Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የማይለመድ የለም!

ጉዞ ከጀሞ ወደ አራት ኪሎ። ተጉዘን የማንጨርሰው፣ አቋርጠን የማንቀጥለው ጎዳና በየአቅጣጫው ብዙ ነው፣ ሆኖም እንጓዛለን። በዚህች ጣጣዋ በበረከተና ከሚያስደስተው የሚያስቆዝመው ነገሯ በተንሰራፋባት ምድር አልንቀሳቀስም ማለት፣ ራስን የማጥፋት ፍርድ በራስ ላይ የመወሰን ያህል ነው። ቢጥምም ባይጥምም፣ ቢዋጥም ባይዋጥም ሁን ተብለን ተፈጥረናልና የመዳከርን ቀንበር ተሸክመን ወዲያ ወዲህ እንላለን። በእልፍ ጥያቄዎች ተከበን፣ በእልፍ እንቆቅልሾች ተወዛግበን ከዘመን ዘመን በትውልድ ቅብብሎሽ የምንኖር የሥውር ኃይል ትብታቦች ነን። የሕይወታችንን ሚስጥር ለመገንዘብ የመንገዳችንን አባጣ ጎርባጣነት ብቻ ማጤን ይበቃል። ከዚያ እስከዚህ ድረስ አጭደን ከከመርነው በተስፋ የጠበቅነው የጥጋብ ቀን ጥቂት አይደለም። ሥሌቱም የዘመን ቀመር ነው። አሻራውም እያንዳንዱ ጎዳና ላይ በትውስታ ደምቆ በመከራና በጭንቀት ደልቦ ይኖራል። መንገድ መጀመሪያም ማብቂያም የሌለው የሰው ልጅ ሕይወት መረማመጃ ነው። ይኼንን የሕይወትን ውጣ ውረድ የተገነዘበ ብቻ ነው የሚያውቀው። ከታዋቂነት በፊት አዋቂነት ይቅደም!

ከዚህ ውጪ መሆን አንችልም ነበር? ከዚህ ውጭ ዓለም መዘጋጀት አትችልም ነበር? ለምን ይኼኛው መንገድ ተመረጠ? ለምንስ አማራጭ ምንም የመሆን ዕድል ለሰው ልጅ ሳይተውለት ቀረ? አዕምሮ ተራ እያስጠበቀ የሚያብላላቸው ቋጥኝ ጥያቄዎች ናቸው። ጎዳናው የሙግቶች መናኸሪያ ሲሆን፣ መንገደኛው ደግሞ የመናኸሪያው አስተናባሪና ታዳሚ ነው። ሕይወት በምትባለዋ እንቆቅልሸ ውስጥ ከመወለድ እስከ ጉልምስና የተጓዘ ቢያንስ ለአንዷ ጥያቄ፣ በእንቅልፍ ፍጀው የተባለውን የዕድሜ ሩብ ሲብሰለሰል ገብሮ ጨርሶታል። ያልገበርነውስ ምን አለ? በስንት ጥበቃ የተገኘው ዶልፊን ታክሲ አዛውንት ሾፌር፣ ‹‹ጫናቸው እንጂ ምን ዓይን ዓይናቸውን ታያለህ?›› ሲሉት ደንባራው ወያላ በሩን እየከፈተ ያስገባናል። በዕድሜ ገፋ ያሉት ሾፌራችን በወያላው ዳተኝነት ይነጫነጫሉ። ‹‹እንዲያው ምን ይሻለኛል እናንተ የዘመኑ ሰው ተፈላልጎ ሲሠራ እያየሁ፣ ሲሿሿም እያየሁ፣ ባለሕንፃና ኢንቨስተር ሲሆን እያየሁ እኔ ለምን የማላውቀውን ወያላ እቀጥራለሁ ብዬ ከአገር ቤት የእህቴን ልጅ ባስመጣው እሱ ግን ይንገላጀጃል…›› እያሉ ከባድ ሳል አቋረጣቸው። በግነዋል!

መሀል ወንበር ከተቀመጡ ወጣቶች አንዱ፣ ‹‹እንግዲህ ምን ይደረጋል?›› ሲላቸው እየተገላመጡ፣ ‹‹ገና ሳይጠና ሐሞቱ የፈሰሰ ትውልድ…›› እያሉ አሁንም ሳሉ ሲጠናባቸው፣ ‹‹አይ ፈጣሪ እንዲያው ስትቸገር ነው እንጂ የሚያስለኝ የኑሮዬ ውጣ ውረድ እኮ ይበቃኝ ነበር። መቼም እሱ መቸገር ይወዳል…›› ይላሉ መልሰው እየቀለዱ። ዞር ብለው እያዩ ተሳፋሪዎችን ቦታ እየቀያየሩ፣ ‹‹ግድ የለም አንቺ ቀጠን ያልሽዋ እናታችንን ቦታ ቀይሪያቸው፡፡ ይህንን ደግሞ እዩትማ ሰው እስከዚህ ድረስ ይደነዝዛል?›› ሲሉ ወያላውን ጋቢና ከተቀመጡ ወጣቶች አንዱ፣ ‹‹ፋዘር ይተውት አንዳንዴ ዓይቶ እንዳላየ ማለፍ ነው የሚሻለው። ቀስ እያለ ይለምዳል…›› ሲላቸው፣ ‹‹ስንቱን ነው ዓይተን እንዳላየን የምናልፈው? ቅርባችን ሆነው የራቁንን ሲነግሯቸው የማይሰሙትን፣ ዓይነትን እንዳላየን እናልፋለን። እባካችሁ ከሕይወት ልምዳችን የቀሰምነውን እናካፍላችሁ ስንል ደግሞ አርፋችሁ ተቀመጡ እንባላለን፡፡ ስንቱን ነው ታግሰን የምንኖረው?›› በማለት ደበስበስ አድርገው የሚናገሩት በፖለቲካ የተፈረሸ ነገር ነው፡፡ ሊጀመር ነው!

ጉዟችን ተጀምሯል። ‹‹ሲጮሁ ካልጮሁ፣ ሲንጫጩ ካልተንጫጩ የትኛውም ትውልድ ዕጣ ፈንታ መረገጥ ይመስላል…›› ሲል አንዱ ከአጠገባቸው፣ ‹‹ለመሠልጠን ከተፈለገ መተራረም ጥሩ ነገር ነው፡፡ የሰው ልጅ ከጥንታዊ የጋርዮሽ ዘመን የዱር ፍሬ ለቃሚነትና አዳኝነት ወጥቶ በሥልጣኔ እዚህ የደረሰው፣ አንዱ ከሌላው ጋር በሐሳብ እየተፋጨና በተግባር እየተፈታተሸ ነው…›› ብለው ሾፌራችን ዘለግ ያለ ማብራሪያ ለወያላው ይሰጣሉ። ከተማ ብርቅ እንደሆነበት የሚያስታውቀው ወያላችን በከፊል ማብራሪያውን እያዳመጠ፣ ዓይኖቹን ደጅ ለደጅ ያንከራትታል። ‹‹ምናለበት እርስዎስ ዲስኩርዎን አቁመው መንገዱን እያዩ ቢነዱ?›› ከጀርባቸው የተቀመጠ ተሳፋሪ አንባረቀባቸው። ‹‹ተገኘ ብሎ በልቶ ቁንጣን ስለተያዘ ነው አይፍረዱበት…›› ከጎኑ የተቀመጠች ተሳፋሪ ይቅርታ ትጠይቃለች፣ ቤተሰብ ትመስላለች። ከመሀል መቀመጫ፣ ‹‹እኔ እኮ ስንቱ አግበስባሽ ጉቦኛ ተገኘ ብሎ የሰበሰበውን ሳይተፋ፣ ጉሮሮውን ሳያንቀው፣ በፆም ውስጥ በተጎረሰች መናኛ በየዓይነቱ ሳቢያ ፋርማሲ ለፋርማሲ እንሯሯጣለን…›› አንዲት ሴት ተናገረች። ‹‹ታዲያ የለመደና ያለመደ ሆድ አንድ ነው እንዴ? ሲጮህ የኖረ ሆድ አንዴ ቢጠግብ ላይታመም ነው? ምን ትላለች?›› ይላል፡፡ የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል መሰል!

በመስኮቱ በኩል የተሰየመ ጎልማሳ፣ ‹‹ታዲያስ ለለመደው ደግሞ መርዝ አይገድለውም። መመዝበርና መዝረፍን የተላመዱት ሳይሆኑ የሚገርሙት፣ እኛም እንደ ጀግና ቆጥረን ከወገባችን ዝቅ እያልን ባርኔጣችንን ከፍ የምናደርገው ነገር ነው። ከዚህ በላይ ታዲያ መርዝ ይለመዳል?›› ትለዋለች አጠገቡ የተቀመጠች ወይዘሮ። መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት አንዱ ምሁር ቢጤ ደግሞ፣ ‹‹በመዘራረፍ ከሆነስ የመጀመሪያው ደረጃ ካፒታል አሰባሰብ የሚጠናቀቀው የት እንደሆነ ማን ያውቃል?›› ሲል ነገር ይመዛል። ‹‹አይ ጉድ አለ የአገሬ ሰው ነገር ሲመዘምዘው። አሁን እስኪ የሁዳዴ ፆም ገና ከመጋመሱ በነገር የምንወጋጋው ምን ብንበድል ነው?›› ብላ ከጎኑ ስታጉተመትም እንሰማለን። ‹‹ይሁዳችን በዝቶ ነዋ ልጄ፣ ስናምነው የሚከዳን ስንደገፈው የሚጥለን በዝቶ። ከዚህ በላይ በደል አለ?›› የለበሱትን ባህላዊ ቀሚስ እየደጋገሙ ወደ ታች እየጎተቱ አንዲት አዛውንት እናት ጨዋታውን ተቀላቀሉ። ድምፃቸው ያልተሰማ ጥቂት ተሳፋሪዎች የግራ ቀኙን ጭውውት እያዳመጡ ይመሰጣሉ። አንዳንዴ ከመናገር በማዳመጥ ብዙ የሚወጣልን ይመስላል!

ደንባራው ወያላችን ሒሳብ መሰብሰብ ጀምሯል። ጎልማሳው አዲስ ሐሳብ ይዞ ወጉን ሲያደራ፣ ‹‹ነፍሳችንን የሚምረው ፈጣሪያችን ነው፡፡ ለጊዜው የተቸገርነው በቁም የሚቀብረንን የሚያስጥለን ነው…›› ይላል። አንዳንዶች ፈገግ ሲሉ ሌሎች ግራ ይጋባሉ። ‹‹ታዲያ ባስነጠስን ቁጥር ግብር ይቀነስልን ልንል ነው? እሱ ነበር የቀረን። እንዴት ነው ነገሩ ዘመኑ እኮ የልማት ነው…›› የምትለው ጥግ ላይ የተቀመጠች ተሳፋሪ ነች። ‹‹እስኪ አሁን የኮሪደር ልማቱን ከግብር ቅነሳ ጋር ምን አዛመደው?›› ብሎ አንዱ ነገር ሲጀምር ዝም ተባለ፡፡ ከወደ ጋቢና ወጣቶቹ ምንጭ ሳይጠቅሱ የሰሟትን ቀልድ ይጫወታሉ። ‹‹አንዱ ፊልድ ሰንብቶ ለፋሲካ ቤቱ ይመለሳል…›› ይላል አንደኛው። ‹እሺ?›› እያለ ሁለተኛው ያደምጣል። ‹‹እናም እጮኛው ንፍቅ ብላዋለች፣ ይደውልና ‘ውዴ ሆይ ይኼው ተመልሻለሁ’ ሲላት፣ ‘መልካም እንኳን ለቤትህ አበቃህ’ ትለዋለች። ‘አንገናኝም?’ ብሎ ይጠይቃታል። ‘እንገናኛለን እንጂ’፡፡ ‘እኮ መቼ?’ በጉጉት ተንጧል። ‘ሰሞኑን’ ትለዋለች። ‘ለምን ነገ አንገናኝም?’ ሲላት ‘ነገማ የልማት ስብሰባ’ አለ ትለዋለች። ‘እሺ ለምን ተነገ ወዲያ አንገናኝም?’ ብሎ ሌላ ጥያቄ ሲያቀርብ ‘የኮሪደር ልማት ጉብኘት አለብኝ’ አለችው፡፡ ‘በቃ እሺ ከዚያ ወዲያ’ አላት መጨረሻ ላይ። ‘የዚያን ቀን ደግሞ ግምገማ አለ’ ብትለው፣ ‘እንዴ ምነው ይኼን ያህል አገር የምትመሪው አንቺ ነሽ እንዴ?’ ብሏት አረፈው እልሃለሁ…›› ብሎት እነሱ ሲስቁ ቀልዱ የለዘዘባቸው ደግሞ ፀጥ ብለው ነበር። ድንቄም አትሉም ታዲያ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ጎልማሳው ቀልድ ተብዬውና የወጣቶቹ ሳቅ እያበሳጨው፣ ‹‹የመሠረታዊ አቅርቦቶች ዕጦት ከመራር ድህነት ጋር ግብግብ አጋጥሞን ከቴም ቀልድ እናንተ…›› ሲል በንዴት ይንተከተካል። ‹‹በትንሽ ትልቁ መንተክተክ እንዲያው እኮ…›› የሚሉት እኚያ እናት ናቸው፡፡ ለማጁ ወያላችን በጣም ዘግይቶ መልሳችንን ለመስጠት ብር ሲቆጥር ከእጆቹ እያመለጠ እሱን ለቀማ ፍዳችንን እናያለን። ‹‹ምን የዘንድሮ ገንዘብ እንኳን ተበትኖ መሬት ነክቶ ይቅርና ኪስ ውስጥ ተደላድሎ ተቀምጦ መቼ ዋጋ አለው?›› አዛውንቷ በምሬት ከእግራቸው ሥር ባለአምስትና አሥር ብር እየለቀሙ ይናገራሉ። ‹‹ኧረ የገንዘቡስ አንድ ነገር ነው። ሰውም እኮ ነው ዋጋ እያጣ የተቸገርነው…›› ባዩ ደግሞ ጎልማሳው ነው። መጨረሻ ወንበር ጥጉን ይዞ የተቀመጠው ምሁር መሳይ ደግሞ፣ ‹‹እኔን ደግሞ የሚገርመኝ ስለራሱ በቅጡ የማያውቅና ዋጋውንም ያልተረዳ እየተነሳ፣ በአገራችንና በብራችን ዋጋ ማጣት የሚሰጠው አጉል ፍርድ ነው…›› ይላል። ‹‹ዋጋችንን ለማወቅና በቅጡ ለመኖር ከዘመኑ ጋር በቅጡ መላመድ ያስፈጋል…›› ስትል ወይዘሮዋ ወያላው ‹‹መጨረሻ…›› ብሎ በሩን ከፈተው። ተራ በተራ ስንወርድ አዛውንቷ ወደ ወይዘሮዋ ጠጋ ብለው፣ ‹‹ግን ይህንን አስቸጋሪ ዘመን እንዴት እንልመድ?›› ብለው ሲጠይቁ፣ ‹‹የማይለመድ የለም…›› ብላቸው ተለያየን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት