Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉስለዘር ፖለቲካ

ስለዘር ፖለቲካ

ቀን:

በሀብታሙ ኃይለ ጊዮርጊስ

 ‹‹በቅሎዎች ዝርያችን ከአህያ ነው እያሉ ይመፃደቃሉ›› የጀርመኖች ምሳሌያዊ አባባል።

‹‹ዘረኝነት›› ማለት?

- Advertisement -

‹‹ዘረኝነት›› የሚለውን ቃል ብዙውን ጊዜ ፖለቲከኞችም ሆነ ሌሎች ሰዎች ሲጠቀሙት እንሰማለን። ‹‹የዘረኝነት ፖለቲካ››፣ ‹‹የዘር ፖለቲካ››፣ ‹‹ዘረኛ››፣ ወዘተ. የተሰኙ ሐረጎች ለየትኛው ዓይነት አመለካከት ወይም ተግባር ምላሽ ነው ጥቅም ላይ የሚውሉት ብለን መጠየቅ ያስፈልጋል።

ወደ ጥልቅ ሙያዊ ትንተና ሳንገባ ‹‹ዘረኝነት›› የሚለው ሐሳብ የሚያመለክተው አንድ ሰው ወይም ቡድን ሌላውን ግለሰብ ወይም ቡድን በቆዳ ቀለሙ፣ በብሔረሰቡ፣ በጎሳው ወይም በሌሎች ተዛማጅ በሆኑ ማንነቶቹ ላይ በመመርኮዝ ያ ቡድን ወይም ግለሰብ ጥቅም እንዲያገኝ ወይም እንዲጎዳ ማድረግን ነው። ለምሳሌ ነጮች በሚበዙበት አገር ነጭ በሆነ በአንድ የመንግሥት ተቋም ባለሥልጣን አነሳሽነት በአንድ ጥቁር የተቋሙ ሠራተኛ ላይ ግለሰቡ ጥቁር በመሆኑ ብቻ ከሥራ እንዲሰናበት እንደተደረገ በበቂ መረጃ ቢረጋገጥ፣ ‹‹የዘረኝነት ድርጊት ተፈጽሟል›› ማለት ይቻላል።

ወይም በኢትዮጵያ የድርጅቱ አብዛኛው ሠራተኞች የአንድ ብሔረሰብ አባላት በሆኑበት በአንድ የሥራ ድርጅት ውስጥ፣ አንድ ግለሰብ ለሥራው የሚያስፈልገውን የብቃትና የክህሎት መመዘኛ ሳያሟላ በድርጅቱ ውስጥ በርከት ከሚሉት ሰዎች ጋር በብሔረሰብ ተመሳሳይ በመሆኑ ምክንያት ብቻ የሥራ ዕድል እንዲሰጠው መደረጉ በመረጃ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ይህ ከዘረኝነት የመነጨ አሠራር እንደሆነ ይችላል። ትልቁ ችግር ግን ከላይ በተጠቀሰው መንገድ ዘረኝነት ራሱን በአደባባይ እያጋለጠ አለመፈጸሙ ነው። እንደ ሌሎች ማኅበራዊ ዝቅጠቶች ሁሉ፣ ዘረኝነትም በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ በተወሳሰበና በረቀቀ መልኩ ሊንፀባረቅ ይችላል።

በአገራችን ግን በዘልማድ ‹‹እገሌ ዘረኛ ነው›› ወይም ‹‹እገሌ የሚባለው ብሔረሰብ በጣም ዘረኛ ነው›› የሚል ትችት በአብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ሲሰነዘር እናስተውላለን። ከኅብረተሰቡ መካከል የሚበዛው እንደዚህ ሲያምን ወይም ሐሳቡን ሲገልጽ ከፍ ብሎ የተቀመጡትን ዓይነት ዘረኝነት ለሚባለው የሚያበቁ መሥፈርቶችን ሳይመለከት ባልጠለቀ ትንታኔ የሚፈርጅ ይመስላል። ከዘረኝነት ጋር ጎን ለጎን የሚነሱ ስያሜዎች ‹‹ጎሰኝነት››፣ ‹‹ጎጠኝነት››፣ ‹‹ሠፈርተኝነት››፣ ‹‹ወንዛዊነት››፣ እና የመሳሰሉት ናቸው። በእነዚህ ቃላት መካከል ወዳሉት የትርጓሜ ልዩነቶችና አንድነቶች መግባት ሳያስፈልገን በእንግሊዝኛው ‹‹Racism›› እና ‹‹Tribalism›› ስለሚባሉት ሁለት አስተሳሰቦች በአጭሩ እንወያይ።

‹‹Racism›› (ለዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ‹‹ዘረኝነት›› የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ በትክክል የሚወክለው) ወይም በቆዳ ቀለምና በተያያዥ በሰው ዘር መካከል በሚታዩ የአካል ገጽታ ልዩነቶችና ምስስሎሽ ምክንያት፣ አንዱን የሰው ዘር ምድብ ከሌላው አሳንሶ ወይም አስበልጦ የመመልከት፣ ወይም ይህን አመለካከት በተግባር የማሳየት ችግር ነው። ቃሉም የተፈጠረው ‹‹Race›› ከተሰኘው (‹‹የሰው ዝርያ ምድብ›› በሚል ሊተረጎም ከሚችለው) ግንድ ቃል ነው። በዝርያ ምድብ (Race) ሰዎችን መከፋፈል ምንም እንኳ ሳይንሳዊ ልዩነት ባይሆንም፣ ይኸው የክፍፍል ልማድ በዓለም በእጅጉ የበረታ ከመሆኑ የተነሳ የማኅበራዊ ሳይንስ ሊቃውንት ትኩረት ሳይነፍጉት በዚሁ መሥፈርት ለሰው ልጆች በተሰጡት ልዩነቶች መሠረት ጽሑፋቸውን ያሰፍራሉ።

የዓለምን ሕዝብ አንዱን ከሌላው ለመለየት ከሚያገለግሉ የምደባ መንገዶች አንዱ የዝርያ ምድብ በመሆኑ፣ በዋናነት በምድራችን ላይ ሦስት ዓይነት የሰው ምድቦች እንደሚገኙ ታምኗል፡፡ ጰጰካውካሶይድ››፣ ‹‹ሞንጎሎይድ›› እና ‹‹ኔግሮ››”። ‹‹ካውካሶይድ›› በአብዛኛው የመሀልና ምዕራብ አውሮፓን ‹‹ነጭ›› ሰዎች የሚወክል ሲሆን፣ ‹‹ሞንጎሎይድ›› ደግሞ የሩቅ ምሥራቅን የዓለም ክፍልንና የደቡብ ምሥራቅ እስያ አካባቢ ሕዝብን ያካትታል። ‹‹ኔግሮ›› ደግሞ ጥቁሮችን፣ በተለይም የአፍሪካ ምድር ነዋሪዎችን ይመለከታል።

ከዚህ በተጨማሪም ንዑሳን የዝርያ ምድብ (Race) ክፍፍሎች የሚስተዋሉ ሲሆን፣ እነዚህም ‹‹ላቲኖ›› (የደቡብ አሜሪካን ነዋሪዎች)፣ ‹‹ሂስፓኒክ›› (አመጣጣቸው ስፔን ወይም ላቲን አሜሪካ የሆኑ)፣ ‹‹ሬድ ኢንዲያንስ›› (በአሜሪካ ምድር ከአውሮፓውያን መግባት በፊት ይኖሩ የነበሩና አሁንም በጥቂቱ የሚገኙ ቀያይ ሰዎች)፣ ‹‹ኦሪየንታል›› (በተለምዶ ‹‹ቢጫ›› እየተባሉ የሚታወቁት በአብዛኛው ጃፓናውያን፣ ቻይናውያንና ኮሪያውያን…) ወዘተ. ናቸው።

እንግዲህ ከዚህ የምንረዳው ‹‹ዘረኝነት›› (Racism) በዓለማችን በእጅጉ የተንሰራፋ እንደሆነ ግልጽ ነው። በአፓርታይድ አገዛዝ ወቅት በደቡብ አፍሪካ ታይቶ የነበረው የነጭ ቅኝ ገዢዎች በጥቁር አፍሪካውያን ላይ ያሳዩት የነበረው የበላይነትና በዩናይትድ ስቴትስ እስከ ቅርብ ጊዜያት ድረስ ይስተዋል የነበረው ዘረኝነት ይህን ቅርፅ የያዘ ነበር። ሒትለር የተሰኘው ጀርመናዊ መሪ፣ እሱ የወጣበት የዝርያ ምድብ ከሌላው የተሻለና ከእሱ የተለየው መጥፋት እንደሚገባው በማመን፣ የዓለምን ስንት ስንተኛ ሕዝብ (ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑ አይሁዶችን) ከምድር ገጽ አስወግዷል። መስተዋል ያለበት ነገር እንደዚያ ያለው ዘረኝነት ነጭ የበላይነቱን ሲያሳይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም መልኩ ሊገለጽ የሚችል መሆኑ ነው።

ለምሳሌ በአንድ ዘመን ተነስተው ጥቁር (ኔግሮ) የሚባሉት እኛ የበላይ ነን ቢሉ ወይም እነሱ ‹‹ነጮች›› ከሚባሉት እንደሚያንሱ በመቁጠር ይህን አመለካከት የሚያራግብ ተግባር ቢፈጽሙ፣ ያው በዘረኝነት የሚመዘገብ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። በ‹‹ሞንጎሎይድ›› እና በ‹‹ካውካሶይድ››፣ በ‹‹ሞንጎሎይድ›› እና በ‹‹ኔግሮ››፣ ወዘተ. መካከልም ይህን የመሰለ ግንኙነት ካለም ዘረኝነት ይሆናል።

ይኽኛው ዓይነት ዘረኝነት ዕውን በኢትዮጵያ ትልቅ ችግር ሆኖ ያውቃል ወይ? መልሱን ለማግኘት በኢትዮጵያ ስንት ‹‹የዝርያ ምድቦች›› (Races) ይገኛሉ የሚለውን ጥያቄ መመለስ የግድ ነው። ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በቆዳ ቀለምና መሰል አካላዊ ገጽታዎች በተወሰነ መልኩም ቢሆን የተለያዩ የሰው ዝርያዎች የሚገኙባት አገር ሆና የኖረች ቢሆንም፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚታየው ትልቁ ወገንተኝነት በቆዳ ቀለም ወይም በሌሎች አካላዊ ልዩነቶች ምክንያት የሚታይ ልዩነትን መሠረት ያደረገ እንደሆነ አይደለም የምናስተውለው። ይልቁንስ በአገራችን ውስጥ የበለጠ የሚገነው ወገንተኝነት ሌላኛው ዓይነት ነው።

ይህ ወገንተኝነት ‹‹Tribalism›› የሚባለው (‹‹ነገደኝነት›› የሚል ፍች ሊሰጠው የሚችለው) ነው። የ‹‹Tribalism›› መነሻ ቃሉ ‹‹tribe›› ማለትም ‹‹ነገድ›› ነው። በአማርኛም ሆነ በእንግሊዝኛውም ይህ ቃል በአሁን ዘመን ለሚገኙ ማኅበረሰቦች መጠሪያ በመሆን እምብዛም አያገለግልም። ይሁን እንጂ ‹‹Tribe›› ወይም ‹‹ነገድ›› ስንል በኛ ዘመን ‹‹ብሔረሰብ›› ከምንለው የሰዎች ቡድን ጋር አቻ ባይሆንም ተቀራራቢ እንደሆነ ይረዷል። ቃሉን በምትክነት ለመጠቀም የተፈለገበት ምክንያት በጣም ከተለመደውና የንግግርንም ሆነ የጽሑፍን ለዛ ሊቀንስ ከሚችለው ‹‹ብሔረሰብ›› ወይም ‹‹ብሔርተኝነት›› ከሚለው ለየት በሚል አማራጭ ቃል ለመገልገል በማሰብ ነው።

እናም በኢትዮጵያ አንዱ ማኅበረሰብ በመሠረታዊነት ከሌላው የሚለየው በነገድ ይመስላል። ሰፍቶና ነቀርሳ ሆኖ የሚታየውም የወገንተኝነት ዓይነት፣ ‹‹ዘረኝነት›› (Racism) ሳይሆን ‹‹ነገደኝነት›› (Tribalism) ነው። ለዚህ ድምዳሜ በማስረጃ መድከም አላስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ነገድን ማዕከል ያደረገ ጥላቻ፣ ጦርነትና ውድመት ከህልቆ ወመሳፍርት በላይ ለሆኑ ጊዜያት እየተነሳ አገሪቱን ጎብኝቷታል። ከዚህም የተነሳ ሁለቱን ሐሳቦች በማምታታት በኢትዮጵያ ‹‹ዘረኝነት›› (Racism) እንደተንሰራፋ በመቁጠር፣ ‹‹ነገደኝነትን›› ለማውገዝ የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች በማኅበራዊ ትስስር ሚዲያዎች ሁሉ ሳይቀር ‹‹No to Racism›› (ዘረኝነትን እምቢ እንበል) ብለው ርዕስ ይለጥፉና ወረድ ብለው የሚያነሱት ግን ስለ ‹‹ነገደኝነት›› ነው። የጽንሰ ሐሳብ ልዩነቱ መስተካከል ያለበት ጉዳይ ነው።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...