሰበው ሰው መሀል አንዱ በቦታው ላልነበረ ሰው ትዕይንቱን ሲያብራራ እሰማለሁ። ‹‹እንዲህ ሆኖ እንዲያ ስሆን አሽቀንጥሮ ቢጥለው አስፋልቱ አናቱን ተርትሮ ጣለው…›› ይላል። ‹‹እና ሞተ?›› ይጠይቃል ሰሚው ደንግጦ። ‹‹እና ሊቀርለት ነው? ድብን ነዋ…›› አይለውም? ‹አንተ እንዴት እንዲህ ይባላል?› የሚለው ሰው ካለ ብዬ ስጠባበቅ ደንበኛዬ ደረሰና ተያይዘን ወደ ጉዳያችን ሄድን። ኋላ ለባሻዬ ነገሩን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው አብራርቼ ሳጫውታቸው፣ ያ በኩራትና በተበቃይ ድምፀት ሞቱን ያረዳ የነበረ መንገደኛ ነገር ገርሟቸው ምን ቢሉኝ ጥሩ ነው? ‹‹አንበርብር ተፈራርተንና የሚጀምርልን አጥተን ነው እንጂ ያላበደ የለም ዘንድሮ…›› አሉኝ። ሁሉን እናውቃለን እያልን በሁሉ ነገር ከከሰርን ዘንዳ ድሮስ ሊቀርልን ኖሯል፡፡ ታዲያላችሁ ባሻዬ እንደ ቀልድ የተናገሯት ነገር እያደር ትከነክነኝ ጀመር። አብሬያቸው የምውላቸውን ሰዎች ባህሪና አነጋገር መታዘብ ጀመርኩ። ምን ላድርግ!

‹‹በተለምዶ ዕብደት የምንለው የአዕምሮ ሕመም በአገሬ ባህላዊ ማስታመሚያ መንገድ ስላለው እንጂ፣ ውጭ ቢሆን በእኛ አገር የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሳይሆኑ መገንባት የነበረባቸው የአዕምሮ ሕሙማን ማዕከላት ነበሩ…›› የሚለኝ ደግሞ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው። እሱ ደግሞ የማይለው የለም። ‹‹ለነገሩ ከአራት አንዳችን ጭንቅላታችን ጭው እያለበት እሱ እኮ ተቆጪ ነው፣ እሷ እኮ ተናዳጅ ናት። ስትናገር ወይም ሲናገር እንዳመጣላት/እንዳመጣለት ነው፣ ለዛሬ ለነገ አትልም/አይልም። አብሾ አለበት፣ ሰይጣናም ናት። ምን የማንለው አለ? የአዕምሮ ሕመም በሽታ እንዲህ እንደ ከፋ አናውቀውም፣ ስለዚህም ግራ ተጋብተን ግራ እናጋባለን። ለዚህ እኮ ነው ሕግ መጣስ፣ ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር ችግር ሁሉ ወደፊት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን ሙሉ ለሙሉ ፍሬ እንዳያፈራ የሚያደርጉት፡፡ ዋናው ችግራችን ይኼ ነው…›› ብሎ አስረዳኝ። እንዲህ ካልተዘረዘረ እኮ አይገባኝም!

ምሁሩን ወዳጄን ካዳመጥኩት በኋላ ተሻለ ሲባል እያደር በጉልበት እንጂ፣ በፀባይና በሐሳብ ብልጫ ተሠርቶ የማይኖርባት አገር እየሆነች የመጣችው አገሬ አሳዘነችኝ። ‹‹በነውር ጀምረን በነውር መቋጨት እስከ መቼ እንዲያጨነግፈን እንደምንፈቅድ አላውቅም…›› ብዬ ያሻሻጥኩት ኮንዶሚኒየም ቤት ባለቤት ኮሚሽኔን ሊሰጠኝ ቢደውል አላነሳ አልኩ። እንደ ዝና እንደ መታወቂያ የደፋናቸው ባህሪያትና መለያዎች ከትዕግሥትና ከጥበበኝነት ይልቅ ለምን ጉልበት ተኮር ሆኑ? ማን እንደ እኛ ደመ ሞቃት? ማን እንደኛ አትንኩኝ ባይ? ማን እንደ እኛ የጀግና አገር? መሸሽ የማያውቅ፣ የማይሸነፍና መሰል የብሔራዊ ስሜት መገለጫ ስሞች ዕውን ከአዋቂነት፣ ከአስተዋይነትና ከጥበበኝነት የፈለቁ ናቸው? ወይስ ከግትርነት? እያልኩ እንደ ባለዕዳ ስብከነከን ቆይቼ ወዲያው ረስቼው ገንዘቤን ልቀበል በረርኩ። በኋላ የቤት ኪራይ የምከፍለው ባጣ ዜብራ ላይ ስንከባለል ልገጭና ልሙት ታዲያ? ዜብራ ላይ የሚሻገሩ ቀርፋፋ ተሻጋሪዎች ቤት አልባ ናቸው ሲባል ስለሰማሁ ነው ይቅርታ፡፡ ወገኛ አትሉኝም!

በሉ እንሰነባበት እስኪ። ከዚህ በላይ ተሰብስቦ ማሽሟጠጥ የአገር ልማት ማደናቀፍ ነው። እስኪ አንዳንዴ ሥራ ባንፈጥር ወሬ እየቀነስን ልማቱን እናግዝ ልላችሁ ስል ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ደውሎ አቋረጠኝ። ‹‹ምንድነው?›› ስለው፣ ‹‹ፈጥነህ ድረስ እኔና አንተ የምንመራው ስብሰባ አለ…›› አለኝ። ከራሴ በላይ አጥብቄ ስለማምነው ተነካክቶ አያነካካኝም እያልኩ እንዳለኝ ፈጥኜ ደረስኩ። ጉዳዩን ሲያስጨብጠኝ ‹የሠፈራችን ወጣቶች ሥራ ፈጠራ ከሌላ ሠፈር ወጣቶች ሥራ ፈጠራ ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ ወደኋላ መቅረቱን› አጫወተኝ። ‹‹እና እኔና አንተ ምን አገባን?›› ስለው፣ ‹‹መንግሥት የሚናገረው ነገር ሁሉ የመንግሥት ንብረትና ራዕይ እየመሰለ ልማቱን ስለጎተተው በእናንተው አንደበት አበረታቱዋቸው…›› ተብሎ ነው አለኝ። እያቅማማሁ በርካታ ወጣቶች በወዲያ በኩል፣ እኔና የባሻዬ ልጅ ደግሞ ወዲህ ሆነን ተቀመጥን። ‹‹ይኼ ሁሉ ወጣት ሥራ የለውም?›› ብዬ ግሮሰሪ ያለሁ መስሎኝ ልቀደድ ስል፣ ‹ኧረ እንዳታስበላን አንተ ሰውዬ› በሚል ቁንጥጫ መዘለገኝ። እውነት እውነት እላችኋለሁ በልጅነቴም እንዲያ ያለ ቁንጥጫ አላጋጠመኝም። ታዲያ ይኼን እያየሁ የመናገርና የመጻፍ ሙሉ ነፃነቴ ተጨቆነ ብል ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ልጀምር ነው ማለት ነው? ጉድ እኮ ነው!

በአጭሩ የሥራ ፈጠራ ተነሳሽነታቸው ለምን ዝቅተኛ እንደሆነ ወጣቶቹ አስረዱ። አንዱ ተነስቶ፣ ‹‹የልብስ ስፌት መኪናን የፈለሰፈው ሰው የሞተው ታርዞ፣ በብርድና በቁር ኩርትም ብሎ ነው። እንዲሁም ራዲየም የተባለውን ጨረር በምርምር ያገኘችውና የኖቤል ተሸላሚ መሆን የቻለችው ሜሪኩሪ የሞተችው ጨረሩ ባደረሰባት አደጋ ነው። ስለተመጣጠኝ ምግብና ለሰውነታችን ስለሚኖረው ዓይነተኛ ጥቅም ለመጀመሪያ ጊዜ በመጽሐፍ ያሳተመውም የምግብ ተመራማሪ ምሁር የሞተው በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ነው። ታዲያ እኛ ይኼን ሁሉ እያወቅን በፈጠራ ላይ ጊዜ የማናጠፋው መኖር ስለምንሻ ነው…›› ብሎ ሲቀመጥ ገረመኝ። የገረመኝ የሰጣቸው ምሳሌዎች እውነት መሆን በምሁሩ የባሻዬ ልጅ ሲረጋገጥ እንጂ በወጣቶቹ ድምዳሜ አልነበረም። ማስረጃ አትሉም!

ወዲያው የባሻዬ ልጅ ‹በካውንተር አታክ› ስለቶማስ ኤድሰን ጨለማ ፈሪነት፣ ስለኦሊቨር ራይት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አለማጠናቀቅ፣ ወዘተ ብዙ ምሳሌ ደርድሮ በማሱት ጉድጓድ ያልወደቁ ስመ ጥር ተመራማሪዎችን ዘርዝሮ አሳመናቸው። የአንተ ድርሻ ምንነበር? አላችሁኝ። አለማወቄን አውቄ ዝም ብሎ ማዳመጥ ነዋ። ዘንድሮ እኮ የበጠበጠን ያለ ዕውቀት ሲከፋ ደግሞ በቁንፅል ዕውቀት ትንተና ካላሳመርን፣ ሥልጣን ካልያዝን፣ መድኃኒት ካላዘዝንላችሁና እንደፈለግን ሕዝብ ካላግተለተልን ባይነት ሆኗል። ከስብሰባው በኋላም እኔና የባሻዬ ልጅ ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪያችን አምርተን በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ትንሽ አውርተን ወደ ሌላ ዞርን። እስኪ እናንተም አውሩበት። ትንሽ እሳት ጫካ ታነድ እንዳይሆን፡፡ ትንሽ ዕውቀት አገር ታፈርስ እንዳይተረት እንወያይበት። ግሮሰሪ ውስጥ ደርቶ የሚወራው ግን አካባቢው ለልማት ስለሚፈለግ በሦስት ወራት ውስጥ ነዋሪዎች ተነሱ መባሉ ነበር፡፡ ለልማት መሆኑ መልካም ሆኖ ሳለ ዜጎች ሜዳ ላይ እንዳይበተኑ ይታሰብበት የሚለው ዋናው ጉዳይ ነበር፡፡ ከማፍረስ በፊት ሰብዓዊነት እንዳይዘነጋ የሚለው ጉዳይ ይሰመርበት፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት