Tuesday, May 28, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ወይዘሮ ተሠሩ እንደ እናት እንደ አገር

በየሀብከ ብርሃኔ ጥላሁን

ግጥም፦ አስቻለው ፈጠነ (አርዲ) እና ኃይለ ኢየሱስ ደርብ

መግቢያ

በፎክሎር ጥናት ፎክሎራዊ ጥናትና ልማትን አስተሳስረው የአገራቸውን ዕድገት በየዘርፉ ካፋጠኑ አገሮች መካከል ጃፓን፣ ሩሲያ፣ ቻይናና ጀርመን ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው። የአሜሪካ ፎክሎሪስቶች ደግሞ በዘርፉ ጥናት ላይ ብዙ ነገረ ጉዳዮችን ብለዋል። ችግራቸውን የፈቱበት፣ ከውድቀት ተነስተው ወደ ዕድገት የገሰገሱበት ጥበብ ሁሉ የፎክሎር ውጤት ነው።

ፎክሎር የጽንሰ ሐሳብ ማዕከሉ ሰው ነው። ከሰው ተወስዶ በሰው ተጠንቶ መልሶ ለሰው የሚቀርብ የዕድገት መንገድ ነው። እኔ ፎክሎር ሳጠና አንዱ ኮርስ “ፎክሎር እና ልማት” የሚል ነበር። ዓላማው የፎክሎርን ጥናት ከሸልፍ ማሞቂያነት ባሻገር በተግባር ማዋል እንዲቻል ማድረግን መሠረት ያደረገ ነው።

ከአራቱ የፎክሎር ዘውጎች ውስጥ ማለትም በAlan Dundes ሆነ በሃያ አንዱ የአሜሪካ ፎክሎረኞች የተዘረዘሩትን ዶርሰን በአራት የጥናት ዘርፎች መድቧቸዋል። እነዚህም ሥነ ቃል (Oral Folklore)፣ አገረ ሰባዊ ትውን ጥበባት (Performing Folk Arts) አገረ ሰባዊ ልማድ (Social Folk Customs) እና ቁሳዊ ባህል (Material Culture) ናቸው። (Dorson, 1972:2)፡፡ ለዛሬ ትኩረቴን የሳበው አገረ ሰባዊ ትውን ጥበባት (Performing Folk Arts) ነው። በዚህ የፎክሎር ዘውግ ሥር የሚጠኑት አገረ ሰባዊ ሙዚቃዎች (Folk Music)፣ አገረ ሰባዊ ውዝዋዜዎች (Folk Dance)፣ አገረ ሰባዊ ምህንድስናዎችና የመሳሰሉት ናቸው።

አገረ ሰባዊ ዜማ/ሙዚቃ በታሪክና በባህል ሁነቶች፣ በእምነት፣ የሥራ ባህልን ተከትሎ የተፈጠረና ከተለያዩ ባህሎች እየተወራረሰ፣ በታሪክ ሒደቶች እያለፈ፣ በተለያዩ ሁኔታዎች እየተወሰነ የመጣ በማለት ይገልጹታል (Bohlman,1988)፡፡ አገረ ሰባዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች (Folk Instruments) መሠረታዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ ዓለም አቀፋዊ ዕድገት ካመጡና አገረ ሰባዊ ሙዚቃው (Folk Music) ዜማን ከፍልስፍናዊ ጥበቡ ጋር አሰናስሎ ከተጠቀመበት ዓለም አቀፍ ትኩረት መሳብ ብቻ ሳይሆን የባህል አብዮት ይቀሰቅሳል፣ ሁሉንም ወደ ቀልቡ፣ ወደ ቤቱ ይመልሰዋል። የአገር ፍቅርን በሰው ልብ ውስጥ እንደሰደድ እሳት ያንቀለቅለዋል። ካለቅድመ ሁኔታ ሁሉም እርስ በርሱ እንዲዋደድ ወይም እንዲጠላላ ማድረግ ይቻለዋል። ይሁነኝ ብሎ ስለተጠቀመበት አቻ የማይገኝለት የግብ ማሳኪያ ሆኖ ያገለግለዋል።

የአስቻለው አገረ ሰባዊ ሙዚቃው ማኅበራዊ ትስስርን በማጠናከር፣ ግለሰባዊ ማንነትን የመቅረፅና የማፅናት፣ ሥነ ልቡናን የመገንባት፣ ማኅበራዊ ደረጃን የመለወጥ፣ ሐሴትን የማጎናፀፍ ፋይዳ አለው። ውበት ያለው፣ የተቀናጀ፣ በጊዜና በቦታ ተወስኖ በድምፅ ቅላፄ ታጅቦ ተደጋግሞ በመቅረቡ አይሰለችም፡፡

ትልቁ ጥንቃቄ!! ክሊፑ ሲሠራ ቁሳዊ ባህሎችን በጥንቃቄ ያሳየ፣ ያላቸውን ቅርፅ፣ የቁሱን ገጽታና የማኅበረሰቡን ማንነት መግለጽ ይገባቸዋል፡፡ በቁሳዊ ባህል አገረ ሰባዊ እጅ ሥራ፣ አገረ ሰባዊ ስንክን፣ አገረ ሰባዊ ምህንድስና፣ አገረ ሰባዊ ምግብ፣ መጠጥና አገረ ሰባዊ አልባሳት በጥበቡ ውስጥ ይሁነኝ ተብሎ በጥናት በማስገባት ዓላማውን ሊያሳካ ይገባል፡፡ ትናንት ላይ ብቻ መቆም አገረ ሰባዊ ውዝዋዜውን ከሙዚቃ መሣሪያው እኩል ስለማያሳድገው፣ ትናንትን ከዛሬ፣ ዛሬን ከነገ በክዋኔውና በሚሰጠው ምስል ማስተሳሰር አለበት።

አገረ ሰባዊ ትውን ጥበቡ ልብን በሚያሞቅ ሁናቴ ደምቆ ሊገባ ይገባል፡፡ ውዝዋዜያቸውን፣ ፈገግታቸውን (የደስታ አገላለጻቸው)፣ የትዝታ ስበቱን ወዘተ ሁሉ ስክትክት አድርጎ ሊያስገባ ይገባል፡፡

የአስቻለ የሙዚቃ አልበም የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ወግ፣ ባህል፣ ትውፊትና አኗኗር የሚዳስስ ሲሆን የአገራችን ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ለአድማጭ ጆሮ በሚስማማ፣ ዓለም አቀፋዊ የድምፅ ጥራቱን በጠበቁ መልኩ ተቀናብረዋል። በአልበሙ ውስጥ ዓባይ፣ ዓድዋ፣ በላይ፣ እቅፍ አርጊኝ፣ እንገር ወሎ፣ እመት ሸዋ፣ ወይዘሮ ተሠሩ፣ ፍየሌን ነብር በላት፣ አስቻለ፣ ዊሃ ዊሃ፣ እናትዋ ጎንደር፣ በርታ የተሰኙ ሙዚቃዎች ተካተዋል።

በአስቻለው ፈጠነ አርዲ ሙዚቃ አገረ ሰባዊ ሙዚቃ፣ በውስጡ ፍቅርና አንድነት ተሰብኳል። ታሪክም ተነግሯል። ለሚገባው ደግሞ ጥሪም ተላልፎለታል። በተለይ በላይና እመት ሸዋ የታሪክና የተማፅኖ ዋሻ ናቸው። እንገር ወሎ የፍቅር ዋርካ ነው። ዓድዋ እና ዓባይ የአንድነት ድርና ማግ ናቸው። አስቻለ የጥሪ ደወል ነው። ትዝታና ወይዘሮ ተሠሩ የተነፈግነውን ተስፋ የሚያሳዩ፣ ያልደረስንበት የተስፋ ርዕይ መነጠቃችንን የሚኮረኩሩ ናቸው። እናትዋ ጎንደር አብረው እየኖሩ በናፍቆት መብሰልሰያ ነው። ዊሃ ዊሃ፣ በርታና እቅፍ አድርጊኝ በናትሽ ያልተገለጡ መልካም ገጾቻችን የገለጡ፣ አብረን ሆነን የሌላ ዓለም የመሰሉ ግን የእኛ ሌላ ውብ ገጾች ናቸው። ያላወቅናቸው ግን አስቻለው እናውቃቸው ዘንድ ያቀረበልን ውብ የልደት አምሐዎች ናቸው። ፍየሌን ነብር በላት በቆለኛ አገዎች ዜማ ያንቆረቆራት የፀፀት እንጉርጉሮ ያለማድረግ ትካዜ ናት።

ወይዘሮ ተሠሩ!!

ሙዚቃው ከተለቀቀበት ቀን ጀምሮ ምላሽ ያጣሁላት ወይዘሮ ተሠሩ ማናቸው? ወ/ሮ ተሠሩን ፍለጋ በምናቤ ሳማትር ወ/ሮ ተሠሩ እንደእናት፣ እንደአገር፣ ሆነው አገኘኋቸው። እንዴት? እንዴት ማለት ጥሩ፣ አብረን እንያቸው።

***

እሹሩሩሩሩ፣ (4)
ወይዘሮ ተሠሩ፣ እንደምን አደሩ፣
እንዴት ሰንብተዋል አረ እንዴት አደሩ፣
እኔ እንኳን የጠፋው ወረት ነው ችግሩ፣
ወይዘሮ ተሠሩ እንደምን አደሩ።

***

እናት እና ልጅ!!

 • በተወለደበት ቤትና አልጋ ያረጀው አስቻለው፣ ማሙሽ ያሉት እናቱ አርጅቶባቸው አንቱ ሲሉት፣ በልጇ እንዲህ ሆኖ መቅረት ስትብሰለሰል፣ ሕፃን እያለ ሲያለቅስ እናቱ ለማባበል የተጠቀሙበትን የማባበያ ቃል መዝዞ እሹሩሩሩ አላቸው።
 • እሹሩሩሩሩሩ… ስወጣ ስገባ አይዞዎት እናቴ፣ እሹሩሩሩ እናቴ ወይዘሮ ተሠሩ፣ እንደተኛሁ አልቀረሁም ደሞ ዛሬም ነጋ እንደምን አደሩ?። አብረን እያለን እርስዎ በሐሳብ፣ እኔ በምግባር ተለያይተን ከርመናልና፣ አብረን ሁነን ተነፋፍቀናልና እንዴት ሰንብተዋል ኧረ እንዴት አደሩ ይላቸዋል። እኔ እንኳን የጠፋው አዲስ ወሬ የለኝም፣ አዲስ ሕይወት የለኝም፣ ባዶ እጄን ለመምጣት ዓይንዎን ለማየት ወረት ነው ችግሩ። እናስ? ወይዘሮ ተሠሩ እንደምን አደሩ? ባንፈልግም ይጨልማል፣ ባይነጋም ይነጋል ወይዘሮ ተሠሩ እንደምን አደሩ ይላቸዋል፤ ዛሬንም ውሎ ለማደር እናቱን ሲያባብላቸው። በሙዚቃ የጥያቄው መልስ ልማድም ባህልም ነውና በወይዘሮ ተሠሩ ቦታ ራሱን የከተተ አድማጭ በምናቡ ይጨርሰው ብሎ ትቶታል። “እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ።” ደህና ባትሆንም፣ ቢከፋት ቢደላትም፣ ቢጨንቅ ቢጠባትም፣ ልማድም ባህልም ነውና “እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ።” የሁሉም መልስ ነው።

አገርና ዜጋ!!

 • ወይዘሮ ተሠሩ ከስማቸው ጀምሮ አገር ናቸው። የመጣ የሄደው ሁሉ እሠራሻለሁ የሚሏት ግን የማይሠሯት አገር ኢትዮጵያ ናት። አንቱ ብሎ አንዱ ጎስቋላ ዜጋዋ አስቻለው ቢጠራት አገር በመሆኗ ይገባታል። አንድም ሦስት ሺሕ ዘመን ያስቆጠረች ሽማግሌ አገር ናትና፣ አንድም በስም በዝና የከበረች አገር ናትና፣ አንድም አንቱታ ኢትዮጵያዊ ባህልና ጥበብ ነውና ክብር ያለው ነገር ለአገር ስለሚገባ አንቱ ብሏታል። የወንዙ ልጅ የሶሪቷ አበባ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) በግልጽ ያገቡሻል፣ ይፈቱሻል አሁንም ድንግል ነሽ ብላ የድንግልናን ክብር እንዳጎናፀፈቻት ልብ ይሏል።
 • አስቻለው የዚች አገር ብኩን ዜጋ ግን ባለተስፋ ዜጋ ነው። እንሠራለን ያሉትን ሁሉ ሥራ እየጠበቀ ያላየ ዜጋ፣ የተስፋዋን እንጀራ እንደናፈቀ የቀረ ይልቅንስ ቁጭ ብሎ ሲፈርሱ እንዳያቸው ቅርሶች ለራሱም የፈራ ዜጋ ነው። በወጣ በገባ ቁጥር፣ መሽቶ በነጋ ቁጥር የሁኔታው መለዋወጥ አሳቆት ምላሽ ባያገኝም እንደምን አደሩ? እያለ አገሩንና ዜጎቿን የሚጠይቅ ምስጉን ዜጋ ነው።
 • ወይዘሮ ተሠሩ አገሬ እንደምን አደሩ? አዕላፍ ዘመናት መሽቶ ነጋ፣ ዘመን ሄደ፣ ዘመን መጣ፣ የሞላ ማሰሮ የለም፣ ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ኑሮ ዛሬስ እንደልማድ፣ አንድም እንደተስፋ እንደምን አደሩ? እኔ በዘመኔ ነውና የማየው ያለፈውን ዘመንስ እንዴት ሰነበቱ? ይላታል አገሩን። “እኔ እንኳ የጠፋሁ ወረት ነው ችግሩ” አብሮ እያሉ መጥፋት አለ እንዴ? አዎ በአካል አብረው ቢኖሩ ምን ያደርጋል? በሐሳብ አልተገናኙም፣ በተግባር አልተገናኙም፣ ያም ይመጣል፣ ይኼም ይሄዳል እሱ ግን የተረፈው ያገኘው ነገር የለምና ወረት አለያይቶታልና ችግሩን ወረተኛነት ነው ብሎ ይነግራታል። በተለይ በአስቻለው ዘመን ለብሔር ብሔረሰብ እንጂ ለዜጋ አልተመቸችምና አብረን ሆነን ያለያየን ወረት ነው ከመጣው ጋር መንፈስ ነው ይላታል።

***

ተኩየ ተድሬ፣ ምነው ብወጣበት፣

ማሙሽ ባሉኝ እልፍኝ፣ አንቱ ተባልኩበት፣

በዓል በመጣ ቁጥር ከጓደኞቼ ጋር እያጨበጨብኩኝ፣

ሐውልት እየዞርኩኝ፣

የቀን ሳቅ ስቃለሁ እንደ ደጃች ውቤ መጠው እስኪያፈርሱኝ።

 • አስቻለው በዚህ ሙዚቃ የእናቱ የወይዘሮ ተሠሩ ልጅ፣ የአዲስ አበባ ልጅ፣ የኢትዮጵያ ዜጋ እንደሆነ ልብ ይሏል። እናቴ ሦስት ጉልቻ ብመሠርት፣ ወልጄ ብስም አሁን ምናለበት፣ ጎጆ ብወጣበት ምናለ?፣ ማሙሽ ባሉኝ ዕልፍኝ፣ አርጅቼ ወግና ማዕረጌን ሳላይ አንቱ ተባልኩበት ይላታል። ወይዘሮ ተሠሩ የኢትዮጵያውያን የምናብ እናት ናትና።

ነገር ግን ይኼን ወግ ማዕረግ ለእናቱ ለማሳየት ግን ቢሠራ ቢለፋ አልሳካ ብሎት ጎጆም አልቀለሰ፣ የሚወዳቸው ሴቶችም ዘር እየቆጠሩ ሚስትም አላገባምና ይህን ክፉ ጊዜ በውሸት ሳቅ ሲመሽ የማይደገም የቀን ሳቅ እየሳቀ፣ በትዝታ ሐውልት እየቆዘመና የቀን መዋያ የማታ ማምሻውን የትዝታ ገመዱን ደጃች ውቤን እንዳፈረሱት እሱንም እንዳያፈርሱት እየሰጋ ይቆዝማል።

 • ደጃች ውቤ የብዙዎች የትዝታ፣ የፍቅር፣ የሥራና የቀጠሮ ቦታ ነው። ብዙዎች ተቀጣጥረው ተገናኝተውበታል፣ የሆድ የሆዳቸውን ተጨዋውተውበታል፣ ተጣልተው ታርቀውበታል፣ ፍቅራቸውን መሥርተውበታል። ደጃች ውቤ የታሪኩና የትዝታው ማኅደር ነውና እሱ ሲፈርስ ለራሱ የማይፈራበት አገር አልባ የማይሆንበት ምክንያት የለምና ሥጋቱን ገለጸ።
 • ወይዘሮ ተሠሩ አገር ናትና ያላየችው ግፍና መከራ የለም። ልጆቿ በደርግ ቤተሰብ አልባ፣ በኢሕአዴግ ቤት አልባ እንደሆኑ፣ አሁን ደግሞ አገር አልባ እየሆኑ ነውና የልጇ ችግር ይገባታል። ጎጆ ባይቀልስ፣ ትዳር ባይመሠርት፣ ልጆች ወልዶ ባይስም የደረሰበትና የሆነበት ነገር ሁሉ ለእንደዚህ ያለው ክብር እንደማያበቃ ይገባታል። እናት ልጇ ሕፃን ቢሆንም ቢያረጅም ልጅ ልጅ ነውና አንቱ እስኪባል በተወለደበት አልጋ ተሸክማው ትኖራለች።

***

እሷም ቁማ ቁማ እኔም ቁሜ ቁሜ፣

ወይ ዘመን ወይ ጊዜ ስንት አሳየኝ ዕድሜ፣

ባል በመጣ ቁጥር ዘር እያማረጠች፣

እኔም አላገባሁ እሷም ቁማ ቀረች።

 • አስቻለው ከነችግሩ እንኳ ለትዳር የፈለጋት ሴት ዘር እየመረጠች ቆማ ቀረች፣ እኔም በእሷ ተስፋ ቆሜ ቀረሁ ብሎ ላይ ላዩን ስለራሱና ስላፈቀራት ቆንጆ ይነግረናል። ነገር ግን በዘመናት ሒደት ውስጥ ዕድገቷ ቆሞ የቀረው ለዘረኞች እንጂ ለዜጎቿ ቦታ የሌላት አገሩን አንቺ ቁመሽ፣ እኛም ቆመን ቀረን፣ ባል የቤት ራስ፣ ባል የአገር መሪ በመጣ ቁጥር ዘር እየመረጠ እኩል ሊመራን አልቻለም እያለ የዘመናችንን ውዝፉ ዕዳ፣ የዜጎቿን ሰቀቀን ያንጎራጉራል።

***

ፀጉራችንን ሉዲ እየቀባባነ፣

ቀበሌ መዝናኛ ጃንቦ እየጨበጥነ፣

መሐሙድ ላይ ወርደን ዳሌ እያማተርነ፣

ሦስት አንጓ ጨርሰን አራተኛው ገባ፣

እኛም ሳናገባ።

 • እዚጋ አስቻለው ትዝታና ቁጭት በጅራፍ ሲገርፉት ብሶቱን ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። ይህ ብሶት የብዙ ዜጎች፣ የብዙ የአዲስ አበባ ልጆች መሆኑን ልብ በሉልኝ። ፀጉርን ለመፈረዝና የሸበተውን ለማጥቆር እንደዛሬው የራሱ ቀለም ሳይኖረው ድሮ በሉዲና በኪዊ የጫማ ቀለም ፀጉር ይፈረዝና ሽበቱም ይጠቁር ነበር። በሉዲ ቀለም እየዘነጥን፣ በቅናሽ እየተዝናናን፣ ፒያሳ ቀውጢው ሠፈር፣ መሐሙድ ሙዚቃ ቤት አምሮታችንን እያጠረቃን ሳናስበው ያልፋል ብለን ሳንገምተው ሠላሳ ዓመት ጨርሰን አርባ ዓመት ገባን ብሎ የአርባ ዓመት ሰው ክብርና ሀብት ባለማግኘቱ ይጠዘጥዘዋል።
 • ዳሩ ግን አገራችን ላይ ላዩን ልማትና ዴሞክራሲ በሚባሉ ሉዲ ቀለሞች እውነተኛውን ማዲያቷን ደብቃ መዝናናትን እንደ ዴሞክራሲ፣ መጨፈርና መዘሞትን እንደ ሥልጣኔና እንደ መብት መከበር እየቆጠረች መከራዋን ዘርታ ማጨድ ከጀመረች ሠላሳ ዓመት አልፎ አርባ ገባ እያለን ነው። አንድም ሠላሳ ሲል ሦስት መንግሥት አሳልፈን አራተኛውን ተቀበልን ግን የመከራው ዘመን አልቆመም ሲለን ነው።

ወይ ሰባ ደረጃ ብወጣው ከበደኝ፣

ብወርደው ከበደኝ፣ መቀመጥ ከበደኝ፣

የአንተን ቁጥር በዕድሜ ደረስኩት መሰለኝ።

አረ እናንተ ሆዬ፣

ዘመን ባለጊዜው ከከንፈሩ አዋለኝ፣

ከጣቶቹ አዋለኝ ከምላሱ አዋለኝ፣

እንዲህ አጭሶ ረግጦ፣ የሰው ቁሮ አረገኝ።

 • ለአዲስ አበባ ልጅ ሰባ ደረጃ የልጅነት መቦረቂያው፣ የወጣትነት ጌጡ፣ የጎልማሳነት መቆዘሚያውና የእርጅና ዘመኑ ትዝታው ነው። ትዝታውን እያጨደ ለሚኖር የአገሬው ሰው እንዳሻው ሲመላለስበት የነበረውን ሰባ ደረጃ መውጣት፣ መውረድ፣ መቀመጥና መቆም ሲከብደው የዕድሜውን መግፋት፣ የሰውነቱን መገርጣት፣ የጉልበቱን መድከም፣ የወገቡን መጥመም እያወቀው መጣ። ይህ የማምሻ ዕድሜ ቁዘማ ነው። ዘመኑ አለፈ፣ ውበቱ ረገፈ፣ ጉልበቱ ታጠፈና ትዝታውን ብቻ እየተረከ የሚኖር፣ “እንደተወለደ… አረጀ!” የተባለለት ሰው ሆነ። ምላሱ ብቻ ቀረና ዘመን ባለጊዜው ከከንፈሩ አዋለኝ፣ አጭሶና ረግጦ የሰው ቁሮ አረገኝ ይለናል።
 • ቁሮ ግን ምንድነው? ቁሮ የሸንኮራ አገዳ ምጣጭ፣ አኝከን፣ አኝከን፣ ተጠቅመን፣ መጠን መጠን ስንጨርስ አሽቀንጥረን የምንጥለው ምጣጭና የሸንኮራ አገዳው አንጓ ከላይም ከታችም የማይመጠጠው ውዳቂው ክፍል ቁሮ ይባላል። እናም በትካዜው የወጣትነት ወዛችን ተመጦ፣ ማንም ይጠቅማሉ ብሎ የማያየን የሰው ቁሮ ሆነናል እያለን ነው።
 • ሰባ ደረጃ የእስራኤል ዘሥጋ የሰባ ዘመን መከራ፣ የእኛ የእስራኤል ዘነፍስም የተቀበልነውና የምንቀበለው የሰባ ዘመን መከራችን ይመስለኛል። ግን ለምንድነው የመከራ ዘመናችን የማያልቀው? የእኛ ዘመን ትውልድ የተረከባት አገር መከረኛ ናት። ያለፉትም በመከራ የመጡ ናቸው። እኛ የምናስረክባቸውም መከረኛዋን ኢትዮጵያ ነው። በአጭሩ የመከራ ታሪክ ተረክበን፣ የመከራ ታሪክ ሠርተን፣ መከራ የምናስረክብ ትውልዶች ሆነናል። የሚመጣው ለውጥ ሁሉ መከራ ዘርቶ መከራ የሚያሳጭደን ትውልዶች ሆነናል። ዘመኑ የወሬ ነው፣ ከወሬ በስተጀርባ ተሰሚነት ሳይሆን ሞት አድፍጧል። የሚያምር ንግግር ሁሉ አይሰማም፣ ቢሰማ እንኳ ከመስማት ያለፈ ቅብጠት ሞትን በፉጨት እንደመጥራት ይቆጠራል። እንግዲህ ራሱን ያልጣለ፣ ራሱን ይጠብቅ፣ ምክንያቱም ከማየትና ከመስማት የዘለቀ ቅብጠት ያስጨሳል፣ ያስረግጣል፣ የሰው ቁሮ አድርጎ ሜዳ ላይ ያስጥላል። የሚል ጭብጥ ከግጥሙና ከዜማው ውህደት ውስጥ ጠልቆ ይሰማኛል።

መውጫ!!

ይህ ወይዘሮ ተሠሩን ደጋግሜ ስሰማት የተሰማኝ ስሜት እንጂ የጥናት ውጤት አይደለም። አስቻለው ፈጠነ (ያያ)፣ ሰውመሆን ይስማው (ሶማክ) እና እስራኤል መስፍን (እስርሽ ነፍስ ይማር) በድጋሚ እንኳን ደስ ያላችሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles