Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ 52 ግለሰቦች ላይ የሽብርተኝነት ክስ ተመሠረተ

አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ 52 ግለሰቦች ላይ የሽብርተኝነት ክስ ተመሠረተ

ቀን:

ፍትሕ ሚኒስትር የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀ እና ለ)ን፣ አንቀጽ 35 እና 38ን እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 3(2) ድንጋጌን ተላልፈው ተገኝተዋል ያላቸውን፣ የኢዜማ ከፍተኛ አመራር የነበሩትን አቶ ጫኔ ከበደን፣ የባልደራስ አመራር የነበሩትን አቶ እስክንድር ነጋን (በሌሉበት)፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል የነበሩትን አቶ ዮሐንስ ቧያለው፣ የአብን የፓርላማ አባል የሆኑትን አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል የሆኑት ካሳ ተሻገር (ዶ/ር)፣ አቶ ዘመነ ካሴን (በሌሉበት) ጨምሮ 52 ግለሰቦች ላይ ክስ መሠረተ፡፡

መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሕገ መንግሥትና ሽብር ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ተከፍቶ መጋቢት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ለተከሳሾች የተሰጣቸው ክስ እንደሚያብራራው፣ ተከሳሾቹ የፖለቲካ ርዕዮትን በኃይል ለማስፈጸም አስበው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ቀደም ብሎ በመዝገብ ቁጥር 309200 ተከሰው በክርክር ላይ ያሉት ተከሳሾች ያደራጁትንና ‹‹የአማራ ፋኖ አንድነት ምክር ቤት›› በሚል በህቡዕ ያደራጁትን ዓላማ ለማስፈጸም መንቀሳቀሳቸውን ያብራራል፡፡

አማራ ‹‹አገር ተወስዶበታል፣ ርስቱንም ተቀምቷል፣ አገሪቱ በአማራ ትውፊቶችና እሳቤ ብቻ አልተደራጀችም›› የሚል አቋም በመያዝ፣ ተከሳሾቹ በሙሉ፣ የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ወንድም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር በአንድነት የአገር ባለቤት ሆኖ እያለ፣ ‹‹የአማራ ርስት ናቸው›› ያላቸውን መሬቶች በወታደራዊ ኃይል ለማስመለስና አገር ‹‹በአማራ አስተሳሰብ ብቻ መገዛት አለባት›› በማለት መስማማታቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አገርን በአማራ እሳቤ ብቻ ማስተዳደር የሚቻለው፣ በቅድሚያ በኃይል ዕርምጃ የአካባቢ አስተዳደሮችን በመያዝና የአማራ ክልል መንግሥትን በኃይል ከሥልጣን በማስወገድና የክልሉን ሥልጣን በኃይል በመያዝ፣ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመደራደር ወይም ለመደራደር ፈቃደኛ ካልሆነ በኃይል ዕርምጃ ለማስወገድ መስማማታቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆንና የያዙት ርዕዮተ ዓለም ተግባራዊ እንዲሆን (ለመተግበር) በአማራ ፋኖ አንድነት ምክር ቤት በቀረጹት የስትራቴጂ ሰነድ ላይ በመስማማት ለማስፈጸም፣ የአማራ ፋኖ አንድነትን የምሥራቅ አማራ፣ የሸዋ፣ የጎጃምና የጎንደር አማራ በሚል አራት ቦታ ተደራጅቶ በተለያየ መልኩ ለመምራት መስማማታቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡

አቶ ዮሐንስ ቧያለው እራሳቸውን ቀደም ብለው በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በመዝገብ ቁጥር 309200 የተከሰሱትን ግለሰቦች በመተካት፣ ራሳቸውን ለሽብር ኃይሉ የፖለቲካ ተወካይና ስትራቴጂካዊ አመራር አድርገው በመሰየም፣ አመራር ሲሰጡ እንደነበር ፍትሕ ሚኒስቴር በክሱ ዘርዝሯል፡፡

አቶ ክርስቲያንና ቀድመው ከላይ በተጠቀሰው የክስ መዝገብ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች፣ ቀድመው ስትራቴጂ ቀርጸውና የሽብር ቡድን የፖለቲካ ኃይል ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩ ተከሳሾች መያዛቸውን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀምና እነርሱን በመተካት፣ የሽብር ኃይሉ የፖለቲካ ተወካይና የስትራቴጂ አመራር በመሆን ጎጃም አካባቢ ለሚንቀሳቀሰው ቡድን አመራር ምክር ይሰጡ እንደነበር ክሱ ያስረዳል፡፡

የኢዜማ ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ጫኔ ከበደና ሌላው ተከሳሽ አቶ በላይ አዳሙ የተባሉት ተከሳሾች ዳግም፣ በሌሎች ተጠርጣሪዎች የተቀረጹ ስትራቴጂዎችን አገራዊ ይዞታ እንዲኖራቸው ለማድረግና የክስ ስትራቴጂ አፈጻጸም በአማራ ክልል ብቻ ታጥሮ እንዳይቀርና አገራዊ እንዲሆን፣ ‹‹የኢትዮጵያን አንድነት ግንባር (ኢአግ) የተባለ ህቡዕ የሽብር ቡድን በማደራጀት፣ አገር አቀፍ የሆነ ስትራቴጂ በመቅረጽ ለማስፈጸም ስምምነት እንዲያገኝ የማግባባት ሥራ መሥራታቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

አቶ በላይ አዳሙና አቶ ጫኔ ከበደ በጋራ በመሆን በአማራ ክልል በትጥቅ የተደገፈ የሽብር ድርጊት የሚፈጽም ቡድንን ለመምራትና የሽብር ድርጊቱን አገራዊ ለማድረግ እንዲረዳ፣ ከላይ የተጠቀሰውን የህቡዕ ድርጅት ማቋቋማቸውን ክሱ አክሏል፡፡

አቶ በላይ አዳሙ የተባሉት ተከሳሽ ከሌሎች ተከሳሾች ጋር በአካልና በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች በመገናኘትና በመወያየት፣ ከሰኔ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ አካባቢ ለሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድን አመራሮች፣ ስልክ በመደወልና ወደ አንድ ዕዝ በማምጣት በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲያስተባብሩ እንደነበር ክሱ ያብራራል፡፡ ተከሳሹ በአዲስ አበባ ከተማ የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ ለማስቀጠልና ሽብር ለመፍጠር በማሰብ፣ በከተማው ውስጥ በበጎ አድራጎት ማኅበር ስም የሽብር ቡድኑን ዓላማ አንግቦ በህቡዕ የሚንቀሳቀሰውንና ከላይ የተቀሰውን ቡድን ሲያደራጁና ሲመሩ እንደነበር ፍትሕ ሚኒስቴር በክሱ አብራርቷል፡፡

ጫኔ ከበደ የፖለቲካ ወይም የርዕዮተ ዓለም ዓላማ ለማራመድ የሕዝብ ወይም ሕዝብን ለማሸበርና መንግሥትን ለማስገደድ፣ በአማራ ክልል በተለያዩ ቦታዎች የሚንቀሳቀሱ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ከሌሎች የሽብር ቡድን አመራሮች ጋር በመሆን፣ በማደራጀትና በመምራት ላይ መሳተፋቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡

ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ በተከታታይ ቀናት በአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች ተነስቶ የነበረውን አመፅና የሽብር ድርጊት፣ በአዲስ አበባ ለማስቀጠል ማንነታቸው ካልታወቁ ግለሰቦች ጋር በመሆን፣ በከተማው ላይ የሽብር ድርጊት ለማስቀጠል ‹‹የአዲስ አበባ ፋኖ›› የሚሏቸውን ግለሰቦች በማሰባሰብና በማደራጀት መመርያ ሲሰጡ እንደነበር ክሱ ይተነትናል፡፡

አቶ እስክንድር ነጋ በአስር ላይ የሚገኙትንና በሌላ የክስ መዝገብ ክስ የተመሠረተባቸውን እነ ወንድወሰን አሰፋ (51 ሰዎች)፣ በወንጀል መከሰሳቸው ምክንያት በማድረግ ‹‹የአማራ ፋኖ አንድነት ምክር ቤት የፖለቲካ አመራሮች በመታሰራቸው፣ ትግሉ እንዲቀጥል አዲስ አደረጃጀት ያስፈልጋል›› በማለት፣ የአማራ ሕዝባዊ ግንባር የተባለ የሽብር ቡድን በአማራ ክልል ደብረ ኤልያስ አካባቢ የመሠረቱና ራሳቸውን የግንባሩ መሪ ማድረጋቸውንም ክሱ ያብራራል፡፡

በደብረ ኤልያስ አካባቢው ላይ የሚንቀሳቀስ ‹‹በረኸኛው›› የሚል የጦር ብርጌድ ማቋቋማቸውንና ብርጌዱን በደብረ ማርቆስና አካባቢው ላይ ጥቃት እንዲፈጽም ትዕዛዝ መስጠታቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

የፌዴራልና የክልሉን የፀጥታ ‹‹ኃይል ለመስጠት›› በሚል ከሐምሌ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉ ተከታታይ ቀናት ውስጥ፣ በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ለሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድን አመራሮች፣ ማለትም በጎጃም አሰግድ መኮንን፣ በወሎ ፋንታሁን ሙሀባ፣ በሸዋ አበበ ፈንታው፣ ድርሳን ብርሃኔና ሀብታሙ ደምሴ ለሚባሉ ተከሳሾች፣ የገንዘብ ድጋፍና የተለያዩ መሣሪያዎችን በመስጠት በክልሉ የዞን ከተሞች ውስጥ ባሉ በመንግሥት ኃይሎች ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙ ማስተባበራቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

አቶ ዘመነ ካሴ የተባሉት ተከሳሽ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በመገናኘትና በመወያየት የሌሎች ተከሳሾችን ድርጊትና የሚሰጠውን ውጤት በመቀበል መንግሥትን በኃይል ዕርምጃ ከሥልጣን ለማስወገድ በማሰብ፣ ‹‹የአማራ ሕዝባዊ ኃይል›› የሚል የሽብር ቡድን በማቋቋምና ራሱን መሪ በማድረግ በደብረ ማርቆስና አካባቢው፣ በቢቸና፣ በደብረ ወርቅ፣ በመርጦ ለማርያም፣ በሞጣ፣ በመራዊ፣ በባህርዳርና በሌሎች የምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች፣ የሰላም ማስከበር ሥራ በሚሠሩ የፀጥታ አስከባሪ አባላትና የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ማስተባበሩንና መምራቱን እንዲሁም ማስፈጸሙን ክሱ ያብራራል፡፡

በአጠቃላይ ሁሉም ተከሳሾች በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ በመተላለፍ፣ በወንጀል ድርጊት በመተባበር በሽብር ወንጀል የመሳተፍ የወንጀል ክስ እንደተመሠረተባቸው የክስ ዝርዝሩ ያብራራል፡፡ ተከሳሾቹ መጋቢት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ፍርድ ቤት ቀርበው የክስ ቻርጁ የተሰጣቸው ሲሆን፣ ክሱን በንባብ ለማሰማት ለመጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...