Tuesday, May 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የተባበሩት ብሔራዊ ፔትሮሊየም ካፒታሉን በማሳደግ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ነዳጅ ለማቅረብ ማቀዱን ገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የነዳጅ ማደያ ለመክፈት 450 ሚሊዮን ብር ያስፈልገዋል ተብሏል

የሃያ ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠረው የተባበሩት ብሔራዊ ፔትሮሊየም አክሲዮን ማኅበር ካፒታሉን በማሳደግ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ነዳጅ ለማቅረብ ማቀዱን አስታወቀ፡፡

የማኅበሩ የባለአክሲዮኖች 11ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ሚያዝያ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በኢሊሌ ሆቴል ሲካሄድ፣ ላለፉት 20 ዓመታት ያካበተውን ሀብት ወደ ኢንቨስትመንት ለመቀየር በማቀድ፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ የነዳጅ ሽያጭ ለመጀመር መታሰቡን፣ የኩባንያው ቦርድ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ይስማሸዋ ሥዩም ተናግረዋል፡፡

ማኅበሩ በ2015 ዓ.ም. ያከናወናቸውንና በ2016 ዓ.ም. ታቅዶ በስምንት ወራት ውስጥ ማሳካት የተቻለውን የአፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርቡ፣ የማኅበሩን የመነሻ ካፒታል ከነበረበት 400 ሚሊዮን ብር ወደ 600 ሚሊዮን ብር በማሳደግ በካፒታሉ የማኅበሩን የዕድገት ስትራቴጂ በመከተል የተለያዩ የማስፋፊያ ሥራዎችን ለማከናወን መታሰቡን ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡

ከማስፋፊያው አንዱ ወደ ሆነው የአቬዬሽን ዘርፍ መቀላቀል ያስፈለገበት ምክንያት በአገሪቱ ያሉት አራቱ ትልልቅ ኩባንያዎች እንደ ቶታል ኢነርጂ፣ ኖክና የተባበሩት ነዳጅ አቅራቢዎች በጠቅላላ 70 በመቶ የገበያ ድርሻ (Market Share) ያላቸው ቢሆንም፣ የተባበሩት ከዚህ ውስጥ መያዝ የቻለው ስምንት ብቻ በመሆኑ ነው ሲሉ አቶ ይስማሸዋ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 75 በመቶ የሚሆነውን ነዳጅ ከአገር ውስጥ የሚጠቀም በመሆኑ በፍላጎትና አቅርበት መሀል ያለውን ችግር በመመልከት፣ እንዲሁም ከ122 በላይ የውጭና ከ20 በላይ የአገር ውስጥ መዳረሻ፣ በተጨማሪም በየጊዜው ዕድገት ያለው ተቋም ስለሆነ የነዳጅ ሽያጭ በአየር መንገዱ ለመጀመር ማሰባቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢንቨስትመንት ወጪ ለመቀነስ በአየር መንገድ ውስጥ በሥራ ላይ ካሉ የነዳጅ ማደያዎች ጋር በሽርክና ለመሥራት ካልሆነ ደግሞ በራስ አቅም ለመገንባት 450 ሚሊዮን ብር ካፒታል እንደሚያስፈልግ፣ ቦርዱ በጥናት የለያቸው አማራጮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በተያያዘ ኩባንያው ኅዳር 14 ቀን 2010 ዓ.ም. ባደረገው 6ኛው የባለአክሲዮኖች ጉባዔ የኩባንያው ካፒታል 400 ሚሊዮን እንዲያድግ መወሰኑን አስታውሰዋል፡፡ አክሲዮኖቹ በሙሉ ተሸጠው ገንዘቡ ሙሉ በሙሉ ተከፍሎ ከተጠናቀቀ በኋላ የኩባንያው የሥራ እንቅስቃሴ እያደገና እየሰፋ በመምጣቱ፣ ቦርዱ ባደረገው ውይይት እያንዳንዳቸው አምስት ሺሕ ብር ዋጋ ያላቸው 40 ሺሕ አክሲዮኖች በማውጣት የኩባንያውን ካፒታል ከ400 ሚሊዮን ብር ወደ 600 ሚሊዮን ብር እንዲያድግ፣ የካፒታል ዕድገቱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ እንዲጠናቀቅ ጉባዔውን ሲመሩ የነበሩት የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበርና የጉባዔው ሰብሳቢ አቶ ኃይለ ልዑል ኦላና ተናግረዋል፡፡

የኩባንያው የሀብት ግመታ የተሠራ መሆኑን፣ አጠቃላይ ሀብቱ 1.18 ቢሊዮን ብር በማደረስ ከተጠቀሰው ሀብት ውስጥ 500 ሚሊዮን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና 300 ሚሊዮን ከአዋሽ ባንክ፣ በአጠቃላይ 800 ሚሊዮን ብር የሚገመተውን የሀብታቸውን መጠን የተበደሩት በመሆኑ ቀሪው ሀብት ለችግር ጊዜ ለዋስትና የተቀመጠ መሆኑን ገልጸዋል።

የተባበሩት ብሔራዊ ፔትሮሊየም በ2016 ዓ.ም. የስምንት ወራት አፈጻጸም መሠረት ቤንዚን በዕቅድ ከተያዘው 95 በመቶ ማሠራጨት መቻሉን ገልጸዋል።

የላምባ (ኬሮሲን) አፈጻጸም 55 በመቶ ሲሆን ለቤት ውስጥ አገልግሎት የሚውልና የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅ ያሉ ማኅበረሰቦች የሚጠቀሙት ስለሆነ የተጠቃሚ ችግር በመኖሩ ዝቅተኛ አፈጻጸም ማሳየቱ ተገልጿል።

ነጭ ናፍጣ ከዕቅዱ 74 በመቶ የተሠራጨ ሲሆን፣ አፈጻጸሙም ዝቅ ያለበት ምክንያት በሰሜንና በምዕራብ በኩል ያለው የፀጥታ ችግር ነው ተብሏል።

በተጨማሪም ጥቁር ናፍጣ 102 በመቶና ዘይት 45 በመቶ የተሠራጨ ቢሆንም፣ የዘይት አፈጻጸም ዝቅ ያለበት ምክንያት የውጭ ምንዛሪ እጥረት መሆኑን አቶ ኃይለ ልዑል አብራርተዋል።

ኩባንያው በ2016 በጀት ዓመት ለማትረፍ ያቀደውን 130 ሚሊዮን ብር በስኬት በማጠናቀቁ፣ በ2017 በጀት ዓመት 207 ሚሊዮን ብር ትርፍ ለማድረስ መታቀዱ ተገልጿል።

በስብሰባው ላይ የተገኙ የኩባንያው ባለአክሲዮኖች በበኩላቸው በዳይሬክተሮች ቦርድ በቀረበ ሐሳብ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ያቀረቡ ሲሆን፣ በጥያቄያቸውም የአቬዬሽን ዘርፍን ለመቀላቀል አሁን በሥራ ላይ ካሉት ጋር በሽርክና መጋራት ሕጋዊ እንዳልሆነ እነሱም የማጋራት ዕድላቸው የጠበበ እንደሆነና ያሉትን ማደያዎች በጥንቃቄ አጠናክሮ በመሥራት ኢንቨስት ማድረግ ቢቻል፣ የኩባንያው 12 ማደያዎች አሁን ያሉበት ይዞታ ታይቶ እነሱን የማጠናከር ሥራ ቢሠራ፣ ሱሉልታ የሚገኘው የነዳጅ ማደያ ይዞታ በሌሎች ድርጅቶች የተካሄደበት ወረራ ላይ የተወሰደ ዕርምጃ ምን እንደሆነ፣ የኃይል አቅርቦት ላይ ቢሠራ፣ ካፒታል ገበያ ለመግባት ቢታሰብ፣ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የሚደረጉ ጥረቶች ቢገለጹ፣ እንዲሁም የኩባንያው የማርኬቲንግ ባለሙያዎች የነዳጅ ማደያዎቹን በመዘዋወር እየተመለከቱ ጥገና የሚያስፈልጋቸውን በመለየት ሥራዎች ቢሠሩ የሚሉ ተነስተዋል።

ከባለአክሲዮኖች ለተነሱ ጥያቄዎች የቦርዱ የማኔጅመንት አባላት ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ የውጭ ምንዛሪ ከአንድ ባንክ ብቻ እንደሚወስዱ ከዚያ ውጪ ለማግኘት ከባድ እንደሆነ፣ ባላቸው ንብረት ልክ እንደተበደሩ መሆናቸውን፣ ካፒታል ገበያ ለመግባት ከባለሙያዎች ጋር በመመካከር የመግባት ዕቅድ እንደተያዘ፣ ኩባንያው በአቪዬሽን ዘርፍ ለመሳተፍ ዕድል እንዳለው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ፣ በማደያዎች የፓምፖች እጥረት እንዳለና ለማደስ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳለባቸው፣ ሱሉልታ የሚገኘው 20 ሺሕ ካሬ ሜትር ይዞታ በወረራ እንደተያዘና በክስ ሒደት ላይ እንደሚገኙ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች