Wednesday, May 29, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከኃላፊነታቸው ታገዱ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ጥላሁን ታደሰ ከኃላፊነታቸው ታገዱ፡፡

አቶ ጥላሁን ከኃላፊነታቸው እንደታገዱ የሚገልጸው ደብዳቤ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አስተዳደር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ተፈርሞ ነው የወጣው፡፡

አቶ ጥላሁን ከመጋቢት 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከሥራቸው የታገዱ መሆኑን የዕገዳ ደብዳቤው ከመግለጽ ውጪ፣ የታገዱበትን ምክንያት አያብራራም፡፡ እንደ ሪፖርተር ምንጮች ገለጻ ግን የዕገዳው ምክንያት ከማዕከሉ የውስጥ አሠራር ችግር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አቶ ጥላሁን ታግደዋል መባሉን እሳቸውም ሆኑ ምክትላቸው በሥራ ላይ መሆናቸውን በመግለጽና በማስተባበል ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

መታገዳቸውን የሚያመለክተው ደብዳቤ ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣ ለአዲስ አበባ ብልፅግና ጽሕፈት ቤት፣ ለኤግዚቢሽን ማዕከልና ለገበያ ልማት ድርጅት በግልባጭ እንዲያውቁት መደረጉ ታውቋል፡፡

አቶ ጥላሁን ማዕከሉን በሥራ አስፈጻሚነት ከአምስት ዓመታት በላይ የመሩ ሲሆን፣ በቀድሞው የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ኃላፊነት ጊዜ የተሾሙ መሆናቸው ይታወሳል፡፡

የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ ልማት ድርጅት በአዲስ አበባ አስተዳደር ባለቤትነት የሚተዳደር ሲሆን፣ ለ18 ዓመታት የከተማ አስተዳዳሩ ከአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር በጋራ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ከጥቂት ወራት በፊት አስተዳደሩ ከንግድ ምክር ቤት ጋር ያለውን ስምምነት ማቋረጡ ይታወሳል፡፡

ቀድሞ በነበረው ስምምነት ከማዕከሉ በተጨማሪ የመስቀል አደባባይ አጠቃላይ አገልግሎቶችን በጋራ ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል፡፡ ከአስተዳደሩ የገቢ ምንጮች መካከል አንደኛው የኤግዚቢሽን ማዕከል ነው፡፡

የኤግዚቢሽን ማዕከሉን የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል የማስፋፊያ ሥራዎችን ለማከናወን፣ የከተማ አስተዳደሩ ከባለሀብቶች ጋር በጋራ ለማልማት ውሳኔ ማሳለፉ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች