Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ከቢሻን ጋሪ እስከ ዶባ ቢሻን እንክብል

ዶባ ኢንዱስትሪያል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መጋቢት 24 ቀን 2016 .. ሦስት ዓመታት በላይ ጥናትና ምርምር ያደረገበትንና ለገበያ ያበቃውን ዶባቢሻን እንክብል የውኃ ማከሚያ ምርት ለባለ ድርሻ አካላት አስተዋውቋል። ዶባ ኢንዱስትሪያል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ 2000 .. ጀምሮ ቢሻን ጋሪ የውኃ ማጣሪያን ለገበያ ሲያቀርብ የቆየው የቢሻን ጋሪ ፒዩሪፊኬሽን ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እህት ኩባንያ ነው። አቶ ቢያዝን ላቀ የዶባ ኢንዱስትሪያል ትሬዲንግና የዶባ ቢሻን እንክብል ብቸኛ የሽያጭ ወኪል የሆነው የቢሻን ጋሪ ፒዩሪፊኬሽን ኢንዱስትሪ የንግድና ገበያ ልማት ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች።

ሪፖርተር፡- ከ16 ዓመታት በፊት ቢሻን ጋሪ ፒውሪፊኬሽን ኢንዱስትሪ ይዞ የቀረበው የውኃ ማከሚያ ምርት ቢሻን ጋሪ ነበር፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ዶባ ኢንዱስትሪያል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በተባለው እህት ኩባንያው ዶባ ቢሻን እንክብል ተመርቷል፡፡ ልዩነቱ ምንድነው?

አቶ ቢያዝን፡- የቢሻን ጋሪ ምርት ድፍርስ ውኃንና ተዋህሲያንን አብሮ ለማፅዳት የሚያገለግል ነው፡፡ በአብዛኛው የዚህ ምርት ጥቅም ገጠር አካባቢ ለሚኖረውና ውኃን ከወንዝ፣ ከሐይቅ፣ ከምንጭ፣ ከኩሬና ከጉድጓድ ቀድቶ ለሚጠቀመው ማኅበረሰብ  ነው፡፡ ካለፉት 15 ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንያደረገ የሚገኝ ምርት ነው፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2016/17 ከፍተኛ የኮሌራ ወረርሽኝ በነበረበት ወቅት የጤና ሚኒስቴርና ሌሎች አጋር ድርጅት ያቀርቡ ለነበረው የውኃ ማጣሪያ ጥያቄዎች፣ ቀዳሚ ሆኖ በከፍተኛ ደረጃ ምላሽ ሲሰጥ ነበር፡፡ አሁንም ድረስ ትልቅ ኃላፊነት እየተወጣ ያለ ኢንዱስትሪ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መሠረተ ልማት ተዘርግቶ በቧንቧ የሚሠራጭ ውኃ ከመነሻው ባይበከልም፣ በቧንቧ በመተላለፍ ሒደት በሚኖሩ እክሎች ብክለት ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ዶባ ቢሻን የሚኖረውን ግልጋሎት ቢጠቅሱልን?

አቶ ቢያዝን፡- ይህ ነው ሁለተኛ ምርት የሆነውን ዶባ ቢሻን እንክብል እንድናስብና እንድናመርት ያደረገን፡፡ ቢሻን ጋሪ ድፍርስ ውሃ የሚያጣራና ተዋህሲያንን የሚያክም ነው፡፡ ይህ ተመራጨና ተስማሚ የሚሆነው ከቧንቧ ውጭ ለሚገኙ ውኃዎች ነው፡፡ የዚህ አብዛኛው ደንበኞቻችን የመንግሥት አካላትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ናቸው፡፡ በቢሻን ጋሪ ውስጥ ድፍርስ ለማጥራት በተጨመረው ኬሚካል ምክንያት ለቧንቧ ውኃ አይውልም፡፡ በመሆኑም ደንበኞቻችን የተለየ ምርት እንድናቀርብ በጠየቁን መሠረት ለቧንቧና በአይን ሲታይ የተበከለ ለማይመስል ውኃ ተስማሚ የሆነውን ዶባ ቢሻን እንክብል አምርተናል፡፡ በዚህ መሠረት ከሦስት ዓመታት በፊት ጀምሮ የዶባ ቢሻን እንክብል የውኃ ማከሚያ ለማምረት ጥናት፣ ምርምርና ሙከራ ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ውኃ በቧንቧ ቢመጣም ከመነሻው እስከ ተጠቃሚው እስኪደርስ ብዙ ችግር ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ከመነሻው በደንብ በክሎሪን ታክሞ ነው የሚመጣው፡፡ ነገር ግን መንገድ ላይ የመበከል አጋጣሚ ሊኖር ይችላል፡፡ በተለይ ብረት መስመር ሆኖ 20 እና 40 ዓመታት የሞላቸው ውስጣቸው ዝገት የመፍጠር ሁኔታ አለ፡፡ ይህ ባክቴሪያ ለመፍጠር አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ አንዳንድ ጊዜም በቁፋሮና በተለያየ ምክንያት የቧንቧ መስመሮች ሊሰነጠቁ፣ ሊሰበሩና ከውጭ ሊበከሉ ይችላሉ፡፡ ለዚህ ቢሻን ጋሪ ተመራጭ አይደለም፣ አይመከርም፡፡ ምክንያቱም ቢሻን ጋሪ በቧንቧ ለሚመጣ ውኃ ጥቅም ላይ ሲውል ክሎሪን ከመጠን በላይ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ለዚህ ይዘን የመጣነው መፍትሔ በተለይ ቧንቧ ነክ ለሆነና በዓይን ሲታይ ንፁህ ለሚመስለው ውኃ ዶባ ቢሻን እንክብል ነው፡፡ ይህ ውኃን በተመለከተ ለሚገጥሙ ብክለቶች ምሉዕ መፍትሔ ይዘን የመጣንበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በውኃ ዙሪያ የተጠኑ ጥናቶች ምን ያሳያሉ?

አቶ ቢያዝን፡-  ለገጠሩ ማኅበረሰባችን የንፁህ ውኃ ተደራሽነት በተለያዩ አካላት ጥናት ተሠርቷል፡፡ በእኛ በኩል ዝርዝር ጥናት ባናደርግም፣ የብዙዎቻችን መነሻ ገጠር ነውና ያለውን ሁኔታ እናያለን፣ እናውቃለን፡፡ ችግሮች እንዳሉም ይታወቃል፡፡ ለዚህ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት የንፁህ ውኃ ተደራሽነት እንዲኖር ይሠራል፡፡ ነገር ግን ተደራሽነትና ጥራት ሁሌ አብሮ ይሄዳል ማለት አይደለም፡፡ ይህንን ክፍተት ደግሞ መንግሥት ብቻውን ስለማይወጣው፣ ክፍተቱ የሚሞላው በባለሙያና በባለሀብቱ ነው፡፡ በገጠር ክፍተት አለ፡፡ ከተማም ላይ ውኃ በተራ የሚመጣላቸው አሉ፡፡ ውኃ በጀሪካንና በተለያዩ ዕቃዎች ከሌላ ቦታ ሲመጣ ሊበከል ይችላል፡፡ በየቤቱ ከመጣ በኋላም ከአቀማመጥና አጠቃቀም ንፅህና ጉድለት የሚመጡ ችግሮች አሉ፡፡ የአሜሪካ ልማት ተራድኦ ድርጅት በታኅሣሥ 20 ቀን 2022 ይፋ ባደረገው ጥናት፣ በኢትዮጵያ የውኃ ሽፋን 57 ከመቶ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህ መልካም መሻሻል ቢሆንም፣ በአገሪቱ የሚከሰተው ድንገተኛ ዝናብ እንዲሁም የመሠረተ ልማት መጓደል ውኃ በባክቴሪያ እንዲበከል ያደርጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ዶባ ቢሻን እንክብል አጠቃቀሙ እንዴት ነው?

አቶ ቢያዝን፡-  ቢሻን ጋሪ ኅብረተሰቡ ቀጥታ ከመሬት የሚያገኘውን ውኃ የሚያክምበት የቤት ውስጥ ውኃ ማከሚያ ነው፡፡ በባህሪው ለማኅበረሰብ ወይም እንደየአቅማቸው ውኃ አልምተው ለኅብረተሰቡ ከሚያድሉ ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ በዶባ ቢሻን እንክብል ሃያ ሺሕ ሊትር ውኃ በሚይዝ ታንከር አክሜ አቀርባለሁ የሚል ካለ ለመጠቀም ይቻላል፡፡ አሥር እንክብል ከሚይዘው እሽግ አንዷ እንክብል ሃያ ሊትር ውኃ ታክማለች፡፡ የውኃው መጠን እስከታወቀ ድረስ ማከም ይቻላል፡፡ የዝናብ ውኃ ለሚጠቀሙ ዝናቡ በቀጥታ ከላይ እሚመጣ ከሆነ ማከም አያስፈልግም፡፡ ነገር ግን በጣራና በአሸንዳ የወረደ ከሆነ ለብክለት ስለሚጋለጥ ማከም ያስፈልጋል፡፡ የቀለም ችግር ከሌለበት በዶባ ቢሻን እንክብል አክሞ ማጥለል ይገባል፡፡ ሲያዩት የደፈረሰ ከሆነ በቢሻን ጋሪ መታከም አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በአገር ውስጥ በመመረቱ ምን ያህል ከውጭ የሚገባን የውኃ ማከሚያ ተክተናል ብላችሁ ታስባላችሁ?

አቶ ቢያዝን፡- ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ዳሰሳ አድርገን ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በዱቄትና በእንክብል መልክ የውኃ ማከሚያ የምናመርት እኛ ብቻ ነን፡፡ ክፍተቱ የሚሸፈነው ከውጭ በሚመጣ ምርት ነው፡፡ ምን ያህል ያሟላል? የሚለው ጥናት ቢፈልግም፣ እኛ በነበረን ዳሰሳ ቢሻን ጋሪ አጠቃላይ ለኢትዮጵያ እየቀረበ ከነበረው 17 በመቶ ያህሉን እያቀረበ መሆኑን ዓይተናል፡፡ ሌላው ከውጭ የሚመጣ ነው፡፡ ቢሻን ጋሪ የውጭ ምንዛሪንና ሌሎች ችግሮችን አልፎ እዚህ ደርሷል፡፡ በዚህም የውጭ ምንዛሪን አገር ውስጥ በማስቀረትም ሆነ በኢኮኖሚው ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ አሁን ያመረትነው ከውጭ ከሚመጣው ጋር ተወዳዳሪ ሆኖ ይቀርባል፡፡ በርካታ የተለዩ ጥቅሞችን ይዟል፡፡ በአገር ውስጥ መመረቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍና የገቢ ምርቶችን ለመተካት የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ሙሉ ለሙሉ ሽፋኑን ለማሟላት ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ ቢያዝን፡- ኢንዱስትሪው ካለው ጠቅላላ አቅሙ እየሠራ ያለው በ15 በመቶ ያህሉ ብቻ ነው፡፡ ቢሻን ጋሪ በቀን ከ450 ሺሕ እስከ 480 ሺሕ ለሃያ ሊትር ውኃ የሚሆኑ ማከሚያዎችን የማምረት አቅም አለው፡፡ ነገር ግን በቀን እያመረትን ያለነው ከ20 ሺሕ እስከ 40 ሺሕ ነው፡፡ ይህም ጥሬ ዕቃው ካለ ነው፡፡ በሰዓት ወደ 40 ሺሕ እንክብል ማምረት እንችላለን፡፡ ሁሉንም ምርቶች ባለን ሙሉ አቅም ብናመርት፣ ከአገር አልፈን ለጎረቤት አገሮች መድረስ እንችላለን፡፡ ውጭ ለመላክም አቅሙ አለን፡፡ አቅማችን ከአገራችን ፍላጎት በላይ ነው፡፡ የምንሠራው ግን ከአቅማችን በታች ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህን እንዳታሳኩ እክል የሆነባችሁ ምንድነው?

አቶ ቢያዝን፡-  ከሌላው ኢንዱስትሪ የተለየ ችግር የለብንም፡፡ በአብዛኛው ከውጭ ምንዛሪ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ በተለይ ኮቪድ ከመጣ በኋላ ችግር ነው፡፡ ሌሎች ድርጅቶች ሥራ ሲያቆሙ፣ ቢሻንጋሪ መቆየት የቻለው ጠንካራ ስለሆነ ነው፡፡ ባለው ችግር ምክንያት ከዓመቱ 365 ቀናት 15 በመቶ ቀናት ብናመርት ነው፡፡ ይህ የሆነው በውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡ የምናመርተው መድኃኒት ቢሆንም፣ ችግራችን ለጤና ሚኒስቴርና ለብሔራዊ ባንክ ቢቀርብም፣ የውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ እያገኘን አይደለም፡፡ ዋናው ችግር ይህ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለዚህ ምን መፍትሔ አበጃችሁ?

አቶ ቢያዝን፡- ወደ ውጭ ልከን ችግራችንን ለመቅረፍ እያሰብንበት ነው፡፡ የቢሻን ጋሪ 50 ከመቶ ግብዓቱ ከውጭ የሚገባ ነው፡፡ ለዚህ የውጭ ምንዛሪ ያስፈልገናል፡፡ የእኛ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት በዓመት 300 ሺሕ ዶላር ባይሞላም፣ ማግኘት አይቻልም፡፡ ለዚህ መፍትሔ ብለን ያሰብነው የአገር ውስጥ ምርቶችን ለመጠቀም የመንግሥት አቅጣጫም ስላለ የውጭ የዕርዳታ ኤጀንሲዎች በውጭ ምንዛሪ እንዲገዙን ነው፡፡ ወደ ጎረቤት አገሮች ለመላክና የውጭ ምንዛሪ ለማግኘትም አስበናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ከዕውቀት እስከ ሕይወት ክህሎት

ዋርካ አካዴሚ ከትምህርት አመራርና ፔዳጎጂ፣ ከሳይኮሎጂ፣ ከዓለም አቀፍ ኪነ ጥበብ፣ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ከባንኪንግና ዓለም አቀፍ ፋይናንስ አመራር ሙያዎች በተውጣጡ ባለሙያዎች የተቋቋመ የትምህርት ተቋም ነው፡፡...

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...