Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ከኢትዮጵያ ባሻገር የታለመው የጥርስ ሕክምና

የስበን ልዩ የጥርስ ሕክምና ማዕከል መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ሜሮን ኃይለ ማርያም (ዶ/ር) ትምህርታቸውን የተከታተሉት በጅማ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ በ2005 ዓ.ም. በጥርስ ሕክምና ሙያ መስክ ከዩኒቨርሲቲው በዶክትሬት ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ አርባ ምንጭ ጨንቻ አካባቢ ለሁለት ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የተወሰኑ የግል የጥርስ ሕክምና ማዕከላት ውስጥና በኮሪያ ሆስፒታል አገልግለዋል፡፡ማዕከሉ እየሰጠ ስላለው አገልግሎትና በአጠቃላይ በአገራችን የጥርስ ሕክምና ዙሪያ የማነ ብርሃኑ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ሰበን ልዩ የጥርስ ሕክምና ማዕከል መቼ ተቋቋመ? ማዕከሉን ለመመሥረት ምክንያት የሆናችሁ ምን ነበር?

ሜሮን (ዶ/ር)፡- ሰበን ልዩ የጥርስ ሕክምና ማዕከል የተቋቋመው በ2011 ዓ.ም. ነው፡፡ በ1.75 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል የተጀመረ ነው፡፡ በወቅቱ ይህ ገንዘብ የጥርስ ሕክምና ማዕከል ለመክፈት ትልቅ የሚባል ነበር፡፡ ድርጅቱን ለመመሥረት የተነሳነው ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለአገራችን ማኅበረሰብ በተመጣጣኝ ክፍያ አገልግሎት መስጠትን ዓላማ አድርገን ነው፡፡ ድርጅቱ የልዕቀት ማዕከል እንዲሆንም ዓላማ ሰንቀን የተነሳን ሲሆን፣ ይህንንም በተግባር ለመተርጎም ከፍ ያሉ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- በአገራችን የጥርስ ሕክምናው ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል?

ሜሮን (ዶ/ር)፡- የጥርስ ሕክምናው በአገራችን ከቀድሞው የተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል ብዬ አምናለሁ፡፡ በአሁኑ ወቅት በርካታ የጥርስ ሕክምና የሚሰጡ ማዕከላት መኖራቸው በራሱ ኅብረተሰቡ ስለጥርስ ያለው ግንዛቤ እየተለወጠ መምጣቱን አመላካች ነው፡፡ እኔ እንኳን እንደማስታውሰው በቤተሰብ ደረጃ ሕፃን እያለን ጥርሳችንን በጥርስ ብሩሽና በሳሙና ተጠቅመን እንድናፀዳ አይፈቅዱልንም ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አፍ ያሸታል ስለሚባል ነው፡፡ ይህ ከግንዛቤ እጥረትና ማነስ የመጣ ነው፡፡ ዛሬ ግን ግንዛቤውም ስላለ፣ ዘመኑም የውበት በመሆኑ ወላጆች የልጆቻቸውን ጥርስ ለማሠራትና ለማስተካከል ወደ ጥርስ ሕክምና ይመጣሉ፡፡ ከተማ ውስጥ ብሬስ አድርገው የሚሄዱ ልጆችን መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ግን ‹‹ማሉኪሊዥን›› (ትክክለኛ ያልሆነ የጥርስ አበቃቀል) የሚያሠሩት አልፎ አልፎ ወጣቶችና በዕድሜ ተለቅ ያሉ ሰዎች ብቻ ነበሩ፡፡ የጥርስ ሕክምናው ከትናንት ዛሬ መሻሻሎች የሚታዩበትና በኅብረተሰቡ ዘንድም ግንዛቤው ያደገበት ነው፡፡ ሆኖም ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር ዘርፉ ገና አሁንም ልጅ ነው ለማለት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ጥርስን ጨምሮ ለአጠቃላይ ሕክምናው ዘርፍ የሕክምና መሣሪያዎች ዘመናዊነት ወሳኝ ነው፡፡ የእርስዎ ድርጅት ዘመናዊነት እንዴት ይገለጻል?

ሜሮን (ዶ/ር)፡- ድርጅታችን በዘመናዊ መሣሪያዎች የተሟላ ነው፡፡ የራሴን ድርጅት ከመክፈቴ በፊት ኮርያ ሆስፒታል መሥራቴ ዘመናዊ መሣሪያዎችን እንዳውቅ፣ እነዚህንም መሣሪያዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳስገባና ትልቅ ሕልም እንዲኖረኝ አድርጓል፡፡ የድርጅታችን ዕቅድ የጥርስ ሕክምናውን በአገራችን ማዘመን ነው፡፡ ለዚህም እንደ ካድካም (CAD CAM) ያሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ወደ አገር በማስገባት ከዚህ በፊት ውጭ አገሮች ተልኮ ይሠራ የነበረውን ዚርኮኒያ (Zirconia) ጥርስ በአጭር  ቀናት ውስጥ ለመሥራት እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡ አገልግሎቶቻችንንም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተደግፈን እየሰጠን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የካድ ካም (CAD CAM) ማሽን የሚሰጠው አገልግሎት ምንድነው?

ሜሮን (ዶ/ር)፡- ይህ የካድ ካም (CAD CAM) ማሽን እኔ እስከማውቀው በአገራችን ሁለት ቦታ ያለ ይመስለኛል፡፡ አንደኛው ዶክተር እመቤት የጥርስ ሕክምና ማዕከል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ኮርያ ሆስፒታል ነው፡፡ እነሱም አገልግሎቱን የሚሰጡት ለራሳቸው ታካሚዎች (ደምበኞች) ብቻ ነው፡፡ እኛን ጨምሮ ሌሎች የጥርስ ሕክምና ማዕከላት የካድ ካም (CAD CAM) ማሽን የሚሰጠውን አገልግሎት ለማግኘት ማለትም (Zicornia) ጥርስ እንዲሠራልን ቻይና፣ ህንድና ከአፍሪካ አገር ደግሞ ሩዋንዳ ነበር የምንልከው፡፡ አሁን ግን ይህን ማሽን ድርጅታችን ወደ አገር ማስገባት ችሏል፡፡ ይህ ማሽን አገራችን ካሉት መሰል ማሽኖች የሚለየውም ፋይቨ ኤክስ (Five x) መሆኑ ነው፡፡ እስካሁን አገራችን ላይ ያሉት ፎር ኤክስ (Fore x) ናቸው፡፡ ሦስት አክሲስና አንድ ሮቴሽን ብቻ ነው ያላቸው፡፡ ይኼኛው ግን ሦስት አክሲስና ሁለት ተጨማሪ ሮቴሽን ያለው ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ማሽን አገራችን በመግባቱና በማዕከላችን መገኘቱ ከራሳችን ደምበኞች ባለፈ በአዲስ አበባም ሆነ በመላ አገሪቱ ላሉ የጥርስ ሕክምና ማዕከላት አገልግሎቱን እንድንሰጥ ያስችለናል፡፡ በውጭ አገሮች ተልኮ ሲሠራ ይፈጅ የነበረውን ጊዜና የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት ረገድም ከፍ ያለ አበርክቶ ይኖረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ ምን ያህል ሠራተኞች አሉት? ቀጣይ ዕቅዳችሁስ ምን ይመስላል?

ሜሮን (ዶ/ር)፡-ድርጅታችን 14 ቋሚ ሠራተኞች አሉት፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አምስት ሐኪሞች፣ ስድስት ነርሶችና ሦስት ቴክኒሺያን ይገኛሉ፡፡ የወደፊት ዕቅዳችን በጥርስ ሕክምናው ዘርፍ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ከኢትዮጵያ ባሻገር ለሌሎችም አገሮች አገልግሎቱን ማቅረብ ነው፡፡ ለምሳሌ ሩዋንዳ ያሉ የጥርስ ሕክምና ማዕከላት ለኢትዮጵያ እየሠሩ ይልኩ ነበር፡፡ ተቋማችንም ይህንን ዚኮርንያ (Zicorinia) ጥርስ እየሠራ ኤክስፖርት (Export) የማድረግ ዕቅድ አለው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ቀላል ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ሲደረግ እንደነበረው አገልግሎት ፈላጊዎች ዲጂታል ኢሜጁን ሲልኩልን እኛ ደግሞ በDHL ወይም በሌላ መላላኪያ ዘዬ በመጠቀም ጥርሱን ሠርተን ማስረከብ ነው፡፡ ለዚህም ከውጭ አገሮች ከሚገኙ መሰል ተቋማት ጋር የሥራ ኔትወርክ ለመፍጠር እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በአሁኑ ወቅት ከ21 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ሰብዓዊ ዕርዳታ ይፈልጋል›› አቶ አበራ ሉሌሳ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ምክትል ጸሐፊ

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ላለፉት 89 ዓመታት በመላ አገሪቱ የሰብዓዊነት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በድርቅ፣ በበሽታና በግጭት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የምግብ፣ የመጠለያ፣ የመድኃኒትና የ24 ሰዓት...

ከቢሻን ጋሪ እስከ ዶባ ቢሻን እንክብል

ዶባ ኢንዱስትሪያል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሦስት ዓመታት በላይ ጥናትና ምርምር ያደረገበትንና ለገበያ ያበቃውን ዶባ-ቢሻን እንክብል የውኃ ማከሚያ...

ለሴቶች ድምፅ ለመሆን የተዘጋጀው ንቅናቄ

ፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በፆታ እኩልነት፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲሁም የሴቶችን ማኅበራዊ ችግር በማቃለል ዙሪያ በተለያዩ ክልሎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ...