Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዘረፋና የተቀማጭ ገንዘብ ዋስትና ጅማሮ ግጥምጥሞሽ

በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ ባንኮች ለሚያሰባስቡት ተቀማጭ ገንዘብ ለመጀመርያ ጊዜ ዋስትና የሚሰጥ አገልግሎት በይፋ ሥራ መጀመሩ የተገለጸው መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ነበር፡፡ ይህም በእጅ ስልካችን ለገንዘብ አስቀማጮች በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ሥራውን በይፋ የጀመረ ሲሆን በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ተቀማጭ የተደረገ ገንዘብ ላይ ለሚያጋጥም ኪሣራ እስከ 100 ሺሕ ብር የኢንሹራንስ ሽፋን ይሰጣል›› በሚል የተገለጸ ነው፡፡ በዚሁ ዕለት ምሽት ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተዘረፈ ተባለ ይህንንም መረጃ በማግስቱ ሰማን፡፡

አስቀጮች ለሚያስቀምጡት ገንዘብ ዋስትና ማግኘታቸውን የሚያረጋግጠው መልካም ዜና በተሰማ በሰዓታት ልዩነት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስደንጋጭ የመዘረፍ ወሬ ግጥምጥሞሽ ምን ሊባል እንደሚችል ባላውቅም ትልቅ ትርጉም የሚሰጥ ነው፡፡ እስከዛሬ የአገራችን ባንኮች በሆነ ምክንያት ቢሰነካከሉ የአስቀማጮችን ገንዘብ ለመተካት በሕግ የተደገፈ አስተማማኝ ሕግና አሠራር ስላልነበር የአገልግሎቱ መጀመር ለባንክ ኢንዱስትሪው አዲስ ምዕራፍ መከፈቱን አመላክቷል፡፡

ምናልባት የመንግሥት ኃላፊነት የበዛ ነውና ባንኮች ተንኮታኩተው የሕዝብ ገንዘብ መመለስ እስኪያቅታቸው ድረስ ምን ትጠብቅ ነበር ተብሎ መጠየቁ አይቀርም፡፡ በዚህም መነሻነት ዜጎች በደራ ያስቀመጡትን ገንዘብ ሊመልስ ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ያን ያህል አቅም ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ አሁን ግን ይህንን ሥጋት የሚቀንስ ዕርምጃ ወስዷል፡፡ እስከ መቶ ሺሕ ብር ድረስ በየትኛውም ባንክ ተቀማጭ ያላቸው የባንክ ደንበኞች ገንዘባቸውን ማግኘት ይችላሉ፡፡ አንድ ባንክ በተለያዩ ምክንያቶች ከሥራ ውጪ ቢሆን ገንዘቡን መመለስ ባይችል የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ለአስቀማጮች የሰጠውን ዋስትና ተፈጻሚ ያደርጋል፡፡

የአስቀማጮች ገንዘብ በየዓመቱ እያደገ ከመምጣቱና ከወቅታዊ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አንፃር ባንኮች ባይወድቁ እንኳን እጅ ሊያጥራቸው የሚችልበት ዕድል ሰፊ በመሆኑ፣ በሕግ አስተማማኝ ዋስትና መፈጠሩ በእርግጥም ትልቅ ነገር ነው፡፡ ፈንዱ እስከዛሬ ያለመኖሩ የዘገየ ቢሆንም አሁንም አልረፈደም፡፡ እንደ ዕድል ሆኖ የኢትዮጵያ ባንኮች ኪሣራ ሳይጎበኛቸው የዘለቁ መሆኑ በጀ እንጂ በሌሎች አገሮች እንደሚሰማው ከሠሩና ተዘጉ ቢባሉ ማጠፊያው ያጥር እንደነበር መዘንጋት የለብንም፡፡ ለማንኛውም ይህ ጊዜውን የጠበቀ አሠራር በይፋ ስለመጀመሩ በእያንዳንዳችን የእጅ ስልክ ላይ መልዕክቱ በደረሰ ዕለት ምሽት ላይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ እንደተፈጠረው ዓይነት ስርቆት ተከስቶ ችግር ቢፈጠር ለአስቀማጮች የተሰጠው ዋስትና ባንኩንም አስቀማጩንም ይታደጋል እንደ ማለት ነው፡፡ ደግነቱ ባንኩ ላይ የደረሰው አሳዛኝ ስርቆት ከባንኩ አጠቃላይ አቅም አንፃር ጉዳቱ ኢምንት የሚባል መሆኑ እንጂ ጉዳቱ ቢኖር የተቀማጭ ገንዘብ ዋስትናው መፈጠር ጠቀሜታን ለመግለጽ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡

እንደ አገር እንደምልክት ከምናያቸው ተቋማት መካከል አንዱ በሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደረሰበት ጉዳት እንደተባለው የአስቀማጭ ደንበኞችን ጥቅም የማይነካ ቢሆንም፣ ቢነካ እንኳን ደንበኞች ገንዘባቸውን የሚያገኙበት መልካም ዕድል ያለ መሆኑ በተነገረበት በዚሁ ዕለት ባንኩ መመዝበሩ ግጥምጥሞሹ ማስገረሙ አይቀርም፡፡

ለማንኛውም በኢትዮጵያ ታሪክ ያልታየው ሌብነት ግን ከጉዳቱ ባለፈ በአስተማሪነቱም የሚጠቀስ ሆኖ መታየት አለበት፡፡ እያደገ ከመጣው የዲጂታል ባንኪንግ ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ ስህተቶች ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍሉ ትምህርት ሰጥቶን አልፏል፡፡ እየሰፋ ያለው ቴክኖሎጂ ቀመስ አገልግሎት ምን ያህል ጥንቃቄ የሚሻና ደኅንነት ላይ በብርቱ መሠራት እንደሚገባ ያመላከተም በመሆኑ መጣርና የወደፊት አቅጣጫና ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ሌብነቱ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተፈጸመ ነው መባሉን በተመለከተ ግን እንደ አገር አንገታችንን የሚያስደፋ ተግባር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በጉዳዩ ላይ ብዙ መሥራት የሚጠበቅብን መሆኑም መዘንጋት የለበትም፡፡ ንግድ ባንክ ከመሰረቁ በላይ አስደንጋጭ ሊሆን የሚገባውም አገርን በደቦ በግልጽ ለመስረቅ የሚደፍር ትውልድ ማጋጠሙ ነው፡፡ በዚህ ድርጊት ብዙኃኑ ተማሪ ባይሳተፍም ጥቂት የማይባሉት ግን እጃቸው አለበት መባሉ በራሱ የሚነገረን ነገር አለ፡፡

ስለሆነም የዲጂታል የባንክ አገልግሎት በአሁኑ ወቅት እየተስፋፋ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ባንኮች በጋራም ሆነ በተናጠል መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

የዘመናዊ አገልግሎት አንዱ መገለጫ ለሚሰጡ አገልግሎቶች ዋስትና መስጠትና ደንበኞች ሥጋት እንዳይገባቸው ማስቻል ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ግን ሳይገለጽ መታለፍ የሌለበት ነገር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የገጠመውን ክፍተት ተከትሎ የተካሄደው ሌብነት እንደ አገር ያለንበትን ሁኔታ ፍንትው ያደረገ መሆኑ ነው፡፡

ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የደረስንበትን ደረጃ የሚያሳብቀው ይህ ድርጊት በምን ሊጠገን እንደሚችል ባይታወቅም የማኅበራችን ትልቅ ስብራት ጥሩ ማሳያ ነው፡፡

እንዲህ ያለው ልምምድ በሌሎች ዘርፎች ስለመታየቱ የማያጠራጥር ቢሆንም ያለአግባብ መጠቀም፣ በአቋራጭ የመበልፀግና መሰል ብልሹ ምግባሮች ከምንም በላይ ለአገር ውድቀት መንስዔ መሆናቸውን አምኖ እዚህ ላይ ካልተሠራ ነገም ይባስ ነገር ሊገጥመን እንደሚችል ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ የነገ አገር ተረካቢዎች በሚባሉ ወጣቶች ደረሰ የተባለው ጉዳት ምንጭ ባልተገባ ሁኔታ ለመጠቀም ያለውን ፍላጎት ያሳየ ነው እንዴት እዚህ ደረጃ ላይ ደረስን ከተባለም በየትኛው መስክ ያሉ ብልሹ አሠራሮች ውጤት ስለመሆኑ ሊሸሽግ አይችልም፡፡

ተማሪዎቹ የማኅበረሰባችን ውጤቶች ናቸውና ሁሉንም ነገር እነርሱ ላይ ብቻ ለመደፍደፍ ላይቻል ይችላል፡፡ ነውር የሆኑ ድርጊቶችን እያዩ ማደጋቸውንም ሊያመላክት ይችላልና ሁሉም በየደረጃው ተጠያቂ መሆኑ አይቀርም፡፡

በመሆኑም ሰሞናዊው ድርጊት አስደንጋጭና አሳፋሪ በሚል ብቻ መታለፍ የለበትም፡፡ ምዝበራና ያለአግባብ ተጠቃሚነት የአገር ጉዳት ስለመሆኑ መገንዘብ ትውልድ እንዲፈጠር አንዱ ዕርምጃ ከሥር ጀምሮ ክፉና ደጉን ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ የትምህርት ሥርዓታችን ውስጥ ምግባርን የሚያንፀባርቅ ትምህርት በየትኛውም የትምህርት ደረጃ ደግሞ ማስተማርን ሁሉ ይጠይቃል፡፡ ትውልድን በመልካም አንፃር ትልቁ ኃላፊነት የወላጆች ነው፡፡ ራስን ይጠቅማል፣ ማኅበረሰቡን ያግዛል አገርም ያሳድጋል ብለው ወደ ዩኒቨርሲቲ የላኳቸው ልጆች በዚህ ደረጃ መገለጻቸው ለምን? ብለው ከጠየቁ ችግሩ እኛም ወላጆች ላይ መሆኑን እያስገነዘብን ይሆን? ስለዚህ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍልና መንግሥት ለማስተማር ይህን አጋጣሚ እንደ ጥሩ ዕድል መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ለዘለቄታውም ወጣቱ ትውልድ ብሔራዊ አገልግሎቱን የሚወጣበት አስገዳጅ ሕግ ማውጣትንም ሊጠይቅ ይችላልና ይህም ሊታሰብበት ይገባል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት