Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወልጄ እንደማደጌና በርካታ አገሮችን የማየት ዕድል እንደማግኘቴ፣ የከተማችንም ሆነ የአገራችን መለወጥ እጅግ በጣም ደስ ከሚያሰኛቸው ዜጎች መካከል እመደባለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ የአዲስ አበባችን መለወጥና መዘመን ደስ የሚያሰኘኝ፣ አዲስ አበባ ስሟን የማትመጥን ከተማ ስለሆነች ነው፡፡ አዲስ አበባ እንደ ስሟ የተዋበች አበባ እንድትሆን ፈርሳ መሠረቷ የግድ ነው፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የዛገና የነተበ ከተማ ውስጥ መኖር ስለሚያሳፍር፣ አዲስ አበባ ውብና ፅዱ መሆን ይኖርባታል ብዬ እሞግታለሁ፡፡ ትናንት አንድ ሚሊዮን ያህል ዜጎቿ በዘር ጭፍጨፋ ያለቁባት ሩዋንዳ ዋና ከተማዋን ኪጋሊን ያየ ሰው፣ አዲስ አበባን በነበረችበት ትቀጥል ለማለት ድፍረቱ አይኖረውም፡፡ ምክንያቱም የአፍሪካ ኅብረትና የተመድ መሥሪያ ቤቶችና እነሱን ተከትለው የመጡ በሙሉ፣ ወደ ኪጋሊ ወይም ሌላ ቦታ ከመሰደድ እንደማይመለሱ ይታወቃልና፡፡ ምልክቶችም እየታዩ ነው፡፡

መንግሥት አዲስ አበባን ለመለወጥ የያዘው ግዙፍ ዕቅድ በምን ያህል በጀት እንደሚከናወን መረጃው ባይኖረኝም፣ ከተያዘው ሰፊ እንቅስቃሴ አኳያ ዳጎስ እንደሚል እገምታለሁ፡፡ በዚህ መጠን የአዲስ አበባን በርካታ አካባቢዎች እያፈረሰ ያለው መንግሥት ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ጥንቃቄ መጀመር ያለበት በልማት ስም የሚነሱ ወገኖችን ከመንከባከብ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ከኖሩበት መንደር ሲነሱ በመጀመሪያ በአገር አቅም የተመቹ መኖሪያዎችና መሥሪያ ቦታዎች ሊያገኙ ይገባል፡፡ በኖሩበት አካባቢ የነበራቸው መስተጋብር እንዳይበጣጠስ በተቻለ መጠን ተቀራራቢ ቦታዎች ላይ ቢሠፍሩ ይመረጣል፡፡ ልማቱ ለአፍ ያህል ‹‹ሰው ተኮር ነው›› ከማለት ይልቅ፣ በተግባር አሳይቶ የተቺዎችን አፍ ማዘጋት መቻል አለበት፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው ማድበስበስ ነገ ተጠያቂነት እንደሚያስከትል መታወቅ አለበት፡፡

እኔ ከላይ ያነሳኋቸው ሐሳቦች የራሴ ብቻ ሳይሆኑ ከብዙ ሰዎች ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ስንነጋገር በአማካይ የተስማማንበት መሆኑን መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ፒያሳ ሠራተኛ ሠፈርና ዶሮ ማነቂያ ይኖሩና ይሠሩ ከነበሩ የተለያዩ ሰዎች ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ስነጋገርም የሰጡኝ ሐሳብ ተመሳሳይ ነው፡፡ ስድስት ኪሎና ምኒልክ ሆስፒታል ዋናው መንገድ ላይ ንብረታቸው ፈርሶ ከተነሱ ሰዎችም ጋር ስወያይ ማንም ልማትን የጠላ አላጋጠመኝም፡፡ የሁሉም ሰዎች ሐሳብ ማዕከላዊ ጭብጥ ግን ልማቱ ደሃን ነቅሎ ሀብታም የመትከል ፍርኃት አለው፡፡ ይህንን ሐሳብ ሰፋ አድርገው ያብራሩልኝ በደርግ ዘመን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበሩና አሁን አሜሪካ ነዋሪ የሆኑ አንጋፋ ምሁር ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት የአካባቢ ልማት ዜጎችን በፍትሐዊነት ተጠቃሚ ማድረግ ሲሳነው፣ ድሆችን ነቅሎ ሀብታሞችን መትከል (Gentrification) ይጀመራል፡፡ መንግሥት እንዲህ ዓይነቱ አደገኛ ወጥመድ ውስጥ እንዳይገባ ይጠንቀቅ ነው ያሉኝ ምሁሩ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እሳቸው እንዳሉት ድሆችን ነቅሎ ሀብታሞችን የመትከል ድርጊት (Gentrification) በተለያዩ አገሮች ተከስቶ ከባድ ቀውስ ፈጥሯል፡፡ ይህ ድርጊት ከተማ በማሳመር ስም ሀብታሞች የተለቀቀውን መሬት በጉቦና በጥቅም ትስስር ተቀራምተው ዘመናዊ ቪላዎችና አፓርታማዎች፣ የንግድ ሕንፃዎችና የመዝናኛ ማዕከላት በማስፋፋት ተጠቃሚነታቸውን በእጥፍ ሲያሳድጉ የተፈናቀሉ ወገኖች ግን ለኑሮ ተስማሚ ያልሆኑ ቦታዎች ተጥለው ፍዳቸውን ይቆጥራሉ ማለት ነው፡፡ ቀደም ሲል ዝቅተኛ የገበያ ዋጋ የነበራቸው ቦታዎች በአንዴ ከፍተኛ ዋጋ የሚጠራባቸው ሆነው ጊዜ የሰጣቸው ሀብታሞች ሲከብሩ፣ ለዓመታት የኖሩባቸው ወገኖች ግን ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያ ሳያገኙ በግዴታ በልማት ስም በመነሳት በድህነት እንደሚማቅቁ ነው ያስረዱኝ፡፡ ለዚህም ነው መንግሥት ከተማዋን በፍጥነት ለመለወጥ ሲተጋ የነባር ነዋሪዎችን ጉዳይ ችላ ማለት የለበትም ያሉኝ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ የከተማዋ ከንቲባ ከነባር አካባቢዎች የሚነሱ ወገኖች ወደ ተሻሉ የመኖሪያ አካባቢዎች እንደሚዛወሩ ተናግረዋል፡፡ የተወሰኑ ተነሺዎች መልካም ዕድል እንደገጠማቸው በቴሌቪዥን ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ በሌላ በኩል ቤት ለመባል ያልበቁ ኮንዲሚኒየሞች የተሰጧቸው ወገኖች በተለያዩ ሚዲያዎች በምሬት ሲናገሩም ሰምቻለሁ፡፡ የተመቸ መኖሪያ ያገኙት በመደሰታቸው እኔም ተደሳች ነች፡፡ ነገር ግን በር፣ መስኮት፣ ውኃ፣ ኤሌክትሪክና የመሳሰሉ መሠረታዊ ነገሮች ሳይሟሉ ችላ የተባሉ ወገኖች ጉዳይ ግን ሁላችንንም ሊያሳስበን ይገባል፡፡ ‹‹ሰው ተኮር›› የተባለው የልማት ውጥን ‹‹ግማሽ ልጩ ግማሽ ጎፈሬ›› ሆኖ ቅሬታና ተቃውሞ እንዳያስነሳም ጥንቃቄ ይደረግ እላለሁ፡፡ እኔ አንድ ተራ ዜጋ የአገሬ ሰላምና ደኅንነት ስለሚያሳስበኝ መንግሥት ለዜጎች ትኩረት ይስጥ እላለሁ፡፡

በሌላ በኩል የከተማዋን መለወጥ ከፖለቲካ ዓላማ አኳያ በተለያዩ ዓውዶች መተንተኑ ለእኔ ምንም ችግር የለውም፡፡ ዋናው ነጥብ ግን የሁሉም ሐሳቦች ማዕከላዊ ነጥብ የአገር ልማትና ዕድገት ቢሆን ይመረጣል፡፡ ከዚህ ውጪ ለአገርና ለሕዝብ የማይጠቅሙ ንትርኮችና ከንቱ ነገሮች ቆመው፣ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በእኩልነት ማኖር ስለሚገባት አገርና ከተማ የልማት አማራጮች እንነጋገር፡፡ በመንግሥት ወገን ያላችሁ ባለሥልጣናትም ሆናችሁ ያገባናል ባዮች፣ የአገርን ልማት ከብሔርና ከእምነት ጋር እየሸራረባችሁ ሕዝቡ ውስጥ ክፍፍል አትፍጠሩ፡፡ የማንም ብሔር ተነቅሎ የማንም ብሔር እንደማይተከል፣ ነገር ግን ሁሉንም በኅብር የምታስተሳስር የጋራ ከተማ እንደምትኖረን አምናችሁ ለሥራ ተነሱ፡፡ ጥቂቶችን ለማጥገብ ሲባል በብሔርም ሆነ በእምነት ስም የሚደረግ አጉል ቅስቀሳ ለማንም አይጠቅምም፡፡ በተቃራኒው ያላችሁትም ከማይረባ ትርክትና ሕዝብ ከሚያራቅቅ ትንኮሳ ታቀቡ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰለቸው እንዲህ ዓይነቱ ፋይዳ ቢስ እሰጥ አገባ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የምታድገውና በዓለም ፊት ክብርና ሞገስ የምታገኘው በጠባብ ዕይታ በታጠረ ፍላጎት አይደለም፡፡ በውሸት፣ በሌብነት፣ በአጭበርባሪነት፣ በአስመሳይነትና በአጉል ፉከራም አይደለም፡፡ አዲስ አበባ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ጥሩ ከተማ መሆን የምትችለው ሥርዓት ባለው መንገድ ተገንብታ፣ ለመጪው ትውልድ ለመተላለፍ የሚያስችል ሁሉንም ወገኖች የሚያግባባ የጋራ ዓላማ ሲኖር ነው፡፡ አዲስ አበባ ፈርሳ ስትገነባ እንደተባለው የልማቱ ዓላማ ብዙኃኑን በመንቀል ጥቂቶችን የመትከል ከሆነ ግን፣ ቅራኔው እየሰፋና እያደገ የማይወጡበት ቅርቃር ውስጥ ይከታል፡፡ አንጋፋው ምሁር መንግሥት በዚህ ወሳኝ ወቅት ብልህ መሆን አለበት ይላሉ፡፡ በግራና በቀኝ ሰቅዘው የያዙትን አክራሪ ደጋፊዎችና ነቃፊዎች ችላ ብሎ፣ ከአርቆ አሳቢው ሕዝብ ጋር በግልጽ እየተነጋገረ ሥራውን ያከናውን፡፡ ደጋፊዎችን ለማስደሰት ተብሎ የሚሠራም ሆነ፣ የሚቃወሙትን ለማናደድ ተብሎ የሚከናወን ሥራ ከሕዝብ ጋር ያቀያይማል ነው ያሉት ምሁሩ፡፡ እኔም ይህ ሐሳብ ይደመጥ ነው የምለው፡፡

(ጥላሁን ዘመዴ፣ ከቀጨኔ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...