Tuesday, May 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከበርካታ ባንኮች ከፍተኛ ብድር የሚወስዱ ተበዳሪዎችን የሚቆጣጠር ሕግ ሊወጣ መሆኑ ተሰማ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ሁሉም ባንኮች ካበደሩት 1.9 ትሪሊዮን ብር 23 በመቶው ለአሥር ተበዳሪዎች መሰጠቱ ታውቋል

ከበርካታ ባንኮች ብድር የሚወስዱ ተበዳሪዎችን መቆጣጠርና የብድር ክምችትን ማስተካከል የሚችል ሕግ፣ እየተሻሻለ ባለው የባንክ ሥራ አዋጅ ውስጥ ለማካተት እየተሠራ መሆኑ ተነገረ።

ጥቂት ተበዳሪዎች ከበርካታ ባንኮች ተደጋጋሚ ብድሮችን የሚወስዱ እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎች ሲገልጹ ነበር፡፡ ከባንኩ የሚወጡ ሪፖርቶችም ይህን የሚያሳዩ ሲሆን፣ ብሔራዊ ባንክ አሁን እየከለሳቸው ባሉት ሕጎች አማካይነት ይህን ድርጊት ለማስቆም እያሰበ እንደሆነ ሪፖርተር ከባንኩ ከፍተኛ ኃላፊ አረጋግጧል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የብሔራዊ ባንክን የሥራ ኃላፊ እንደገለጹት፣ ተበዳሪዎች ከሁሉም ባንኮች ጋር በአንድ ጊዜ እየሠሩ የሚያንቀሳቅሱት የንግድ ሥራ ቢበላሽ ብድር የሰጧቸውን ሁሉንም ባንኮች በአንድ ጊዜ ችግር ውስጥ ሲከቱ በተደጋጋሚ ታይቷል።

‹‹በሁሉም ባንኮች በሚባል ደረጃ ከፍተኛ ተበዳሪ የሆኑ አንድ ዓይነት ሆነው እናገኛቸዋለን፤›› ያሉት ኃላፊው፣ ይህን ዓይነት የክምችት ችግር ከመቆጣጠር አንፃርም ብሔራዊ ባንክ ያልሠራበት ዘርፍ እንደሆነ ተናግረዋል። አሁን የባንኮችን ሀብት እየተጠቀሙበት ያሉት “በጣት የሚቆጠሩ” መሆናቸውንም ገልጸዋል።

‹‹ከ18 ባንኮች እየሄደ ብድር የሚወስድ ድርጅት አለ፡፡ ይህ ድርጅት ችግር ገጠመው ማለት ሁሉም ባንኮች ናቸው የሚጎዱት፤›› ብለዋል።

ብሔራዊ ባንክ ሐሙስ ሚያዝያ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው የፋይናንስ ስታቢሊቲ ሪፖርት (Financial Stability Report) ላይ እንደተጠቀሰው፣ የባንክ ብድሮች በጥቂት ተበዳሪዎች እጅ ተከማችተው ይገኛሉ።

በአገሪቱ ያሉት ሁሉም ባንኮች እስካለፈው ዓመት ሰኔ መጨረሻ ድረስ በሥራ ላይ ካዋሉት አጠቃላይ 1.9 ትሪሊዮን ብር ብድር ውስጥ 23.5 በመቶውን ያበደሩት ለአሥር ተበዳሪዎች እንደሆነ በሪፖርቱ ተጠቅሷል። ከፍተኞቹ አሥር ተበዳሪዎች ከአጠቃላይ የባንክ ብድር መጠን ውስጥ በ2014 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ከነበረው 18.7 በመቶ ነው በ2015 ዓ.ም. መገባደጃ ላይ ወደ 23.5 ያደገ ነው ተብሏል።

የባንክ አገልግሎቶችና የፋይናንስ ዘርፉ በተወሰኑ ዘርፎች፣ አካባቢዎችና በጥቂት ተበዳሪዎች ላይ ብቻ በከፍተኛ መጠን ተከማችቶ የሚገኝ መሆኑን ጥናት በማድረግ እንደተደረሰበትና ውጤቱም ድንጋጤ መፍጠሩን፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ ባለፈው ሳምንት በአንድ መድረክ መግለጻቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው።

‹‹በኢትዮጵያ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር የአገሪቱ ፋይናንስ በተወሰነ ዘርፍ ተከማችቶ ይገኛል። ዘርፉ በተወሰነ አካባቢ መከማቸቱ በእጅጉ የሚያስገርም ነው፤›› ሲሉ አቶ ማሞ ገልጸው፣ ‹‹ለምን በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ትኩረት እንዳደረገ ስናይ አስደንግጦናል፤›› ብለው ነበር።

አሁን ባለው አሠራር ግለሰቦች የባንክ አክሲዮን ሲገዙ የአክሲዮን መጠናቸው በአንድ ባንክ ውስጥ ከአምስት በመቶ እንዳይበልጥ በሕግ የሚገደዱ ሲሆን፣ ያላቸው የአክሲዮን መጠን ከሁለት እስከ አምስት በመቶ ከሆነ ደግሞ ከፍተኛ ባለአክሲዮን ተብለው ይመደባሉ። በሥራ ላይ ያለው ሕግ አንድ ባንክ ላይ ከፍተኛ ባለአክሲዮን ተብሎ የተመደበን አካል በሌላ ባንክ ላይ አክሲዮን የመግዛት ዕድል እንዳይኖረው የሚያደርግ በመሆኑ፣ ይህም ሕግ የባንክ ባለቤትነት በጥቂት አካላት ላይ ብቻ እንዳይወድቅ የሚያደርግ ነው።

በብድር አወሳሰድ ላይም ተመሳሳይ ነገር እንዲደረግና ጥቂት አካላት የባንክ ብድርን እየወሰዱ ያለበትን አሠራር ለማስቀረት በሚወጣው ሕግ ላይ ማሻሻያው እንደሚደረግ ነው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት ኃላፊ ለሪፖርተር የገለጹት። ‹‹ልክ የአክሲዮን ድርሻ የሚተዳደርበት ዓይነት ሕግ ነው ለዚህም የሚዘጋጀው፤›› ብለዋል።

እየተስተካከለ ያለው የባንክ ሥራ አዋጅ በብሔራዊ ባንክ ተጠናቆ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት አለመላኩን፣ ነገር ግን እንደ የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዓይነት ተቋማት እያዩት አስተያየታቸውን እየሰጡበት መሆኑንም ኃላፊው ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች