Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች ተብለው ከተመረጡ የንግድ ማኅበረሰብ ጋር ያደረጉት ውይይት አንዱ ነው፡፡ በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ከቀረቡ ጥያቄዎች ውስጥ የውጭ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ቤትና መሰል ንብረቶችን ለማፍራት የሚከለክለው ሕግ እንዲሻሻል፣ በሌሎች ንግድ ሥራዎች ለመሰማራትም ይኸው ክልከላ እንቅፋት እንደሆንባቸው የሚያመላክተው ይገኝበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በደፈናው መንግሥት የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ ንብረት እንዲያፈሩ የሚፈቅድ ሕግ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እንዲህ ያለው ሕግ መዘጋጀቱ አሉታዊና አዎንታዊ ተፅዕኖ አለው የሚሉ የተለያዩ አመለካከቶች ይንፀባረቃሉ፡፡ የውጭ ዜጎች ኢትዮጵያ ውስጥ ንብረት ማፍራታቸው ምን ዓይነት አንድምታ አለው? በሚለው ጉዳይ ላይና በውይይት መድረኩ የተነሱ አንዳንድ መረጃዎችን መነሻ በማድረግ፣ ዳዊት ታዬ ከኢኮኖሚ ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር) ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ለውጭ ዜጎች ክልክል የነበረ አንድ ሕግ እንደሚሻሻል ገልጸዋል፡፡ ይህም ሕግ የውጭ ዜጎችን ንብረት ማፍራትና ተያያዥ  መብቶችን የሚሰጣቸው ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ እንዲህ ያለው ሕግ ቢተገበር ምን ያህል ጠቀሜታ አለው?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- ቀድሞም ቢሆን ክልከላው ተገቢ አልነበረም፡፡ ክልከላው ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ በሌሎች አገሮች የውጭ ዜጎች ንብረት ማፍራት ይችላሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካ፣ ዚምባብዌ፣ ማላዊ፣ ኬንያና የመሳሰሉት ብንሄድ ክልከላ የለም፡፡ በኒውዮርክ ጭምር የውጭ ዜጎች ቤት መግዛት ይችላሉ፡፡ ቤት መግዛትና ባለቤት መሆን ምንም ችግር የለውም፡፡ ዱባይ የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲገዙ ትፈቅዳለች፡፡ ስለዚህ ይህ አሠራር በተለያዩ አገሮች የተለመደ ነው፡፡ በእኛ አገር በንጉሡ ጊዜ እሳቸው እየፈቀዱ ሰዎች ንብረት የሚገዙበት አሠራር ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ በኢሕአዴግ ጊዜ ኤምባሲዎችና ተቋማት ቤትና የመሳሰሉትን ለመግዛት ተፈቅዶላቸዋል፡፡ የውጭ ዜጎች በአገር ውስጥ ንብረት እንዳያፈሩ መከልከል አገሪቱን ጎድቷል ብዬ አምናለሁ፡፡ ማንኛውም ሰው እዚህ መጥቶ ንብረት ማፍራት ቢፈልግ በውጭ ምንዛሪ ስለሚገዛ እንዲህም ያለ ጠቀሜታ ሊሰጥ ይችላል፣ ይህም ጥቅም ነው፡፡ ሁለተኛ በተለይ ፕሮፌሽናሎች በዚህ አገር እንዲኖሩና አገር እንዲያግዙም ይረዳል፡፡ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የተቋቋመው፡፡ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት በፊት የተቋቋመ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች መጥተው የጡረታ ጊዜያቸውን ቢያሳልፉ ያካበቱትን ዕውቀት ሊያካፍሉና ሊያስተምሩ ይችላሉ፡፡

የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ሌላው እንደ ጥቅም የሚታየው እምነት የሚፈጥር በመሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም በደርግ ጊዜ መንግሥት ሙልጭ አድርጎ ንብረት ስለወረሰ ብዙ ኢንቨስተሮች ጥያቄ አላቸው፡፡ ሌላ መንግሥት መጥቶ እንዲህ የሚያደርግበት ምን ማረጋገጫ አለ የሚሉ ጥያቄዎች ያነሳሉ፡፡ እንዲያውም ከ15 ዓመታት በፊት የተሠራ አንድ ጥናት፣ ኢትዮጵያውያን በዚህ ጉዳይ ያላቸውን ምልከታ አሳይቶ ነበር፡፡ ልሂቃንም፣ ፖለቲከኞችም፣ የመንግሥት አስተዳደር ውስጥም ሰዎችም የውጭ ሰዎች መጥተው ይዘርፉናል፣ ይቀሙናል፣ ያጠፉናል፣ አገር ይወስዱብናል የሚል እምነት ነው ያላቸው እንጂ ሌላ አመለካከት የላቸውም የሚል ነገር አስፍሯል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት መቀየር አለበት፡፡ የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው ብዬ ነው የማምነው፡፡ በተለይ ሦስተኛ ትውልድ የሆኑ ረዥም ጊዜ የቆዩ የውጭ ዜጎች ሳይቀሩ ንብረት የማፍራት መብት ስላልነበራቸው ይኼ መታሰቡ ጥሩ ነው የሚል አመለካከት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ ቤትና መሰል ንብረቶችን እንዲገዙ መፍቀድና በባለቤትነት ንብረት እንዲያስተዳድሩ ማድረግ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት አለው የሚለውን ምልከታ የሚጋሩ አሉ፡፡ እንደተባለው ንብረት የማፍራት መብት የሚሰጠው ሕግ ሥራ ላይ ቢውል የዋጋ ንረትን የበለጠ ይጨምራል፣ የቤትና መሰል ንብረቶች ዋጋ እንዲወደድ ያደርጋል በሚል ሥጋታቸውን የሚናገሩ አሉ፡፡ ሕጉ ወጥቶ መተግበሩ በእርግጥ እነዚህ የተጠቀሱ ችግሮችን ያስከትላል?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- አሁንም እኮ ንብረት ያላቸው አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኤምባሲዎች ያሉባት የዓለማችን ሦስተኛ አገር ነች፡፡ እነዚህ ኤምባሲዎች ውስጥ ያሉ ዜጎች እኮ ከእኛው ጋር ተጋፍተው ነው ሽንኩርትና ቲማቲም የሚገዙት፡፡ የኑሮ ውድነቱ ያለ ነገር ነው፣ ሁሉንም የሚመለከት ነው፡፡ የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ የቤት ዋጋን ያስወድዳል የሚለው አመለካከት ትክክል አይመስለኝም፡፡ በኢትዮጵያ የቤት ኪራይ በጣም ከፍተኛ እየሆነ የሄደው ይከራዩ የነበሩ ቤቶች ቁጥር ጥቂት ስለነበሩ ነው፡፡ በተለይ የውጭ ዜጎች ሊፈልጓቸው ይችላሉ የሚባሉ ቤቶች ጥቂት በመሆናቸው ከፍተኛ የኪራይ ዋጋ ይጠየቅባቸዋል፡፡ ሕጉ ከተሻሻለ በኋላ የውጭ ዜጎች ቤት እንገዛለን ካሉ ልክ እንደ ዱባይ ለውጭ ሰዎች ተብሎ ቤቶች ሊገነቡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህ የውጭ ሰዎች ቤት የሚገነቡ ከሆነ ዋጋው ሊቀንስ ይችላል፡፡ የቤት ሽያጭ ብቻ ሳይሆን የቤት ኪራይ ዋጋም እየቀነሰ ይሄዳል የሚል ግምት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች የራሳቸውን ቤት በሚይዙበት ጊዜ የኪራይ ዋጋ ይቀንሳል፡፡ አሁን እኮ ኢትዮጵያውያን ከውጭ ዜጎች ጋር እየተወዳደሩ ነው የሚከራዩት፡፡ ስለዚህ የሚባለው ሥጋት አይታየኝም፡፡ ለምሳሌ እነሱ ቤት ገዝተው መጠቀም የሚችሉ ከሆነ ሊለወጡ የሚችሉ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ እኔ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በምሠራበት ወቅት በሄድኩባቸው አገሮች በሙሉ የሚሠሩ የተመድ ሠራተኞች ቤት ይገዛሉ፡፡ በዚያ አገር ሥራ ላይ የሚቆዩበት ጊዜ ቢበዛ ሦስት ዓመት ነው፣ ግን ቤት ይገዛሉ፡፡ ወደ ሌላ ቦታ ሲዛወሩ ደግሞ ቤቱን ያከራዩታል፡፡ ወይም ይሸጡታል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለው ሁኔታ ገበያው እንዲቀላጠፍ ያደርጋል፡፡  አዲስ አበባ የቤት ኪራይ ዋጋ ሰማይ የወጣበት አንዱ ምክንያት አከራዮች ለውጭ ሰዎች ቤት ሲያከራዩ በዶላር እየጠየቁ ጭምር በመሆኑ ነው፡፡ ሆቴሎችም በዶላር ነው የሚጠይቁት፡፡ ስለዚህ ለውጭ ዜጎች መብት የሚሰጠው ሕግ ከፀደቀ ጥቁር ገበያ አካባቢ ያለው ችግር የሚቀንስበት ዕድል ይኖራል፡፡ ባይሆን አንዳንድ የዲፕሎማቲክ ጥቅማ ጥቅሞች ገበያውንም እያቃወሱት ስለሆነ፣ ከዚህ ጋር አብረው የሚመጡ ሌሎች ችግሮች ካሉ እነሱን ለመቆጣጠር ሥርዓት መዘርጋት እንጂ ዝም ብሎ ሕጉ ይጎዳል ማለት ተገቢ አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ከእርስዎ ገለጻ የተረዳሁት የሕጉ መውጣት ምንም ችግር የሌለው መሆኑን ነው፡፡ ግን ምንም  ተፅዕኖ የለውም ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- ምንም የሚታየኝ ነገር የለም፡፡ ተከራይተው ይኖሩ የለም እንዴ? እንዲውም ተፅዕኖው ተከራይተው መኖራቸው ነው፡፡ ምናልባት ተፅዕኖ አለ ከተባለ ወይም ሊኖር የሚችልበት ዕድል ሊታይ የሚችለው ሕጉ ሥራ ላይ ሲውል፣ መጀመሪያ አካባቢ ውድድሩ ሊበዛ ከመቻሉ ጋር ተያይዞ ሊፈጠር የሚችል ነገር ካለ ነው፡፡ ሕጉ ወጥቶ የውጭ ዜጎች ቤት መግዛትና ንብረት ማፍራት ይችላሉ ሲባል ሁሉም መግዛት ወይም መሥራት ሊፈልግ ይችላል፡፡ ከዚያ ውጭ ምንም ችግር የለውም፡፡ ለምሳሌ አሁን በአዲስ አበባ ከተማ ብዙ ሪል ስቴቶች እንገነባዋለን የሚሏቸውን ቤቶች መሸጥ አቅቷቸው፣ በየዕለቱ በርካታ ሰዎችን ቤት ግዙን እያሉ አራት አምስት የተለያየ ስልክ ይደወላል፡፡ አሁን እንዲያውም የሪል ስቴት ሊያበቃለት ይችላል፡፡ ይህ የሚያሳየን እስካሁን ድረስ በርከት ያለ የመኖሪያ ቤት እየተሠራ ባለመሆኑ ነው፡፡ በአብዛኛው የሚሠሩት ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ነበሩ፡፡ አሁን ለቢሮ የተገነቡ ሕንፃዎች የሚከራያቸው ሰው እየቀነሰ ነው፡፡ ይህ በመሆኑ ብዙዎች ወደ መኖሪያ ቤት ግንባታ እየገቡ ነው፡፡ ከእስከ ዛሬው ልምዳቸው መታዘብ የቻልነውም ሪል ስቴት አልሚዎቹ የግንባታ ሥራውን ከመጀመራቸው በፊት፣ በቅድሚያ በማስከፈል በሰበሰቡት ገንዘብ ነው ግንባታውን ሲያካሂዱ የቆዩት፡፡ በሰው ገንዘብ ነው የሚሠሩት፡፡

አሁን ደግሞ ትልልቅ ሪል ስቴቶች እየታዩ ነው፡፡ ሰፋፊ የሆኑ ሪል ስቴቶች እየተስፋፋ ሲሄዱ ደግሞ ዋጋቸው እየቀነሰ ይሄዳል የሚል ግምት አለኝ፡፡ አሁን በአዲስ አበባ ያለው የሪል ስቴት ዋጋ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከኬንያና ከመሳሰሉት አገሮች ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ የሆነበት አንዱ ምክንያት ከሲሚንቶ በስተቀር በተለይ እንደ ብረትና የፊኒሽንግ ዕቃዎች በሙሉ ከውጭ የሚመጡ በመሆናቸው ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ምርቶች ከውጭ ቢመጡም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እንዳየነው የሪል ስቴት ዋጋን በዚያን ያህል ደረጃ ዋጋውን የሚሰቅለው አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ብረት ማምረት አለብን የሚሉት ለሁሉም ዓይነት የኮንስትራክሽን ግንባታ ብረት ወሳኝ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ በቤት ልማት የሚሰማሩ ሰዎች ከጨመሩና አንዳንንድ ግብዓቶችን እዚህ የምናመርት ከሆነ ዋጋው አሁንም ይቀንሳል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ዜጎች ንብረት ማፍራት የሚችሉበት ሕግ እንዲወጣ ዝግጅት ከመኖሩ በተጨማሪ፣ ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተገደቡ አንዳንድ የንግድ ሥራዎችን ለውጭ ሰዎች ለመፍቀድ የታሰበ ይመስላል፡፡ ለምሳሌ እንደ ዎል ማርት ያሉ ኩባንያዎች ይግቡ ቢባል በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ የተሻለ ነገር ሊያመጡ ይችላሉ ተብሎ ይታሰባል? በእርግጥ እንዲህ ላሉ ድርጅቶች ገበያውን መክፈት ጠቀሜታው ምንድነው?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- እንዲህ ያሉ ዕርምጃዎች በገበያ ውስጥ ውድድር ያሰፋሉ፡፡ እዚህ ከተማ ውስጥ አንድ ኪሎ ሽንኩርት 150 ብር ገባ እየተባለ በሌላ በኩል ደግሞ ከገበሬው የሚባለው ድርጅት ደግሞ 25 ብር ይሸጣል፡፡ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች የሚያሳዩት ገበያው ቀውስ ውስጥ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለማስተካከል እነዚህ ኩባንያዎች ይሻላሉ፡፡ የራሳቸው የሥነ ምግባር መመርያ አላቸው፡፡ ሕዝብን እንዝረፍ ብለው የሚገቡበት ነገር አይደለም፡፡ ሁለተኛ እንዲህ ያሉ ኩባንያዎች የውጭ ምንዛሪ ስለሚያገኙና ሥራቸው ከፋይናንስ ዘርፉ ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ እዚያ አካባቢ ያሉ አሠራሮችን ማስተካከል ግን ይጠይቃል፡፡ እንዲሁ አይመጡም፡፡ ለምሳሌ እነ ማክዶናልድ ቢመጡ እነሱ የሚሠሩት በርገር ወይም ሳንዱች በሁሉም አገር ተመሳሳይ ጥራት ያለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም መሠራት ያለበት በዚሁ የጥራት ደረጃ በመሆኑ አቅርቦቱን ያሻሽሉታል፡፡ ውድድሩ እየጨመረ ይመጣል፡፡ ትልልቅ ሞሎች መምጣታቸው ለሕዝቡ ምርጫ ይሰጣል፡፡ ሌላው እነዚህ ኩባንያዎች መጥተው ሥራ በሚጀምሩበት ጊዜ ሰው ከእነሱ እየተማረ የራሱን ተለቅ ያለ ነገር ሊከፍት ይችላል፡፡ የካፒታል ገበያው በሚጀመርበት ጊዜም አክሲዮን እየሸጡ ነው ገንዘባቸውን የሚያዳብሩት፡፡ ቢዝነሱንም ቢሆን በአብዛኛው የሚይዙት ኢትዮጵያውያን ስለሚሆኑ እንዲህ ላሉ ኩባንያዎችም በር መክፈቱ ለአገራችን ገበያ ይጠቅማል፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ፍሬሽ ኮርነር ያሉት ሱፐር ማርኬቶች ግብርና ውስጥ ገብተው ጭምር የሚያመጡት ነው፡፡ ከውጭም ያስገባሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህን ትልልቅ ሞሎች ለመመገብ ይሠራሉ፡፡ ኢንዱስትሪዎችም እነሱ የሚሸጧቸውን ዕቃዎች ለማምረት ብዙ ጥረት ያደርጋሉ የሚል ግምት አለ፡፡ ስለዚህ እነዚህም የሚከለከሉበት ምንም ምክንያት አይታየኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ ወሳኝ የሆነ ሚና አላቸው ተብለው ከሚጠቀሱ ኢንዱስትሪዎች መካከል የብረታ ብረት ማምረቻዎች ወይም የብረት ማቅለጫዎች ናቸው፡፡ ይህንን ወሳኝ የኢንዱስትሪ ዘርፍ በላቀ ደረጃ ለመገንባት ፍላጎት እንዳለ ተጠቅሷል፡፡ በተለይ የብረት ማቅለጫ መገንባት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው እንዴት ይገለጻል? ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ግዙፍ ማምረቻ እንዲኖራትስ ምን መደረግ አለበት?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- ይህ የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ አንደኛ ንጥረ ነገሩ አለን ወይ የሚለውን ጥያቄ ከመመለስ ይነሳል፡፡ እየተናገርን ያለው ለብረታ ብረት ምርት የሚሆን ንጥረ ነገሩ መኖሩ ነው፡፡ የድንጋይ ከሰል አለ፡፡ የብረት አፈር አለን፡፡ ነገር ግን የአገራችን ማዕድን በሚገባ የተጠና አይደለም፡፡ የሌሎች የአፍሪካ አገሮች የነዳጅም ሆነ የማዕድናት ሁኔታ በቅኝ ግዛት ወቅት በደንብ የተጠና ነው፡፡ እኛ ግን ከእነሱ ጋር ስንዋጋ፣ እርስ በርሳችን ስንዋጋ ይህንን ሀብት በበቂ ሁኔታ አጥንተናል ማለት አይቻልም፡፡ ትልልቅ ኩባንያዎች መጥተው ነዳጁም፣ ጋዙም ፍለጋ ላይ ቢሰማሩ ጥሩ ነው፡፡ በአንፃሩ ካሉብ ጋዝን ስንመለከት ለስንት ዓመታት ወደ ሥራ ሊገባ ነው እየተባለ ሲነገረን ቆይቷል፡፡ ጋዙ ተገኝቷል መባሉ ብቻ ሳይሆን ማስተላለፊያ መስመር ተሠርቶ በጂቡቲ በኩል ወደ ቻይና ኤክስፖርት ይደረጋል ተብሎ ነበር፡፡ በተለይ የጋዝ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበበት ባለበት በዚህ ወቅት እንኳን ምንም ነገር አልተሠራም፡፡ ቢዝነስ ለመሥራት ቀላል ነገር ካለ በሁሉም ዘርፍ መትጋት ያስፈልጋል፡፡ አገራዊ ጠቀሜታ አላቸው የተባሉ ሥራዎች ላይ ደግሞ የግል ዘርፉ ተሳትፎ ከፍተኛ መሆን አለበት፡፡ ተበዳሪ መንግሥት ብቻ መሆን የለበትም፡፡ የግል ኩባንያዎች ተበድረው መሥራት የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ ተበድረው ሠርተው ኤክስፖርት የሚያደርጉበት ሁኔታ ሊመቻች የሚችለው በቂ ፋይናንስ ሲኖር ነው፡፡ የፋይናንስ ሥርዓቱ ከተስተካከለ እመርታ ሊኖር ይችላል፡፡ ስለዚህ ብረት ለማምረት የታሰበው በትክክል የሚተገበር ከሆነ ለአገር ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ ጣሊያኖች ከምፅዋ እስከ ጋምቤላ ድረስ መንገድ የሠሩት በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ብረት እያመረቱ መሆኑን ሲነገር ነበር፡፡ ይህ የብረት ሀብት ስለመኖሩ ጠቋሚ ነው፡፡ ይህንን ለመጠቀም ግን ምቹ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይገባል፡፡ አማራጮችን በማየት የተሻለ የሚሆነውን ማድረግ የታሰበውን ለማሳካት የሚቻልበት ዕድል አለ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የሪል ስቴት ገበያ ውስጥ ባልተለመደ ሁኔታ የቤቶች መሸጫ ዋጋ እየቀነሰ ነው፡፡ የመሬት ዋጋም ተመሳሳይ ሁኔታ ቅናሽ እየታየበት መሆኑም እየተሰማ ነው፡፡ ይህ ለምን የሆነ ይመስልዎታል? አንዳንድ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች አሁን በሪል ስቴት ገበያ ላይ የታየውን የዋጋ መቀነስ ከባንኮች የብድር ገደብ ጋር ያያይዙታል፡፡ ብድር በመቀነሱ የቤት ዋጋ ሊቀንስ ይችላል ይላሉ?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን የሪል ስቴቶች ብቻ ሳይሆን የመኖሪያ ቤቶች ዋጋ እየቀነሰ ለመምጣቱ አንዱ ምክንያት እንደሆነ የምንገምተው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባንኮች በሚሰጡት ብድር ላይ ገደብ ስለጣለና ለዘርፉ የሚሆን ገንዘብ ከባንኮች ማግኘት ባለመቻሉ ነው፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ባንክ የወሰደው ዕርምጃ እንደ አንድ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት እየሰጠ ያለው ብድር ትንሽ እየቀነሰ መምጣቱ እየተሰማ መሆኑም ለታየው የዋጋ ቅናሽ ምክንያት እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ ምክንያቱም በዚህ ፖሊሲ ምክንያት የገንዘብ ዝውውሩ እየቀነሰ ነው፡፡ ሌላው እንደ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችለው መግዛት የሚችሉ ሰዎች ገዝተው ጨርሰዋል የሚል ምክንያት ሊቀርብ ይችላል፡፡ ዳያስፖራውም ቢሆን አሁን ካለው የአገሪቱ አለመረጋጋት ቤት ወይም ንብረት መግዛት ጥቅም የለውም ብሎ በማሰቡ ገበያው ቀዝቅዞ ሊሆን ይችላል፡፡ የሪል ስቴት ገዥ በአብዛኛው ዳያስፖራው ነው ተብሎ ስለሚታመን እንዲህ ያለው አስተያየትም ይሰማል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያሉት ትንታኔዎች በሙሉ በትክክል ለመግለጽ በተጨባጭ ጥናት መደገፍ አለበት፡፡ በጥቅል ሲታይ ግን እነዚህ ምክንያቶች የየራሳቸው ድርሻ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ትልቁ ችግር እዚህ አገር ወቅታዊ የገበያ ዋጋዎችን በተከታታይ ማቅረብ አለመቻል ነው፡፡ በሁሉም ዘርፍ በአግባቡ መረጃ ይዞ ያልተቋረጡ አኃዛዊ የገበያ ዋጋዎች መቅረብ አለባቸው፡፡ በተለይ ቤትና መሰል ንብረቶች ዋጋ ላይ ችግር አለ፡፡ እነ ኬንያ እንኳን የመሬት፣ የቤትና የመሰል ንብረቶች ዋጋ ምን ያህል እንደጨመረና እንደቀነሰ በፐርሰንት ጭምር በየወሩ ያሳውቃሉ፡፡ እኛ አገር ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ውጪ ይህንን የሚያመላክት የለም፡፡ ስለዚህ የገበያ ዋጋን በአግባቡ ማሳየት አስፈላጊ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ቀደም ብለው የሪል ስቴት ኩባንያዎች ሊዘጉ ይችላሉ የሚል አስተያየት ሲሰጡ ሰምቻለሁና ለምን?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- ሪል ስቴቶች በታሪክ በአንድ ወቅት ይነሱና በሌላ ጊዜ ደግሞ ይቆማሉ፡፡ ለምሳሌ በቻይና ይህ አጋጥሟል፡፡ የቻይና መንግሥት እነሱን ለመደገፍ ወደ 60 ቢሊዮን ዶላር እየደጎማቸው ነው፡፡ የተወሰነ ጊዜ ሰው ይገዛል፣ ይሄዳል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ገበያው ይቀዘቅዛል፡፡ ስለዚህ ወጣ ገባ ያለ ነገር ይታያል፡፡ በእኛ አገር ሁኔታ ስታየው ለምሳሌ በከተማችን ውስጥ በተለይ በቦሌ መንገድና በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የተሠሩ ሕንፃዎች ላይ ከሦስት ፎቅ በላይ ምንም ነገር እንቅስቃሴ አይታይም፡፡ የሚከራይ ቀንሷል ማለት ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ? በሌላ በኩል ደግሞ ለአንድ አፓርትመንት 40 እና 50 ሚሊዮን ብር መጠየቅ ተገቢ አይደለም፡፡ ምንም ያህል ዋጋው ቢጨምር፣ ምንም ያህል የሲሚንቶና የማጠናቀቂያ ዋጋ ተጨመረ ቢባል እንኳ የቤት ዋጋ 30 እና 40 ሚሊዮን ብር የሚደርስበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ኢኮኖሚው ውስጥ ብዙ ተፅዕኖ የለውም፡፡ ምክንያቱም ዘርፉ ለኢኮኖሚው ያለው አስተዋጽኦ ሲታይ የተወሰነ ነው፡፡ ይወድቃል (ኮላፕስ) ግን አይደለም፡፡ ይወድቃል ማለት ገንቢዎቹ ይከስራሉ ማለት ነው፡፡ ቤት የሚገዛቸው ሰው የለም ማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ታሪክ አይፈጠርም፡፡ ግን ዋጋው በሚገባ ሊቀንስ ይችላል የሚል ግምት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- እየቀነሰ የመጣው የአገራችን የሪል ስቴት ዋጋ ቀድሞም ቢሆን የተጋነነና ተገቢ አልነበረም ማለት ነው?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- ዋጋው ሲንር የነበረበት አንዱ ምክንያት የብር ምንዛሪ እያሽቆለቆለ በመሄዱ ነው፡፡ ቀደም ብሎ እንደገለጽኩልህ ከውጭ የሚገቡ የግንባታ ግብዓቶች ዋጋ እየናረ መሄድ አንድ ምክንያት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ ዋጋውን የበለጠ ለማውረድ ከውጭ የሚመጡ ምርቶች እዚህ የሚመረቱበት መንገድ ካለ የበለጠ ዋጋው ይወርዳል፡፡ እዚህ አገር ቀድሞ ይመረቱ የነበሩ ተቀዛቅዘው ከቻይና መጥቶ ሲሠራ ማየት ትልቅ ችግር ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ምርቶችን እዚህ የማምረት ጅማሮዎች ይታያሉና ይህንን ማድረግ ብዙ ነገር ይቀይራል፡፡ ሰሞኑን እንደ ብረትና የማጠናቀቂያ ያሉ ምርቶችን እዚህ ለማምረት የተፈጠረው መነሳሳት ኢንዱስትሪው እየዳበረ እንዲሄድ ስለሚያደርግ ወደ ትክክለኛ ዋጋ ለመግባት ያስችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይት መድረኮች በተደጋጋሚ ሲጠቅሱት የነበረው የኢትዮጵያ ባንኮች ችግር ያለባቸው መሆኑን ነው፡፡ እንዲያውም በባንክ ዘርፍ ሌብነትም አለ እስከማለት ደርሰዋል፡፡ በዚህ ደረጃ የፋይናንስ ዘርፉን የገለጹበት ምክንያት ምንድነው ብለው ይገምታሉ? እንደ አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያ እርስዎስ የአገራችንን የፋይናንስ ዘርፍ እንዴት ይገመግሙታል?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- እንዲህ ያሉበትን ምክንያት ይኼ ነው ብሎ ለመግለጽ አይቻልም፡፡ እሳቸው ይህንን ያሉበት መረጃና ማስረጃ ይዘው ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን አባባላቸው የውጭ ባንኮች መግባት አለባቸው የሚለውን አመለካከት ያሳያል፡፡ የውጭ ባንኮች መግባት አስፈላጊነት ላይ ብዙ ተብሏል፡፡ አንዱ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ ካፒታል ይዘው ይመጣሉ፡፡ ሁለተኛ ገበያው ላይ መተማመን ይፈጥራሉ፡፡ ምክንያቱም የውጭ ኢንቨስተሮች ሲመጡ የምንፈልገውን ገንዘብ የሚያበድረን አለ ወይ ብለው ስለሚጠይቁ፣ የውጭ ባንኮች ካሉ የፋይናንስ ፍላጎታቸውን እነዚህ ባንኮች ሊመልሱ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም እንደ ሚድሮክ ያሉ ኩባንያዎች ከንግድ ባንክ ብድር ወስደው ሲሠሩ ነበር፡፡ ሸራተን አዲስ ሲሠራ ሆቴሉ ማስያዣ ሆኖ ብድር ተፈቅዶ ነው የተሠራው፡፡ የውጭ ባንኮች ሲመጡም እንዲህ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ኢንቨስት ለማድረግ ያግዛሉ፡፡ ሁለተኛ የውጭ ባንኮች ሲገቡ የፋይናንስ ሥርዓቱ አብሮ ይሻሻላል፡፡ የፋይናንስ ሥርዓቱ ይሻሻላል ማለት በተለያየ መንገድ የሚገለጽ ነው፡፡

አሁን ለምሳሌ የግል ባንካች 50 እና 60 በመቶ ትርፍ ያስመዘግባሉ፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ዓለም ላይ የሌለ ነው፡፡ ዝም ብሎ አንዱን የኅብረተሰብ ክፍል አስደስታለሁ በሚል የሚደረግ ነገር ይታያል፡፡ የውጭ ባንኮች ሲመጡና ውድድሩ ሲፈጠር እንዲህ ያሉ የተጋነኑ ነገሮች ሊቀየሩ ይችላሉ፣ በልክ ማትረፍ ይመጣል፡፡ የባንክ ሥራ ሙያዊ ሥራ ነው፡፡ እንደ ዱባይ ያሉ አገሮች የውጭ ባንኮች በሚመጡበት ጊዜ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ ለማድረግ ነው፡፡ ኢንዱስትሪን፣ ንግዱን፣ መሠረተ ልማቱን ፋይናንስ ለማድረግ ተጠቅመውባቸዋል፡፡ እንደ ሌተር ክሬዲት ዓይነት ያሉ ትንንሽ አገልግሎቶችን በአገር ውስጥ ባንክ እንዲከፈት በማድረግ፣ የአገር በቀሉንና የውጭውን ባንክ ሥራ በመለየት ጭምር ጠቀሜታቸው ከፍ እንዲል አድርገዋል፡፡ የውጭ ባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ አይሰበስቡም፡፡ ይኼ ለአገር ውስጥ ባንኮች የሚተው ነው፡፡ እንዲህ ያለው አሠራር እንዲተገበር ከውጭ ባንኮች ጋር ተደራድሮ ነው የሚወሰነው፡፡ በእርግጥ በአንዳንድ አገሮች የውጭ ባንኮች ችግር የፈጠሩበት ሁኔታ አለ፡፡ አሁን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ግን ይህ ሥጋት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡

ሪፖርተር፡- ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጋር በተደረገ ውይይት አንድ የተነሳ ጥያቄ የሙስና ችግር ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ጉቦ የሚጠይቃችሁን ካላጋጣችሁ እናንተም መስጠት ካላቆማችሁ ችግሩን መቅረፍ ያስቸግራል ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ ሙስናን ለመከላከል ምን መደረግ አለበት?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- ሙስና የሚያሳየው ይህንኑ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሪፖርቶችን ብትመለከት በርከት ያለ ዘረፋ መኖሩን ይጠቁማሉ፡፡ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ሙስና አለ፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ሳይቀር ሙስና ያለ መሆኑ ታይቷል፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች አሁን ያላቸው ገቢ ከሚሰጣቸው ኃላፊነት አንፃር በቂ አይደለም፣ መኖር አቅቷቸዋል፡፡ በሚሰጣቸው ደመወዝ መኖር ስለማይችሉና ሥራቸውን ለመሥራት ስለሚቸገሩ የሚቀርብላቸውን ማባበያ ይቀበላሉ፡፡ ይህንን አምጡ ይላሉ፡፡ የዕንባ ጠባቂ ተቋም አንድ ከፍተኛ ኃላፊ መግለጫ ሲሰጡ ጉቦ በአካውንት አስገቡ እስከመባል ደረጃ መድረሱን ተናግረዋል፡፡ ይህ እጅግ አሳሳቢ ነገር ነው፡፡ በውይይቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹትም ሙስናን ለመከላከል መተባበር ያስፈልጋል፡፡ የንግድ ኅብረተሰቡ ጉቦ ስጠየቅ እንዲህ ተባልኩ ብሎ ማጋለጥና እንቢ ማለት አለበት ብለው የገለጹትም ትክክል ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥት ሙስናን ፈጻሚዎችን እየተከታተለ ዕርምጃ መወሰድ ግን ኃላፊነት አለበት፡፡ ሌላ ሙስናን መዋጋት የሚቻለው ጠንካራ የሲቪል ማኅበረሰብና ጠንካራ የምርመራ ሚዲያ ሲኖር ነው፡፡ ችግሩን ለመከላከል ሌላው ሊወሰድ የሚገባው ዕርምጃ እንደ መሬት አስተዳደር፣ ገቢዎችና መሰል ሙስና ይፈጸምባቸዋል የተባሉ ተቋማት ሠራተኞች በቂ የሆነ ደመወዝ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡ በመቶና በቢሊዮን ብሮች የሚቆጠር ሙስናም ሆነ ሌላ ወንጀል የሚመረምር አካልንና መሰል ሥራዎችን የሚሠሩ ተቋማት ሠራተኞችን ደመወዛቸውን ማስተካከል ካልተቻለ ብዙ ችግር መፈጠሩ አይቀርም፡፡ ባይሆን የተሻለ ኑሮ እንዲኖራቸው ዕድል ተሰጥቶ ሙስና ውስጥ ሊዘፈቅ ለሚችለው ደግሞ ሕጉን ማጥበቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ጉቦ የሚጠይቁትን ለማጋለጥ ደፍሮ ማጋለጥ ያስፈልጋል፡፡ ጉቦ የሚጠይቁ ባለሥልጣናትን የሚያጋልጡ ሰዎችም ሕጋዊ ከለላ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ስለዚህ ሙስና የአገሪቱ አደገኛ ችግር እየሆነ በመምጣቱ የሙስና ቁጥጥሩ በሲቪል ማኅበረሰብ ጭምር እንዲታገዝ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አንዳንዴ ጉቦ ተቀባዩም የፀረ ሙስና ተከታይ የሚሆንበት ሁኔታም ስላለ ችግሩ ጠንከር ያለ አሠራር ያስፈልገዋል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹ዜጎች ሳይፈናቀሉ የልማት ሥራዎችን ማከናወን የሚቻልባቸው በጣም በርካታ አማራጮች አሉ›› እንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር)፣ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ

ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ሆነው መሾቸው ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የሕዝብ ተወካዮች...