Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እረኛና መንጋው!

ከአያት ወደ መገናኛ ልንጓዝ ነው። አንድ ገብስማ ጎልማሳ ታክሲ ጥበቃ የተሠለፍንበት ቦታ  እየተጎንራደደ፣ ‹‹በደርግ ጊዜ ያነበብኩት መጽሐፍ ላይ ‹ኑሮ ዜማቸው በተበላሸ እንጉርጉሮዎች ሲበደል አይ ነበር› ያለው ገጸ ባህሪ እኔን ይመስለኝ ነበር…›› እያለ በምፀት ሲናገር፣ ‹‹ምነው ብልፅግና ማንበብ የከለከለ ይመስል አንድ ዓረፍተ ነገር ለማስታወስ ደርግ ዘንድ ሄድክሳ?›› ብላ አንዲት ቀናነት የወረሰው ፈፈግታ የተላበሰች ዘመናይ ጠየቀችው። ‹‹ማንበብማ በፊት ቀረ፣ አሁን እኮ ንባብ እርሙ የሆነ ትውልድ ነው በቅጡ አላስኖር ያለን…›› አላት። የጠባቂዎች ቁጥር እየጨመረ ቢሆንም ታክሲ ደብዛው የለም። ‹‹ደግሞ በየት አገር ነው የማያነብ አላስኖር አለ የሚባለው? የእናንተ ትውልድ መስሎኝ ለዚህ ሁሉ መከራና ሥቃይ የዳረገን…›› የሚሉት ዕድሜና ኑሮ ተባብረው ያጎበጧቸው አዛውንት የዚያን ትውልድ አባላት አንድ ላይ ደርበው ሲናገሩ፣ ‹‹አይ አባታችን ያ ትውልድ እኮ አፈጻጻም ላይ በመሳሳቱ ቢተችም፣ ለአገር ዕድገትና መለወጥ ሲል ነው ውድ ሕይወቱን የገበረው…›› ጎልማሳው ከትውስታው እየታገለ ሲመልስላቸው፣ ‹‹ይኼንንም ያነበብከው  በደርግ ጊዜ እንዳይሆን ብቻ?›› ብሎ አንድ ጎረምሳ ሲያላግጥ ቅሬታ ያዘለ ዝምታ ለጊዜውም ቢሆን ሰፈነ፡፡ ሳይሻል አይቀርም!

የታክሲው ነገር አላዋጣ ሲል ብዙዎች ሠልፉን ትተው ባቡር ለመሳፈር ሄዱ፡፡ ከስንት ጥበቃ በኋላ ከመሬቱ ይልቅ ሐዲዱን አምነን ባቡር ላይ ወጥተናል። ‹‹አይ ባቡር፣ ባቡር ብሎ ዝም፡፡ ጥንት ማንም ሳያውቀው እያወቅነው ዛሬ እንደ አዲስ ከች ሲል ግን ሰው አይደነግጥም?›› ይላል አንዱ በስላቅ ይሁን በቁምነገር።  ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን መደንገጥ አልፈጠረብንም፣ ደንግጠን ምን ለመፍጠር?›› አለው ምኑም ያልገባው ችኩል። ‹‹ሰው ሲደነግጥ ምን ይሆናል? ወይም የሚሄድበት ሥፍራ ትልቅነት፣ ግርማዊነት ሲያስፈራው ምን ያደርጋል? ቀላል እኮ ነው፣ የግል ንፅህናውን ይጠብቃል። አይደለም? የክት የሚላትን ይለብሳል። በተቻለው አቅም ዓይን ለመሙላት ይጥራል…›› ሲል አቅጣጫውን መለየት ያቃተን የጫማ ሽታ የወሬው መነሻ እንደሆነ የገባን ተጠቃቀስን። ‹‹ጉድ በል የአገሬ ሰው። የእኛ ሰው ለክብሩ ሟች፣ ለአገሩ ሟች፣ ለትዳሩና ለልጆቹ ሟች ነበር የሚባለው፣ የዛሬን አያድርገውና፡፡ ይኼው ሙት ይዞ ይዞራል…›› ሲል ሌላው ፈገግ አሰኘን። ተጀመረ ማለት አሁን ነው!

ምፀቱ የከነከነው አንድ ጎልማሳ፣ ‹‹ልብስ አምሮ ጭንቅላት ቢቆሽሽ ምን ዋጋ አለው? ሥጋ ደልቦ መንፈስ ቢቀጭጭስ? በዚህ ዘመን ያስቸገረን ከላይ እያማረ ውስጡ የቆሻሻ የአስተሳሰብና የልብ ጥመት ነው…›› እያለ አንዱን ቡድን ለሁለት ከፈለው። ‹‹እውነት ነው…›› ሲል የወዲኛው የወዲህኛው ደግሞ፣ ‹‹ሰው ባለው ነው፣ እስኪ መጀመሪያ በትንሹ እንታመን። መጀመሪያ ከግል ንፅህና እንጀምር። ከዚያ ወደ ልብ እንሄዳለን…›› እያለ ተቃወመ። ይኼን ጊዜ አዛውንቱ፣ ‹‹የደላችሁ ናችሁ እናንተ…›› ብለው ዘው አሉ። ‹‹ማ?›› አለ በአንድነት ከሁለቱም ጎራ ዓይኑን እሳቸው ላይ ተክሎ። ‹‹ሁልሽም፣ ምን ታፈጫለሽ? ውኃ ሳይኖር ልብስ ይታጠባል? ጥበብ ደብዝዞ፣ አዋቂ በአላዋቂ ተረግጦ አዕምሮ ይለወጣል እንዴ? ወዶ መሰላችሁ የተዳፈነ የሚጨሰው? ከራስ ጉያ እሳት ሽሽት እንጂ…›› ብለው  ጀማውን ዝም አሰኙት። ዝም የሚያስብል ሰው እንዲህ ብርቅ ሆኗል ዘንድሮ? ነው ወይስ የዘመኑ ሰው እንደሚባለው ከላይ ከላይ ብቻ ሆኗል? ያሰኛል!  

መተፋፈጉ ያስመርራል። ምሬቱን መቋቋም ያልቻለ አንድ ወጣት፣ ‹‹ምንም ሳንሠራ እንዲህ ካላበን በሥራ ብንወጠር ምን ልንሆን ነው?›› እያለ ነገር ይጎነጉናል። ‹‹ምን ጥያቄ አለው ሌላ ግድብ መገደብ እንጀምራለን…›› ትለዋለች ሰበዝ የመሰለች ቀጭን ለግላጋ። ‹‹ውኃ እንጂ ላብ ይገደባል እንዴ?›› አሏት አዛውንቱ። ‹‹ለአገር ጠቃሚ ሆኖ እስከተገኘ ድረስ እንኳን ላቡ ሰውም ይገደባል…›› እያለች ፈገግ ስትል፣ ‹‹ለዚህ ነዋ እነ ፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ ቀበና እየፈረሱ ቅንጡ መንገዶች ለመገንባት ሰው የሚነቀለው…›› ብሎ አንዱ ከመጨረሻ መቀመጫ በከፍተኛ ድምፅ መናገር ሲጀምር፣ ‹‹ወንድም በሕግ አምላክ ብያለሁ፣ እዚህ ባቡር ውስጥ ፀረ ልማት ቅስቀሳ ጀምራለሁ ብለህ እኛንም ራስህንም ችግር ውስጥ እንዳትከት…›› ሲሉት፣ ‹‹አባቴ ዝም ይበሉት ይህንን ሱሰኛ፡፡ በእሱ ቤት እኮ ከተማዋ እሱ እንደሚቅምበት ሥርቻ ተጎሳቁላ እንድትቀጥል ነው ፍላጎቱ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ገራባውን የሚጥልበት ቆሻሻ መጣያ የመሰለች የሱሰኞችና የወሬኞች ከተማ ከሌለች የእሱና የቢጤዎቹ ደካማ መንፈስ መቀጠል አይችልም…›› ብላ ስትወረገረግ አንዷ ፀጥ እረጭ አልን፡፡ ከባድ ነው!

 ‹‹እንዴት ያለ ነገር ነው እባካችሁ? በአገር ጉዳይ ሰከን ብለን መነጋገር አንችልም እንዴ?›› ብሎ ያ የአብዮቱ ዘመን ጎልማሳ ፀጥታውን ሲገፍ፣ ‹‹ለእዚህማ እንኳን ባቡሩ መሬቱም፣ ኮንዶሚኒየሙም፣ በየቦታው የሚዘራው ምንጩ የማይታወቅ ሀብት አልበቃንም…›› አሉት አዛውንቱ። ‹‹ምነው ይኼን የሚያህል ሰፊ የቆዳ ስፋት ያለው አገር ይዘን እንዴት ብሎ ነው መሬቱ የማይበቃን?›› ጎልማሳው ምፀቱን እያስቀጠለ ዝም አልል ብሏል። ‹‹እሱን ሂድና  የሚመለከታቸውን ጠይቅ…›› ብላ ጠይሟ ፋይሉን ዘጋችላቸው። ‹‹እግዚኦ ከላይ ፀሐይ ከሥር ንዳድ፣ መጨረሻችንን እሱ ይወቀው…›› እያሉ ሳለ አዛውንቱ አፈናቸውና ሦስቴ ካሳሉ በኋላ ዝም አሉ። ‹‹አስም አለብዎ?›› ብሎ አንዱ ቢጠይቃቸው፣ ‹‹ማን የሌለበት አለ? አፍኖ ይዞት እንጂ እንጂ አፋኝ በበዛበት ጊዜ ማን የሌለበት አለ?›› እያሉት ማባሪያ የሌለው ሳል ወጥሮ ያዛቸው። እሳቸው ትንፋሻቸው መለስ እስኪል ድረስ እኛም ከወሬያችን ታቅበን ጠበቅናቸው፡፡ የግድ ነው!

ጉዟችን ቀጥሏል። በሩን ታከው ሸብረክ ብለው የቆሙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዶርም ሲገቡ በሚያዩት ፊልም ምርጫ ተጣልተዋል። ‹‹ኦፐንሃይመርን ደጋግመን ሳናይ ፑር ቲንግስ ብሎ ፊልም አይታሰብም…›› ይላል አንደኛው። ‹‹ምነው አንተ ከእሱ ፊልም ጋር እንዲህ ችክ አልክ? የአቶሚክ ቦምብ ፈጠራን እያየህ የቭላድሚር ፑቲን የኑክሌር ጦርነት ማስጠንቀቂያ ሥጋት ፈጠረብህ እንዴ?›› ሌላኛው ይጠይቀዋል። ‹‹የት ነው የምትማሩት?››  አንድ በዕድሜ ጠና ያለ ተሳፋሪ ጠየቃቸው። ክርክራቸውን አቁመው፣ ‹አምስት ኪሎ› አሉት አንድ ላይ። ‹‹ለዚህ ነው እንዴ ሳይንሳዊ ፈጠራው ከኑክሌር ፊዚክስ ጋር ያገናኛችሁ?›› ሲላቸው አንደኛው በመገረም ስሜት፣ ‹‹ጋሼ ምናለበት እንደ እርስዎ የገባው ሰው በብዛት እዚህች አገር ቢኖር…›› እያለ ተቆጨ፡፡ ‹‹ትምህርታችሁን ትታችሁ ለምን ፊልም ታያላችሁ የሚለው የሚበዛው እኮ፣ የእኛ ትምህርትና የምናየው ፊልም ተቀራራቢነት ስላለው ስለማይገነዘብ ነው…›› ብሎ ሌላው ተማሪ ሲያብራራ አንገታችንን በአዎንታ ወዘወዝን፡፡ ልክ ነዋ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል።  ይኼን የሚያስተውል አብሮን አንገቱን የሚወዛወዝ ተሳፋሪ፣ ‹‹ያለፍንበት ተዋረዳዊ አሠራር ነው፣ ምንም ማድረግ ስለማይቻል መቻል ነው…›› ሲል ከጎኑ ያሉት ወይዘሮ፣ ‹‹ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ ማለት ይኼም አይደል፡፡ ልጆቹ ከምንማረው ነገር ጋር የሚገጥም ነው የምናየው ፊልም ሲሉን እኛ ስለማይገባን ይሁንላችሁ ነው ማለት ያለብን፡፡ ሁላችንም በወጣትነት ውስጥ አልፈናል፡፡ ነገር ግን ሁሉንም ነገር ለዘመኑ ሰው መተውን የመሰለ ነገር የለም…›› ሲሉ ሰማናቸው፡፡ ‹‹ኋለኛው ወደፊት ፊተኛው ወደኋላ ሆነ እኮ ነገረ ዓለሙ እናንተ…›› ለግላጋዋ ወጣት በለበጣ ሳቅ ታጅባ ነገር ታሸሙራለች። ‹‹እንደ ዘንድሮ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አንገት ለአንገት ትንቅንቅ ማለትሽ እንዳይሆን?›› ይላታል አንዱ ከንፈሩን በምላሱ እያበሰ። ‹‹አይ እኛ ካልጠፋ ማነፃፀሪያ ካልጠፋ ማያስተያያ ምሳሌያችን ሁሉ ኳስ ሆኖ ቀረ በቃ?›› የደርግ ዘመኑ ጎልማሳ ገባበት። ‹‹መለኪያ ጠፍቶ ሁሉ ተናጋሪ ሁሉ ነገር ተንታኝ ሲሆን፣ የሁሉም የሆነውን ከማውራት ሌላ ታዲያ ምን ታሪክ እንፍጠር?›› አለው ወጣቱ። ‹‹ታሪክ መተረኩን ትታችሁ እስኪ ታሪክ ሥሩ…›› አሉ አዛውንቱ ቆጣ ብለው። ‹‹ኦኦ እሱ እንኳን አያዋጣም አባት። ሌላው ነገር ብዙ ያነጋግረናል፣ ያውም አብዮቷ ባልተጠናቀቀባት አገር?›› ቆንጂት ተቃወመች። መላቀቅ የለም!

‹‹እንግዲያውስ የኋለኛው ወደፊት የፊተኛው ወደኋላ ከሆነ የዚህ ዓለም ነገር፣ ፊተኛው ወደኋላ ኋለኛው ወደፊት እንዲሆን ማድረግ ነዋ። ከመገለባበጥ በቀር የሰው ልጅ  ዕጣ ፈንታው ምንድነው?›› ሲሉ አዛውንቱ፣ ‹‹ደገሙት ልበል አባባሉን?›› ብትል ወጣቷ፣ ‹‹ያው ነው፣ የቦታ ለውጥ ነው ያደረግኩት። መቀያየር መድገም፣ መድገም መቃየያር ነው ያልሽው አንቺው ነሽ። ስለዚህ ወደኋላ ከሆንሽ ወደፊት ነይ። ከፊት ከሆንሽ ደግሞ ለኋለኞቹ ዕድል ስጪ…›› ብለው ትዝብት ሲጀምሩ፣ ‹‹ለመሆኑ ይኼ ባቡር ወደፊት ነው ወደኋላ የሚሄደው? ራሱና ጅራቱ ይምታታብኛል…›› በማለት ወይዘሮዋ ጠየቁ። ‹‹እሱ እንደ መንገዱ ነው…›› ሲላቸው አጠገባቸው ቆሞ ቲክቶክ የሚጎረጉር ወጣት፣ ‹‹ካልሆነ ራስ እንጂ ጅራት የማያደርገንን መንገድ እንፈልግ እንዴ?›› ብለው ከመቀመጫቸው ተነሱ። መገናኛ ወራጆች ተጠራርገን ከባቡሩ ላይ ወረድን። አዛውንቱ፣ ‹‹እረኛና መንጋው ያልተግባቡበት ምን ዓይነት ዘመን ነው?›› እያሉ ሲያጉተመትሙ ዝም ብሎ ከማዳመጥ ውጪ መልስ የሰጠ አልነበረም፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት