Saturday, April 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

አገር ከመከራ ዓውድማ ውስጥ እንድትወጣ መፍትሔ ይፈለግ!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተከታታይ ያነጋገሯቸው የክልሎች፣ የቤተ እምነቶችና የንግድ ማኅበረሰቦች ተወካዮችና መሪዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በርካታ ጥያቄዎች፣ ማሳሰቢያዎችና አስተያየቶች ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ የአገር ሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ያልተነሳበት መድረክ አልነበረም ማለትም ይቻላል፡፡ ቁጥራቸው ባይበዛም ሰላም ለማስፈን ሽምግልና ውስጥ ለመሳተፍ ፈቃደኛ የሆኑ ግለሰቦችም ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡ በአዛውንትነት ዕድሜ ላይ ያሉ ዜጎች የአገር ሰላም ማጣት አሳስቧቸው ራሳቸውን ለሽምግልና ማጨታቸው የሚጠበቅ መልካም ተግባር ነው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተወያዩት ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች አዛውንቶችና የቤተ እምነት ተወካዮች ተባብረው፣ የሽምግልና ሚናቸውን እንዲወጡ ለማድረግ የሚረዳ ግንኙነት ቢፈጥሩ ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በጣም ውስብስ የሚባል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሆነች ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ፣ የውጭዎቹ ሳይቀሩ በከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ሆነው ኧረ እባካችሁ እያሉ ነው፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያ የሁለት ዓመታት ደም አፋሳሽና አውዳሚ ጦርነት በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ቢገታም፣ ከዚያ አስጨናቂና አስደንጋጭ ሰቆቃ የዞረ ድምር ውስጥ ሳይወጣ በአማራ ክልል ከባድ ጦርነት ተጀምሮ ዕልቂቱና ውድመቱ መቀጠሉ ያሳዝናል፡፡ በኦሮሚያ ክልልም በተመሳሳይ በተለያዩ ሥፍራዎች ውጊያ እየተካሄደ ነው፡፡ ይህ ሁሉ አልበቃ ብሎ በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል ሌላ ዙር ጦርነት ሊያስነሳ የሚችል ንትርክ ተጀምሯል፡፡ መፍትሔ ያላገኘው የግዛት ይገባኛል ሙግት ከሰሞኑ ሁለቱን ክልሎች እንደገና አደገኛ ምዕራፍ ውስጥ ለማስገባት ዳር ዳር እያለ ነው፡፡ ከሁለቱም ክልሎች እየወጡ ያሉ መግለጫዎች ችግሩን አባብሰው ወደ ለየለት ጦርነት ከመክተታቸው በፊት፣ በፍጥነት መፍትሔ የሚፈለግባቸው ሰላማዊ አማራጮችን መቃኘት ይገባል፡፡ ከዚህ ቀደም የፈሰሰው የንፁኃን ደም ሳይደርቅና ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ወገኖች ሳያገግሙ ጦርነት ለመጀመር ማሰብ ጤነኝነት አይደለም፡፡

በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለዘመናት ሲሠራባቸው ከኖሩ አገር በቀል መልካም እሴቶች መካከል አንደኛው ሽምግልና በመሆኑ፣ በሁሉም ቤተ እምነቶችና ኅብረተሰቦች ዘንድ እምነት የሚጣልባቸው የዕድሜ ባለፀጋዎች አገርን ከመከራ ዓውድማነት እንዲያላቅቁ ግፊት መደረግ አለበት፡፡ አገር ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰላሟ ተገፎ የለየለት የመፍረስ አደጋ ውስጥ ከመግባቷ በፊት፣ የአገራቸው ዕጣ ፈንታ የሚያሳስባቸው ዜጎች በሙሉ ችግሮች በድርድርና በዕርቅ እንዲፈቱ ዕገዛ ያድርጉ፡፡ ግራና ቀኝ ሆኖ ጎራ በመለየት የሚከናወነው ድርቅና የተሞላበት ሽኩቻ፣ አገር ከማፍረስ የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው መገንዘብ ይገባል፡፡ በዚህ ድርጊት የተሰማሩ የጎራ ፖለቲከኞችም ሆኑ አጃቢዎቻቸው አሸናፊና ተሸናፊ ከሌለበት ሕዝብ አስጨራሽና አገር አውዳሚ ድርጊቶች ታቅበው፣ የመከራ ዓውድማ የሆነችው ኢትዮጵያ በፍጥነት ከገባችበት አዘቅት ውስጥ እንድትወጣ ትብብር ያድርጉ፡፡ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ይገንዘቡ፡፡

በተለያዩ ሙያዎች የተሰማሩ ዜጎችም ‹‹ፖለቲካና ኮረንቲ›› ከሚባለው አጉል ፍርኃትና የዳር ተመልካችነት በመላቀቅ፣ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እየገባች ያለችውን አገራቸውን ለመታደግ አስተዋፅኦ ለማበርከት ይድፈሩ፡፡ ዳሩ መሀል፣ መሀሉ ደግሞ ዳር እየሆነ ባለበት በዚህ ጊዜ አሸዋ ውስጥ ጭንቅላቷን በመቅበር ለመደበቅ እንደምትሞክረው ሰጎን፣ ‹‹ጎመን በጤና›› በማለት መሸሽ የማይቻልበት ጊዜ ላይ ተደርሷል፡፡ እኔና ቤተሰቤ ላይ ምንም እስካልደረሰ ድረስ ተብሎ የአገርን ጉዳይ ለሌሎች መተው አይቻልም፡፡ የአገር ጉዳይ የሁሉም ዜጎች ኃላፊነት ስለሆነ ሰላም በማስፈን በእኩልነት ለመኖር የሚያስችል መፍትሔ መፈለግ የግድ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ጦርነት ሳይሆን በሰላም ተከባብሮ መኖር፣ በሕግ ፊት በተግባር የተረጋገጠ እኩልነትና የጋራ ተጠቃሚነት ነው፡፡ ይህ ዕውን መሆን የሚችለው ግን ሁሉም ዜጎች መብታቸውን ብቻ ሳይሆን ግዴታቸውን ሲወጡ ነው፡፡

በንግድና በኢንቨስመንት የተሰማራችሁ ወገኖችም እንደ ሌሎች ወገኖቻችሁ ኃላፊነት እንዳለባችሁ ተረዱ፡፡ መድረኩ ሲገኝ መሬት፣ የባንክ ብድር፣ የውጭ ምንዛሪ፣ ከቀረጥ ነፃ ዕድልና የመሳሰሉትን መጠየቅ ብቻ ሳይሆን በንፅህና ሠርታችሁ አገር ማገልገልን በተግባር ማሳየት አለባችሁ፡፡ ግብር ከመሰወርና ከማጭበርበር መታቀብ፣ የኮንትሮባንድ ንግድን ዕርም ብሎ መተው፣ ከባለሥልጣናትና ቤተሰቦቻቸው ጋር መነገድና መጠቃቀምን ማቆም፣ ምርቶችን በገፍ በመደበቅ ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት መፍጠርና ገበያውን በዓድማ መቆጣጠር መግታት፣ ለአገርና ለወገን የማይበጁ ኢሞራላዊ ድርጊቶችን መፀየፍና ለመሳሰሉት ልዩ ትኩረት ስጡ፡፡ እናንተ ተመቸን ብላችሁ እንዳሻችሁ ስትሆኑ ለልጆቻችሁ የምትሆን አገር እንዳታጡ ተጠንቀቁ፡፡ የሥራዎቻችሁ ዓላማ፣ ተልዕኮና ግብ በአቋራጭ መበልፀግ ሆኖ አገር የራሷ ጉዳይ ካላችሁ ያከማቻችሁት ሀብትና ንብረት መና ሆኖ እንደሚቀር ተረዱ፡፡ ለአገር ሰላም ስትሉ መልካም ሁኑ፡፡

የኢትዮጵያ ምሁራንና ልሂቃን ከዚህ ቀደም ቢጤዎቻችሁ ተማሩ፡፡ የእናንተ ቢጤዎች ከዚህ በፊት አብዮት በማስነሳት የፈጸሙት ስህተት አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ብዙዎቻችሁም በተለያዩ ጎራዎች ውስጥ ሆናችሁ ከተለመደው ስህተት ውስጥ ለመውጣት ፈቃደኛ አይደላችሁም፡፡ እናንተ ያዋጣናል ብላችሁ በምታምኑበት መንገድ መውረግረግን እንጂ፣ ከትናንት ስህተት ለመማር ግን አሁንም ፈቃደኛ አይደላችሁም፡፡ አገር እናድን ብለው ሽማግሌዎች ሲነሱ እነሱን አዋክባችሁ ከመድረኩ ለማጥፋት ማንም አይቀድማችሁም፡፡ ነገር ግን የእነሱን ሚና ለመተካትም ሆነ መልካም ሥራ ለማከናወን ግን እርስ በርስም አትስማሙም፡፡ በዚህና በሌሎች መሰል ምክንያቶች ከተመቻችሁ ፓርቲ ወይም የፖለቲካ ቡድን እየተጠጋችሁ ሥልጣን ወይም ጥቅም ማነፍነፍ የዘወትር ተግባራችሁ ነው፡፡ አሁንም ጊዜው ቢረፍድም ከብልሹው ድርጊታችሁ ታቀቡ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ከምንም ነገር በላይ የሚያስፈልጋት ሰላም ስለሆነ፣ ከመከራ ዓውድማ ውስጥ እንድትወጣ ለመፍትሔ ተረባረቡ! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...