Thursday, June 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግብርና ገቢ ግብር ለመጀመር ጥናት ሊደረግ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት የግብርና ገቢ ግብር ለመጀመር የሚያስችል ጥናት በዚህ ዓመት እንደሚጀመር አስታወቀ፡፡

በቅርቡ ይፋ በተደረገው ዝርዝር የሁለተኛው የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሰነድ ውስጥ፣ ‹‹የግብርና ታክስ ለመጀመር የሚያስችል ጥናት ይደረጋል፤›› ይላል፡፡

ጥናቱን እንዲያደርግ የተመረጠው የገንዘብ ሚኒስቴር ሲሆን፣ ለጥናቱ በሰነዱ ላይ የተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳም ሰኔ 2016 ዓ.ም. መሆኑን ሪፖርተር የተመለከተው ሰነድ ያሳያል፡፡

‹‹የመንግሥትን የታክስ ገቢ መሠረት ለማስፋት የተለያዩ የሕግ ማሻሻያዎች ይደረጋሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የግብርና ገቢ ግብር ሲሆን፣ በዚህ ላይ ጥናት በማድረግ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ የግብርና ገቢ ግብር የሚጣለው ከፍ ያለ ገቢ በሚያገኙ አርሶ አደሮች ላይ ይሆናል፤›› ይላል ሰነዱ፡፡

ታክሱ የሚጣለው በአነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮች ወይም በትልልቅ የግል እርሻዎች ላይ ብቻ መሆኑን በተመለከተ ሰነዱ የሚገልጸው የለም፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የግብርና ባለሙያዎች፣ የግብርና ገቢ ግብር የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ ልከው የተሻለ የውጭ ምንዛሪ በሚያስገኙት ላይ ካልሆነ በስተቀር፣ በአነስተኛ ገበሬዎች ላይ ከተጀመረ ለዘርፉ ከባድ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ የግብርና ገቢ ግብር መጀመር እንዳለበት ገልጸው፣ ለዚህም መንግሥት ግብዓቶችን በድጎማ ማቅረቡን እንደ ምክንያት ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ የግብርና፣ የገቢዎችና የገንዘብ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ስለዕቅዱ ተጠይቀው ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር የታክስ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ዋሲሁን አባተ ስለጉዳዩ ተጠይቀው ‹‹አላውቅም›› ብለዋል፡፡

በግብርና ዘርፍ ውስጥ ከ15 ሚሊዮን የሚበልጡ አባወራ (Households)  አርሶ አደሮች ሲኖሩ፣ ከእነዚህ ውስጥ ከ95 ከመቶ አነስተኛ አርሶ አደሮች ናቸው፡፡ ትልልቅ የግል እርሻዎች ከአምስት ከመቶ በታች መሆናቸው ይታወቃል፡፡

የግብርናው ዘርፍ ባለፉት ዓመታት በአማካይ ስድስት በመቶ እያደገ ሲሆን፣ በባለፉት ሦስት ዓመታት ለወጪ ንግድ ገቢ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በየዓመቱ በአማካይ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች