Saturday, April 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለፀፀትና ለቁጭት የሚዳርጉ ድርጊቶች ይታሰብባቸው!

‹‹ምከረው ምከረው እንቢ ካለ መከራ ይምከረው›› የሚለው አገራዊው ዕድሜ ጠገብ ምሳሌያዊ አባባል፣ በግለሰብም ሆነ በአገር ደረጃ በሚፈጸም ስህተት ወይም ደንታ ቢስነት ሊከሰት የሚችለውን ጣጣ ቀድሞ ማመላከቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከሚታወቁበት ምሳሌያዊ አነጋገር አንዱ፣ ‹‹የውድቀት ጥሪ የቀረበው የአዋቂ ምክር አይሰማም›› የሚለው ይጠቀሳል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ባህሉና የአኗኗር ዘይቤው ይለያይ ይሆን እንጂ፣ ምክር ለማይሰሙ ሰዎች የሚነገሩ በርካታ ምሳሌያዊ አነጋገሮች አሉ፡፡ አገር በቀል የሆኑት ምሳሌያዊ አነጋገሮች የሕዝቡን ዘመን ተሻጋሪ የጋራ ማኅበራዊ እሴቶችና መስተጋብሮች ከማንፀባረቃቸው ባሻገር፣ ለአገር ሰላምና ደኅንነት የሚጠቅሙ ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ምክሮችና ማሳሰቢያዎች በውስጣቸው ያጨቁ ናቸው፡፡ እነዚህ ምክሮችና ማሳሰቢያዎች ችግር አጋጥሞ በአገርና በሕዝብ ላይ መከራ ከመድረሱ በፊት፣ እንደ ቅድመ ማስጠንቀቂያ የሚያገለግሉ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገሩ እዚህ ዘመን የደረሱ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ካለፉት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኝነት በመጥፋቱ በርካታ ወርቃማ ዕድሎች ማምለጣቸው ብዙ ጊዜ ተወስቷል፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት በየካቲት 1966 ዓ.ም. አብዮት ከመገርሰሱ ዓመታት በፊት፣ የአገር ጉዳይ ያሳሰባቸው ወገኖች ሥርዓቱ ማሻሻያ እንዲያደርግ በተደጋጋሚ ማሳሰባቸው ይነገራል፡፡ ፍፁም ፈላጭ ቆራጭ የሆነው ዘውዳዊ ሥርዓት ወደ ሕገ መንግሥታዊ ዘውድ ተለውጦ፣ የአገሪቱ መንግሥት ለፓርላማ ተጠሪ በሆነ ጠቅላይ ሚኒስትርና ካቢኔ እንዲመራ ልመና ቀርቦ እንደነበር በቁጭት ሲነገር ይደመጣል፡፡ በአገሪቱ የተንሰራፋው የፊውዳል ሥርዓት የመሬት ሥሪቱ ተስተካክሎ ዜጎች ከገባርነት እንዲወጡ የቀረበው ተደጋጋሚ የመሬት ለአራሹ ጥያቄ ምላሽ በማጣቱ፣ ለአብዮቱ መፈንዳትና ለሥርዓቱ መንኮታኮት ምክንያት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ አብዮቱ ሥር ነቀል የለውጥ ጉዞ ውስጥ ገብቶ ለአገር የሚበጁ መልካም የልማት ጅምሮች መቀጨታቸው ይታወሳል፡፡

በአብዮቱ ጠንሳሾችና ተዋንያን የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ፈሩን እንዲስት በመደረጉ፣ ለሕዝባዊ መንግሥት ምሥረታ የተጀመረው እንቅስቃሴ በወታደራዊ ደርግ ተጠለፈ፡፡ ‹‹ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ተቅደም›› የሚለው መሪ መፈክር ተገልብጦ በኢትዮጵያ ምድር ደም እንደ ጎርፍ ፈሰሰ፡፡ በተለይ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ከዙፋናቸው እንዲነሱ ከተደረገ በኋላ፣ ሁሉም ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመታገዳቸው አብዮተኞች ጎራ ለይተው የሚጨራረሱበት የዕልቂት ድግስ ውስጥ ተገባ፡፡ ደርግ የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመሰብሰብና የመደራጀት መብቶችን በይፋ ከመከልከሉም በላይ ማሰብ ጭምር አይቻልም በማለቱ ቅራኔው በአንዴ ጣሪያ ነካ፡፡ ከደርግ ጋር ያበሩት በአንድ ጎራ ሲሠለፉ፣ ተቃውሞ የጀመሩ ደግሞ ግማሹ ወደ በረሃ የተቀሩት የከተማ የትጥቅ ትግል ውስጥ ገቡ፡፡ አገርን ይታደጋል የተባለው አብዮት የእርስ በርስ ፍጅት አስከተለ፡፡

የደርግ ዘመን አብቅቶ በረኸኞች አገር ሲቆጣጠሩ የኢትዮጵያን ገጽታ የሚቀይር አዲስ ክስተት ተፈጠረ፡፡ ይህ ክስተት ኤርትራን ከእናት አገሯ ኢትዮጵያ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የለያየ ነው፡፡ በፊት የነበረው የመደብ ትግል ወደ ብሔር ትግል ተለውጦ አዲስ የፖለቲካ ዓውድ ተፈጠረ፡፡ በኢሕአዴግ መሪነት ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. ተዘጋጅቶ የፀደቀው ሕገ መንግሥት፣ ለኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓትን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀ ሰነድ ነበር፡፡ ሕገ መንግሥቱ ፀድቆ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት ገና በረቂቅ እያለ ለቅራኔ በር ከፈተ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከመግቢያው ጀምሮ ‹‹ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች›› የሚል ጽንሰ ሐሳብ ማስተዋወቁ አንደኛው ነው፡፡ ሌላው አንቀጽ 39 ክልሎች በፈለጉ ጊዜ መገንጠል የሚችሉበት ድንጋጌ መያዙ ነው፡፡ እንዲሁም የመሬት ባለቤትነትን በተመለከተ የሠፈረው ድንጋጌ ይገኝበታል፡፡

ከላይ ከተጠቀሱትና ከሌሎች ድንጋጌዎች ጋር ተያይዞ የፌዴራል ሥርዓቱ ብሔርን ብቻ መሠረት አድርጎ መዋቀሩ ቅራኔውን እያጦዘ፣ ከነፃነትና ከመብት ጋር የሚነሱ ጥያቄዎች እየተበራከቱ ሄዱ፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶችና ሌሎችም ለእስርና ለስደት ተዳረጉ፡፡ በወቅቱ በነበረው መንግሥትና በሕዝብ መካከል የነበረው ግንኙነት እየሻከረ፣ ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር ለማድረግ ያዳገታቸው የትጥቅ ትግል ጀምረው፣ በራሱ በኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች መካከል ነበረ የሚባለው አንድነት ላልቶና በአጠቃላይ አገር የሚመራበት ቁመና አጥቶ በሕዝባዊ ማዕበል ተገፈተረ፡፡ ምንም እንኳ ከውጭ ያለው የተቃውሞ ግለት ከበድ ያለ ግፊት ቢፈጥርም፣ በውስጡ የነበሩ የለውጥ ኃይሎች በመናበብ ባደረጉት ሥልታዊ ትግል አስፈሪ የነበረው ኢሕአዴግ ከመንበሩ ላይ ተሸኘ፡፡

ከውስጥም ከውጭም የነበረው የለውጥ ኃይል ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መግባባት ቢፈጥርም፣ የነበረው ቆይታ ግን በጣም አጭር ነበር፡፡ መስከረም 5 ቀን 2011 ዓ.ም. በቡራዩ በንፁኃን ላይ ከተፈጸመው ጭፍጨፋ ጀምሮ እስከ ቅርቡ የአማራ ክልል ጦርነት መጀመር ድረስ፣ በለውጡ ባቡር ላይ ተሳፍረው የነበሩ በርካቶች በየፌርማታው ተንጠባጥበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በበዓለ ሲመታቸው በፓርላማ ባደረጉት ያልተጠበቀ ንግግር ከተማረኩት፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መካከል ብዙዎቹ ዛሬ በተለያዩ ጎራዎች ውስጥ ተሠልፈዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማት፣ ዕድገትና ዘለቄታዊ ህልውና በጋራ መቆም የሚገባቸው ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ምክንያቶች ተከፋፍለው እንደ ጠላት እየተያዩ ነው፡፡ ይህንን አደገኛ ሁኔታ በቅርብም ሆነ በሩቅ የሚታዘቡ ታሪካዊ ጠላቶች አጋጣሚውን እንደሚጠቀሙበት አይጠረጠርም፡፡ ሕዝብና አገርን ማዕከል አድርጎ ለተፈጠሩ ችግሮች ሰላማዊ ንግግርና ድርድር ማስቀደም አቅቶ ችግሩ እየከፋ ነው፡፡

ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ በአጋጣሚ አግኝታ የመከኑባቸውን ወርቃማ ዕድሎች በተመለከተ፣ በተለያዩ መስኮች አገራቸውን ያገለገሉ አንጋፋ ዜጎች አሉ የሚባሉ ምክንያቶችን ዘርዝረዋል፡፡ የብዙዎቹ ማሳረጊያ ግን ተመሳሳይ ነው፡፡ በኢትዮጵያውያን መካከል ለአፍታ ሰከን ብሎ ለመነጋገር የሚያስችል መድረክ መፍጠር አለመቻል የሚለው አንደኛው ሲሆን፣ ሌላው የተመቸው ሁሉ ጊዜ ባገኘ ቁጥር ጉልበተኛ መሆኑ ነው፡፡ ካለፉት ስህተቶችና ውድቀቶች ተምሮ ለመጪው ትውልድ ያማረችና ያሸበረቀች አገር ከማስተላለፍ ይልቅ፣ ከሥልጣንና ከጥቅም ተጋሪዎች ጋር በማበር ጊዜያዊ እርካታ ላይ ማተኮር ከባድ ዋጋ አስከፍሏል፣ አሁንም እያስከፈለ ነው፡፡ አገር በቀል ዘመን ተሻጋሪ ምሳሌዎችን እያስታወሱ ካለፉት ስህተቶችና ወድቀቶች ጠቃሚ ነገሮችን በመቅሰም፣ በታሪክ የሚያኮራ ሥራ ለማከናወን ፈቃደኝነት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ለፀፀትና ለቁጭት የሚዳርጉ ድርጊቶች ይታሰብባቸው!    

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...