Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ዜጎች ሳይፈናቀሉ የልማት ሥራዎችን ማከናወን የሚቻልባቸው በጣም በርካታ አማራጮች አሉ›› እንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር)፣ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ

ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ሆነው መሾቸው ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 24ኛ መደበኛ ስብሰባ ስምንት አባላት ያሉት ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ ተቋቁሞ ምርጫው ሲካሄድ ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ የሆነ፣ በሥነ ምግባሩ መልካም ስም ያተረፈና የወንጀል ጥፋት የሌለበት በሚሉ መሥፈርቶች ዕጩ ሆነው ከቀረቡት 77 ሰዎች መካከል በሙሉ የምክር ቤቱ ድምፅ ነበር የተመረጡት። በግል ተቋማት ላይ ስለሚቀርቡ አቤቱታዎች፣ ስለሙስና፣ የሽግግር ፍትሕ፣ ስለጦር ወንጀሎችና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ የአገራዊ ተቋማት ሚናና ሌሎችም በርካታ ሐሳቦችን ያነሱበት ናርዶስ ዮሴፍ ከዋና ዕንባ ጠባቂው እንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር) ጋር ያደረገችው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል።

ሪፖርተር፦ የዕንባ ጠባቂ ተቋም በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን የአስተዳደር በደሎችን በራስ ተነሳሽነት ሥልታዊ ምርመራ የማካሄድ ሥልጣን አለው። በዚህ ረገድ ያላችሁን አፈጻጸም ቢያስረዱን? በምን ዓይነት ሁኔታ የራስ ተነሳሽነት ምርመራዎች ታካሂዳላችሁ? ሥልታዊ ምርመራ የሚባለውስ ምን ምንን ያካትታል?

እንዳለ (ዶ/ር)ኃላፊነታችን ምርመራ ማካሄድን ያካትታል። ምርመራ ማካሄድ ሦስት ዓይነት አሠራሮች አሉት። የመጀመሪያው በመንግሥት ተቋማት አሁን ደግሞ የግል ተቋማትን ጨምሮ የአስተዳደር በደል ደርሶብኛል ብሎ ወደ ተቋሙ መጥቶ አመልክቶ ወይም በሌሎች አማራጮች በኢሜይል፣ በነፃ የስልክ ጥሪ፣ አልያም በሦስተኛ ወገንም ሊሆን ይችላል የቀረበ አቤቱታ ወስደን ምርመራ እናካሂዳለን። ሌላው በራስ ተነሳሽነት ምርመራ የሚባለው የመልካም አስተዳደር ችግር የሚበዛባቸው ወይም ጫጫታ ያለባቸው ጉዳዮች ላይ የራስ ተነሳሽነት ምርመራ እናካሂዳለን። አሁን ለምሳሌ  ከፓስፖርት ጋር ተያይዞ ያለ ችግር በተለያዩ ሚዲያዎች እንደሚሰማው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግሮችን በዚህ ሥር ይታያሉ። በአዲስ አበባ ከተማ ከመኖሪያ ቤት ተያይዞ፣ ከዚህ በፊትም ሸገር ከተማ ውስጥ ከዚህ ከመፈናቀል ጉዳይ ጋር የሚገናኙ መሰል ጉዳዮችን ከሚዲያው ወይም ከኅብረተሰቡ የምናገኘውን መረጃ መሠረት አድርገን የራስ ተነሳሽነት ምርመራ አካሂደናል፣ እናካሂዳለን። ሌላው ሥልታዊ ወይም (systematic) ምርመራ የሚባለው አንዳንድ ምርመራዎች ሊሆኑ ይችላሉ፣ አዋጆች ሊሆኑ ይችላሉ፣ ተቋማት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሰውን ጥቅም ይጎዳሉ ተብሎ ሲታሰብ የዚያ ዓይነት ሥልታዊ ምርመራ እናደርጋለን። ለምሳሌ ከዚህ በፊት እንደሚታወሰው ገቢዎችና ጉምሩክ አንድ ላይ በነበሩበት ወቅት በተቋሙ ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች በሙስና ጠርጥሬያቸዋለሁ ካለ፣ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ያለ ምንም ሒደት የተጠረጠረውን ግለሰብ የመሰማት መብት በሚገድብ መንገድ ዕርምጃ የሚወሰድበት ሁኔታ ነበር። እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች በሚኖሩበት ጊዜ በሥልታዊ መንገድ ምርመራ እናካሂዳለን። አጠቃላይ አሠራሩ ምን ይመስላል? የዜጎችን መብት በመጣስና ባለመጣስ መካከል ሕጎቹና መመሪያዎቹ ምንድናቸው? የሚለውን መሠረት አድርገን ምርመራ የምናካሂድበት የማጣራት ሒደት ነው።

ሪፖርተር፦ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የተሻሻለው አዲስ ማቋቋሚያ አዋጅ በግል ተቋማት ላይ የሚቀርብ ቅሬታ እርስዎም እንደጠቀሱት መቀበል እንደሚችል ይገልጻል። እርስዎ ደግሞ በአንድ ወቅት እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ ቅሬታዎች በግል ተቋማት ላይ የሚቀርቡ ናቸው ብለዋል። በግል ተቋማት ላይ እስካሁን ምን ያህል ቅሬታዎች  ቀርበዋል?

እንዳለ (ዶ/ር)እንደተባለው አዋጁ ከመሻሻሉ ከወራት በፊት በየዓመቱ በአማካይ ወደ ስድስት ሺሕ አቤቱታዎችን እንቀበላለን። ስድስት ሺሕ ስል ከ40 እስከ 50 ሺሕ ዜጎችን የሚይዙ ጉዳዮች ናቸው የሚቀርቡት። ከእነዚህ ውስጥ ሦስት ሺሕ አካባቢ በተቋሙ ሥልጣን ሥር የማይወድቁ ነበሩ። ከሦስት ሺሕ ውስጥ ደግሞ አብዛኛው ከግል ተቋማት የሚመጡ ጉዳዮች ስለነበሩ፣ ይኼ የዕንባ ጠባቂ ተቋምን አይመለከትም ወይም ከተቋሙ ሥልጣን ገደብ ውጪ ነው ብለን የምንመልሰው ነበር።

ሪፖርተር፦ አሁን በተሻሻለው አዋጅ የትኞቹ ዓይነት የግል ተቋማት ላይ ነው በብዛት አቤቱታ የሚቀርበው? ምን ዓይነት ይዘት ያላቸው አቤቱታዎች ይበዛሉ?

እንዳለ (ዶ/ር)በግል ተቋማት ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎች በብዛት ከሚታዩት ውስጥ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢ ከደመወዝ አከፋፈል ጋር ተያይዞ ቅሬታ ይነሳ ነበር። እንደ እውነታው ከሆነ አሁንም ያ ችግር አልተፈታም፡፡ ዝቅተኛው የደመወዝ ወለል ተወስኖ አልተቀመጠም። ማለትም አንድ ተቋም አንድን ሰው በሚቀጥርበት ወቅት በሲቪል ሰርቪሱ ሥርዓት ዝቅተኛ ተብሎ የተቀመጠ መጠኑ የተወሰነ የደመወዝ መነሻ (threshold) ተቀምጦለታል፣ አለ። በግል ተቋማት የዚህ ዓይነት አሠራር የለም። አሁን የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ፣ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) በየጊዜው ከሚያነሱት እኛም ተግባራዊ እንዲደረግ የሚደግፍ ሐሳባችንን ከምንገልጽበት ጉዳዮች አንዱ ይህ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በኢንዱስትሪ ፓርኮች በርካታ የማስፈጸም ክፍተቶች ይፈጠራሉ። በሌሎችም የግል ተቋማት አካባቢ በሴቶች ላይ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጫናዎችና ትንኮሳዎች አልፎም ጥቃት የሚደርስበት ሁኔታ አለ። ኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢ ሰፋ ያሉ ችግሮች አሉ። ከዚህ ቀጥሎ ተመሳሳይነት ባለው ደረጃ የአበባ እርሻዎች አሉ፡፡ በእርግጥ አሁን አሁን እየጠፉና እየቀነሱ ነው ያሉት። ነገር ግን ከእነሱ አካባቢ የሚመጡ አቤቱታዎች ነበሩ። ሌሎች ደግሞ ፋብሪካዎች አካባቢ እጅግ በጣም በሚያሳዝንና በሚሰቀጥጥ ሁኔታ እጃቸው ተቆርጦ ወይም ቋሚ የሚባለው የአካል ጉዳት ደርሶባቸው፣ ከአሥር ሺሕ እስከ 11 ሺሕ ብር ድረስ ብቻ ተከፍሏቸው እንዲሸኙ የሚደረግበት ሁኔታ ነው ያለው። ያለ በቂ ሕክምና፣ ያለ በቂ ካሳ የተሰናበቱ ሠራተኞች አሉ፡፡ ከፋብሪካዎች አካባቢ የሚመጡ እነዚህን መሰል የአቤቱታ ጉዳዮች ነበሩ። ስለዚህ እነዚህን መሠረት አድርገን ነው አዋጁ እንዲሻሻል ያደረግነው።

ሪፖርተር፦ በአሁኑ ወቅት በግል ተቋማት ከሚቀርቡ በዛ ያሉ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ለአብነት የሚጠቀሱ ይኖራሉ?

እንዳለ (ዶ/ር)አሁን እየደረሱን ያሉ የአቤቱታ ጉዳዮችን ስንመለከት የገንዘብ ሚኒስቴር ከግብር ነፃ እንዲያስገቡ ለድርጅቶች ፈቃድ ሰጥቶ የታክሲ ማኅበራት ተደራጅተው ነበር፡፡ እነዚያ ፈቃድ የተሰጣቸው ድርጅቶች እያሉ (እየደመደምኩ አይደለም ገና በሒደት ላይ ያለ ጉዳይ እንደሆነ ታሳቢ ይደረግልኝ)፣ ነገር ግን ግለሰቦች ከግብር ነፃ መኪኖችን እያስገቡና እየሸጡ ለማኅበራት ግን እየደረሰ አይደለም የሚል አቤቱታ 50 ያህል ከሚሆኑ ማኅበራት ክስ መጥቷል። ይህንን እያየን ነው ያለው። አሁን ባለው ሁኔታ ከእነሱ አካባቢ ቅሬታዎች አሉ። ሌላው ከሥራ ሲሰናበቱ በቂ ጥቅማ ጥቅም ካለመስጠት ጋር ተያይዞ የሚመጡ ቅሬታዎችም እንዲሁ በዛ ያሉ ናቸው።

ሪፖርተር፦ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አቤቱታ መቀበል፣ መመርመር፣ ውጤቱን የማሳወቅ ሥራዎች ቢኖሩትም የማስፈጸምና በሕግ ተጠያቂ የማድረግ አቅም ስለሌለው ጥርስ አልባ ተቋም ነው የሚሉ ቅሬታዎች ይቀርቡበታል። ተቋሙ የሚያቀርባቸው የመፍትሔ ሐሳቦች ወይም ደግሞ መወሰድ አለባቸው የሚላቸው ዕርምጃዎች መሬት ላይ ወርደው ተፈጻሚ አይሆኑም የሚባል ድምዳሜ ላይ እንዲደረስ ያደረገው ሁኔታ የተፈጠረው እንዴት ነው? ለምንድነው ይህ የሆነው ብለው ያስባሉ?

እንዳለ (ዶ/ር)እሱ የድሮ አባባል ነው፣ መናገር ካለብን በአኃዝ ነው፡፡ ከዚህ በፊት እንዲያ ይባላል፡፡ ግን አሁን ማንኛውንም ሰው ብትጠይቁ የዚህ ዓይነት መልስ ሊሰጥ ይችላል ብዬ አልገምትም፣ አልጠብቅምም። ምክንያቱም በአንዳንድ ጉዳዮች የተለያዩ ትንታኔ መስጠት የሚያስችሉ ነገሮች አሉ፡፡ ግን እንደ አጠቃላይ ሁሉንም መገንዘብና መረዳት እያለበት የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ወይም እንደ አጠቃላይ የዴሞክራሲ ተቋማት በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአገራችን ውስጥ የሕግ አስገዳጅነት ባህሪ የላቸውም፣ እንዲኖራቸውም አይጠበቅም። ይህ ለፍርድ ቤቶች የተሰጠ ሉዓላዊ ሥልጣን ነው። ስለዚህ ፍርድ ቤቶችን ተክተው እንዲሠሩ አይጠበቅም፣ አይፈለግም። ይህ ሲባል ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት በግልጽነትና በተጠያቂነት መሠረት መሥራት አለባቸው። ያንን መሠረት አድርገን ውሳኔዎችን እንሰጣለን። ውሳኔዎች ካልተሰጡ ደግሞ በልዩ ልዩ አግባቦች የማስፈጸም ሥራዎችን እንሠራለን። ያለፉት አራትና አምስት ዓመታት የአሠራር አዝማሚያን ካየነው፣ ከሰጠናቸው የመፍትሔ ሐሳቦች ውስጥ ተፈጻሚ የሚሆኑት እያደጉ መጥተዋል። አሁን የተሻለ የሚባለው በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ 80 በመቶ ነው፡፡ እነ ስዊድንና ካናዳ የሚያስፈጽሙት በዚህ ደረጃ ነው። የእኛ የ2015 ዓ.ም. በጀት ዓመት ካቀረብናቸው የመፍትሔ ሐሳቦች ውስጥ 83 በመቶ ተፈጽሟል። ይህ ትልቅ ስኬት ነው። ነገር ግን የተሰጣቸውን የመፍትሔ ሐሳቦች የማይፈጽሙ አካላት የሉም እያልኩ አይደለም፣ አሉ።

ሪፖርተር፡- በተቋሙ የቀረበላቸውን የመፍትሔ ሐሳብ በማያስፈጽሙ የግልም ሆነ የመንግሥት ተቋማት ላይ ምን ዓይነት ዕርምጃዎች መውሰድ ተችሏል?

እንዳለ (ዶ/ር)ተቋማትን በማስጠየቅ ረገድ የምንሄድባቸው ሦስት የአሠራር መንገዶች አሉ። አንደኛው በሚዲያ ማጋለጥ ነው፣ በተደጋጋሚ እየሠራነው ያለ ሥራ ነው። ሁለተኛ በዓቃቤ ሕግ ወይም አሁን ባለው በፍትሕ ሚኒስቴርና በፍትሕ ቢሮዎች በኩል ክስ እንዲመሠረት እናደርጋለን። ሦስተኛ በልዩ ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉዳያቸው እንዲታይ እንልካለን። ከዚህ በፊት አንዱ መሠረታዊ ችግር በልዩ ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምንልካቸው ያለ መፈጸም ችግሮች ነበሩ። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ራሳቸው ቋሚ ኮሚቴዎቹ የሰጠናቸውን ልዩ ሪፖርቶች መሠረት አድርገው፣ መረጃ ከእኛም አቤቱታ ከቀረበበት ተቋምም ሰብስበው እንዲፈጸም በማድረግ በኩል ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው ያሉት።

ሪፖርተር፦ ለዚህ እንደ ምሳሌ መጥቀስ የሚችሉት ጉዳይ አለ?

እንዳለ (ዶ/ር)አዎ፣ እንደ ምሳሌ የምክር ቤቱ የሕግና ፍትሕ ቋሚ ኮሚቴ የሰጠነውን የመፍትሔ ሐሳብ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ባለመፈጸሙ፣ የማይፈጽምበትን ምክንያት እንዲያሳውቅ በደብዳቤ ጠይቋል። አልፎም የጊዜ ገደብ አስቀምጦ እንዲፈጽም አድርጓል፣ ስለዚህ እዚህ አካባቢ መሻሻል አለ።

ሪፖርተር፦ በአሁኑ ጊዜ የፍትሕ አካላት ገለልተኝነት ጥያቄ ከብዙ አካላት እሮሮ ሲቀርብበት ይደመጣል። የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ቀደም ብለው እንደጠቀሱት ከፍትሕ ቢሮዎች ጋር ተባብሮ የሚሠራበት አሠራሮች ካሉት፣ ከእነዚህ ቢሮዎች ጋር ያላችሁ የተቀናጀ የዜጎችን ጥቅም የማስጠበቅ ሚና አፈጻጸም በምን ያህል ደረጃ የተሟላ ነው ማለት ይቻላል?

እንዳለ (ዶ/ር)መሠረታዊ ችግርና አሁንም ያልተፈታ ባለፈው ሳምንት የምክክር መድረክ ያካሄድንበት ዋነኛ ጉዳዮች አንዱ የፍትሕ ቢሮዎች ጉዳይ ነው። ክስ የሚመሠረተው በፍትሕ ቢሮዎች አማካይነት ነው። የፌዴራል ጉዳይ ከሆነ በፍትሕ ሚኒስቴር፣ ክልሎች ከሆኑ በፍትሕ ቢሮ፣ ዞንም በተመሳሳይ መዋቅሩ በሚወርድበት መንገድ ነው። እዚህ አካባቢ እያጋጠሙን ያሉ ተግዳሮቶች አሉ፡፡ የፍትሕ ቢሮዎችን በሰጠናቸው መዝገብ የመንግሥት አስፈጻሚ አካል የሚሾማቸውን ነው ክሰሱ የምንላቸው። ያ ማለት በመርህ ደረጃ ነፃና ገለልተኛ ናቸው። ነገር ግን ብዙዎች አካባቢዎች ላይ ተግዳሮቶች እየገጠሙን ነው። ስለዚህ ባሳለፍነው ሳምንት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ባሉበት፣ የሁሉም የፍትሕ ቢሮ ኃላፊዎች ወይም ተወካዮቻቸው በተገኙበት ከፍትሕ ሚኒስቴርም ተወካይ ተልኮ የምክክር መድረክ አካሂደናል። ፈተናው ያለው በአሁኑ ወቅት የፍትሕ ቢሮዎች አይከሱም፡፡ በዚህ ምክንያት የሰጠናቸውን የመፍትሔ ሐሳቦች ያለመፈጸም፣ ያ የመፈጸምና የአለመፈጸም ብቻ ሳይሆን የአስተዳደር በደል የደረሰበት አካል መፍትሔ እንዳያገኝ ስለሆነ እዚህ አካባቢ ያለው የሚታይ ችግር አለ።

ሪፖርተር፦ የዕንባ ጠባቂ ተቋም የተሻሻለው አዋጅ ሥልጣንና ተግባር በተዘረዘረበት አንቀጹ ሥር ተቋሙ የተሻለ የመንግሥት አስተዳደር ለማስገኘት፣ ነባር ሕጎች ወይም አሠራሮች ወይም መመርያዎች እንዲሻሻሉ፣ አዳዲስ ሕጎች እንዲወጡ፣ ወይም ፖሊሲዎች እንዲቀረፁ የማሳሰብ ኃላፊነት እንደተጣለበት ድንጋጌው ያመለክታል። የእርስዎ ተቋም በዚህ ረገድ ያለው ተፅዕኖ ምን ያህል ደርሷል? እንዴት ነው እየሠራችሁ ያላችሁት?

እንዳለ (ዶ/ር)በግልጽ በአዋጁ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሚወጡ ሕጎችና አዋጆች ለዜጎች ከተሰጡ ሕገ መንግሥታዊ መብቶች አንፃር የሚጣጣሙ ናቸው አይደሉም የሚለውን ነገር የማየት ሥልጣን ተሰጥቶታል። ግን ይህንን የሚያይ የሥራ ክፍል ስላልነበረ ሠራተኞቻችን ቀደም ሲል እንዳልኩት ቁጥጥር ሲያደርጉና የምርመራ ሥራ ሲያከናውኑ እግረ መንገዳቸውን ነበር የሚታዘቡት። ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ አደረጃጀት ሠርተን ይህንን ጥናት የሚያካሂድ የሥራ ክፍል፣ ቁጥጥር የሚያካሂድ የሥራ ክፍል፣ አልፎም ሕጎችንም እያሰባሰበ ለዜጎች በሕገ መንግሥቱ ከተሰጡ መብቶች አንፃር ምን ሁኔታ ላይ ነው ያለው እውነታው የሚለውን ነገር እንዲያይ የሥራ ክፍል አደራጅተን ሥራዎችን እየሠራን ነው ያለነው። ከዚያ ውጪ ግን ምክር ቤቶች በሚያወጧቸው ሕጎች ላይ ተሳታፊ ነን፣ በቋሚነት እየተሳተፍን ነው። ምክር ቤቱም ይህንን አውቆ መደመጥ በሚገባቸው ጉዳዮች በሚቀርቡለት ወቅት ሕግ ከመፅደቁ በፊት እኛ ግብዓት እንድንሰጥ ይጠይቀናል። ባለሙያም ልከን እንድንተች ወይም ሐሳባችንን እንድንገልጽ እየተደረገ ነው ያለው።

ሪፖርተር፦ አሁን ብዙዎች ሪፖርት እንደሚያደርጉት በአገሪቱ በየቦታው ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ሙስና አለ። በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተቋቋመው ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ የመጀመሪያ ሪፖርቱን እንኳን ሳያቀርብ እስካሁን ፀጥ ብሎ ነው ያለው የሚሉ ትዝብቶችም አሉ። እንደ ዋና ዕንባ ጠባቂ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ የእርስዎ ዕይታ ምንድነው?

እንዳለ (ዶ/ር)ይህን ጥያቄ ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ብታቀርቡ የተሻለ ነው። ነገር ግን በመርህ ደረጃ የሙስና፣ የመልካም አስተዳደርና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እርስ በርሱ የተያያዘ (inter-related) ነው። አንድ ሰው ሙስናን የሚፈጽም ከሆነ ፍትሕ እያዛባ ነው። ፍትሕ ከተዛባ ደግሞ ጫፍ ላይ ሲወጣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው። ስለዚህ እነዚህ ሦስቱ የተጋመዱና የተያያዙ ሲሆኑ፣ እኛ የበለጠ በመልካም አስተዳደር ላይ አተኩረን እንሠራለን። ከሙስና ጋር የሚያያዙ ወይም ደግሞ ተጠርጣሪ ካለ ለፀረ ሙስና ኮሚሽን የምንልክበት ሁኔታ ነው ያለው። የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉዳይ ካለው ደግሞ ለሰብዓዊ መብቶች እንልካለን። በአጠቃላይ ግን አሁን እንደተባለው ኢትዮጵያ ውስጥ ሙስና ያን ያህል የተባለበት ደረጃ ላይ ደርሷል የሚል ግምገማ የለኝም፣ ዕይታ ነው። ጥናት ላይ የተመሠረተ ጉዳይ አይደለም። ግን ደግሞ በዕይታዬ ሙስና እንደ ተራ ጉዳይ እየተወሰደ ነው ያለው።

ሪፖርተር፦ በመላ አገሪቱ የሚፈናቀሉ ሰዎች ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እየመጣ መሆኑን ሪፖርቶች ያሳያሉ። በአዲስ አበባ ለልማት ተብለው ከተነሱ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ለሚዲያ የሚያሰሙ ብዙ አሉ፡፡ በቅርቡ እንደሚያስታውሱት እርስዎም ቀደም ብለው እንዳነሱት በሸገር ከተማ ቤታችን ፈረሰብን ተብሎ ቅሬታቸውን ያሰሙ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች ነበሩ። ዕንባ ጠባቂ ተቋም እንዲህ ዓይነት ቅሬታና አቤቱታዎችን ተቀብሎ ምን ዓይነት እንቅስቃሴዎች አድርጓል? ምን ያህል አቤቱታዎች መጥተውላችኋል? በእንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥስ ምን ዓይነት አሠራሮችን ነው የምትከተሉት?

እንዳለ (ዶ/ር)አሁን ባለው ሁኔታ ዘንድሮ ተናጠላዊ የሆኑ በግለሰብ ደረጃ የመጡ አቤቱታዎች እንጂ፣ በኅብረት ወይም በጋራ የመጡ አቤቱታዎች የሚታይ የለንም። ያው በሚዲያ እንሰማለን፣ በተለያዩ አካባቢዎችም ይታያል። ግን እስካሁን ባለው ሁኔታ በኅብረተሰብ ደረጃ ተደራጅቶ የመጣ አቤቱታ የለም። እንደ ግለሰብ የመጡ አሉ፣ እንደ ግለሰብ የመጡትን ግን እየመረመርን የመፍትሔ ሐሳብ እየሰጠን ነው ያለነው። ግን በአጠቃላይ መታወቅ ያለበት፣ ወይም እንደ መርህ መያዝ ያለበት መንግሥታት የየራሳቸው የተለያዩ ፍልስፍናዎች አሏቸው። በግሌ የማምነው ምንድነው? የሆነ ልማት ስታለሚ የሆነ ኅብረተሰብን ነው የምትጠቅሚው፡፡ የየትኛውም ልማት የመጨረሻ ግብ ዜጎችን መጥቀም ነው። ነገር ግን በአንድ ወገን ሕይወቱን የምንነካው የማኅበረሰብ ክፍል እየፈጠርን በሌላ በኩል ደግሞ ዜጎችን ለመጥቀም ነው የሚባለው፡፡ ሁለት እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ተግባራት ይዞ ልማት በሚከናወንበት ጊዜ ዜጎች በተቻለ መጠን የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ክፍል እንዲያመዝን ነው መሠራት ያለበት። ነገር ግን በአሁኑ የኢትዮጵያ ሁኔታ ነዋሪን ከቀዬው ስናነሳው የሚፈጠሩ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውሶች አሉ። ከቀዬአቸው ለሚፈናቀሉ አሁን ባለው የዋጋ ግሽበት የሚሰጠው ካሳ ያንን የወደመባቸውን ንብረት የሚተካ አይደለም።

ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን ታሳቢ አድርገው ሥራዎች ቢሠሩ የተሻለ ነው። ከዚያ የበለጠ ደግሞ ኅብረተሰቡ ሳይፈናቀል ባለበት ማልማት የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል። የእኛ አቅም ሁኔታ ካልሆነ ምናልባት በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ሲዘዋወር እንደታየው በቻይና ባቡር ሕንፃዎችን ሳያፈርስና በሕንፃዎች መካከል ሾልኮ ሲሄድ ታይቷል፡፡ አሁን የእኔ ቁምነገር ስለእዚህ ቴክኖሎጂ አይደለም፡፡ ያ የሚያመላክተው ምንድነው? ለዜጎቻቸው ምን ያህል ክብር እንደሚሰጡ ነው። እኔ የማየው እነሱ የደረሱበትን የቴክኖሎጂ ዕድገት አይደለም፡፡ እኔ የማየው ለዜጎቻቸው ምን ያህል ክብር ሰጥተው ከአንድ ሕንፃ አንድ ወለል ብቻ ለግንባታ ጥሰውና አስተካክለው የባቡር ሐዲድ የሠሩበትን እውነት ነው። ኅብረተሰቡ ሳይፈናቀል፣ ኅብረተሰቡ መንግሥት ላይ ቅሬታ ሳያቀርብና አቤቱታ ሳያሰማ የልማት ሥራዎች መሥራት ይቻላል ነው እምነቴ። ከዚያ በተረፈ ደግሞ በሚፈርስበት ጊዜ ደግሞ በቢሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ ወጪ እየተደረገ ነው። በኢኮኖሚያዊ ዕይታም አይጠቅመንም። በእርግጠኝነት ከሚፈርሰው በላይ አይገነባም፣ ከዋጋው አንፃር ሲታይ ማለት ነው። እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎችም ከግምት ውስጥ ቢገቡ የተሻለ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ዜጎች ሳይፈናቀሉ የልማት ሥራዎችን ማከናወን የሚቻልባቸው በጣም በርካታ አማራጮች አሉ። እነዚህን አማራጮች ማየት የሚቻልበት ሁኔታ ቢፈጠር መልካም ነው።

ሪፖርተር፦ የሽግግር ፍትሕ የዜጎች የተለያዩ አቤቱታዎች ከሚደመጡባቸው አማራጮች አንዱ ነው። ኢትዮጵያ በቅርቡ የተለያዩ የውስጥ ግጭቶች ላይ እንደ መቆየቷ መጠን አቤቱታዎቹም ያን ያህል ነው የሚስተዋሉት። እናም ከሽግግር ፍትሕ ጋር በተያያዘ የዕንባ ጠባቂ ተቋም ምን ሚና አለው?

እንዳለ (ዶ/ር) በተለያዩ መድረኮች እንሳተፋለን። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በሚያተኩሩ ውይይቶችም ላይ ተሳትፎ ነው የምናደርገው። ከዚያ ባለፈ ግን ወደ ትግበራ በሚገባበት ጊዜ ከተጎጂ ኅብረተሰብ ወገን ሆነን ልናቀርብ የምንችላቸው በርካታ መረጃዎች ይኖራሉ። በዚያ ረገድ ልንሳተፍ እንችላለን የሚል ሐሳብ ነው ያለን።

ሪፖርተር፦ የጦር ወንጀሎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በዓለም አቀፍ ሕጎች የሚታዩት ጎልተው ስለሆነ፣ አገራዊ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ ተቋማት በጠባብ ምኅዳር ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ከተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ ሲወጡ አይታይም ይባላል። አገራዊ ተቋማት በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸው የውይይት ድርሻና የሚጫወቱት ሚናም ውስን ሆኖ ይታያል የሚሉም አሉ።  በዚህ ላይ ምን ይላሉ? የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ለዜጎች መብት ተከራካሪ ሆኖ ችግሮችን ከመፍታት አኳያ፣ በተጨማሪም አገራዊ ተቋማትን እንዴት ነው ማሳተፍ የሚቻለው ይላሉ?

እንዳለ (ዶ/ር) አሁን አሳታፊ፣ ተሳትፎ፣ አካታችነት የመሳሰሉት የሚባሉ ጉዳዮች የዴሞክራሲ መገለጫ መሠረታዊ ባህሪ ናቸው። ትልልቅ ጉዳዮችን ብቻ ሳይሆን መንግሥት አሁን ለምሳሌ 2016 ዓ.ም. ላይ ሆኖ ለ2017 ዓ.ም. ስለሚያቅደውና ስለሚበጅተው በጀት ኅብረተሰቡን ማሳተፍ ይኖርበታል የሚል አጠቃላይ መርህ አለን። አሁን ሪፖርተር ያነሳቸው ጉዳዮች ትልልቅ አጀንዳዎች ናቸው። በእነዚህ ጉዳዮችም ላይ ቢሆን ኅብረተሰቡን ያላሳተፈ፣ ኅብረተሰቡን ያላካተተ ልማት ዘላቂ አይሆንም። የዘላቂ ልማት ግቦች ወይም (Sustainable Development Goals/SDG) እ.ኤ.አ የ2030 ዕቅዶች አንደኛው በየአገሮቹ የሚካሄዱ ልማቶች ኅብረተሰቡን ማሳተፍ አለባቸው ይላል፡፡ ያም ብቻ አይደለም ልዩ ትኩረት የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ያደረገ፣ ማለትም ሴቶችንና ወጣቶችን ታሳቢ ያላደረገ ልማት የትም ሊደርስ አይችልም የሚል አጠቃላይ መርህ አለ። በእዚያ ልክ እየተፈጸመ ነው ወይ? ሲባል ለምሳሌ አንድ ዜጋ በ2016 በጀት ዓመት ምን ዓይነት ሚና ነው የነበረው? አይታወቅም። ያ ማለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወካዮቻችን አሉ፣ ግን እነዚያ ተወካዮቻችን ብቻ አይደሉም ለአጠቃላይ ኅብረተሰቡ ለ2016 ዓ.ም. ከተመደበው በጀት ላይ ለትምህርት ይህን ያህል፣ ለግብርና ይህን ያህል፣ ለመከላከያ ይህን ያህል፣ ለእያንዳንዱ የተመደበው ይህን ያህል ነው የተመደበው የሚለውን ነገር ግልጽ አድርጎ የተለያየ ኅብረተሰብ መፍትሔ ሐሳብ እንዲሰጥ የሚደረግበት ሥርዓት የለም። ስለዚህ እኛ ተወካዮች ብለን የምናስበው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ በአስፈጻሚ አካሉ ተዘጋጅቶ በምክር ቤቱ ያልፋል፣ ከዚያም ይፀድቃል። እና ያ በምክር ቤቱ አልፎ ነው ተብሎ የሚታሰበው፣ ግን ለሕዝቡ ያ አይደለም። ሪፖርተር ቀደም ብሎ ያነሳቸው ሐሳቦች በጥልቀት ታይተው ሲመለሱ አይደለም የዴሞክራሲ ተቋማት ግለሰቦች ሊሳተፉበት የሚገባ ጉዳይ ነው መሆን ያለበት።

ሪፖርተር፦ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አሁን ቀዳሚም ተከታይም የሌለው፣ በዋናነት ያስፈልጋል የሚለው አንድ ነገር ምንድነው?

እንዳለ (ዶ/ር)ሰላም፣ ሰላም የሁሉም መሠረት ነው። ሰላም በሌለበት ሁኔታ ስለመልካም አስተዳደርና አልፎም ስለሰብዓዊ መብት ማሰብ እንደ ቅንጦት ነው የሚቆጠረው። ስለዚህ ሰላም በሌለበት ሁኔታ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸማል፣ የአስተዳደር በደሎች ይፈጸማሉ፣ ዜጎች ይፈናቀላሉ፣ ዜጎች አላስፈላጊ ዕርምጃ ይወሰድባቸዋል፣ ሕግና ሥርዓት የምንለው የሚፈርስበት ሁኔታ ነው ያለውና አሁን እያየን ያለነው ያንን ነው። ስለዚህ መንግሥት ተቀዳሚ ተግባሩ፣ ተቀዳሚ አጀንዳው ሊሆን የሚገባው ሰላምን የማምጣት ነው፡፡ ሰላምን የማስከበር ጉዳይ ነው መሆን ያለበት። ይህ በሌለበት ሁኔታ ኢትዮጵያን ከጫፍ ጫፍ ሊያገናኝ የሚችል የባቡር ሐዲድ ልትገነቢ ትችያለሽ፣ ያ ሰላም በሌለበት ሁኔታ ምንም ማለት አይደለም። ምክንያቱም ያ ሊፈርስ ይችላል። ሱዳኖችን በአሁን ወቅት እያየን ነው። መንግሥት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ለሰላም ነው። በቃ ጠዋትም ማታም ሰላም በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምን እንዴት አድርገን ማስጠበቅ አለብን የሚለው ነው መታሰብ ያለበት። ይህ ባለመሆኑ ብዙ ነገሮች እየተበላሹ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...