Wednesday, May 29, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከአምስት ዓመታት በላይ የተከማቸ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዝቃጭ ቆሻሻ ወደ ሐይቅ እየገባ ነው ተባለ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከአምስት ዓመት በላይ የተከማቸ ዝቃጭ ቆሻሻ ወደ ሐዋሳ ሐይቅ እየገባ መሆኑ በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ተረጋገጠ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ፣ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም.  የኢንዱስትሪ ፓርኮች የተቀናጀ የደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ውጤታማነትን በተመለከተ፣ 2014/15 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ውይይት በተደረገበት ወቅት እንደተገለጸው፣ በሐዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የተከማቸ ቆሻሻ መኖሩ የአካባቢ ብክለት ይፈጥራል ተብሏል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የ2014/15 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ሲመረመር በርካታ ጉድለቶች በመገኘታቸው፣ በቋሚ ኮሚቴ አባል ወ/ሮ ጸሐይ በቀለ በኩል ከተነሱ ጥያቄ መካከል፣ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለዝቃጭ ማድረቂያ ከፍተኛ ማሽነሪ ከፈሳሽ ማጣሪያ ጋር የተቋቋመ ቢሆንም፣ ማሽነሪው ማድረቅ እየቻለ ቆሻሻውን የማድረቅ ሒደት በጸሐይ እንዲሆንና ለማድረቅ የተዘጋጀ ቦታ ሳይኖር መተላለፊያ መንገድ ላይ ተበትኖ በጸሐይ ኃይል በሚደርቅበት ወቅት በንፋስ ኃይል በመበተኑ፣ የአካባቢ ብክለት እያስከተለ መሆኑን በኦዲት ሪፖርቱ መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

የኢንዱስትሪያል ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ በምላሻቸው፣ ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተከማችቶ የሚገኝ ቆሻሻ ለንፋስ ሳይጋለጥ ሳይንቲፊክ በሆነ መንገድ መወገዱን ገልጸዋል፡፡

በሐዋሳ አካባቢ ያለውን የቆሻሻ አወጋገድ በተመለከተ፣ የዝቃጭ ማድረቂያ ማሽነሪ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ፍጆታ የሚፈልግ በመሆኑ በጸሐይ ብርኃን በመጠቀም ችግሩን ለመፍታት ማሽነሪን በክረምት ብቻ በመጠቀም ላይ ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስታንደርድ ባለመኖሩ፣ እንዲሁም ከማሽነሪው ይልቅ በጸሐይ ማድረቅ እስከተቻለ ድረስ አዋጭ በሆነ መንገድ መጠቀም ያስፈልጋል ሲሉ አቶ አክሊሉ ተናግረዋል፡፡

ከቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ እርሻ ማሳ የሚገባ ፍሳሽ እንዳለም በኦዲት ሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከተጠናላቸው አካባቢያዊና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናት ውጪ በሆኑ ዘርፎች ሲሰማሩ፣ ‹‹ተገቢው ጥናት አልተደረገም›› ሲል ቋሚ ኮሚቴው ላነሳው ጥያቄ ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት ካሉት 48 ፋብሪካዎች 33ቱ በግምገማ ላይ ናቸው የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

የኢንዱስትሪያል ፓርኮች ልሣት ኮርፖሬሽን ከቴክስታይልና ጋርመንት ውጪ ያሉ ፋብሪካዎች ወደ ፓርኩ ሲገቡ የኢንቫሮመንታል አሰስመንት የሠሩት 13 ብቻ የነበሩ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት 33 በማድረስ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 25ቱ በአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዕውቅና ያገኙ ናቸው ብለዋል፡፡

የአካባቢ ጥበቃ ጥናት ዕቅድን በተመለከተ የሚቆጣጠረው የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ሲሆን፣ ከአካባቢው ጋር የሚስማሙ ስለመሆናቸው ዕውቅና በመስጠት የሚፈቅደው አካል የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ነው ሲሉ አቶ አክሊሉ ገልጸዋል፡፡

በምርት ሒደት ፋብሪካዎቹ የሚጠቀሙባቸውን ኬሚካሎች ይዘት ለኮርፖሬሽኑና ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሚያሳውቁበት መመሪያ አለመኖሩ ከቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ ተነስቷል፡፡

ኬሚካል አጠቃቀምን በተመለከተ በኮርፖሬሽኑ ሁሉም ፋብሪካዎች በአንድ የሚጠቀሙት የጋራ የቆሻሻ ማስወገጃ ማሽነሪ መሆኑንና እያንዳንዱ ፋብሪካ የግሉን የቆሻሻ ማጣሪያ የመገንባት ግዴታ የለበትም ሲሉ አቶ አክሊሉ ለጥያቄው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በየፓርኩ የሚገኘው ቆሻሻ ማጣሪያ በአግባቡ እንደሚሠራ ማረጋገጥ ያስፈልጋል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ለቆሻሻ ማስወገድ የሚጠቅመው ኬሚካል ዋጋ ውድ መሆኑ አንድ ችግር እንደነበር ገልጸዋል፡፡

የኬሚካል ግዢን በተመለከተ በፊት ይጣል የነበረውን ቀረጥ በገንዘብ ሚኒስቴር ውሳኔ እንዲነሳ በማድረግ ኮርፖሬሽኑ ለኬሚካል ግዢ 404 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሺእመቤት ደምሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ከፓርኮቹ የሚወጡ ቆሻሻዎችና ፍሳሾች በአካባቢውና በማኅበረሰቡ ላይ ተፅዕኖ የማያሳድር መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ጊዜያዊ የማጣሪያ ታንከር የሌላቸው የደብረ ብርሃንና ባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርኮች የታንከር ግንባታ በአፋጣኝ ሊጠናቀቅ ይገባል ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ በኦዲት የድርጊት መርሐ ግብሩ መሠረት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ሊሠራ እንደሚገባው የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ተናግረዋል።

ኮርፖሬሽኑ ለፈሳሽ ቆሻሻ ማከሚያ ያወጣው ወጪና ከአልሚዎች የሰበሰበው ገንዘብ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ተገቢውን ታሪፍ እንዲያዘጋጅም አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች