Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊከባድ ተሽከርካሪዎችና ትራክተሮች አስመጪዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳያስገቡ በመከልከላቸው ቅሬታ አሰሙ

ከባድ ተሽከርካሪዎችና ትራክተሮች አስመጪዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳያስገቡ በመከልከላቸው ቅሬታ አሰሙ

ቀን:

  • ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ለሚመለከታቸው አቤቱታቸውን አቅርበዋል

ከባድ ተሽከርካሪዎችን፣ ትራክተሮችንና ማሽነሪዎችን ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡ አስመጪዎች፣ መንግሥት ምንም ዓይነት መመርያ ሳያወጣ ማስገባት አትችሉም በመባላቸው በሥራቸው ላይ እንቅፋት መፈጠሩን ተናገሩ፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ያለ ምንም በቂ ምክንያት ‹‹የመኪና ማስገቢያ ፈቃድ አልሰጣችሁም›› እንዳላቸው የተናገሩት የከባድ ተሽከርካሪ አስመጪዎች፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ለገንዘብ ሚኒስቴርና ለጉምሩክ ኮሚሽን በአካል ቅሬታቸውን ማሰማታቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት በነዳጅ የሚሠሩ አውቶሞቢሎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ መከልከሉን መስማታቸውን ያስታወሱት አስመጪዎቹ፣ አውቶሞቢሎች እንዳይገቡ የተከለከለበት ዋነኛ ምክንያት እንደ አማራጭ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ተሸከርካሪዎችን ማስገባት እንደሚቻል በማመን ነው ብለዋል፡፡

- Advertisement -

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከባድ ተሸከርካሪዎችንና ትራክተሮችን ማስገባት አትችሉም ካለ ከሳምንት በላይ እንደሆነ ገልጸው፣ ጉዳዩንም በተመለከተ ለተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ቅሬታቸውን በአካል ሲያስረዱ፣ ተቋማቱም እንዲህ ዓይነት መመርያ አለመኖሩን እንደገለጹላቸው አስመጪዎቹ አስረድተዋል፡፡

እንደ አስመጪዎቹ ገለጻ፣ ስለጉዳዩ ዝርዝር መረጃ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤትን ጠይቁ መባላቸውን፣ ክልከላው በሥራቸው ላይ እንቅፋት እንደፈጠረባቸውና የተለያዩ ተሽከርካሪዎችንም ሆነ ትራክተሮችን የሚሸጡ ነጋዴዎች ዋጋ ጨምረው በመሸጥ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከባድ ተሽከርካሪዎችና ትራክተሮችን ጨምሮ ሌሎች ተሽከርካሪዎች እንደ አውቶሞቢሎች በኤሌክትሪክ እንደማይሠሩ የተናገሩት አስመጪዎቹ፣ ችግሩን መንግሥት በአፋጣኝ በመረዳት ክልከላው ይነሳልን ብለዋል፡፡

መንግሥት ከባድ ተሽከርካሪዎችንም ሆነ ትራክተሮች በመመርያ ቢከለክል  በአገር የመጣ ጉዳይ መሆኑን በማመን ሌላ አማራጭ እንደሚፈልጉ የገለጹት አስመጪዎቹ ችግሩን የፈጠረው አንድ የመንግሥት ተቋም መሆኑ ሁኔታውን የተወሳሰበ እንዲሆን አድርጎታል በማለት አስረድተዋል፡፡

መንግሥት ለኮንስትራክሽንና ለሌሎች ዘርፎች ለሥራ ያስፈልጋሉ ብሎ ካላመነ በስተቀር የነዳጅ ተሽከርካሪዎች ከዚህ በኋላ ከውጭ እንደማይገቡ፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡

ተሽከርካሪዎቹ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ መከልከሉን ገልጸው፣ የክልከላ አቅጣጫ የተቀመጠው ሚኒስቴሩ የ2016 ዓ.ም. የሩብ ዓመት ሲገመግም መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በወቅቱ ይህንን በተመለከተ የገንዘብ ሚኒስቴርና የገቢዎች ሚኒስቴር ለሚመለከተው አካላት በደብዳቤ ጭምር እንዲያሳውቁ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸውም ነበር፡፡

በዚህ መሠረት ማንኛውም ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ ተሸከርካሪ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀም መሆኑን እንዳለበት ተናግረው ነበር፡፡

ጉዳዩንም በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርን በስልክ ለማነጋገር በተደጋጋሚ ጥረት ቢደረግም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...