Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንግድ ማዕከላት ባለቤት የሆኑ አክሲዮን ማኅበራት ላይ የተለያዩ የግብር ግዴታዎች ተጣሉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የገቢዎች ሚኒስቴር በንግድ ማዕከልነት የሚያገለግሉ ሕንፃዎችን በጋራ ገንብተው በባለቤትነት የሚያስተዳድሩ አክሲዮን ማኅበራት፣ የተጨማሪ እሴት ታክስና የዲቪደንድ (የትርፍ ድርሻ) ታክስን ጨምሮ የተለያዩ የግብር ዓይነቶችን እንዲከፍሉ ወሰነ።

በንግድ ማዕከልነት የሚያገለግሉ ሕንፃዎችን ገንብተው በባለቤትነት የሚያስተዳድሩ አክሲዮን ማኅበራት የሕንፃውን ሱቆች በማከራየት ከሚያገኙት ገቢ ላይ ለሚገኙበት ከተማ ወይም የአካባቢ አስተዳደር የኪራይ ገቢ ግብር ብቻ ሲከፍሉ ቆይተዋል። የገቢዎች ሚኒስቴር በአክሲዮን ማኅበራት ባለቤትነት ሥር የሚገኙና የሚተዳደሩ የንግድ ማዕከላት ላይ ጥናት ያካሄደ ሲሆን፣ የጥናቱ ግኝትም፣ አክሲዮን ማኅበራቱ በሕግ የተጣለባቸውን ግብር በተገቢው መንገድ እየተወጡ አለመሆናቸው መረጋገጡን ከሚኒስቴሩ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ሚኒስቴሩ በጥናት የደረሰባቸውን ግኝቶች መሠረት በማድረግ ሊወሰዱ ይገባል ያላቸውን የማስተካከያ ዕርምጃዎች የተመለከተ ምክረ ሐሳብ ለመንግሥት አቅርቦ በቅርቡ ተቀባይነት ማግኘቱንም መረጃው ይጠቁማል።

በዚህም መሠረት፣ በአክሲዮን ተደራጅተው የተገነቡና በንግድ ማዕከልነት የሚያገለግሉ ሕንፃዎች ባለቤት አክሲዮን ማኅበሩ በመሆኑ፣ የንግድ ማዕከሉን የሚመለከቱ የግብር ግዴታዎች ላይ ሙሉ ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት ተወስኗል። በመሆኑም በንግድ ማዕከልነት በሚያገለግለው ሕንፃ ውስጥ የሚገኙ ሱቆችን በማከራየት የሚገኘው ገቢ ላይ በግብር አዋጁ መሠረት የሚጣለውን የኪራይ ገቢ ግብር እንደ ከዚህ ቀደሙ በከተማ አስተዳደሮች እንደሚሰበሰብ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።

ይሁን እንጂ ሚኒስቴሩ ባካሄደው ጥናት አክሲዮን ማኅበራቱ በሚያስተዳድሯቸው የንግድ ማዕከላት ውስጥ የሚገኙ የንግድ ሱቆች ኪራይ ተመን ከወቅታዊ ገበያው በእጅጉ አነስተኛ መሆኑ፣ በርከት ያሉ ማኅበራትም በንግድ ማዕከሉ ውስጥ የሚገኙ ሱቆችን በርካሽ ዋጋ ለማኅበሩ አባላት እንዳከራዩ፣ ሌሎች በርከት ያሉ አክሲዮን ማኅበራት ደግሞ የባለቤትነት ማስተላለፍ ሥርዓቶችን ሳይከተሉ በንግድ ማዕከሉ ውስጥ የሚገኙ ሱቆችን እንደ አክሲዮን ድርሻ ለማኅበሩ አባላት አከፋፍለው መገኘታቸውን መረጃው ያመለክታል።

በመሆኑም፣ ከ2016 ዓ.ም. የግብር መክፈያ ወቅት ጀምሮ በንግድ ማዕከላቱ ውስጥ የሚገኙ ሱቆች የኪራይ ተመን በገበያ ዋጋ ተሰልቶ የኪራይ ገቢ ግብር እንዲከፍሉ መወሰኑን ለማውቅ ተችሏል።

በተጨማሪም፣ አክሲዮን ማኅበራቱ በባለቤትነት የያዙት የንግድ ማዕከል ውስጥ ከአንድ ሱቅ የሚያገኙት ዓመታዊ የኪራይ ገቢ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ከሆነ 15 በመቶ የተጨማሪ ዕሴት ታክስ፣ የኪራይ ገቢው ከአንድ ሚሊዮን ብር በታች ከሆነ ደግሞ አሥር በመቶ ተርን ኦቨር ታክስ ለፌዴራሉ ታክስ ሰብሳቢ ተቋም እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል። 

በሌላ በኩል በንግድ ማዕከሉ ውስጥ የሚገኙ የንግድ ሱቆችን ባለቤትነት በድርሻ መልክ ለአክሲዮን ማኅበሩ አባላት ያስተላለፉ እንደሆነ 15 በመቶ የካፒታል ገቢ (Capital Gain) ታክስ በማኅበራቱ ላይ እንዲጣል መወሰኑን መረጃው ያመለክታል።

በተጨማሪም፣ አክሲዮን ማኅበራቱ በንግድ ማዕከላቱ የሚገኙ ሱቆችን በማከራየት የሚያገኙትን ትርፍ እንደ አክሲዮን መጠናቸው ለማኅበሩ አባላት አከፋፍለው ከሆነ ይህ ተሰልቶ ባከፋፈሉት የትርፍ ድርሻ ላይ አሥር በመቶ የትርፍ ድርሻ ታክስ (ዲቪደንድ) እንዲከፍሉ ተወስኗል።

በዚሁ መሠረትም ከላይ የተመለከቱት ውሳኔዎች ከ2016 በጀት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረጉ መወሰኑን መረጃው ያመለክታል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች