Tuesday, May 28, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይዳፈን ጥንቃቄ ይደረግ!

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር አሁንም ጤና አልባ ሆኖ የተለመደው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ሊሻሻል ያልቻለው የፖለቲካ ምኅዳር ሰሞኑን አዲስ ክስተት ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ ባለፈው ሰሞን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ስብሰባ ከተቀመጡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተወሰኑት፣ ለአደባባይ ያበቁት ቅሬታና ስሞታ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ በስብሰባው ወቅት ያነሷቸው ጥያቄዎችና የተሰጧቸው ምላሾች ከመቆራረጣቸው ባሻገር፣ ለሰላማዊ ትግል የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የሚያውኩ ድርጊቶች መብዛታቸውን ድምፃቸውን ካሰሙ ፓርቲዎች ተወካዮች መረዳት ተችሏል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ውስጥ የማይመቹና የሚጎረብጡ ችግሮች መኖራቸው የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ገዥው ፓርቲም ሆነ የሚመራው መንግሥት ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክሩ ጨርሶ እንዳይዳፈን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ የመድበለ ፓርቲ ፖለቲካ ሥርዓት ዕውን የሚሆነው ሰላማዊ ፉክክር ሲኖር ብቻ ነው፡፡

ገዥው ብልፅግና ፓርቲ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የሚኖረው ግንኙነት ጤናማ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ በጋራ ፖለቲካ ምክር ቤት አማካይነትም ሆነ በተጠናል የሚደረጉ ግንኙነቶች ጤነኝነት ሲጎድላቸው፣ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ወደ ጎን እየተገፋ የትጥቅ ትግል አማራጭ ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያዋጣናል እስካሉ ድረስ ቢፈልጉ በነጠላ ካልሆነም በጥምረት ወይም በግንባር የመሰባሰብ ኃላፊነት የራሳቸው ሲሆን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ከመስጠት ይልቅ የፖለቲካ ምኅዳሩ ወለል ብሎ እንዲከፈት ትኩረት መስጠት ነው የሚገባው፡፡ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ዋና ሥራ ገዥውን ፓርቲ በማሳጣት የሕዝብ ድጋፍ ማግኘት ስለሆነ፣ ከገዥው ፓርቲ በኩል የሚፈለገው ሕዝብን የሚያሳምን ሥራ ማከናውን ነው፡፡ ሕዝብ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤትነቱ የሚረጋገጠው ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩል ምኅዳር ውስጥ በነፃነት ሲንቀሳቀሱ ነው፡፡

ሰላም የራቃት ኢትዮጵያ የበለጠ ትርምስ ውስጥ እንዳትገባ የሚያግዘው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ ትግል ነው፡፡ ልዩነቱ እየሰፋና አለመተማመኑ እየጨመረ ሲሄድ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ ይዳፈናል፡፡ ከበቀደሙ የጠቅላይ ሚኒስትሩና የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስብሰባ ማግሥት መገንዘብ የተቻለው፣ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉን የሚገዳደሩና ተስፋ የሚያስቆርጡ አየሩን መሙላታቸውን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ዕሳቤ የሚስፋፋና የብዙዎችን ቀልብ የሚስብ ከሆነ ሰላማዊ ትግል እየተዳከመ፣ የትጥቅ ትግል በየቦታው እየተራባ ሊቋቋሙት የማያስችል ቀውስ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ለዚህም ነው ለመድበለ ፖለቲካ ፓርቲ ሥርዓት መጠናከር ማናቸውም መስዋትነት መከፈል ያለበት፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ለመጣል የሚያስፈልጉት የፖለቲካ ምኅዳሩን የሚያሰፉ ሕጋዊና ፖለቲካዊ መደላድሎች ናቸው፡፡ ከዚያ ውጪ እስር፣ ማስፈራራት፣ ዘለፋና የመሳሰሉ አሉታዊ ድርጊቶች ሰላማዊ ትግሉን ችግር ውስጥ ይከቱታል፡፡

በኢትዮጵያ ምድር ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን ተንከባክቦ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር ጥረት ማድረግ ሲገባ፣ አሁንም የተለመደው ቅራኔና ትንቅንቅ ውስጥ ለመቀጠል መፈለግ ውጤቱ ኪሳራ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪዎቹ ከምንም ነገር በላይ ለሕግ የበላይነት መከበርና ለሰላማዊ ግንኙነት ቅድሚያ ይስጡ፡፡ ልዩነቶቻቸውን የሚያስተናግዱበት ጨዋነት ያሳዩ፡፡ ለጉልበተኝነትና ለሕገወጥነት ከሚያደፋፍሩ ድርጊቶች ይቆጠቡ፡፡ በተለይ ገዥው ፓርቲ አርዓያ ሆኖ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ እንዲጠናከር ኃላፊነቱን ይወጣ፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ውስጠ ዴሞክራሲ አሠራራቸውን እያጎለበቱ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል መዳበር የሚፈለግባቸውን ይወጡ፡፡ ገዥው ፓርቲ አገር የሚመራ በመሆኑ በርካታ ኃላፊነቶች ቢኖሩበትም፣ ለሰላማዊ የፖለቲካ ምኅዳር የሚጠበቅበትን ማድረግ ካልቻለ ዋናው ችግር ፈጣሪ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያን ተስፋ ከሚያጨናግፉ አጉል አስተሳሰቦች መላቀቅ የግድ መሆን አለበት፡፡

ከበቀደሙ ውይይት በኋላ ከአንዳንድ ወገኖች በኩል ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ እንዳበቃለት ዓይነት ንግግሮች ሲደመጡ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን ወደ ጎን ገፍቶ የተለመደውን ትንቅንቅ ማበረታታት፣ ከሚያስከትለው ዕልቂትና ውድመት ባሻገር አገር የሚያፈርስ መዘዝ ያመጣል፡፡ አሁንም ካለፉት የጥፋት ስህተቶች መማር ባለመፈለግ ግጭትን ማበረታታት ከቀጠለ፣ ተከትሎ የሚመጣው አገርን ተባብሮ የማፍረስ ዘመቻ ነው፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ በጊዜያዊ የፖለቲካ ሙቀት ስሜት በመናጥ ሰላማዊና ሕጋዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲዳፈን ከማገዝም ሆነ ከማበረታታት መታቀብ አለባቸው፡፡ እነ ሶማሊያ፣ የመን፣ ሊቢያ፣ ሶሪያና መሰል አገሮች ቀውስ ውስጥ ገብተው መውጣት ያቃታቸው የፖለቲካ ልሂቃኖቻቸው አርቀው ማሰብ ባለመቻላቸው ነው፡፡ ከእነዚህ የጨነገፉ አገሮች የውድቀት ታሪክ አለመማር ቋፍ ውስጥ ያለችውን ኢትዮጵያን እንጦረጦስ መክተት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ በጣም አስቸጋሪው ነገር በንግግርና በድርድር ችግርን መፍታት አለመለመዱ ነው፡፡ ልዩነትን ይዞ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በሰከነ መንገድ መነጋገር ባህል ባለመሆኑ፣ ከመቀራረብ ይልቅ በሩቅ ሆኖ መጠማመድና አመቺ ጊዜ ሲገኝ አንዱ ሌላውን ለማጥፋት ማድባት ክፉ ልማድ ሆኖ ዘልቋል፡፡ ሥልጣን ላይ የወጣው ከመንበሩ ላይ እንዳይነቀነቅ ጉልበትን አማራጭ በማድረግ መብቶችን ሲያፍን፣ ለሥልጣን የሚታገለውም በለሱ ሲቀናው ያንኑ የጥፋት መንገድ ለማስቀጠል ይማስናል፡፡ ሕዝብና አገርን ማዕከል በማድረግ ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች፣ ለፍትሕና ለነፃነት፣ ለእኩልነትና ለጋራ ጥቅም መከበር መሥራት አይፈለግም፡፡ ይልቁንም ለቅራኔና ለተቃውሞ ምክንያት የሚሆኑ ብልሹ አሠራሮችን በማስፈን አገርን የጥፋት ቤተ ሙከራ ማድረግ ቀላሉ መንገድ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ድርጊት ግን ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡ አሁንም ጊዜው ቢረፍድም የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይዳፈን ጥንቃቄ ይደረግ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ያቀረቡት መልቀቂያ ተቀባይነት ማግኘቱ ተሰማ

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት የቀድሞው የውኃ ሀብት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለዘመኑ በማይመጥን ዕሳቤ አገር ማተራመስ ይብቃ!

ዘመኑ እጅግ ድንቅ የሚባሉ የሥልጣኔ ትሩፋቶችን በረቀቁ ቴክኖሎጂዎች እያቋደሰ ነው፡፡ ለልማትና ለዕድገት የሚማስኑ የኑሮን ጫና ቀለል የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን በብዛትና በስፋት ሲጠቀሙ፣ ያላደላቸው ደግሞ እርስ...

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...