Tuesday, May 28, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ʽያ ትውልድ!’ _ የኢሕአፓው

በአሰፋ ጉያ

ያ ትውልድ! የሶሻሊዝምና የኮሚዩኒዝም ተስፈኛ ነበር። ሶሻሊዝምና ኮሚዩኒዝም ከማንኛውም መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ግቦች ሁሉ የበለጠ የመንግሥተ እኩልነት፣ የመንግሥተ ብልፅግና፣ የመንግሥተ ፍፁማዊ ሕይወት መቀዳጃ የተስፋ መዳረሻዎቹ ነበሩ።

ʽያ ትውልድ!’ _ የኢሕአፓው | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ማርክሲዝም ሌኒንዝም ከማናቸውም መሠረተ ሐሳቦች የጎላና የገዘፈ መሠረተ አስተምህሮው፤ ቃለ ክህነቱ፣ ቃለ እምነቱና ቃለ ኃይሉ ነበር። የማጭድና የመዶሻ ሰያፍ መስቀለኛ ጥምር፣ የአርሶ አደሩንና ላብ አደሩን የዓላማና የትግል አንድነት ማሳያ ምልክቱ ነበር። እነዚህ ሁለት የዓለም ግፉአንና ምዝብር የምድር ጎስቋሎች በሚያካሂዱት የጋራና የአንድነት ተጋድሎ አድህሮቱን፣ ፊውዳሊዝሙን፣ ካፒታሊዝሙንና ኢምፔሪያሊዝሙን አቸንፈው የላብ አደሩ አምባገነንነት የሰፈነበትን መንግሥተ ዓለም የመቀዳጀታቸውን አይቀሬነት ከወዲሁ የሚያበስር ትዕምርተ ድሉ ነበር።

ያ ትውልድ! የአሲምባ ምርኮኛ ነበር። አሲምባ ከቅድስት ኢየሩሳሌም፣ ከመካ እና መዲና፣ ከሆራ አርሰዲ (ኢሬቻ)፣ ከደብረ ሮሃ አብያተ ክርስቲያን፣ ከሸህ ሁሴን፣ ከግሸን ደብረ ከርቤ፣ ከአርሲዋ እመቤት፣ ከአክሱም ጺዮን ሆነ ሌላ ማናቸውም የተቀደሰ የጸሎት፣ የምስጋናና የቡራኬ ቦታ ሁሉ የላቀ መካነ ቡራኬውና መካነ ክህነቱ ነበር ለዚያ ትውልድ።

ያ ትውልድ! የነፃነት አርበኛ ነበር። አካሉንና ሕይወቱን ለነፃነት ለመገበርና መስዋዕት ለመሆን የማይሳሳ የነፃነት ቀንዲል ነበር። ለሕዝብ ደኅንነትና ነፃነት የሚገደው ቆራጥ ተሟጋች ነበር።

ያ ትውልድ! የቀይ ኮከብ ፋኖ ነበር። አድህሮትንና ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን አገዛዝን ለመፋለም በየጎራው የተዋደቀ የኣርነት ተጋዳይ፤ ሞትን የናቀ፣ ሕይወቱን የገበረ፣ ጀግና ነበር ያ ትውልድ!።

      ‹ፋኖ ተሰማራ _ ፋኖ ተሰማራ

እንደ ሆቺሚኒ እንጀ ቼ ጉቤራ

ትግሉን እንድትመራ›

ዝማሬን እያዜመ የኢሕአፓ አባል እና ደጋፊ ከዓለም ማዕዘናት ሁሉ ወደ አሲምባ ተራራ ወደ ትግሉ ጎራ ያማትር የነበረው።

‹ልጓዝ በድል ጎዳና…

በወደቁት ጓዶች ፋና›

እያለ ነበር ያ ትውልድ የነፃነት ችቦ አንግቦ ከየነበረበት ቦታ ሁሉ በእግሩም በልቡም ወደዚያች ‹ቅድስት› ተራራ እና የትግል ሜዳ ሌት ተቀን ይተም የነበረው። በዚህ ጉዳይ ላይ ‹ወጣትነት በዘመነ አብዮት› ወይም ‹ኩ!.. ኩ!…በረከቴ› በሚል ርዕስ የፃፍኩት ግጥሜ (በሰምና ወርቅ መጽሐፌ በገጽ 64) መካተቱን ልብ ይሏል!

 በወቅቱ የነበረን የወጣትነት ሕይወት እና እኔም ያሳለፍኩትን የትግል ዘመኔን የቃኘሁበት ነው። ለቅምሻ የተወሰኑ ስንኞችን ልጥቀስ።

ስማኝ ልጄ!

ሕዝብን ብዬ በወጣትነት

በጦራ በዕድገት በኅብረት

በፈረስ ጀርባ ሆኜ ስጣደፍ

ጭቆናና ብዝበዛን ልናደፍ።

ውስጤ ሲግል በለውጥ ረመጥ

ወደ ዚያች ቅድስት አምባ

ወደ አሲምባ ልሸመጥጥ፡፡

ከነተሼ ጋር በአሶሳ በኩል ስናቆራርጥ

በፋሺስቶች መዳፍ ተይዘን…፡፡

ይህንንና ከላይ የጠቃቀስኩት የ‹ያ ትውልድን› ታሪክ ለማተት ሳይሆን ትውልዱ በዚያ የፈተና ዘመን በምን ሁኔታ ውስጥ እንደ ነበርና ያን አስከፊ ሁኔታ ለውጦ አገሩን የት ለማድረስ ይታገል እንደ ነበር ሊያስቃኝ ይችላል ብዬ ነው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በ1968 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ ‹‹ቀኖናዊነትና ጥገናዊነት›› በሚል ርዕስ በስሜ የጽፍኩትን የወቅቱን የኢሕአፓ የፖለቲካ አቋም የሚገልጽ ጽሑፍ ለዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ልኬ ነበር። ሆኖም ግን በወቅቱ የዕድገት በኅብረትና የሥራ ዘመቻን አቋርጬ እንደኔው ዘመቻውን ካቋረጡ አራት የትግል ጓዶቼ ጋር የነፃነት አምባ ወደ ሆነችው ወደዚያች ማግኔታዊ ተራራ- አሲምባ ፥ ለመጓዝ በአሶሳ በኩል አቆራርጠን ወደ ሱዳን ለማምራት ጉዞ ጀመርን። አሶሳ ከተማ ልንገባ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ሲቀረን በጉዞ ላይ እንዳለን በኬላ ጠባቂዎች መዳፍ ውስጥ ወደቅን። ኬላ በመድፈር ተከሰን፣ ከሁለት ወራት በላይ ወህኒ ቤት ታስረን ፍርድ ቤት ቀርበን፣ ከእስር ተፈታን። ከእስር ቤት ስለመፈታታችንም ከፍርድ ቤቱ የጽሑፍ ማስረጃ ተሰጠን።

ይሁንና ከፍርድ ቤቱ ደጃፍ ፈቀቅ ሳንል ወዲያው መልሰው በቁጥጥር ስር አዋሉንና እንደገና ወደ ወህኒ ቤት መለሱን። ለምን? በማለት ጠየቅናቸው። እነሱም ‹ፍርዱ የተሰጣችሁ ኬላ በመድፈር ነው። የዕድገት በኅብረት ዘመቻን በማቋረጣችሁ ሌላ ክስ በአዲስ አበባ ይጠብቃችኋል›; በማለት መልስ ሰጡን። በተመሳሳይ ምክንያት እዚያው አሶሳ ወህኒ ቤት ታስሮ የነበረ አንድ ወጣት ከኛ ጋር ታክሎ በሁለት ፖሊሶች ታጅበን ስድስት እስረኞች ሆነን ከተወሰኑ ቀናት በኋላ አዲስ አበባ ከተማ ደረስን። አዲስ አበባ ከተማ እንደገባን የማምለጥ ሙከራ ብናደርግም ሳይሳካልን ቀረ። ትግሉን ቀጥዬ ጎጃም ክፍለ ሀገር ደብረማርቆስ ከተማ ለረጅም ጊዜ ታስሬ ተፈታሁ፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፤ በዚሁ ልቋጨው፡፡

ነግር ግን የወቅቱን ስሜት (የትግል እንቅስቃሴ) ‹‹ተነሱ!!!›› በሚል ርዕስ ሥዕል የሣልኩ ሲሆን ቀጥሎ ከጽሑፍ ማብራሪያ ጋር አካትቸዋለሁ፡፡

ቃል ከምስል ሲገናዘብ፡-

የሥዕል ቦታ

ከላይ የቀረበው ሥዕል ‹‹ተነሱ!!!›› የሚል ርዕስ የሰጠሁት ሲሆን ቃል ከምስሉ ሲገናዘብ:- በኮሚዩኒስት ሊግ ተለኩሶ፤ የቦታንና የጊዜን ድንበር ጥሶ ዓለማችንን ከዳር እዳር አዳርሶ የነበረውን የሠራተኛውን መራር የመደብ ጦርነት ነው ለማስረዳት የሚሞክረው።

በሥዕሉ መሃል ለመሃል የሚታየው የሠራተኛው መደብ አስተማሪና መሪ፣ የሠራተኛው መደብ ርዕዮት ቀማሪ የሆነው ካርል ማርክስ ‹‹ተነሱ!!!›› እያለ፥ ሞራላቸው ለደቀቀ፣ መንፈሳቸው ለወደቀ፣ ተስፋቸው ለመነመነ፣ ጉልበታቸው ለኮሰመነ፣ በጭቆናና ብዝበዛ ለሚማቅቁ የዓለም ላብ አደሮች የትግል ጥሪ ሲያደርግ ነው።

ቀዩ ሰንደቅ የባርነት ሰንሰለቶችን ለመበጣጠስ በአቸናፊነት መንፈስ በዓለም ዙሪያ ሲውለበለብ፣ ኮሚዩኒስት ማኒፌስቶ ዓለምን ከሥር ደግፎና አቅፎ፣ ማጭድና መዶሻው ደግሞ የላብ አደሩንና የአርሶ አደሩን አንድነት ሲፈነጥቅ እና ምድሩ በአመፃ ሲርድ፣ ሰማዩ በጪስ ሲታፈን ነው ሥዕሉ የሚያሳየው።

በተጨማሪም ማዕከላዊ መልዕክቱ:-

‹‹ተነሱ!!!›› የምድር ጎስቋሎች የትግል ጥሪ ነው።

‹‹ተነሱ!!!›› የዓለም ላብ አደሮች የኅብረት ድምፅ ነው።

‹‹ተነሱ!!!››; የኮሚኒስት ማኒፌስቶ መሪ ቃል ነው።

ነገር ግን ሰንሰለቶቹ አለመበጣጠሳቸውን፣ ጨለማውም አለመገፈፉንና ራዕዩ ከግብ ሳይደርስ ህልም ሆኖ መቅረቱን ነው

የሞዛይኩ ዋና መልዕክት!

‹ባናሸንፍም አልተቸነፍንም

አያልቅም ይህ ጉዞ› ብሎ ነበር ያ! ታላቁ የጥበብ ሰው፦ ገጣሚውና ሠዓሊው የደብተራ ደስታ ነገዎ ልጅ- ገብረክርስቶስ ደስታ።

ይህ ጉዞ ጓድ ሌኒን እንዳለው ‹አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት እርምጃ ወደ ኋላ› … እንደ ሊቀመንበር ማኦ ‹ረዥሙ ዘመቻ› … እንደ ጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም ‹ወደፊት!› … እንደ ጓድ መለስ ‹ቆረጣ› &… እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ‹ቁልቁለት› …እንደ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ‹ሁለገብ›… እንደ ልደቱ ‹ሦስተኛው› … እንደ ፕሮፌሰር መረራ ‹መስቀለኛ መንገድ›;… እንደ ኦቦ ለማ ‹ሱሴ›… እንደ ጃዋር ‹ከበባ› … እንደ ኦቦ ዳውድ ‹…›፣ እንደ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ‹…›;… ወይስ … እንደ ዶ/ር ዓብይ /አብቹ/ ‹መደመር› …

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ሠዓሊ፣ ገጣሚና ደራሲ ሲሆኑ ከግጥም መድብሎቻቸው መካከል፣ የከንፈር ወዳጅ፣ ከዝርው ሥራዎቻቸው መካከል ሰምና ወርቅ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles