Wednesday, May 29, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዲስ የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ በተያዘው ዓመት ተግባራዊ ሊደረግ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በ2014 ዓ.ም. ተጀምሮ የነበረው አዲስ ኤሌክትሪክ ኃይል የታሪፍ ማሻሻያ ጥናት ተጠናቆ፣ በተያዘው ዓመት ተግባራዊ እንደሚደረግ ታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና አገልግሎት በጋራ በዓለም ባንክ ድጋፍ በውጭ አማካሪ ድርጅት ያስጀመሩት ጥናትና የተዘጋጀው አዲሱ የታሪፍ ፖሊሲ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ካፀደቁት በኋላ፣ በተያዘው ዓመት ሦስተኛው ሩብ ዓመት ላይ ተግባራዊ ሊያደርጉት እንደሚችሉ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኃላፊዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡

ሪፖርተር በሐምሌ 2014 ዓ.ም. አቅርቦት በነበረበት ዘገባ መንግሥት የታሪፍ ማሻሻያውን ለማድረግ ጥናት ማስጠናት ጀምሮ እንደነበር፣ በወቅቱም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኃላፊዎች በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ያለው ታሪፍ የዋጋ ንረትን ያላገናዘበና በኑሮ ውድነት እየተዋጠ›› እንደነበረ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ (ኢንጂነር) የታሪፉ ማሻሻያው ያለበትን ደረጃ ሲገልጹ፣ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸጥበት ታሪፍ ወጪን ያላማከለና በኢነርጂ ዘርፉ መዋዕለ ንዋይ ለሚያፈሱ ባለሀብቶች በቂ ክፍያ የማያስገኝ ነው ብለዋል፡፡

‹‹በኢነርጂ ዘርፉ ላይ ለእኛ አንደኛውና ትልቁ አስቸጋሪ ነገር ታሪፍ ነው፤›› ሲሉ በኢነርጂ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ባለሀብቶችና አማካሪዎች የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ማሻሻያው ይህንን እንደሚቀርፍና በተያዘው ዓመት በሦስተኛው ሩብ ዓመት ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

አሸብር (ኢንጂነር) ይህንን የተናገሩት በራዲሰን ብሉ ሆቴል የእንግሊዝ ኤምባሲ ባዘጋጀው ሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በተካሄደው የዩኬ-ኢትዮጵያ አረንጓዴ ቴክኖሎጂ ፎረም ላይ ሲሆን፣ በዕለቱም በርካታ ከእንግሊዝ የመጡ በኢነርጂ ዘርፍ የተሰማሩ የግል ድርጅቶች፣ አማካሪዎችና ሌሎች የመንግሥት ተወካዮች ተገኝተው ነበር፡፡

በመድረኩ ላይ ተሳታፊ ከነበሩት የተወሰኑ ድርጅቶች ተወካዮች ታሪፉን በተመለከተ አለ ስለሚሉት ማነቆ ያላቸውን አስተያየት ተናግረው የነበረ ሲሆን፣ በማማከር ሥራ ላይ የተሰማራው ቬሪታስ የተባለ ድርጅት ኃላፊ በኢትዮጵያ ያለውን የኤሌክትሪክ ታሪፍ ከጎረቤት አገሮች ጋር በማወዳደር እንዴት ዝቅ እንደሚልና ምን ያህል በመንግሥት ድጎማ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

እንደ አማካሪ ድርጅቱ ኃላፊ ገለጻ፣ በኢትዮጵያ ለመኖሪያ ቤት የሚደጎመው የኤሌክትሪክ ኃይል ዋጋ በኪሎ ዋት ሰዓት (kWh) 0.035 ዶላር ሲሆን፣ በጎረቤት አገሮች ግን ከዚህ በእጅጉ ከፍ ይላል፡፡ በምሳሌ በጠቀሷቸው በኬንያ 0.16 ዶላር ሲሆን፣ በታንዛኒያ ደግሞ 0.14 ዶላር ነው፡፡

አሸብር (ኢንጂነር) እንደተናገሩት፣ እነዚህንና መሰል የታሪፍ ልዩነት ችግሮችን ለመቅረፍ ነው በዓለም ባንክ አጋዥነት የውጭ አማካሪ ኩባንያ በመቅጠር ጥናት የተደረገው፡፡፡ በአጥኚ ድርጅቱ የተዘጋጀውን የታሪፍ ፖሊሲ ማሻሻያ ለኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን በመላክ ማፅደቅ ቀጣይ ሥራ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

‹‹በእርግጥም በመጨረሻ ላይ የሚፀድቀው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው፤›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ‹‹ሒደቱ እየተጠናቀቀ ነው፣ በዚህ ዓመት ሦስተኛው ሩብ ዓመት ላይ ይፀድቃል ብለን እየጠበቅን ነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

ሪፖርተር ስለጉዳዩ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ኃላፊዎችን ለማነጋገር ቢሞክርም፣ ‹‹በአገልግሎቱ በኩል አዲስ ነገር እንደሌለና የማሻሻያው ሒደት እንዳልተጠናቀቀ፣ ወደፊት ግን ማሻሻያ ሊደረግ ይችላል፤›› የሚል መረጃ ብቻ ተገኝቷል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች