Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበአዲስ አበባ የታቀደ ጥቃት ማክሸፉን መንግሥት አስታወቀ

በአዲስ አበባ የታቀደ ጥቃት ማክሸፉን መንግሥት አስታወቀ

ቀን:

  • በኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያ የተጠረጠሩ መያዛቸው ተነገረ
  • የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና ኢሰመኮ ግድያው በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጠየቁ

በዮናስ አማረ

ዓርብ ሚያዝያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሊሞከር የነበረ ህቡዕ ጥቃት ማክሸፉን የፀጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡ ግብረ ኃይሉ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ‹‹ፅንፈኛ ቡድን›› ሲል የጠራው የቡድን አባላት፣ በአዲስ አበባ ጥቃት ሊያደርሱ በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ ቀድሞ ማክሸፉን የገለጸው ግብረ ኃይሉ፣ የቡድኑ አባል በሆኑ ግለሰቦች ላይ ዕርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ ጥቃት ሊያደርሱ ከነበሩ ግለሰቦች መካከል ናሁሰናይ አንዳርጌ፣ ታረቀኝ አቤኔዘርና ጋሻው አባተ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ መገደላቸውን ያስታወቀው ግብረ ኃይሉ፣ ሀብታሙ አንዳርጌ ተሰማ የተባለው ግለሰብ ደግሞ በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን የግብረ ኃይሉ መግለጫ አመልክቷል፡፡

- Advertisement -

ናሁሰናይ የቡድኑ አመራርና በአዲስ አበባ ተወጥነው ለነበሩ ሆኖም ለከሸፉ የጥቃት ዕቅዶች ዋና አቀነባባሪ እንደነበር መግለጫው ያትታል፡፡ አባላት መልምሎም ለጥቃት ሲዘጋጅ ነበር ብሏል፡፡ ለዚሁ ተልዕኮ ዓርብ ዕለት በተለምዶ ቦሌ ሚሊኒየም አዳራሽ አቅራቢያ በመኪና ሲንቀሳቀሱ በፀጥታ አካላት በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ ቢጠየቁም፣ ፈቃደኛ ከመሆን ይልቅ የተኩስ ምላሽ መስጠታቸው በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡ በዚህም ሳቢያ በተካሄደው የተኩስ ልውውጥ የሁለት የፖሊስ አባላት ላይ ከባድ የመቁሰል አደጋ ማድረሳቸውን ጠቁሟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አቶ እንደሻው ጌትነት የተባሉ ግለሰብ በመኪናቸው እንዲጭኗቸው ሲያስገድዷቸው አልተባበር በማለታቸው፣ በቡድኑ አባላት እንደተገደሉ መግለጫው ያትታል፡፡

ፅንፈኛ የፋኖ አመራርና አባላት ናቸው ባላቸው ላይ ዕርምጃ መወሰዱን ያረጋገጠው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስት ልዩ ቦታው ሚሊኒየም አዳራሽ አቅራቢያ እጃቸውን እንዲሰጡ ቢጠየቁም፣ እንቢ በማለታቸውና ተኩስ በመክፈታቸው ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው ይገልጻል፡፡ የቡድኑ አባላት የግለሰቦችን ቤት ተከራይተው ለጥቃት ራሳቸውን ሲያዘጋጁ ቆይተዋል ሲል ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ፣ ግለሰቦቹን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በተደረገ እንቅስቃሴ ወቅት፣ እጅ ላለመስጠት ከፍተኛ የሆነ ትግል እንዳደረጉ ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ሒደት የአንድ ግለሰብ ሕይወት ማለፉን የተናገሩት ኃላፊው ከተጠርጣሪዎቹ መካከል፣ ‹‹ናሁሰናይ አንዳርጌ ቆስሎ ወደ ሕክምና ከተላከ በኋላ ሕይወቱ አልፏል፡፡ ሀብታሙ አንዳርጌ ደግሞ በተኩስ ልውውጡ መካከል ሞቷል፡፡ አቤኔዘር ጋሻው የተባለው የፋኖ አባል ሳይቆስል በቁጥጥር ሥር ውሏል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ የደረሱበትን ተጨማሪ የምርመራ ውጤት በየጊዜው ለሕዝብ እንደሚያቀርቡ ነው ግብረ ኃይሉና ፖሊስ የገለጹት፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያን በተመለከተ በርካታ መግለጫዎች ከየአቅጣጫው መውጣት ቀጥለዋል፡፡ አቶ በቴ በትውልድ ከተማቸው መቂ ሚያዝያ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ተገድለው መገኘታቸውን በተመለከተ በርካታ ወገኖች ከሐዘን መግለጫ ባለፈ፣ ጉዳዩ በአስቸኳይ ተጣርቶ ለፍትሕ እንዲቀርብ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለሪፖርተር በላከው መግለጫ፣ የፖለቲከኛውን ግድያ አጥብቆ እንደሚያወግዝ አስታውቋል፡፡ ግድያውን በአስቸኳይ በገለልተኛ ወገን ማጣራት አስፈላጊ መሆኑን ያስገነዘበው የጋራ ምክር ቤቱ ለዚህ ሙሉ ትብብር አደርጋለሁም ብሏል፡፡

ከጋራ ምክር ቤቱ መግለጫ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የምሥራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስን ዋቢ በማድረግ በአቶ በቴ ግድያ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ስለመያዛቸው የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ ከዚሁ ግድያ ጋር በተያያዘ በጥርጣሬ ተያዙ የተባሉት ሰዎች ቁጥር 13 መሆኑም ተነግሯል፡፡

ዓርብ ዕለት ቀብራቸው በተወለዱበት በመቂ ከተማ መፈጸሙ የተነገረው አቶ በቴ፣ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የሚታወቁና የአደባባይ ፖለቲከኛ እንደነበሩ በርካቶች እየተናገሩላቸው ነው፡፡ እናት ፓርቲያቸው ኦነግ ተገደሉ በተባለ ዕለት ድርጊቱን አውግዞ መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ በአስቸኳይ ድርጊቱ እንዲጣራ ጠይቋል፡፡ ‹‹በነቁ የኦሮሞ ፖለቲከኞችና በታዋቂ ሰዎች ላይ የሚደረገው ግድያ ቀጥሏል፤›› ያለው ኦነግ፣ የአቶ በቴን ግድያ ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር አመሳስሎታል፡፡

ግድያውን ተከትሎ የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀመንበር ሴናተር ቤን ካርዲን ባወጡት መግለጫ፣ የአቶ በቴ ግድያ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ለሕግ እንዲቀርብ ጠይቀዋል፡፡ አያይዘውም በተቃዋሚዎች፣ በሚዲያዎች፣ በማኅበራዊ አንቂዎችና በሲቪክ ማኅበራት ላይ እየደረሰ ነው ያሉትን ጫና አውግዘዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ የአቶ በቴ ግድያ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ከጠየቁት አንዱ ሲሆኑ፣ የሕግ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ለዕርቅና ለስምምነት መንገድ ይከፍታል ብለዋል፡፡

በጥይት ተደብድበው በግፍ ተገድለው አስከሬናቸው የተገኘው አቶ በቴ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ሲሆኑ፣ በተወለዱበት መቂ አካባቢ የሚተዳደሩበት የእርሻ ሥራ እንደነበራቸው ተነግሯል፡፡ ይህን በየጊዜው ከአዲስ አበባ እየተመላለሱ የሚከታተሉትን የእርሻ ሥራ ለማየት ወደ መቂ በሄዱበት ወቅት በዚያው መገደላቸው ተነግሯል፡፡

ግድያውን ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በሰጠው መግለጫ ምርመራ ባልተደረገበትና ወንጀል ፈጻሚው ገና ባልታወቀበት ሁኔታ፣ ክስተቱን ለፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ የሚጠቀሙ ኃይሎች መኖራቸውን አስታውቆ ነበር፡፡ ‹‹ከመንግሥት ጋር የአቋም ልዩነት ስላላቸውና የፖለቲካ አቋማቸው ስለሚለይ ብቻ ግድያው በመንግሥት አካል እንደተፈጸመ ተደርጎ የሚነዛው ፕሮፖጋንዳ ፍፁም ተቀባይነት የለውም፤›› በማለት የክልሉ መንግሥት ጉዳዩን በተመለከተ ያለውን አቋም አንፀባርቋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም ይህንኑ የአቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያን የተመለከተ መግለጫ አውጥቷል፡፡ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ ‹‹ኮሚሽኑ ከተቃዋሚው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ፓርቲ አባል በቴ ኡርጌሳ ግድያ ጋር ተያይዞ ወንጀለኞቹ በሕግ እንዲጠየቁና በኦሮሚያ ክልልና በኢትዮጵያ ፌዴራል ባለሥልጣናት አፋጣኝ፣ ገለልተኛና ሙሉ ምርመራ እንዲደረግ ይጠይቃል፤›› ብለዋል።

ፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ ግድያውን በተመለከተ በማኅበራዊ ገጹ በለጠፈው መረጃ፣ ‹‹የትኛው እጅ ነው ጨክኖ በቴ ኡርጌሳን በሌሊት ከእንቅልፋቸው አስነስቶ የሚረሽነው? እንዴትስ በቴን የሚያውቅ ሆዱ አስችሎት ዓይኑ እያየ ሊገድለው ቻለ? ወገኖች ይህ ምን ይባላል አሁን?›› በማለት ጠይቋል፡፡ ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌውም መግለጫ ካወጡት አንዱ ሲሆኑ፣ የአቶ በቴ ኡርጌሳ ዕጣ ፈንታ ነገና ተነገ ወዲያ በሁሉም ሰው ላይ ሊደርስ የሚችል መሆኑን ጠቅሰው መንግሥት ላይ ወቀሳ ሰንዝረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...