Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህል‹‹የተራራው መብረቅ››

‹‹የተራራው መብረቅ››

ቀን:

ከ1960ዎቹ መገባደጃ እስከ 1980ዎቹ መጀመሪያ የነበረው አብዮታዊው የኢትዮጵያ መንግሥት በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ ካደራጃቸው ልዩ ልዩ ክፍሎች በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ መካከል 18ኛው ተራራ ክፍለ ጦር ይገኝበታል፡፡

‹‹የተራራው መብረቅ›› | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ይህ የሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት አንዱ አካል የነበረው ክፍለ ጦር፣ በተለይ በ1974 ዓ.ም. በኤርትራ በተከናወነው የቀይ ኮከብ ሁለገብ አብዮታዊ ዘመቻ በአስመራ ከረን፣ አፈ አበት ግንባር በመፋለም ጀብዱ መፈጸሙ ይወሳል፡፡

- Advertisement -

‹‹የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት›› (Former Ethiopian Armed Force) በሚል በሚታወቀው የማኅበራዊ ትስስር ገጽ እንደተጠቀሰው፣ የሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት አካል የሆኑ 18ኛ እና 19ኛ ተራራ ክፍለ ጦሮች በታጠቅ ጦር ሠፈር የተመሠረቱት በ1972 ዓ.ም. ነበር፡፡

የሠራዊቱ መሪ ከመኰንኖች የሆለታ 39ኛ ኮርስ መኰንኖች እንደነበሩ፣ የ18ኛው ክፍለ ጦር መሥራች አዛዥም ብርጋዲየር ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተ ማርያም እንደሆኑ ገጸ ታሪኩ ያሳያል፡፡ ከወር በኋላ አዛዥነቱን የተረከቡት ደግሞ ሜጀር ጄኔራል መርዳሳ ሌሊሳ ናቸው፡፡

ክፍለ ጦሩ በተለያዩ ጊዜያት በፈጸመው የጀግንነት ውሎና ተጋድሎ በአብዮታዊው መንግሥት የላቀ የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳይና ዓርማ ተሸላሚ ሆኗል፡፡

የዚህን የሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት አካል ስለነበረው 18ኛው ክፍለ ጦር ታሪክ የሚያወሳና የሚተርክ መጽሐፍ ከሰሞኑ ለንባብ በቅቷል፡፡

በገስጥ ተጫኔ የተጻፈው ታሪካዊ መጽሐፍ ‹‹የተራራው መብረቅ›› ይሰኛል፡፡

362 ገጾች፣ 16 ምዕራፎች፣ 28 ፎቶግራፎችና ስድስት የካርታ ንድፎችን አካትቶ ከ1972 ዓ.ም. እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ ክፍለ ጦሩ በተለያዩ ዓውደ ውጊያዎች ጠላትን ለመደምሰስ ያካሄደውን ተጋድሎና የተቀዳጃቸውን ድሎች በዝርዝር እንደሚተርክ የገለጹት ሻምበል ያለው አክሊሉ ናቸው፡፡

 መጽሐፉ መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ሲመረቅ አስተያየት የሰጡት ሻምበል ያለው እንደጠቀሱት፣ መጽሐፉ የተራራው ክፍለ ጦር ግዳጅ አፈጻጸም፣ የማጥቃትና የመከላከል ልዩ ብቃቱን ፍንትው አድርጎ በዝርዝር የሚያብራራ ነው፡፡

ክፍለ ጦሩ ለኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ የገባውን ቃል ሳያጥፍ ‹‹አብዮታዊት ኢትዮጵያ ወይም ሞት!›› በማለት በየተራራው ከመሸገው ጠላት ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ በመተናነቅ ጠላትን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣትና የሚመካበትንም ምሽግ በማፈራረስ ታሪክ የማይረሳው አኩሪ ድል ማስመዝገቡን በማመልከት መጽሐፉ በሰፊው እንደሚተርክ ነው የተናገሩት፡፡  

‹‹አንድ ጦር የውጊያ ብቃት እንዲኖረው ለማድረግ በቅድሚያ በቂ ሥልጠና፣ የሞራል ግንባታና በወታደራዊ ሳይንስና ታሪክ ሊታነፅ ይገባል፤›› ያሉት ደግሞ የቀድሞው የናደው ዕዝ ዋና አዛዝ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል ውበቱ ፀጋዬ ናቸው፡፡ እንደ ጄኔራል መኰንን አባባል ከላይ የተጠቀሱት ቅድመ ሁኔታዎች ባልተሟሉበት አኳኋን ጦርነት መጣ ተብሎ ኃይልን ማንቀሳቀስ ‹ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ› እንደማለት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ ሁልጊዜ ለጦርነት ተጋላጭ እንዳደረጋት፣ ይህንንም ለመከላከከል የተካሄደውን ትንቅንቅና የተከፈለውን መስዋዕትነት የሚያወሳ ታሪክ እምብዛም እንዳልተጻፈም ብርጋዴር ጄኔራል ውበቱ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ የ18ኛ ተራራ ክፍለ ጦር ተጋድሎን የሚተርክ መጽሐፍ ታትሞ ለንባብ መብቃቱ ለሌሎችም በአርዓያነት የሚታይ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡

የአሥራ ስምንተኛ ክፍለ ጦር መረዳጃ ዕድር ሰብሳቢ ሻለቃ ግርማ ገረሱ፣ ለንባብ የበቃው ይህ መጽሐፍ ለወታደራዊ ታሪክ፣ ለምርምርና ለጥናት በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢሕዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢሠፓ ፖሊት ቢሮ ተለዋጭ አባል የነበሩት አቶ ፋሲካ ሲደልል በሰጡት አስተያየትም፣ ‹‹መጽሐፉ የ18ኛ የተራራ ክፍለ ጦር ተጋድሎን በዝርዝር ያብራራል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ይህ የአንድ ክፍለ ጦር ተጋድሎ ብቻ ነው፡፡ ልክ እንደዚሁ ክፍለ ጦር 500 ሺሕ የሚደርስ ጦር ለሕይወቱ ሳይሳሳ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጓል፡፡ ጥያቄው ግን ለምንድነው ለዚህ ሁሉ ተጋድሎ ያበቃን? እንዴትስ ነው ያንን ሁሉ ትልቅ ክብርና ዓላማን ይዘን በጠላት ልንሸነፍ የቻልነው? የሚል ነው፤›› ብለዋል፡፡

በሥልጣን ላይ በነበሩበት ዘመን እሳቸውና አብሯቸው የነበሩ ባለሥልጣናት ሁሉ በአንድ ጉዳይ ላይ እርስ በርሳቸው እንደማይስማሙና ይነታረኩም እንደነበር ገልጸው፣ በዚህም የአመራር ጉድለት እንደነበረባቸውና ኢትዮጵያ ዛሬ ለተጫናት የተለያዩ ችግሮች ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ አስረድተዋል፡፡

የክፍለ ጦሩ ዋና አዛዥ የነበሩትና የዕድሩ የበላይ ጠባቂ ሜጀር ጄኔራል መርዳሳ ሌሊሳ መጽሐፉ ታትሞ ለንባብ መብቃቱ እንዳስደሰታቸው፣ በዚህም ዙሪያ ሳይታክቱ የሠሩትን ወገኖች ሁሉ አመስግነው፣ መታረም ይገባቸዋል ያሏቸውን አንዳንድ ነጥቦች በመዘርዘር እንዲስተካከሉ አሳስበዋል፡፡

በመጽሐፉ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የክፍለ ጦሩ የቀድሞ አባላትና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም የቀድሞው ሠራዊት ከፍተኛ ጄኔራል መኮንኖች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...