Thursday, May 30, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ያልተወራረዱ ችግሮች!

ሰላም! ሰላም! እንደምን ሰነበታችሁ ወገኖቼ፡፡ የአራዶቹ ሠፈር የፒያሳ ልጆች እንዴት ናችሁ? ይገርማል የጊዜ ነገር፡፡ ‹‹መገን የአራዳ ልጅ እነ ድንጋይ ኳሱ፣ ከምኔው ተጩኾ ከምኔው ደረሱ… እንዳልተባለ፣ አራዳ ፈርሳ ልትሠራ ተብሎ የአራዳ ልጆች ተነቀሉ…›› እያለ በሐሳብ ሲብሰለሰል የሰነበተው አንዱ የአራዳ ወዳጄ ደላላ ነው። ደሃብ ሆቴል ደጅ ሆኖ ሥራውን ሲከውን የኖረ ይህ ደላላ ወዳጄ እንዲህ ከማለቱ አብሮን የነበረ ሌላው ወዳጃችን፣ ‹‹የተመቻቸው ምን አለባቸው? የኑሮ ውድነት አያጎሳቁላቸው፣ የቤት ኪራይ አያንገበግባቸው፣ ከመሥሪያና ከመኖሪያ አካባቢ ተነቅሎ መባረር የሚያስከትለው የኑሮ ዳፋ አያስፈራቸው፣ ሥራና ምግብ ጠፋ ብለው አይሳቀቁ፣ ሁሉም በእጃቸው ሁሉም በደጃቸው…›› አለን። በየምክንያቱ የምናነሳው ጉዳያችን የት ድረስ እንደሚለጠጥ አያችሁ? የጊዜያችን አኗኗር ጉዳይ ግን ጥልቅ ምርመራ ሳያስፈልገው አይቀርም፡፡ ‹‹ዘመን ሲለወጥ በሰው ልጅ ላይ ይዞት የሚመጣው ለውጥ  ነው የሚያሳስበኝ…›› እያለ የሚነግረኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አንበርብር ለውጥ አስፈላጊና የማያቋርጥ ሒደት ቢሆንም እንደ ደራሽ ወንዝ የሰው ልጅ ላይ ሲከነበል ግን አደጋ አለው፡፡ የዛሬ 50 ምናምን ዓመታት በኢትዮጵያ ምድር የፈነዳ የአብዮት ጂኒ ነው ለዚህ ሁሉ የዳረገን…›› ሲለኝ ሰነበተ፡፡ ለውጥ ወይስ ነውጥ እንበለው!

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት የመስጠት ችሎታና አቅም ስላልነበረኝ ሐሳቤን ለወር ቀለብ የሚያስፈልግ የቤት ወጪ ዝርዝር ላይ ጣድኩት። ሰብስቦ ለመበተን ጠብ ሲል ለመድፈን አይደል የእኛ ኑሮ? በቃ አንዱ የሠፈራችን ዘናጭ፣ ‹‹እየተለወጠ ያለው ‹ስታይላችን› እንጂ ‹ስታተሳችን› አይደለም›› የሚል አባባል አለው። የሚገርማችሁ ታዲያ ከሁለቱ የእንግሊዝኛ ቃላት የማውቀውና ቶሎ የሚገባኝ ‹ስታይል› የሚባለው ነው። ‹‹እስቲ ‹ስታይል› ይኑርህ…››፣ ‹‹እሱ እኮ ‹ስታይለኛ› ነው…›› ማለት የዘወትር ልማዳችን ስለሆነ ብቻ ሳይሆን፣ በይሉኝታ የታሰረው አኗኗራችን ውጤት ጭምር ይኼንን ቃል በደንብ እንዳውቀው ሳያግዘኝ አልቀረም መሰለኝ። ወሰብሰብ ካለው ነገር ወጥተን እንዲህ ባሉት ነገሮች ዘና ማለት ባንችል እኮ የዘንድሮ ነገር አዙሮ ይደፋን ነበር፡፡ ዝም ብዬ ሳስበው የሕይወታችን መስመር ቀያሽ የሆነው አስተሳሰባችን ላይ ካልሠራን አያያዛችን አሁንም ወደፊትም አሥጊ ነው። ‹‹ምን ዋጋ አለው? ዘናጭ ከተማ ለመገንባት ሲነሱ አስተሳሰብን ሳያስተካክሉ መውረግረግ ፋይዳ ቢስ ነው…›› የምትለው ውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ናት፡፡ ቆይ እስቲ ብዙ ጊዜ ስለኢንቨስትመንት ሲወራ ቁሳዊው ነገር ላይ እንበረታለን፡፡ ለአስተሳሰብና ለአመለካከት ምጥቀት ኢንቨስትመንቱ ቢኖረን እኮ ሰብዓዊው ጉዳይ አይርቀንም ነበር፡፡ በነበር እንዳታልፉት!

እንደምታውቁት የዘመኑ ጨዋታ ዕድሜ ለቴክኖሎጂ በመረጃ ሆኗል። ምን ሆነ መሰላችሁ? ኮሚሽን ለማግኘትና ውዷ ማንጠግቦሽ የለመደችው እንዳይቀርባት ሮጥ ሮጥ ማለት አለብኝ አልኩና ተፍ ተፍ ማለት ጀመርኩ። የእኛ ነገር ምን ዓይነት ስም ቢወጣለት እንደሚሻል አላውቅም ወዲያው የሚያደናቅፈኝ በዛ። ማንጠግቦሽ ደወለች። ‹‹ምን ሆንሽ?›› ስላት ሠፈር ውስጥ በጠና ታመው ሲጠበቁ የነበሩ አዛውንት ማረፋቸውን አረዳችኝ። የኑሮ መርዶ በዝቶ ነው መሰል የሰው ሞት ማርዳት እንዲህ ቀላል ይሁን? ‹‹እና?›› አልኳት በጠፋ ሥራ በስንት መከራ የተገኘው እንዳያመልጠኝ ስል እንዳትጠራኝ ፈጣሪን እየተማፀንኩ። ‹‹ቶሎ መጥተህ አብረን ለቅሶ እንድረስ…›› ተባልኩላችሁ። ደልቶት ለሞተውና ተኮራምቶ ለሞተው እኩል ለቅሶ ተቀምጠን እንዴት እንደምንዘልቀው አላውቅም። እሱ ብቻ አይደለም አያ ሞት አጅሬው በዚህ ዘመን ምን እንደሚያጀግነው አልገባኝም። በቅጡ ካስተዋላችሁ ሞት ይበዛል። ምንም እንኳን ማኅበራዊ የትስስር ገጽ ማኅበራዊ ኑሮውን ቢተካውም፣ ሰው ያለ ሰው አይኖርምና እየተነጫነጭኩ ደረስ ብዬ ለመምጣት ከነፍኩ። ለቅሶ ሳሳድድ ባዶ እጄን እንዳልቀር ነዋ!

ቆይቼም የባህልና የወግ ተፅዕኖን ለያይቼ ለማሰብ እየሞከርኩ ራሴን ለማፅናናት ብዙ ጣርኩ። ድንገት ግን ቆይ ብቀርስ? ብዬ መሀል መንገድ ላይ መመለስ ጀመርኩ (ሰው ለካ ወዶ አያብድም እናንተ?)፡፡ የዘንድሮ ሰው እንኳን መንገድ ሰጥተውት እንዲያውም እንዲያው ነው፡፡ አሁን ለቅሶ ቀረ ብሎ መንደርተኛው ሰው ሊያደርገኝ ነው? ብዬ ሳስብ ወደ ሥራ ያዞርኩትን እግሬንና ቀልቤን ወደ ለቅሶ ቤት ቀለበስኩት። አንዱን ሲነሳ አንዱን አያሳጣም፡፡ ለቅሶ ቤት ቁጭ ብዬ ሰው በሹክሹክታ የሚነጋገረውን እየሰማሁ ፈታ አልኩ። በሐሜትና በአሉባልታ የተከበበ ከመሆኑ ባሻገር እውነተኛው የንግግር ነፃነት፣ እውነተኛና ነፃ የሕዝብ ፓርላማ ማለት እንዲህ ያለው መድረክ ነው እስክል ድረስ። አንዳንዴ ሳስበው በሰነፎች የተሞላው መንግሥታችን በቋንቋም በባህሪም ከማያውቃቸው አገሮች ሳይቀር የተለያዩ ተሞክሮዎችን ከሚያሰባስብ፣ የለቅሶ ቤቱን እሴት ሳይንሳዊ ለማድረግ ቢጥር ዴሞክራሲያችን ባልቀጨጨ ያስብላል እኮ። ሰሚ ጠፋ እንጂ እሱስ ሲባል የኖረውማ ‹የሰው ወርቅ አያደምቅ› ነበር፡፡ በትክክል!

 እናላችሁ ለቅሶ ቤት ብቀመጥም ቀልቤና ሐሳቤ እኔ ዘንድ አልነበሩም። በጎን ሞባይል ስልኬ ያለማባራት እየጮኸ ይበጠብጠኛል። እነሳለሁ፣ እቀመጣለሁ። ‹መጣሁ› እላለሁ እዋሻለሁ። ይህን ያዩት አዛውንቱ ባሻዬ፣ ‹‹አንበርብር ኔትወርክ ተመርጦ በነፃ መሰጠት ጀመረ እንዴ?›› ብለው ሳቁ። ሰውን የሚያንቆራጥጠው የኔትወርክ ዋጋ እኔ ስልክ ላይ አለመከሰቱ የገረማቸው ይመስላሉ። ‹‹እባክዎን ስንቱን ሥራ እኮ ነው በእንጥልጥል ትቼው ስሮጥ የመጣሁት…›› አልኳቸው። ይኼን ጊዜ፣ ‹‹እኔ የምለው የቫት ክፍያውን መንግሥት ዘንድ ሄደን እናወራርደዋለን። እንዲህ ለሟች በማይጠቅምና ቋሚን በማያበረታ ጊዜ ማጥፋት የምናቃጥለው ዕድሜ ግን የት ይሆን የሚወራረደው?›› ቢሉኝ ሳቄ መጣብኝና ሰው እስኪታዘበኝ ድረስ ላለመሳቅ ታገልኩ። ማንጠግቦሽም ከሩቅ ዓይታኝ ኖሮ መሰስ ብላ መጥታ፣ ‹‹ኧረ አንተ ሰውዬ ሰው ሲሞት የሚስቅ ቀጣዩ ሟች ነው ይባላል እኮ…›› ስትለኝ ባሰብኝ። ጭራሽ ዕጣ ወጥቶልኝ ይረፈው? ጉድ እኮ ነው ዘንድሮ እባካችሁ፡፡ እየቆየሁ ስሄድ የሞት ፍርኃት ወረሮኝ (ሰው ሲሞት ነው ሞት እንዳለ ትዝ የሚለን) መጨረሻውን ሳላይ የምለው ነገር በዛብኝ። እስኪ አስቡት አልወለድ ያለውን ዴሞክራሲያችንን መጨረሻ፣ አንበላም አንጠጣም ብለን ያዋጣንለትን የህዳሴ ግድባችንን መጠናቀቅ ሳላይ እንዲህ እንደ ቀልድ ጭልጥ? ‹‹ዘራፍ አንበርብር!›› ስል፣ ‹‹ኧረ ጠላትህ!›› አሉኝ ባሻዬ። ለካስ ድምፄን ከፍ አድርጌው ኖሯል። ሊሞት አምስት ደቂቃ ብቻ ቀረው የተባለ ሰው በሞት ፍርኃት ፈንታ አምስቱን ደቂቃዎች ለተለያዩ ክንዋኔዎች ከፋፍሎ እንዴት ሊጠቀምባቸው እንደሞከረ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ያጫወተኝ ትዝ ቢለኝ ደግሞ እመር ብዬ ተነስቼ ወደ ሥራዬ ገሰገስኩ። ታዲያስ ህያው ለመሥራት መሮጥ እንጂ ለሙታን ሲያለቅስ መኖር አለበት እንዴ? ‹ነፍስ ይማር› ማለትን አረሳሁም፡፡ ወግና ባህል ነው!

ደላሎች የምንሰበሰብበት ሥፍራ ስደርስ አካባቢው ቀውጢ ሆኖ ነበር የጠበቀኝ። ‹‹ምንድነው እሱ አካባቢውን ጋዛ ያስመሰላችሁት?›› ብዬ ብጠይቅ አንዱ፣ ‹‹ምነው አንበርብር? መፍትሔ የታጣለትን የሞት ቀጣና ከእኛ ጋር ታመሳስላለህ?›› አይለኝ መሰላችሁ? ‹ከሰው ጋር ሲኖሩ ተቻችሎ ነው፣ አጥሩም ግድግዳውም ነገረኛ ነው› ብለው ባሻዬ የሚተርቱት ወዲያው በአዕምሮዬ አቃጨለና ያላሰብኩትን ያሳሰበኝን ወዳጄን ይቅር ብዬው ሄድኩ። ምን ዘንድሮ እልፍ እያሉ ካልሆነ አየሩ ደስ አይልም። እልፍ ከማለቴ ደለብ ያለ ረብጣ የሚቆጠርባቸው ሥራዎች ድንገት በመከሰታቸው ምክንያት ምድረ ደላላ ግርግሩን እንዳስነሳው አንድ ወዳጄ ነገረኝና በተጨማሪ የደረበውን ሥራ ለእኔ አስተላለፈው። በደላላ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ደግነት ሳይ እኛ ከክፋትና ከምቀኝነታችን ጀርባ የመተሳሰብና የቀናነት ባህሪ ባለቤቶች መሆናችን ትዝ እያለኝ ተመሥገን አልኩ። ደግሞ መልሼ እንዲህ ያለው መተሳሰብ ርቆን በአገሩ ራስ ወዳድነት በዝቶ ለዘመናት በችግር ላይ ችግር ስንሸምን መኖራችንን አሰላሰልኩና ዝም አልኩ፡፡ ሌላ ምን ይባላል? እንዲህ በሐሳብ ከሙቅ ወደ ቀዝቃዛ፣ ከቀዝቃዛ ወደ ሙቅ ስናውዝ ሳለሁ ራሴን አንድ ጥያቄ ጠየቅኩት፡፡ ‹ለምን ይሆን የማይከፈልበትን ደግነት ስንሸሽ እየኖርን ለክፋት የምንከፍለውን ዕዳ የምናበዛው?› ስል። እውነቴን አይደል? እስኪ እንነጋገርበት!

እናላችሁ አዲስ የተባለ ግሬደር ሊገዛ የሚችል ሰው ፈለግ ፈለግ ሳደርግ ቆየሁ። እንደ ቀልድ ፈለግ ፈለግ አልኩ እንጂ እኔ አዲስ አበባን ያካለልኩትን ያህል ቫስኮ ደጋማ ዓለምን አልዞረም ብል ይቀል ነበር። የጠበቅኩትና የለመድኩት ዓይነት ሰው ግን አልገጠመኝም። ገዥ የተባለችው በጣም ወጣት ናት። ልቤ ‹አንበርብር በከንቱ እንዳትለፋ ተጠንቀቅ› ሲለኝ፣ ‹‹እንዴት ነው ቢዝነስ ላይ የወጣት ሴቶች ተሳትፎ እያደገ መጣሳ?›› ብዬ ኢቲቪ ያሳደረብኝ ተፅዕኖ እንዳይታወቅብኝ አድርጌ ጠየኳት። እሷም ሁኔታዬን ዓይታ ነገሬ ገባት መሰል፣ ‹‹ያለፈውን ጊዜ የጭቆናና የግፍ ዘመን ቆጥሮ ይሆናላ…›› ብላ ከምፀት አዘል ፈገግታ ጋር መለሰችልኝ። እየቆየን የበለጠ ስንግባባ ቤተሰቦቿ እያገዟት እንዲህ ያለ ‹ቢዝነስ› ውስጥ እንደገባች አጫወተችኝ። ‹ወንድ ባለ በዕለት ሴት ባለች በዓመት› የሚሉት ኋላቀር አባባል ሲያልፍ የማይነካት ይህች ወጣት፣ ማሽኑን በደንብ አስፈትሻና በቅድመ ሁኔታዎች ላይ ተደራድራ እንደምትገዛው ስታሳውቅ እኔ ግራ ገባኝ። ምን ግራ የሚያጋባ ነገር አገኘህ አትሉኝም እንዴ? ወሬና ፍቅር እኮ ከአንድ ወገን ሲሆን ጥሩ አይደለም። ከጠየቃችሁኝ ግራ የገባኝ ፈርጀ ብዙው እየሆነ የመጣው የወጣቶች ሕይወት ነው። ገሚሱ ራሱን ለማሻሻል ‹ፀሐይ ሳለ ሩጥ አባት ሳለ አጊጥ› እያለ ዕድሜውን በአግባቡ ለመጠቀም ሲጥር ታዩታላችሁ። ይማራል፣ ይሠራል፣ ይጥራል፣ ይደክማል። ገሚሱ ደግሞ ትርጉም በሌለው ወሬ ተወጥሮ አገር ላይ መርገምት ለማምጣት የሐሰት መረጃ ይረጫል። በዘረኞችና በሴረኞች ተታሎ የሚይዝ የሚጨብጠውን አጥቶ አገር ያተራምሳል። ለሁሉም ማስተዋል ይስጥ እንጂ ሌላ ምን ማለት ይቻላል!

ከመልከ መልካሟ ታታሪ ወጣት ልጅ የተበረከተልኝ የኮሚሽን ገጸ በረከት የሚነገርም አይደል። ከጎልማሳነቴ ጋር አብሮ ጨዋታዬ ስለጣማት በቆይታዋ ተደስታለች። በጥሩ ሁኔታ ስላሳለፍነው የአብሮነት ጊዜያችንን ጭምር ታሳቢ አድርጋ ‹ቦነስ› ጀባ ብላኝ ስንለያይ፣ ምሁሩን የባሻዬ ልጅ ደውዬ ግሮሰሪያችን ቀጠርኩት። የዛሬውን አያድርገውና የአራዳ ልጅ እኮ ብቻውን በልቶ አያውቅም፡፡ ‹…አራዳ ደግ ነው በጣም ያዝናል ሆዱ…› እኮ ነው ግጥሙ። ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር ግሮሰሪያችን ተገናኝተን እየተጫወትን በድንገት፣ ‹‹ስማ እንጂ አንበርብር?›› ብሎ ወግ ሊጀምር ሲል፣ ‹‹እየሰማሁ ነው…›› ስለው፣ ‹‹ያኔ ድሮ አራዳ ስትሠራ ሚናስ የሚባል አርመናዊ መሐንዲስ ነበር አሉ፡፡ በጊዜው ማስተር ፕላን መሠረት አራዳን እንዲገነባ ትዕዛዝ ሲሰጠው በወቅቱ የነበሩ ቤቶችን ማፈራረስ ጀመረ፡፡ ያኔ ንብረታቸው የፈረሰባቸው ሰዎች፣ ‹‹ጣሊያንም መጣ ሄደ ተመለሰ፣ ሚናስ ብቻ ቀረ ቤት እያፈረሰ› ብለው ገጠሙለት…›› ብሎ ያላሰብኩትን ሲነግረኝ፣ ‹‹ከአሁኑ የአራዳ ማፍረስ ጋር ምን ይሆን ግንኙነቱ?›› ብዬ ጠየቅኩት። ‹‹ግንኙነቱ ተመሳሳይ ነው፡፡ የጊዜ እንጂ የሐሳብ ልዩነት የለውም…›› እያለ ሲያስረዳኝ የግሮሰሪያችን አስተናባሪ የባሻዬን ልጅ ሰምቶት ይሁን አላውቅም፣ ‹‹አፈረሱት አሉ ውቤ በረሃን ያለ አባት ያለ እናት ያሳደገንን…›› የሚለውን የከተማ መኮንን ዘፈን ሲከፍተው የግሮሰሪያችን ደንበኞች በትዝታ ነጎዱ፡፡ እንዲያ ነው!

በዚህ መሀል አንዱ፣ ‹‹ዕድገት የሚገኘው በሞቅታ መንፈስ ውስጥ ሳይሆን ሁሉንም በሚያማክል የጋራ መግባባት ነው፡፡ ይልቁንስ በዕድገት ስም እየተሳበበ ስለሚፈጸመው ማኬያቬላዊ ድርጊት መጥፎነት እየተነጋገርን፣ ሁሉንም ወገን በእኩልነት ስለሚያኖረው ዕድገት እናስብ…›› ሲለን ከሞቅታው በቀር አስተሳሰቡ የመጠቀ መሰለኝ፡፡ ሰውዬው ዲስኩሩን ሲቀጥል ምሁሩ የባሻዬን ልጅ፣ ‹‹ይህ ሰው ምን እያለ ነው?›› ብዬ ጠየቅኩት፡፡ የባሻዬ ልጅም የጠጠረው ሐሳብ እንዳልገባኝ ተረድቶ፣ ‹‹ሰውየው የሚለው ማኬያቬላዊ ከሆነው በአሻጥርና በተንኮል ከተተበተበ መንፈስ ተላቀን በጋራ የሚጠቅመን ዕድገት ላይ እናተኩር ማለቱ መሰለኝ…›› ሲለኝ አሁን ገና ገባኝ፡፡ ‹‹ሰማህ አንበርብር ዙሪያህን ተመልከት፡፡ ሁሉም ቦታ ቅራኔ አለ፡፡ ቤተሰብ ውስጥ፣ በወዳጆች መሀል፣ ሃይማኖት ውስጥ፣ መንግሥት ውስጥ፣ ሕዝብ ከመንግሥት ጋር ያልተወራረዱ ሒሳቦች አሉ፡፡ በአገሪቱ ላለፉት በርካታ ዓመታት ያልተወራረዱ የፖለቲካ ሒሳቦችና አሁን ደግሞ ከክፋት ጋር የሚደመሩት ችግሮች የሰላም ጠንቅ መሆናቸውን አትዘንጋ፡፡ እነዚህ ችግሮች ሳይወራረዱ የተገባበት ሌላ ዙር አንጃ ግራንጃ ያስፈራል…›› ሲለኝ ሁሉም ነገር ግልጽ ሆነልኝ፡፡ ወገኖቼ እስኪ ያልተወራረዱ ችግሮች በሰከነ መንፈስ ተወራርደው ለአገር ግንባታ መሠረት እንጣል፡፡ መልካም ሰንበት!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት