Tuesday, May 28, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማክበር፣ ለአድልኦና ለሙስና በር የሚከፍቱ ብልሹ አሠራሮችን ማስወገድ፣ ሕግና ሥርዓት ማስፈንና ልማትን በስፋት ማቀላጠፍ ነው፡፡ እነዚህን ተግባራት ሲያከናውን ሥራው ከላይ እስከ ታች በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ መንግሥት ለመምራት የሕዝብ ድምፅ ያገኘ ገዥ ፓርቲ፣ በተቻለ መጠን ሥራው ከመንግሥት ሥራ ጋር እንዳይደባለቅ መጠንቀቅ አለበት፡፡ የሚመራው መንግሥት ተሿሚዎች በዕውቀት፣ በሥራ ልምድ፣ በሥነ ምግባርና በሕዝብ ዘንድ ባላቸው ተቀባይነት መለካት ይኖርባቸዋል፡፡ እነሱ በዚህ መሠረት ብቁ ሲሆኑ የሚመሯቸው ተቋማትም ጥንካሬ እያገኙ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ የሚዳኙትም በሕዝብ ህሊና ስለሆነ በሙገሳ አይታለሉም፣ በነቀፋም አይደናገጡም፡፡

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት በ1966 ዓ.ም. አብዮት ከተገረሰሰ በኋላ በየተራ ሥልጣን ላይ የወጡት ደርግ፣ ኢሕአዴግና ብልፅግና የሚለያዩበት የየራሳቸው መገለጫ ቢኖራቸውም፣ የሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት የሚሄዱበት ርቀት ግን ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው፡፡ በደርግ ጊዜ ሕዝቡ በግዳጅ በነቂስ የያኔው አብዮት አደባባይ ወጥቶ ድጋፍ እንዲሰጥ፣ ወይም ክብረ በዓላትን እንዲያዳምቅ ይደረግ ነበረ፡፡ በወቅቱ በአብዮት ጠባቂዎች እየተዋከበ አብዮት አደባባይ በግዳጅ ይገኝ የነበረ ሕዝብ፣ በዘመነ ኢሕአዴግም በተለያዩ ምክንያቶች በግፊት መስቀል አደባባይ እየተገኘ ተመሳሳይ ድጋፍ ሲሰጥ ነበር ዓመታት የነጎዱት፡፡ አሁንም በዘመነ ብልፅግና በተለያዩ አደረጃጀቶች አማካይነት ለድጋፍ የሚፈለገው ሕዝብ፣ መስቀል አደባባይን ሲያጨናንቅ መመልከት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በየክልሉም ተመሳሳይ ድርጊት ነው የሚፈጸመው፡፡ ለተቃውሞ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ግን ያለው ችግር ይታወቃል፡፡

በመላ አገሪቱ በተለያዩ መልክዓ ምድሮችና የአየር ፀባዮች ውስጥ የሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከድሮ ጀምሮ መንግሥትን ያከብራል፡፡ ለሕግና ለሥርዓት መስፈን ክብር ስላለው ሕገወጥ ድርጊቶች ውስጥ መገኘት አይፈልግም፡፡ በተለምዶ እንደሚባለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአገዛዝ የሚመች ብቻ ሳይሆን፣ ‹‹በሕግ አምላክ›› ከተባለ አንዲት ጋት ለመራመድ የማይፈልግ ነው፡፡ አንዳንድ ሕገወጦችና ሥርዓተ አልበኞች ይህንን የመሰለ አኩሪ እሴት ለመናድ ሙከራ ቢያደርጉም፣ አብዛኛው ሕዝባችን ሕግና ሥርዓት አክብሮ ለመኖር ፍፁም ፈቃደኛ እንደሆነ ማንም አይክድም፡፡ ይህንን የመሰለ ታሪክ ያለው ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ በቅጡ ለመምራት የሚያስፈልገው፣ በሀቅና በቅንነት ላይ የተመሠረተ የአመራር ዘይቤ ነው፡፡ ሕዝቡ እያንዳንዱን አገራዊ እንቅስቃሴ በሚገባ ስለሚገነዘብ፣ ማን እንደሚጠቅመውና እንደሚጎዳው ስለሚረዳ አጉል ሽንገላ አይፈልግም፡፡ ይልቁንም በሥርዓት መመራት ነው የሚሻው፡፡

መንግሥትን የሚመራው ብልፅግና ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪዎቹ ከማንም በላይ ማክበር የሚገባቸው፣ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ ብልፅግና ፓርቲ የሕዝብ ድጋፍ እንዳለው ማሳያው በየምክንያቱ አደባባይ የሚጠራው ሕዝብ እንዳልሆነ ማወቅ አለበት፡፡ ለሥልጣን የሚፎካከሩ ሌሎች ፓርቲዎችም ምንም ሳይሠሩ በስማቸው ጠብ የሚልላቸው ነገር እንደሌለ መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ሁሉም ፓርቲዎች ሕዝብ ዘንድ ሲቀርቡ ምን ዓይነት ዓላማና የልማት አጀንዳ እንዳላቸው ከሚያስረዳው ማኒፌስቷቸው ጋር፣ በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ሕዝብን ለማሳመን የሚያስችል ከሴራና ከአሻጥር የጠራ ቅንነት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ አገር እያስተዳደረ ያለው የብልፅግና መንግሥት በተለያዩ ጉዳዮች በርካታ ጥያቄዎች ስለሚነሱበት፣ በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ ሥራውን እያከናወነ አሳማኝ ሆኖ ለመቅረብ ጥረት ማድረግ አለበት፡፡ ከደጋፊ ምስክርነት በላይ የነቃፊን ድምፅ ማዳመጥም ይጠቅመዋል፡፡

ባለፈው ሰሞን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በነበራቸው ቆይታ የተነሱላቸውን ጥያቄዎች በፅሞና ማጤን ይገባል፡፡ በመንግሥታቸው ለተከናወኑ ሥራዎች የተሰጠውን ሙገሳ ያህል ነቀፌታም ሲቀርብ ለምን ብሎ ማዳመጥ ተገቢ ነው፡፡ ነቀፌታና ተቃውሞ በምክንያታዊነት ሲቀርቡ ጆሮ ሰጥቶ ማዳመጥ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም፡፡ ሙገሳ ሲበዛና ነቀፌታ ሳይኖር ሲቀር ለምን ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ በሙገሳ የተካኑ አስመሳዮችና አድርባዮች አንድ ችግር ሲያጋጥም ወይም ጊዜ ዘንበል ሲል፣ ለወቀሳና ለማሳጣት ማንም እንደማይቀድማቸው ሥርዓት በተቀያየረ ቁጥር በየቴሌቪዥን ጣቢያው ምን ሲሉ እንደነበረ የታወቀ ነው፡፡ በመርህ ላይ የተመሠረቱ ነቀፌታዎች ወይም ማሳሰቢያዎች ለአገረ መንግሥቱ ብቻ ሳይሆን፣ ለሥርዓቱ ጭምር እንደ መልካም ዕድል ይታዩ፡፡ በጨዋነት፣ በመከባበርና በአርቆ አሳቢነት መደመጥ የሚገባቸው መልካም ሐሳቦች እየጠፉ ነው አገር ለችግር የምትዳረገው፡፡

ዜጎች መንግሥትን የመደገፍም ሆነ የመቃወም ሕጋዊ መብት አላቸው፡፡ ይህንን መብታቸውን ሲጠቀሙም ሕጋዊና ሰላማዊ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ መብቱን የሚጠይቅ ግዴታውን መዘንጋት የለበትም፡፡ የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብቶች ጽንሰ ሐሳብ የሚያተኩረው፣ ማንም ሰው መብቱን ሲጠይቅ ግዴታውንም መዘንጋት እንደሌለበት ነው፡፡ በዚህ እውነታ ላይ ተመሥርቶ የሚከናወን የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ዋና ግቡ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የተመቻቸ ንጣፍ ማዘጋጀት ነው፡፡ በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥትም ሆነ በዚህ መንገድ ሥልጣን ለመያዝ የሚዘጋጅ የፖለቲካ ፓርቲ፣ ማክበር ያለበት የሥልጣን ሉዓላዊ የሆነውን መራጭ ሕዝብ ነው፡፡ ብልፅግና ፓርቲም ሆነ የሚመራው መንግሥት በኢትዮጵያ ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክሩ መሬት ረግጦ እንዲከናወን፣ ከድጋፍ ባሻገር ያለውን ተቃውሞ ሥርዓት ባለው መንገድ ለማስተናገድ ቁርጠኛ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ መስጠት አለበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ያቀረቡት መልቀቂያ ተቀባይነት ማግኘቱ ተሰማ

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት የቀድሞው የውኃ ሀብት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለዘመኑ በማይመጥን ዕሳቤ አገር ማተራመስ ይብቃ!

ዘመኑ እጅግ ድንቅ የሚባሉ የሥልጣኔ ትሩፋቶችን በረቀቁ ቴክኖሎጂዎች እያቋደሰ ነው፡፡ ለልማትና ለዕድገት የሚማስኑ የኑሮን ጫና ቀለል የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን በብዛትና በስፋት ሲጠቀሙ፣ ያላደላቸው ደግሞ እርስ...

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...