Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በነባር አከፋፋዮች አካባቢ አዳዲስ አከፋፋዮችን ያሰማራው ቢጂአይ ኢትዮጵያ ተቃውሞ ገጠመው

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ‹‹የሽያጭ ዞን አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜ በብቸኝነት የማሻሻል መብት አለኝ›› ቢጂአይ ኢትዮጵያ
  • ጉዳዩ ፍርድ ቤት ደርሶ ዕግድ ተሰጥቷል

የቢጂአይ ኢትዮጵያን ምርቶች ለዓመታት ሲያከፋፍሉ የነበሩና የቢጂአይ ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ወኪል አከፋፋይ አሠሪ ማኅበር ሥር የሚገኙ 36 አከፋፋዮች፣ ለማከፋፈል በተሰጣቸው አካባቢ አዳዲስ አከፋፋዮችን ማሰማራቱ፣ ከጅምሩ በድብቅ ይዞት የነበረውን ዓላማውን ለማስፈጸም የተደረገ እንቅስቃሴ ነው በማለት ቢጂአይ ኢትዮጵያ ላይ ቅሬታ አቀረቡ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንተርፕራይዝና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ከ14 ዓመታት በፊት የተመዘገበው ማኅበሩ፣ መጋቢት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተገለጸው፣ አንድ አከፋፋይ ተለይቶ በተሰጠው ቦታ (ግዛት) ላይ አዲስ አከፋፋይ በማምጣት ውል እየተጣሰ መሆኑንና አንድ አከፋፋይ የሚይዘውን ቦታ ለአራት የተለያዩ አከፋፋዮች እየተሰጠ መሆኑ አግባብ አለመሆኑን የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ስንታየሁ ገብረ ሥላሴ ተናግረዋል፡፡

በመላ አገሪቱ በማኅበሩ ሥር የሚገኙት 36 አከፋፋዮች እስከ ስድስት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የማከፋፈያ መጋዘን፣ 40 ቶን ድረስ የሚሸከሙ ተሽከርካሪዎች፣ የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ቢሮዎች፣ እንዲሁም 4,000 የሚጠጋ የሰው ኃይል ያላቸው ቢሆንም፣ ቢጂአይ ለአከፋፋዮቹ ለይቶ በሰጠው ግዛት ላይ ተጨማሪ አከፋፋይ ወኪሎች መጨመሩ አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡

በመግለጫው ዕለት የተገኙ የማኅበሩ አባላትና ወኪል አከፋፋዮች እንዳሉት፣ ቢጂአይ አዲስ ስትራቴጂ የማዘጋጀትና ከተጨማሪ አከፋፋዮች ጋር የመዋዋል መብት ያለው ቢሆንም፣ ይህን ማድረግ የሚችለው አሁን በሥራ ላይ ያለውን ውል ካጠናቀቀ በኋላ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

የአካፋፋዮቹን ቅሬታ በተመለከተ ሪፖርተር ለቢጂአይ ኢትዮጵያ ጥያቄ አቅርቦ፣ ቢጂአይ በምርት አከፋፋይነት ውል መሠረት የሽያጭ ዞን (Sales Territory) አስፈላጊ ሆኖ ባገኘው ጊዜ በብቸኝነት የማሻሻልና የመቀየር የውል መብት እንዳለው ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ‹‹ይህ የሚደረገው የድርጅቱን የገበያ ድርሻን በማሳደግ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማምጣት ነው፤›› ሲሉ የቢጂአይ ኢትዮጵያ ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ በኃይሉ አየለ ተናግረዋል፡፡

በማኅበሩ ሥር ያሉት አከፋፋዮች ላለፉት አሥር ዓመታት ከቢጂአይ ጋር ሲሠሩ የቆዩት በየዓመቱ በሚታደስ ውል ቢሆንም፣ ከወረቀት ውሉ ባለፈ በመተማመን የሚሠራ ሥራ ነበር ብለዋል፡፡

ነገር ግን ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ በቢጂአይ በኩል የተነሳ አዲስ የውል ሐሳብ በየዓመቱ የሚታደስ ሳይሆን፣ ለሁለት ወር ብቻ የሚቆይ ውል ማሰር እንደሚፈልጉ እንደተነገራቸው የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ስንታየሁ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ከቢጂአይ ጋር በአከፋፋይነት ከሚሠሩ የንግድ አጋሮች ጋር በተደረገው ውል፣ የሁለት ወራት ጊዜ ገደብ አለመኖሩን ቢጂአይ ኢትዮጵያ አስታውቋል፡፡

አከፋፋዮቹ ከቢጂአይ ጋር የተለያዩ ውይይቶች ካደረጉ በኋላ፣ በሐምሌ ወር ለሁለት ዓመት የሚቆይ ውል ማድረግ እንደተቻለ ግን አቶ ስንታየሁ ይናገራሉ፡፡

ሪፖርተር የደረሰው የአንድ አከፋፋይ ውል ሰነድ አንቀጽ 12 እንደሚገልጸው ከሆነ፣ ውሉ ከሐምሌ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሐምሌ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. እንደሚቆይ ይገልጻል፡፡ 

በዚህ ውል መሠረት የአከፋፋዩ መሠረታዊ ሥራ ምርቱን በገበያው ውስጥ ማድረስ ሲሆን፣ ቢጂአይ የማስታወቂያ ሥራዎችን በውስጥ ሴልስ የሚያሠራ መሆኑን ይገልጻል፡፡

አከፋፋዮቹ በአሁኑ ወቅት የተገለጸላቸው ግልጽ የውል ማቋረጥ ጉዳይ አለመኖሩን በመግለጽ፣ ቢጂአይ ለረጅም ዓመታት የቆየነውን አከፋፋዮች በተሰጣቸው ግዛት ውስጥ ተጨማሪ አከፋፋዮች እንዲገቡ ከማድረጉም በተጨማሪ፣ ካለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ የትራንስፖርት ነዳጅ ታሪፍ እንዲሻሻል ጥያቄ ሲያቀርቡ ቢቆዩም ምላሽ አለመስጠቱ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡

አከፋፋዮቹ ሲጠይቁት የነበረውን የአገልግሎት ክፍያ በተመለከተ ማንኛውንም የክፍያ ጥያቄ በተገቢው ሁኔታ የተሟላ ዶክመንት ለሚያቀርቡ አከፋፋዮች ጊዜውን ጠብቆ እየከፈለ መሆኑን በመግለጹ ቢጂአይ ኢትዮጵያ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ሪፖርተር የደረሰው የአከፋፋይና የቢጂአይ የውል ሰነድ አንቀጽ ዘጠኝ እንደሚያሳየው፣ ውሉን በጋራ ስምምነት ስለማቋረጥ የሚመለከት ሲሆን፣ ቢጂአይና አከፋፋዩ የማከፋፈያ ውሉን በጋራ ስምምነት የማቋረጥ መብት አላቸው ይላል፡፡

በተጨማሪም በአንቀጽ አሥር፣ ያለ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ውሉን ወዲያውኑ ስለማቋረጥ በተመለከተ፣ ቢጂአይ ወዲያውኑ ማቋረጥ የሚችለው የአከፋፋዩ ንግድ ፈቃድ ከተሰረዘ፣ ሌላ ምርት ይዞ ከተገኘ፣ ችሎታው ከቀነሰ፣ ኪሳራ ከገጠመው፣ እንዲሁም ከተመደበበት ግዛት ውጪ ምርት ሲሸጥ ወዲያውኑ የማቋረጥ መብት እንዳለው መሆኑን ያስረዳል፡፡

የቢጂአይ ወኪል አከፋፋዮች ተደጋጋሚ ቅሬታቸውን በመያዝ ወደ ድርጅቱ ኃላፊዎች ይዘው የቀረቡ ቢሆንም፣ ቅሬታቸው ምላሽ ባለማግኘቱ ለከፍተኛ ኪሳራ እንዳይጋለጡ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተር ያገኘው የፍርድ ቤት ሰነድ እንደሚያሳየው ከሆነ፣ በታኅሳስ ወር 2016 ዓ.ም. ከፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ በተሰጠ ትዕዛዝ መሠረት፣ ክሱን የመሠረቱት አከፋፋዮች የግልግል ዳኝነት አቤቱታ እስከሚያቀርቡ ድረስ፣ ‹ተጠሪ› የሆነው ቢጂአይ ኢትዮጵያ የቦታ ሽንሸና እንዳይፈጽም ለአንድ ወር ታግዷል፡፡

ከአንድ ወር ቆይታ በኋላ ቢጂአይ ኢትዮጵያ ዕግድ እንዲነሳላት አቤቱታ ቢያቀርብም፣ የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕግዱ ባለበት እንዲቆይ፣ የፍርድ ቤቱ የንግድና ኢንቨስትመንት ሦስተኛ ምድብ ችሎት ወስኗል፡፡

አፈጻጸማቸው መልካም ከሆኑና የቢጂአይን እሴትን በማክበር አብሮ ለመሥራት ፈቃደኛ ከሆኑ አከፋፋዮች ጋር፣ ሁሌም እየሠራ ይቀጥላል ሲል ቢጂአይ ኢትዮጵያ ምላሽ ሰጥቷል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች