Wednesday, May 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየዳኞች ደመወዝ አነስተኛ መሆን በፍርድ ቤቶች አሠራር ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው ተባለ

የዳኞች ደመወዝ አነስተኛ መሆን በፍርድ ቤቶች አሠራር ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው ተባለ

ቀን:

የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ፍርድ ቤቶች ተወካዮችን ጨምሮ የ12 ክልሎች የፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች በተገኙበት መድረክ፣ የዳኞች ደመወዝ አነስተኛ በመሆኑ በፍርድ ቤቶች አሠራር ላይ ችግር እየፈጠረ እንደሆነ ተነገረ፡፡

በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስተባባሪነት መጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ በተካሄደው የሕግ ተርጓሚዎች መድረክ ላይ የተገኙ የክልል ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶች ባቀረቡት የአፈጻጸም ሪፖርት፣ በርካታ የፍርድ ቤት የአሠራር ችግሮችን ከመፍትሔዎች ጋር አመላክተዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት የጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎሺፕ ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ፓስተር ዳንኤል ገብረ ሥላሴ፣ የዳኞች ደመወዝ አነስተኛ መሆን ለሙስና ሊያጋልጥ ስለሚችል ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል፡፡ ጠበቆች የሚያገኙት ክፍያ የተሻለ ስለሆነ፣ ዳኞች ሥራቸውን በመልቀቅ ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

በፍርድ ቤት አገልግሎት አሰጣጥ በርካታ ችግሮች በማንሳት የዳኞች ደመወዝ አነስተኛ በመሆኑ  ዳኞች የኑሮ ውድነት መቋቋም ባለመቻላቸው ሥራ እየለቀቁ ነው ያሉት ደግሞ፣ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ገዛሊ አባሲመል ናቸው፡፡

አዲስ አበባን ጨምሮ አዳማ፣ ሻሸመኔ፣ ነቀምትና ጅማ አካባቢዎች ባሉ ፍርድ ቤቶች ከ600 ሺሕ በላይ ጉዳዮች በዓመት በሚንቀሳቀሱባቸው የኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች፣ የዳኞች አገልግሎት ጥራት አለመኖር፣ የቅልጥፍናና የተደራሽነት ችግር፣ የተጠያቂነትና የሚዛናዊነት፣ እንዲሁም የውስጥ መልካም አስተዳደርና የማስፈጸም አቅም ማነስ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው ብለዋል፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ማነቆ የሆኑ ሕጎችን ማሻሻል ዋነኛው ሥራ በመሆኑ፣ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ያፀደቀውን የፍርድ ቤቶችን ማቋቋሚያ ሁለት አዋጆችን በማሻሻል፣ በከፍተኛ ፍርድ ቤትና በጠቅላይ ፍርድ ቤት ተንጠልጥሎ የነበረው ሥልጣን ወደ ወረዳ እንዲወርድና ሕዝቡ በአቅራቢያው አገልግሎት እንዲያገኝ መደረጉን፣ አዋጆችን ተከትለው የተለያዩ ደንቦችና መመርያዎች ፀድቀው ወደ ሥራ መግባታቸውን አብራርተዋል፡፡

የዳኞች አስተዳደር ጉባዔን ለማቋቋም በወጣው ደንብ መሠረትም የዳኞች መብቶችና ነፃነቶች እንዴት ማክበር እንደሚቻል፣ ዳኞችን ከሥራ ለማሰናበት የሚያስችሉ ምክንያቶች ምን እንደሆኑ፣ ዳኞችን ለመቅጠርና ዕድገት ለመስጠት የሚረዳ ደንብ ፀድቋል ብለዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች ከተከናወኑ ዋነኛ ለውጦች መካከል በክልሉ ባሉ ወረዳዎች በሙሉ ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን በማቋቋም የከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ሥራ በመውሰድ፣ በዘንድሮ በጀት ዓመት ከባለጉዳዮች ይወጣ የነበረውን እስከ 1.4 ቢሊዮን ብር ወጪ ማዳን አንዱ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት በአንድ ዳኛ ብቻ የሚታዩ የነበሩ ከ300 ሺሕ ብር በላይ ያሉ ጉዳዮች፣ በ2016 ዓ.ም. በሦስት ዳኞች እንዲታዩ ማድረግ መቻሉ አንዱ ማሻሻያ የተደረገበት ነው ብለዋል፡፡

አንድ ዳኛ በተደጋጋሚ የሚሰጠው ውሳኔ ይግባኝ በመሄድ የሚሻርበት ከሆነ፣ የዳኛው የሥራ አፈጻጸም የሚገመገምበት አሥራር በማዘጋጀት የለውጥ ሥራዎች መከናወናቸውን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ የክልል ፍርድ ቤቶች ባቀረቡት ሪፖርት ከተገለጹ ችግሮች መካከል በፌዴራል ደረጃ የሚወጡ ሕጎች ከክልል ሕጎች ጋር የሚቃረኑ መሆናቸው፣ ሕጎች በክልል ቋንቋ አለመተርጎማቸው፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ውስንነት፣ የዳኞች ተጠያቂነት፣ የደንበኞች በቀጠሮ መጉላላት፣ እንዲሁም የበጀት እጥረት  ናቸው ተብሏል፡፡

የፍርድ ቤቶች የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የሦስት ዓመታት ዕቅድ ያካተተው የፍርድ ቤቶች የለውጥ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት የዳኝነት ነፃነት፣ ተጠያቂነትና ፍጥነት ያካተተ ተግባር እየተከናወነ ነው ሲሉ የገለጹት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት ናቸው።

የለውጥ ሥራው ኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ቅሬታ ለመቅረፍና ከተጠያቂነት ጋር ተያይዞ ሲነሱ ለነበሩ ውዝፍ የሥነ ምግባር ጥሰት አቤቱታዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት፣ የለውጡን ፍኖተ ካርታ ለመተግበር የአሠራር ማሻሻያ ሥራ እንደሚደረግ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

የአገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች መድረክ ውይይት ከተጠናቀቀ በኋላ የጋራ የአቋም መግለጫ ወጥቷል፡፡ በፌዴራልና በክልል ለሚገኙ ፍርድ ቤቶች በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማስቻልና በክልል ፍርድ ቤቶች የቀረቡ የለውጥ ሒደቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ለዳኝነት አገልግሎት ጥራት ተግዳሮት የሆኑ ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶችን መፍታት እንደሚያስፈልግ በአቋም መግለጫው ተጠቅሷል፡፡

በተያያዘም መጋቢት 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ በተካሄደው ስድስተኛው ዙር የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጉባዔ የውይይት መድረክ ላይ እንደተገለጸው፣ አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ቁጥር 1234/2013  መሠረት  አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ አዳዲስ ሕጎች እንዲወጡ ወይም ነባር ሕጎች እንዲሻሻሉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሳብ ማቅረብ፣ በአጠቃላይ የፍርድ ቤቶችን  ውጤታማነት ከፍተኛ የሚያደርጉ የማሻሻያ ሐሳቦችን ማዳበር የጉባዔው ሥልጣንና ኃላፊነት መሆኑን፣ የጉባዔው ሰብሳቢና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም በፌዴራል ፍርድ ቤቶች  ጉባዔ  የተከናወኑ ተግባራትና  የተገኙ ውጤቶች የቀረቡ ሲሆን፣ ወደፊት  ሊሠሩባቸው የሚገቡ የትኩረት አቅጣጫዎች ምን ምን ሊሆኑ እንደሚገባም ውይይት ተደርጓል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...