Friday, April 19, 2024

የአማራና የትግራይ ክልሎች ሌላ ዙር የጦርነት ሥጋት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ገና ወደ ሥልጣን በመጡ በሁለተኛ ሳምንቱ ጎንደር ከተማ ሄደው ነበር፡፡ ከሕዝብ ጋር ውይይት ለማድረግ ባደረጉት በዚህ ጉዞ ወቅትም ከእስር ከተፈቱ ገና ጥቂት ጊዜ ከሆናቸው የወልቃይት አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባላት ጋር ተገናኝተውም መነጋገራቸው ይታወሳል፡፡ ይህ አጋጣሚ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደ ወልቃይት ዓይነት አጨቃጫቂ ጉዳዮችን ለመፍታት ዘዴ ብልኃቱ ያላቸው መሪ ናቸው የሚል እምነት በሰፊው ያሳደረ አጋጣሚ እንደነበር ይነገራል፡፡

ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን እንደመጡ በመጀመሪያዎቹ ወራት ድፍረት የተሞላባቸው ያልተጠበቁ የሰላም ዕርምጃዎችን በመውሰድ ብዙዎችን ማስደመማቸው ይጠቀሳል፡፡ በወቅቱ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ እንዲሁም የሕወሓት ከፍተኛ አመራሩ ጌታቸው ረዳ ጭምር ድፍረታቸውን እስኪያደንቁ ድረስ ባልተጠበቀ ሁኔታ አስመራ ተገኝተው ለሃያ ዓመታት የዘለቀውን የሁለቱን አገሮች ቁርሾ የሚያረግብ ሥራ ሲያከናውኑ ታይተው ነበር፡፡

በቪዲዮ የተቀዳ የሰላም ጥሪ ለኤርትራ ከመላክ ጀምሮ አስመራ እስከ መሄድ ድረስ ለሰላምና ለዕርቅ በመሥራታቸው በዓለም አደባባይ የተወደሱትን የሄሰን የሰላም ሽልማትና የኖቤል የዓለም ሰላም ሽልማት እስከ መቀዳጀት ደርሰዋል፡፡ በዚህ የተነሳም ለረጅም ጊዜ የአማራና የትግራይ ክልሎችን ሲያወዛግቡ የቆዩ እንደ የወልቃይትና ራያ ያሉ አጨቃጫቂ ጉዳዮችንም በቶሎ መፍትሔ በመስጠት በአጭሩ ይቀጯቸዋል የሚለው ግምት ከፍተኛ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ዓመታት ነጎዱ፡፡ የትግራይ ጦርነት ፈነዳ፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢ በከባድ ግጭትና ደም መፋሰስ አሳለፈ፡፡ ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት ተከተለ፡፡ ይህ ሁሉ አልፎ ግን የወልቃይትና የራያ ጉዳይ ዛሬም ሁለቱን ክልሎች እንዳወዛገበ ነው፡፡ ከሰሞኑ ውዝግቡ የተባባሰ ሲሆን፣ የተኩስ ልውውጥን ጨምሮ መሬት ወረራ ተፈጸመ የሚል የእርስ በርስ ክስ ሲሰማ ሰንብቷል፡፡

ይህ ደግሞ በመግለጫና በቃላት ውርወራ የታጀበ ሲሆን፣ በብዙዎች ዘንድ ለጦርነት የመጋበዝ ድርጊት ሆኖ ነው የተቆጠረው፡፡ አሁን ግን የትግራይና የአማራ ክልሎች ወደ ጦርነት ሊገቡ ይችላሉ የሚለው ግምት ያየለ ሲሆን ይህም ገና ከጦርነት የዞረ ድምር ላልተላቀቀውና በአንዳንድ አካባቢዎችም ትኩስ ግጭቶች ለሚታይበት ለሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ዳግም የቀውስ ምንጭ እንዳይሆን በመሠጋት ላይ ነው፡፡

የአማራ ክልል የትግራይን መሬት ያካተተ ካርታ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ አካቶና በመጻሕፍት አሥፍሮ ልጆችን ማስተማሪያ አድርጓል ሲል በሳምንቱ መጀመሪያ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የክስ መግለጫ አወጣ፡፡ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ ባወጣው መግለጫ የወልቃይት፣ የአበርገሌ፣ የጠለምትና የራያ አካባቢዎችን የአማራ ክልል አካል መሆናቸውን የሚያሳይ ካርታ አማራ ክልል ማሳተሙን ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ አስታውቋል፡፡

የትግራይን መሬት በካርታ አሥፍሮ ማስተማር ሆነ ተብሎ የሚፈጸም ትግራይን ዒላማ ያደረገ ጥቃትና ግፍ መሆኑን በመግለጫው ተመልክቷል፡፡ የአማራ ኃይሎች በሕገወጥ መንገድ በወረራ በያዟቸው የትግራይ መሬት ውስጥ በሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ላይ ግፍ መፈጸማቸው ሳያንስ ካርታ በመጽሐፍ አሳትመው እናስተምር ማለታቸው፣ በትግራይ ላይ ግፍ እየፈጸሙ ለመቀጠል ካላቸው ፍላጎት የመነጨ እንደሆነም ያስረዳል፡፡

የአማራ ኃይሎች ለቀደሙ ግፎቻቸው ተጠያቂ ሳይሆኑ መቆየታቸው ሳያንስ፣ እንዲህ ያለ ጥረት መጀመራቸው ታሪካዊ ስህተት መሆኑንም ይኼው መግለጫ ያትታል፡፡ የፌዴራል መንግሥቱም ቢሆን እንዲህ ዓይነት ሕገወጥ ድርጊት ሲፈጸም የእርምት ዕርምጃ መውሰድ ሲገባው ዓይቶ እንዳላየ ማለፉ፣ የጥፋቱ አንዱ ተዋናይ እንደሆነ እንደሚያመለክት ነው ብሏል፡፡

ይህ ጠንከር ያለ ይዘት ያለው የትግራይ ክልል መግለጫ ደግሞ ከአማራ ክልል በኩል ጠንካራ ምላሽ አስከትሏል፡፡ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መግለጫ ባወጣ በጥቂት ቀናት ልዩነት የአማራ ክልል መንግሥትም ጠንከር ያለ የአፀፋ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ክልሉ በዚህ መግለጫው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ‹‹የካርታ ፖለቲካ ጨዋታውን ያቁም›› በማለት ነው አቋሙን ያንፀባረቀው፡፡

የአማራ ክልል በመግለጫው የትግራይ ክልል መግለጫን የትምህርት ሥርዓት የተሳሳተ ካርታን ያጣቀሰ የዛቻና ጠብ አጫሪነት መግለጫ ስለመሆኑ ይገልጻል፡፡ ወደ ትግራይ ክልል ተካተው በካርታ ቀረቡ የተባሉት መሬቶች በታሪክም ሆነ በተጨባጭ ማስረጃ የአማራ ክልል ስለመሆናቸው ሞግቷል፡፡

የአማራ ክልል መግለጫ አክሎም የትግራይ ክልል መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም. የራያ አላማጣ አንዳንድ አካባቢዎችን በኃይል ስለመያዙ ያወሳል፡፡ በያዛቸው ቀበሌዎችም ነዋሪዎችን በመግደልና በማሰቃየት ላይ ይገኛል ይላል፡፡ የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የጠለምት፣ የኦፍላ፣ የራያ አካባቢዎች የማንነት ጥያቄ ያሉባቸው ወረዳዎች ላለፉት 30 ዓመታት ጉዳያቸው እልባት ሳያገኝ መቆየቱን መግለጫው ያነሳል፡፡

የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር መብቶቻቸው እንዲከበር ሲጠይቁ የቆዩ ሕዝቦችን የትግራይ ክልል ዜጎች ላነሱት ሕጋዊና ታሪካዊ ጥያቄ ሕጋዊ አሠራርን የተከተለ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፣ በኃይል ጥያቄዎቹን የማዳፈን ዕርምጃ ሲወስድ ቆይቷል በማለትም ይከሳል፡፡ ጥያቄ ያነሱ ወገኖችን በመግደል፣ በማሰርና በማሳደድ ጥያቄዎቹ መልስ እንዳያገኙ ለማድረግ ሲጥር ቆይቷል ብሏል፡፡

ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ክህደት በመፈጸም ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ በተወሰደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ፣ የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ያነሱ ሕዝቦች ዘመቻውን መቀላቀላቸውን የአማራ ክልል መግለጫ ያስታውሳል፡፡ በዚህም በሕወሓት ተገፎ የነበረውን የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር መብቶች ሕዝቡ ለመጎናፀፍ እንደበቃ ይዘረዝራል፡፡

የአማራ ክልል መግለጫ በመማሪያ መጻሕፍት ታተመ ስለተባለው ካርታ በቀጥታ የሰጠው ምላሽ ባይኖርም፣ የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ያነሱ አካባቢዎች ታዳጊዎችን የመማር መብት ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥራ ማከናወኑን አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ጉዳይ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በኩል ጠንካራ ትችት ነው የገጠመው፡፡

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ረዳኢ ሀለፎም የአማራ ክልልን በጠባጫሪነት ከሰዋል፡፡ ‹‹በማይካድራ ዘር ማጥፋት ፈጽሟል፤›› ሲሉ የማካድራውን ጭፍጨፋ ወንጀል ባልተለመደ ሁኔታ ለአማራ ክልል ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ወደ ጦርነት የመግባት አማራጭን›› የትግራይ ክልል እንደማይከተልም ጠቅሰዋል፡፡

የትግራይ ክልል ለጦርነት እንደማይቻኮል የተናገሩት አቶ ረዳኢ፣ ‹‹ወደ ጦርነት የሚያስገቡ ገፊ ምክንያቶች ቢኖሩም የሰላም በሩ ገና አልተዘጋም፡፡ ስለዚህ ዕድሉ እስካለ ድረስ የሰላም አማራጮችን እንጠቀማለን፤›› ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ባለሥልጣናት ባለፈው ሳምንት ወደ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሄዱ ሲሆን፣ በቁራሪት ከተማ ከሕዝብ ጋር አደረጉት በተባለው ውይይት ላይ ከሰሞኑ ውዝግብ ጋር የተያያዘ ጉዳይ መነሳቱ ተዘግቧል፡፡

የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ አቶ አማረ ሰጤ፣ የአማራ ክልል የማንነት ጥያቄ የተነሳባቸው አጨቃጫቂ ቦታዎችን የመፍቻ አማራጩ ሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሆነ ስለመናገራቸውም ተዘግቧል፡፡ በዚሁ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ በደም የተገኘው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ መሬትና ማንነት ጥያቄ የማይቀለበስ ስለመሆኑ ከሕዝቡ በኩል ጎልቶ ስለመስተጋባቱ ነው የተነገረው፡፡

ከሰሞኑ ከሁለቱ ክልሎች ባለሥልጣናትና ከመገናኛ ብዙኃን በኩል የተስተጋቡ ድምፆች፣ በሁለቱ ወገኖች በኩል አጨቃጫቂ ወሰኖችን በሚመለከት ገና ሊታረቅ ያልቻለ ሰፊ ልዩነት መኖሩ በጉልህ ተንፀባርቋል፡፡ በርካቶች የፕሪቶሪያው ስምምነት ሳይሸራረፍ ሙሉ ለሙሉ በሥራ ላይ በማዋል የአጨቃጫቂ መሬቶችን ጉዳይ መቋጨት ይቻላል የሚል አቋም ሲያራምዱ ይታያል፡፡ ይሁን እንጂ የፕሪቶሪያው ስምምነት እንደ ወልቃይትና ራያ ያሉ ውስብስብ የማንነትና የመሬት ጥያቄዎችን የቀየጡ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አይደለም የሚሉ ወገኖች ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡

በፕሪቶሪያው ስምምነት ሰነድ ላይ የአጨቃጫቂ ቦታዎች ጉዳይ ሕገ መንግሥቱን በተከተለ መንገድ እንደሚፈታ ተቀምጧል፡፡ መንግሥት በበኩሉ የአጨቃጫቂ መሬቶች ጉዳይ በሕዝበ ውሳኔ መፍትሔ እንደሚያገኝ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

ይሁን እንጂ የሁለቱ አጨቃጫቂ ቦታዎች ችግር አፈታት ዝርዝር ሒደት ፍኖተ ካርታ (ሮድ ማፕ) ተዘጋጅቶለት የተቀመጠበት አግባብ አለመታየቱ፣ ጉዳዩ በቀላሉ እልባት ያገኛል የሚለውን ግምት ጥርጣሬ ውስጥ ከቶታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ ‹‹እኛ ደቡብ አፍሪካ የሄድነው ወልቃይት ወደ ትግራይ ወይም ወደ አማራ ይሂድ የሚለውን ለመወሰን አይደለም፡፡ የፕሪቶሪያ ስምምነት ይህን የመወሰን ሥልጣን የለውም፤›› ብለው በቅርቡ በፓርላማ መናገራቸው ደግሞ፣ መንግሥት በጉዳዩ ላይ የጠራ አቋም መያዙን ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይከተዋል የሚሉ ድምፆች ይሰማሉ፡፡

የተፈናቀሉ ሰዎችን መልሶ የማስፈር፣ የአካባቢው የበጀት ጉዳይ፣ አካባቢያዊ መስተዳድር የመመሥረት ዕቅድም ሆነ ለሕዝበ ውሳኔ ማካሄድ መደላድል የሚሆኑ ሁኔታዎችን የመፍጠር ሥራ በቅርቡ አልተሠራም የሚል ስሞታ ጎልቶ ይሰማል፡፡

የመከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በቅርቡ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ ሕዝበ ውስኔ ለማካሄድም ሆነ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማስፈር ምቹ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራ ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በብዙዎቹ እምነት የወልቃይትና የራያ ጉዳይ በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተት ሰንብቷል የሚለው ሐሳብ ገዝፎ ይደመጣል፡፡ ይህ ደግሞ መንግሥት ጉዳዩን ለመፍታት ያለው ቁርጠኝነት ምን ድረስ ነው የሚለውን ጥያቄ ደጋግሞ እንዲነሳ እያደረገው ነው፡፡

የፌዴራል መንግሥት የወልቃይትና የራያ ጉዳይን ለመፍታት ያለው ቁርጠኝነት ወይም ያዘጋጀው ዝርዝር ዕቅድ ብቻ አይደለም ጥያቄ ውስጥ ሲወድቅ የሚታየው፡፡ መንግሥት ይህን ጉዳይ ለራሱ የፖለቲካ ፍጆታ ሊያውለው ይችላል የሚለውን ሐሳብም በጥርጣሬ የሚያነሱ አሉ፡፡

አንዳንድ ወገኖች ይህ ግጭትን እንደ አንድ የፖለቲካ ስትራቴጂ ከማራመድ  የመጣ ነው ሲሉ መንግሥትን ይከሳሉ፡፡ ሌሎች ወገኖች በበኩላቸው የአማራና የትግራይ ክልሎችን በማያባራ የግጭት አዙሪት ውስጥ ለመጣል ባለ ፍላጎት የመጣ ነው ሲሉ ይወነጅላሉ፡፡

ጥቂት የማይባሉ ወገኖች የአማራና የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ጭምር ምንም ቢሆን የሰሞኑ ውዝግብ ለሌላ ዙር ጦርነት የሚዳርግበት ዕድል አለመኖሩን እየተናገሩ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከዚያ በተቃራኒ በአጨቃጫቂዎቹ ቦታዎች የተኩስ ልውውጥ ጭምር መከሰቱን የሚጠቅሱ ወገኖች ግን፣ ጉዳዩ በቅጡ ካልተያዘ ሌላ ዙር ጦርነት የሚያስነሳበት ዕድል ሰፊ መሆኑን በመናገር ላይ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -