Tuesday, May 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በባንክ ብድር አቅርቦት ላይ የተጋረጠው ሙስና ለንግድ ማኅበረሰቡ ፈተና መሆኑ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱ ሁሉም ባንኮች ብድር ለማቅረብ የሚያስችሉ መሥፈርቶች ቢኖሯቸውም፣ ብድር የሚፈቅዱ አካላት የሚፈጽሙት ሙስና የንግድ ማኅበረሰብን ፈተና ውስጥ መክተቱ ተገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ‹‹የብድር አቅርቦት በቢዝነስ ላይ ያለው ተፅዕኖ›› በሚል ርዕስ ሐሙስ ሚያዚያ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ባዘጋጀው የውይይት መድረክ የተገኙ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፣ ብድር ለማግኘት የሚጠየቁት ጉቦ እንዳስመረራቸው ተናግረዋል፡፡ 

የብድር አቅርቦቱን በሚፈለገው መጠን ተደራሽ ለማድረግ ሁሉም ባንኮች በሚባል ደረጃ የገንዘብ እጥረት እንዳለባቸው በውይይቱ ላይ የተነሳ ሲሆን፣ ያለውን የብድር አቅርቦትም ቢሆን መሥፈርቱን ላሟላ ትክክለኛ ተበዳሪ ተደራሽ ከማድረግ ይልቅ በሙስና መፈቀዱ ችግሩን የከፋ አድርጎታል ብለዋል፡፡

ጉርሻ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ አክሲዮን ማኅበርን በመወከል በውይይት መድረኩ የተገኙት አቶ ሁንልኝ ጥጋቡ በአሁኑ ጊዜ የባንክ ብድር በሙስና እንደሚሰጥ ሁሉም የሚያውቀው ነው ብለው፣ ‹‹ብድር የሚፈቀደው በሙስና ነው፣ ሙስናው ደግሞ ከፖለቲካ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ችግሩን ዘርዝሮ መግለጽ ይቻላል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ችግሩን መቅረፍ ካስፈለገ ስለጉዳዩ በግልጽ መነጋገር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ አቶ ሁንልኝ እንደሚሉት፣ ባንኮች ውስጥ በሚፈጸሙ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች ምክንያት ብድር ማግኘት አልተቻለም፡፡

‹‹ችግሩን ሁሉም ሰው የሚያውቀውና በየኮሪደሩ የሚሰማ ነው፤›› ያሉት የአፍሪካ የፋይናንስ ግልጽነትና ተጠያቂነት ፕሮግራም ኃላፊ አቶ ጌታቸው ተክለ ማርያም ናቸው፡፡ የባንክ ብድርን ጥቂት ግለሰቦች መቆጣጠራቸውን፣ ባንኮች ውስጥ ብድር እንዲፈቀድ የሚወስኑ ግለሰቦች የአዋጭነት ጥናት በእጅ አዙር እንደሚሠሩና በብድር አሰጣጥ ሒደት ውስጥ ያሉ ሁሉም ሰዎች ምርመራ ሊደረግባቸው ይገባል ብለዋል፡፡ ‹‹የሚከፈላቸውን ገንዘብና ኑሮዋቸውን መመልከት ብቻ በቂ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የሙስና ድርጊት በብድር አሰጣጥ ላይ እየተንሰራፋ ቢመጣም የብድር አሰጣጥ ሒደቱ መጓተት፣ የገንዘብ እጥረትና ተደራሽ አለመሆን ችግር የራሳቸው አስተዋፅኦ እንዳላቸው ይነገራል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተባለውን ችግር ለማጣራት እንደሚሞክርና መረጃ በተገኘባቸው ላይም ከበድ ያለ ዕርምጃ እንደሚወስድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸው፣ ብሔራዊ ባንክ ግን የደኅንነት ሥራ መሥራት አይችልም ብለዋል፡፡

በየጊዜው ቅሬታዎች ለብሔራዊ ባንክ እንደሚቀርቡና መሰል የሙስና ድርጊቶች እየተለመዱ መሆናቸውን ገልጸው፣ በመሻሻል ላይ ባለው የባንክ ሥራዎች አዋጅ ብሔራዊ ባንክ የደኅንነት ሥራዎችን መሥራት እንዲችል ለማካተት እየተሞከረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህ ዕውን ከሆነ እየተሰማ ያለው ችግር ሊፈታ እንደሚችልም አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች