Saturday, April 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በውስብስብ ችግሮች ውስጥ የምታልፈው ኢትዮጵያ ዕፎይታ ትሻለች!

ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች በበርካታ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ እያለፈች ነው፡፡ ሰላም የራቃት ኢትዮጵያ በተለያዩ ሥፍራዎች በሚካሄዱ ግጭቶች መታመስ ከጀመረች ዓመታት እየተቆጠሩ ነው፡፡ ግጭቶቹ የበርካታ ንፁኃን ወገኖችን ሕይወት ከመቅጠፋቸው ባሻገር፣ በአገርና በሕዝብ ንብረት ላይ ከባድ ጉዳት እያደረሱ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የፓርኮች፣ የሪዞርቶችና ከቱሪዝም ጋር የተገናኙ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች ድርጅቶች ራሳቸውን በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች እያስታጠቁ ነው፡፡ ከባንኮችና ከቴሌኮም ኩባንያዎች በተጨማሪ ከዘመኑ ዕድገት ጋር እኩል ለመራመድ የሚተጉ የመንግሥትና የግል ተቋማት፣ ፈጣኑን የዲጂታል ቴክኖሎጂ በመጠቀም እየዘመኑ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ ግዙፍ አፍርሶ የመገንባት ሥራ ውስጥ ገብታለች፡፡ እነዚህ ከብዙ በጥቂቱ የቀረቡ ማሳያዎች ላይ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን መጠነኛ ማሳያዎች መነሻ በማድረግ ስንነጋገር የሰላምና የፀጥታ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት እንደሚሻ ነጋሪ አያስፈልገውም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተከታታይ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር እያደረጓቸው ባሉ ውይይቶች በስፋት እየተነሳ ነው፡፡ ብዙዎች እንደ መጡበት የኅብረተሰብ ክፍል ባህሪ የሚነሱ የተለያዩ ጉዳዮች ቢኖሩም፣ በብዙዎች ግን የሰላምና የፀጥታ ጉዳይ ሳይነሱ አላለፉም፡፡ አሁንም ከእነዚህ ውይይቶችና ወደፊት ይደረጋል ተብሎ ከሚጠበቀው የአገራዊ የምክክር መድረክ ባሻገር፣ የሰላምና የፀጥታ ጉዳይ ከምንም ነገር በላይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ኢትዮጵያን በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟን ከግጭትና ከውድመት ጋር የሚያስነሳው የጥፋት ምዕራፍ መዘጋት አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሕጋዊና ከፖለቲካዊ የሰላም ጥረቶች በተጨማሪ፣ ለአገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች ዕድል መስጠት ይተኮርበት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ኃላፊዎች በመንግሥት በኩል ያለውን አቋም ከማስረዳት ጋር፣ እግረ መንገዳቸውንም በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አማካይነት የሚቀርቡ አማራጭ ሐሳቦችን ያዳምጡ፡፡ ውይይቱም ሆነ ንግግሩ የአንድ ወገን ሐሳብ ብቻ ጎልቶ የሚወጣበት ሳይሆን፣ ሌሎች ሐሳቦችም ተደምጠው ለሰላም ማስፈን ግብዓት ይሆኑ ዘንድ ይታሰብበት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም አካባቢዎች ግጭትን ለመፍታት፣ ለማግባባትና ዕርቅ ለመፈጸም የሚያስችሉ የሚያኮሩ ማኅበራዊ እሴቶች እንዳሉ ይታወቃሉ፡፡ እነዚህ እሴቶች የሟችና የገዳይ ወገኖችን ከበለጠ ጥፋት ታድገው ዕርቅ በማከናወን በጋብቻ ጭምር ደም የሚያደርቁ ሲሆኑ፣ ከፍ ተደርገው ከታሰበባቸው ደም እንደ ጎርፍ እየፈሰሰባት ላለችው ኢትዮጵያ መድን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ መንግሥትም ሆነ የአገር ጉዳይ የሚመለከታቸው ወገኖች በሙሉ ለእነዚህ እሴቶች ዋጋ ይስጡ፡፡ የንፁኃን ደም መፍሰስና የአገር ሥቃይ ያብቃ፡፡

ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ታስቦባቸው በሁሉም የአገሪቱ የመንግሥትና የግል ተቋማት የሚከናወኑ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥርዓቶች ጥንቃቄ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የአገልግሎት አሰጣጦችን ማዘመንና በቴክኖሎጂ ማስደገፍ የግድ መሆን ያለበት የዘመኑ የአሠራር ሥልት ነው፡፡ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግን በሥርዓት መያዝ አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ከፍተኛ ዲሲፕሊን፣ ሥልጠና፣ ኃላፊነትና ትጋት ይጠይቃል፡፡ በፋይናንስ ተቋማት፣ በቴሌኮም፣ በግብርና በጉምሩክ መሥሪያ ቤቶች፣ በውኃና በኤሌክትሪክ፣ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችና በተለያዩ ዘርፎች ሥራን ለማቀላጠፍ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ተተኪ የሌለው የአሠራር ሥርዓት ነው፡፡ ነገር ግን በብዙ ተቋማት ‹‹ሲስተም የለም›› እየተባለ የሚሳበበው ዳተኝነት፣ ከሌብነትና ከማጭበርበር ጋር የተያያዘ ብልሹ አሠራርና መሰል ግድፈቶች ተገልጋዮችን ለጉዳት እየዳረጉ ነው፡፡ የሰሞኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ‹‹የዲጂታል ቴክኖሎጂ ማዘመን የገጠመው ችግር›› በትክክል ምክንያቱ ታውቆ ዕርምጃ ካልተወሰደ ጥፋቱ ወደ ሌሎች መዛመቱ አይቀሬ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ያለው መጠነ ሰፊ የማፍረስና የመልሶ ግንባታ ሥራ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያሻዋል፡፡ በከተማ አስተዳደሩ የተያዘው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት የበርካታ ዜጎችን ሕይወት የሚነካ በመሆኑ፣ የታሰበው ዓላማ ላይ ሲተኮር የዜጎች የሥራና የመኖሪያ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡ መኖሪያዎቻቸው የፈረሱባቸው የሚጠለሉበት ቤት ማግኘታቸው፣ ሥራዎቻቸውን እያጡ ያሉ ዜጎች በፍጥነት ገቢ ማግኘት መቻላቸው በተግባር መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ከቀድሞ ቀዬአቸው የተነሱ ወገኖች መኖሪያ ቤት እያገኙ እንደሆነ የከተማ አስተዳደሩ እየገለጸ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ በዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት ምክንያት ከሥራዎቻቸው የተፈናቀሉ ሰዎችም ጉዳይ ሊያሳስብ ይገባል፡፡ ልማቱ የጋራ የሚሆነው ግዙፉ ፕሮጀክት ሰው ተኮር መሆኑን በተግባር ሲያረጋግጥ ነው፡፡ አዲስ አበባ ስታምር ዋነኛ ተጠቃሚዎች ለከተማዋ እዚህ ደረጃ መድረስ የለፉ ነዋሪዎች መሆን አለባቸው፡፡

ኢትዮጵያ ሰላምና ፀጥታዋ ከተመለሰ ትልቅ ተስፋ ያላት አገር ናት፡፡ በአፍሪካ ከናይጄሪያ በመቀጠል በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ ከ120 ሚሊዮን በላይ ከሚሆነው ሕዝቧ ከ70 በመቶ በላይ ወጣት ነው፡፡ ይህን ወጣት ኃይል ይዞ ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ ከድህነት አዘቅት ውስጥ ለማውጣት ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ሰላም ሲኖር ወጣቱ ኃይል በሁሉም ዘርፎች ዘመን አፈራሽ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም፣ በአፍሪካ ተዓምር መሥራት ለመቻል ምንም ነገር አያዳግተውም፡፡ ወጣቱ ጥራት ያለው ትምህርት አግኝቶ ቴክኖሎጂን በስፋት ሲጠቀም አገር ታድጋለች፡፡ ወጣቱ በሥርዓት ሲታነፅ ሌብነትና ኢሞራላዊ ድርጊቶች ይወገዳሉ፡፡ ለሰላም መጥፋት ምክንያት የሆኑ ችግሮች በንግግር ፈር ይይዛሉ፡፡ ከራስ በፊት የአገር ጥቅም ማስቀደም ባህል ይሆናል፡፡ በውስብስብ ችግሮች ውስጥ የምታልፈው ኢትዮጵያም ዕፎይታ ትሻለች!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...