Wednesday, May 29, 2024

አከራካሪው የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

  • በኦሮሚያና በአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል የሚነሳ የፍትሐ ብሔር ክርክር በማን ይዳኛል?

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሚቀርቡለት የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄዎች ላይ የሕገ መንግሥት ክርክር (constitutional litigation) በሚያስነሱ ጉዳዮች ላይ፣ ዕውቀት ያላቸውን አካላት በመጋበዝ የመስማት ሒደት (Public Hearing) የማካሄድ ሥልጣን ተሰጥቶታል።

በዚሁ መሠረትም ጉባዔው ከኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀረበለትን አንድ አከራካሪ የሕግ መንግሥት ጉዳይ እየተመለከተ ይገኛል። የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለጉባዔው ያቀረበው አከራካሪ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጉዳይ፣ በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ከተማ በሚኖሩ ነዋሪዎች መካከል በሚነሱ የፍትሐ ብሔር ክርክሮች ላይ የኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች የሥረ ነገር ዳኝነት ሥልጣን አላቸው ወይስ የላቸውም? የሚል ሲሆን፣ በዚህም መሠረት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔው የቀረበውን ጉዳይ መርምሮ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት ተጠይቋል።

የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህንን አከራካሪ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ለጉባዔው ለማቅረብ ያስገደደው መነሻ ጉዳይ፣ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኝ አንድ መኖሪያ ቤት ላይ የውርስ መብት እንዲከበርላቸው የጠየቁ ሁለት በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ግለሰቦች የፍትሐ ብሔር ክርክር ነው። ጥያቄ የተነሳበት ቋሚ ንብረት በአሮሚያ ክልል የሚገኝ ቢሆንም፣ በንብረቱ ላይ የውርስ መብት ካነሱት ተከራካሪዎች መካከል አንዱ በኦሮሚያ ክልል ነዋሪ ሲሆኑ ሌላኛው ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ናቸው። 

ሁለቱም ግለሰቦች ጉዳያቸው በሚኖሩበት አከባቢ ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት መታየት አለበት የሚል አቋም በመያዝ፣ በኦሮሚያ ክልል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የጀመሩት ክርክር እልባት ሳያገኝ ይግባኝ እየተጠየቀበት በስተመጨረሻ ጉዳዩ ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርቧል። 

የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ቢሆን በተነሳው የዳኝነት ሥልጣን ክርክር ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ተቸግሯል። ምክንያቱ ደግሞ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ (ሸ) ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ ነው። በአንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ (ሸ) ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ፣ ‹‹መደበኛ ነዋሪነታቸው በክልሎች፣ በክልልና በአዲስ አበባ ከተማ፣ በክልልና በድሬዳዋ ከተማ፣ በአዲስ አበባ ወይም በድሬዳዋ ከተማ ውስጥ በሆኑ ሰዎች መካከል የሚነሱ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ላይ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣን ይኖራቸዋል›› የሚል ነው።

በዚህም ምክንያት የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ (ሸ) ድንጋጌ ሕጋዊነትን ላይ ጥያቄ በማንሳት፣ የፌዴራሉ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ መርምሮ ትርጉም እንዲሰጥበት ጠይቋል። 

የተነሳው ጥያቄ አከራካሪ መሆኑን የተረዳው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ፣ አከራካሪ ጉዳዮችን በሚያይበት ውስጣዊ አሰራሩ መሠረት ከጉባዔው ውጪ ያሉ የሕግ ባለሙያዎች ትንታኔና ምክረ ሐሳብ እንዲሰጥበት ወስኗል። በዚህም መሠረት በሕግ ጉዳይ ላይ የሚሠሩ የተመረጡ የፌዴራል መንግሥትና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ተቋማት በተጠቀሰው ጭብጥ ላይ ሙያዊ ትንታኔና ምክረ ሐሳብ እንዲያቀርቡ የጋበዘ ሲሆን፣ ተቋማቱም ጥያቄውን ተቀብለው ምክረ ሐሳብ የሚሰጡ ባለሙያዎቻቸውን ወክለዋል። 

ባለሙያዎቹ የሚያቀርቡት ሙያዊ ትንታኔና ምክረ ሐሳብ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እየተመለከተ ያለውን የፍትሐ ብሔር ክርክር ሥረ ነገር ወደ ጎን በመተው፣ በቀረበው የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ላይ ብቻ እንዲያጠነጥን የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አቅጣጫ አስቀምጦላቸዋል። በዚህም መሠረት ባለሙያዎቹ የፌዴራል መንግሥት ያወጣው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ (ሸ) ድንጋጌን ሕጋዊነት ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50 ንዑስ አንቀጽ ሁለትና ስምንት፣ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 78 ንዑስ አንቀጽ ሦስትና ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 52 ንዑስ አንቀጽ አንድ ድንጋጌዎች አንፃር በመመዘን ድምዳሜቻቸውን ማስቀመጥ ነው። በዚህ መሠረት የተጋበዙት የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል ተቋማት ባለሙያዎች የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም በተዘጋጀ ይፋዊ መድረክ ላይ ትንታኔና ምክረ ሐሳባቸውን አቅርበዋል።

ከኦሮሚያ ክልል ተቋማት የተወከሉት ባለሙያዎች ምክረ ሐሳብ 

አጣሪ ጉባዔው ምክረ ሐሳብ እንዲሰጡት ከኦሮሚያ ክልል ከጋበዛቸው ተቋማት መካከል የኦሮሚያ ክልል ስቴት ዩኒቨርሲቲ፣ የኦሮሚያ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት፣ በአሮሚያ ክልል የሚገኝ ኢንስቲትዩት ይገኙበታል።

የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የባለሙያዎች ቡድን ተወካዮች ባቀረቡት ትንታኔ ዳኝነት የተጠየቀበት ጉዳይን የማየት ሥልጣን የማን ነው? ዳኝነት የተጠየቀበት ጉዳይስ በየትኛው ሕግ ሊዳኝ ይገባል? የሚለውን መመለስ እንደሚያስፈልግና ጉዳዩን ከዚህ አንፃር ለመመዘን ደግሞ የግድ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች መፈተሽ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በዚሁ አግባብ ትንታኔያቸውን የቀጠሉት የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተወካዮች፣ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 50 ሥር በተቀመጡት ድንጋጌዎች መሠረት ክልሎች የራሻቸውን ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚና አስፈጻሚ አካላት የማዋቀር መብት እንዳላቸው አስረድተዋል። በሌላ በኩል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 82 ድንጋጌዎች መሠረት የክልል ፍርድ ቤቶች በቤተሰብ ጉዳይ፣ በውርስ፣ በመሬት አስተዳደርና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ የዳኝነት ሥልጣን እንዳላቸው መደንገጉን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ክልሎች እነዚህን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሕግ የማውጣት ሥልጣን ሳይኖራቸው ያወጡ ከሆነ፣ ወይም ጉዳዩ ከሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ጋር የተያያዘ ከሆነ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመዳኘት ሥልጣን እንደሚኖረው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 83 (ሀ) ላይ መደንገጉን አስረድተዋል።

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ (ሸ) ድንጋጌ በዋናነት መሠረት ያደረገው ተከራካሪ ወገኖች የሚኖሩበትን አድራሻ ብቻ መሆኑ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል። ምክንያታቸውን ሲያስረዱም አዋጁ የጉዳዩ መነሻ የሆነው ንብረት የሚገኘበትን አካባቢ፣ እንዲሁም በክልል የሚካሄዱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን የሚመለከቱ ውሎችን ከግምት ያላስገባ ነው ብለዋል። በሌላ በኩል በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 25 የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች የዳኝነት ሥልጣን ንብረቱ በሚገኝበት አካባቢ ሥልጣን ያለው ፍርድ ቤት እንደሆነ የሚደነግግና ይህ ሕግ ያልተሻረ ወይም በሥራ ላይ የሚገኝ መሆኑን አውስተዋል። አዋጅ ቁጥር 1234 አንቀጽ 5 (ሸ) ከላይ ከቀረቡት አመክንዮዎች አንፃር ሲታይ ከሕገ መንግሥቱም ሆነ ከሌሎች ሕጎች ጋር የሚጋጭ ነው ብለዋል። በመሆኑም የፌዴራል ተከራካሪ ወገኖች የመኖሪያ አድራሻን ብቻ ከግምት በመውሰድ ጉዳዩን የማየት ሥልጣን የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ነው የሚለው የአዋጅ ቁጥር 1234 ድንጋጌ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል። 

በመቀጠል ሙያዊ ትንታኔያቸውን ያቀረቡት ደግሞ ከኦሮሚያ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተወከሉ ባለሙያ ሲሆኑ፣ የተቋሙ ባለሙያ የመጨረሻ መደምደሚያ ሐሳብም በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም የሚል ነው። 

የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተወካዩ ወደዚህ ድምዳሜ ለመድረስ ካስቀመጧቸው አመክንዮዎች መካከል ዋነኞቹ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50 መሠረት ክልሎችና የፌዴራል መንግሥት ራሳቸውን ችለው የተዋቀሩና ሁለቱም የየራሳቸው ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚና አስፈጻሚ አካል የሚኖራቸው መሆኑ አንደኛው ሲሆን፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 52 ላይ ደግሞ ክልሎች ራሳቸውን በራሻቸው የማስተዳደር ሥልጣን የተሰጣቸው መሆኑ ነው።

ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳደራሉ ሲባል በክልላቸው ውስጥ የሚገኙ የሚንቀሳቀሱም ሆነ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን ያስተዳድራሉ ማለት እንደሆነ፣ በተለይ እንደ ቤት ያሉ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን በተመለከተ ለፌዴራል ያልተሰጠ በመሆኑና በግልጽ ለፌዴራል መንግሥት ወይም ለፌዴራል መንግሥትና ለክልሎች በጋራ ያልተሰጡ ጉዳዮች የክልሎች ሥልጣን እንደሚሆን፣ ከሚያስቀምጠው ሕግ መንግሥታዊ ድንጋጌ አኳያ ጥያቄ የተነሳበት ጉዳይ የክልል ሥልጣን እንደሚሆን አስረድተዋል። 

ሕገ መንግሥቱ የፌዴራል መንግሥትና የክልል መንግሥታት የዳኝነት ሥልጣን ክፍፍል በግልጽ ያስቀመጠ መሆኑን የገለጹት የኦሮሚያ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ተወካዩ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 70 እና 80 ላይ የጣምራ ዳኝነትን የሚያመለከቱ ድንጋጌዎች የተቀመጡበትን ምክንያትም አስረድተዋል። 

ተወካዩ እንደገለጹት፣ ስለጣምራ ዳኝነት በሚገልጹት የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መሠረት የፌዴራል መንግሥት ማንኛውንም የሕግ ስህተት የማረም ሥልጣን እንደሚኖረው፣ ቢዚህም መሠረት በየትኛውም ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተሰጠ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ጥያቄ ከተነሳ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የማየት ሥልጣን እንዳለው ነው። በሌላ በኩል የፌዴራል መንግሥት የመጀመሪያና ከፍተኛ ደረጃ ፍርድ ቤቶችን በክልሎች እስኪያቋቁም ድረስ፣ የክልል ፍርድ ቤቶች የፌዴራል ጉዳዮችን በውክልና የመዳኘት ሥልጣን እንደተሰጣቸው አስረድተዋል። 

በመሆኑም አንድ ጉዳይ የፌዴራል ወይም የክልል እንደሆነ እንጂ፣ በተመሳሳይ ጊዜ የፌዴራልና የክልል ሥልጣን ውስጥ መውደቅ የሚችልበት ድንጋጌ በሕግ መንግሥቱ የተቀመጠ ባለመሆኑ፣ በኢትዮጵያ የጣምራ ዳኝነት የሚባል ነገር በተጨባጭ የለም ብለዋል። 

ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የተወከሉ ባለሙያዎች አስተያየት 

ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የተወከሉ ሦስት የሕግ ባለሙያዎች ፋሲል ዓለማየሁ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ ምሥጋና ክፍሌ (ዶ/ር) እና ተጓድ አለባቸው (ዶ/ር) አስተያየት እንዲሰጡበት የተመራላቸውን ጉዳይ በጋራ የተመለከቱት ቢሆንም፣ ድምዳሜያቸው ላይ በሐሳብ መለያየታቸውን በመግለጽ የደረሱበትን በተናጠል አቅርበዋል።

በዚህም መሠረት ፋሲል (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ ትንታኔያቸውንና የደረሱበትን ድምዳሜ በቀዳሚነት አቅርበዋል። 

በመጀመሪያ በኢትዮጵያ ያለውን የዳኝነት ክፍፍል ሦስቱም ባለሙያዎች በጋራ ሆነው የተመለከቱ ሲሆን በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ የሕግ ማውጣት ሥልጣንን መሠረት በማድረግ የዳኝነት ሥልጣን ክፍፍል መደረጉን አስረድተዋል። 

በመሆኑም የትኞቹ ጉዳዮች የፌዴራል ሥልጣን፣ የትኞቹ ጉዳዮች የክልል ስልጣን እንደሆኑ በቅደም ተከተላቸው መሠረት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 እና በአንቀጽ 51 ሥር በዝርዝር መደንገጉን አስረድተዋል። በዚህም ላይ ሦስቱም ባለሙያዎች ልዩነት እንደሌላቸው ገልጸዋል። ይህንን ጉዳይ ከአዋጅ ቁጥር 1234 ድንጋጌ አንፃር ሲታይ አዋጁ በኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤት ሊታይ የሚገባን ጉዳይ፣ የተከራካሪዎቹን የመኖሪያ አድርሻ ብቻ ከግምት በማስገባት የዳኝነትን ሥልጣን ከክልል ወደ ፌዴራል ፍርድ ቤት የሚያስተላልፍ ሆኖ እንዳገኙት ገልጸዋል። ይህንን ማድረግ በሕገ መንግሥቱ ተፈቅዷል ወይ የሚለውን በጋራ ሆነው በመረመሩበት ወቅትም፣ ከኢትዮጵያ የዳኝነት ሥልጣን ክፍፍል ጋር ተቀራራቢ ሆኖ ያገኙትን የአሜሪካ የዳኝነት ሥልጣን ክፍፍል መርህን ለመዳሰስ እንደሞከሩ ገልጸዋል።

በአሜሪካ የዳኝነት ሥልጣን ክፍፍል ውስጥ ብዝኃነትን ለማስተናገድ ተብሎ የ‹‹Diversity Jurisdiction›› መርህ መቀመጡን አስረድተዋል። በዚህ መርህ መሠረት በሁለት የተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ የሚኖሩ ተካራካሪዎች ጉዳያቸውን ለክልል ፍርድ ቤት አልያም በተከራካሪዎቹ ምርጫ ለፌዴራል ፍርድ ቤት ማቅረብ እንዲችሉ መብት የሚሰጥ ነው። ይህም ብዝኃነትን ለማስተናገድ ተብሎ በአሜሪካን ሕገ መንግሥት አንቀጽ ሦስት ላይ የተደነገገ መሆኑን ያስረዱት ፋሲል (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ በሁለት የተለያዩ የአሜሪካ ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ተከራካሪዎች መካከል አንደኛው እርሱ ከሚኖርበት ግዛት ውጪ በሆነ ሌላ ግዛት ብዳኝ ትክክለኛ ፍትሕ አላገኝም ወይም አድሎ ይደርስብኛል ብሎ ካመነ፣ ጉዳዩ በፌዴራል ፍርድ ቤት እንዲታይ ማድረግ የሚችልበትን መብት የሚሰጠው እንደሆነ አስረድተዋል። ይህ ማለት ግን የአንድ ግዛት የዳኝነት ሥልጣን የመንጠቅ ወይም ለሌላ የማስተላለፍ ዕሳቤ እንደሌለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234 አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ አንድ (ሸ) ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ መንፈስም ብዝኃነትን ለማስተናገድ ተብሎ የተቀረፁ ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰዋል። ነገር ግን ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ሊኖር ይገባል ያሉት ፋሲል (ረዳት ፕሮፈሰር)፣ በአሜሪካ ብዝኃነትን ለማስተናገድ የተሰጠው መብት ሕገ መንግሥቱን መሠረት ማድረጉን በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ግን ይህንን መብት የሚሰጥ ድንጋጌ እንደሌለ ጠቅሰው፣ አዋጅ ቁጥር 1234 ድንጋጌ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም በማለት ደምድመዋል። 

ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የተወከሉት ሌላዋ የሕግ ባለሙያ ተጓደ አለባቸው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የዳኝነት ሥልጣን ክፍፍልን በተመለከተ የተለያዩ ፍላጎቶችን ለማስጠበቅ ፍላጎት አለው ብለው እንደሚያምኑ የገለጹ ሲሆን፣ ጥያቄ የቀረበበት አዋጅ ቁጥር 1234 ድንጋጌ በሁለት የተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ ተከራካሪዎች ጉዳያቸው በገለልተኛ ፍርድ ቤት እንዲታይላቸውና በዚህም ትክክለኛ ፍትሕ የማግኘት መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ታሳቢ ያደረገ ነው ብለው እንደሚረዱ ተናግረዋል። 

ይህንን አዋጅ ያዘጋጁት ባለሙያዎች አስበውበትም ይሁን ሳያስቡት ውጤቱ ግን ዜጎች ጉዳያቸው በገለልተኛ ፍርድ ቤት እንዲታይላቸው መብት የሚሰጥ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ፍፁም አለመሆኑን፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ለዜጎች መብት የበለጠ ጥበቃ ለማድረግ እንጂ መብቶችን ለመገርሰስ እንዳልሆነ፣ በመሆኑም አዋጅ ቁጥር 1234 ድንጋጌ ሕግ መንግሥታዊ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። 

ሌላው የሲቪል ሰርቪስ የሕግ ባለሙያ ምሥጋና ክፍሌ (ዶ/ር) ባቀረቡት ድምዳሜም፣ አዋጅ ቁጥር 1234 ድንጋጌ ሕገ መንግሥታዊ ነው የሚል ድምዳሜ ሰጥተዋል። ነገር ግን ወደዚህ ድምዳሜ ያደረሳቸው ትንታኔ ከሌሎቹ ባልደረቦቻቸው ትንታኔ የተለየ ነው። እንደ ምሥጋና (ዶ/ር) ትንታኔ፣ የቀረበው ጥያቄ በሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ሳይሆን በሕግ መጣረስ መርህ ነው መታየት ያለበት ብለዋል።

የውርስ ጥያቄ የክልል መንግስታት ሥልጣን ነው፣ በመሆኑም ጉዳዩ በቀጥታ የኦሮሚያ ክልል ሥልጣን ነው። ነገር ግን አሁን የቀረበውን ጉዳይ አከራካሪ ያደረገው ነገር አንደኛው ተከራካሪ የአዲስ አበባ ነዋሪ መሆናቸውና አዲስ አበባ ደግሞ ክልል አለመሆኗ ነው ብለዋል።

በቀረበው ጉዳይ ላይ በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ ተከራካሪ ግለሰብ፣ ‹‹የአማራ ክልል ወይም የሌላ ክልል ነዋሪ አድርገን ለመመልከት ብንሞክር ጉዳዩን የማየት ሥልጣን የበለጠ አከራካሪ ያደርገዋል፣ ምክንያቱም ሁለቱም ውርስን በተመለከተ ጉዳይን የመዳኘት ሥልጣን አላቸው፤›› ብለዋል።

በመሆኑም ዳኝነት የተጠየቀበትን ጉዳዩ ለመዳኝት ጥቅም ላይ በሚውለው ሕግ መካከል መጣረስ እስከሌለ ድረስ ጉዳዩ በኦሮሚያ ወይም በፌዴራል ፍርድ ቤት ሊታይ እንደሚችል ገልጸዋል። ይሁን እንጂ የሕግ መጣረስ በሚኖርበት ጊዜ በየትኛው ሕግ ይታያል የሚለውን የሚመለስበት የሕግ ማዕቀፍ የሌለ በመሆኑ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 62 (8) መሠረት በማድረግ ገዥ ሕግ ሊያወጣለት ይገባል ብለዋል።

በጥቅሉ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የጋባዛቸው ባለሙያዎች በሰጡት ምክረ ሐሳብ ገሚሱ አዋጅ ቁጥር 1234 ድንጋጌ ከሕግ መንግሥቱ የተጣረሰ ነው ሲሉ፣ የተወሰኑት ደግሞ የአዋጁ ድንጋጌ ሕገ መንግሥታዊና እንዲያውም ብዝኃነትን ለማስተናገድ የሚያስችል ጭምር ነው ብለዋል። የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በዚህ ጉዳይ ላይ የቀረቡለትን ሙያዊ ምክረ ሐሳቦች እንደ ግብዓት በመጠቀም የመጨረሻ ውሳኔውን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -