Wednesday, May 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉከሴራ ፖለቲካ በስተጀርባ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቁ ኃይሎች

ከሴራ ፖለቲካ በስተጀርባ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቁ ኃይሎች

ቀን:

በመኮንን ሻውል ወልደ ጊዮርጊስ

የአፄ ቴዎድሮስ መንግሥት የወደቀው ከመቅደላ በፊት ነው። ቴዎድሮስ በመቅደላ  ሚያዚያ 6 ቀን 1860  ዓ.ም.  ሽጉጡን ጠጥቶ፣

‹‹መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ፣

- Advertisement -

የሴቱን አናውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ››

ተብሎ ለጀግና አሟሟቱ መታሰቢያ ዘመን ተሻጋሪ ግጥም ሳይገጠምለት በፊት ነበር፣ በፀረ ቴዎድሮስ መንግሥት ፕሮፓጋንዳ ክፉኛ ተገዝግዞ በቅርቡ ባሉት የጦር አባላት ብቻ ተደግፎ ቆሞ የነበረው።

የመይሳው ካሰን የአንድነትና ኢትዮጵያን ኃያል የማድረግ ሕልም ለማጨናገፍ ሺ He የሥልጣን ጥመኛ ጋረዶችና ጥቂት የመሰሪ ፕሮፓጋንዳ ፈብራኪ ”አክሊሉዎች” ወዳጅ መስለው በስተጀርባውና በፊት ለፊት በመውጋት የመንግሥትነት አቅሙን አሳጥተውት ነበር።

አፄ ቴዎድሮስ  ከመቅደላ ከተደነቀበት የጀግንነት ሞቱ  ጥቂት ዓመታት አስቀድሞ፣   የተለያየ  የጥቅም  አጀንዳ ካላቸው ግለሰቦች ካደራጇቸው  ቡድኖች ጋር በመፋለም ጦሩ ተዳክሞ ነበር።

በሰው ኃይል፣ በትጥቅና በስንቅም የተመናመነ ኃይል ስለነበረው፣ አገርን የማበልፀግ ድንቅ ሕልሙ በመሰሪዎች፣ በሥልጣን ጥመኞችና በኢትዮጵያውያን አንድነት ሥጋት ውስጥ በሚገቡ የውጭ ኃይሎች የተቀናጀ ተንኮል፣ ደባና ግልጽ ጥቃት በመክሸፉና እንግሊዞች ሊያጠፉት በወቅቱ አለ የሚባለውን ጦር መሣሪያ ሁሉ አንግበው  ስለመጡበት የመጨረሻ የመከላከያ ምሽጉን  መቅደላ  ላይ አደረገ። በመጨረሻም የገዛ ሽጉጡን ምላጭ ስቦ ጥይቱን ጠጥቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ  ለዘለዓለም የሚኮራበትን የጀግና ሞት ሞተ።

የአፄ ቴዎድሮስ መንግሥት በውሰጥ ሴረኞች ሰበብ አገርን ለማበልፀግ እንዳልቻለ፣ ለሞት ወደ መቅደላ እንደተጓዘ (ወደ ቀራንዮ በሉት) ዕውቁ ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁን “የቴዎድሮስ ዕንባ” በተሰኘ ታሪካዊ ድርሰቱ ግሩም አድርጎ ጽፎታል።

አፄ ቴዎድሮስ በወጣትነታቸው  በጀግንነታቸው እየታወቁ በመምጣታቸው የራስ ዓሊን ልጅ ተዋበች ዓሊን  በማግባት በደጃዝማች ማዕረግ ቋራን እንዲያስተዳድሩ ከመደረጋቸው በፊት ካሳ ኃይለ ጊዮርጊስ፣ አክሊሉና ጋረድ ጓደኛሞች ነበሩ ይለናል የብርሃኑ ዘሪሁን “የቴዎድሮስ ዕንባ” መጽሐፍ።

እንደ እነ አክሊሉና ጋረድ ዓይነት ለአፄው ቅርበት ያላቸው  በሥልጣን ጥምና በግል በደል ባረገዙት ቂም ያበዱ  ግለሰቦች የአፄ ቴዎድሮስን ሕልም ለማጨለም  ዓይነተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ የብርሃኑ ዘሪሁን መጽሐፍ ይተርካል (ብርሃኑ በብስለት ከጻፈው “የታንጉት ሚስጥር” መጽሐፉ በፊት  ይህ መጽሐፍ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በ1958 ዓ.ም.  የተጻፈ ታሪክ ቀመስ አጭር ልቦለድ ነው)፡፡

መሰሪው አክሊሉ (ኢትዮጵያዊው ኢያጎ)  ጋረድ የተባለውን የባላባት ልጅ ቴዎድሮስ ለተቀመጡበት ዙፋን እሱ እንደማያንስ፣ እንዲያውም ተገቢው ሰው እሱ እንደሆነና ሰብዕናውን በማግዘፍ፣  ጀግንነቱን በማወደስ ፣ የዘሩን ጥራት በመጥቀስ  በአፄ ቴዎድሮስ ላይ  የመጀመሪያው ሸፋች ሹመኛ እንዲሆን አድርጎታል።

አክሊሉ በወጣትነቱ እንደ  ካሳ ኃይለ ጊዮርጊስ (በመቀጠል አፄ ቴዎድሮስ) የአንድ መስፍን  ጠመንጃ አንጋች (በዘመኑ አጠራር ሎሌ) ነበረ። አክሊሉ እዚህ ተንኮል ውስጥ የገባው በገና ጨዋታ ወቅት ቴዎድሮስ የመታት ቁር ወይም ድቡልቡል  የገና መጫወቻ  የወይራ ኳስ፣ የዘር ፍሬዎቹን አፍርጣ ዘሩን እንዳይተካ አድርጋው ስለነበር ነው። ይህንን ቂም ግን ለማንም አልተናገረም።

ከአክሊሉ ጋር የልጅነት ጓደኛ የነበሩት ልጅ ካሳ ኃይለ ጊዮርጊስ ታሪክ በጻፈው  የጀግንነት ተጋድሏቸው  የሸዋን ምንሊክ ሳይቀር ማርከው፣ ጎንደር በፋሲል ቤተ መንግሥት በአቡነ ሰላማ አማካይነት ንጉሠ ነገሥት  ዘ ኢትዮጵያ በመሰኘት አፄ ቴዎድሮስ ተሰኙ።

አክሊሉ በቅናት አረረ። በቂም በታጀበ ቅናት ተነሳስቶ ያለ እኔ ወንድ የለም ባዩን ጋረድን በኢዮጋዊ ችሎታው በንጉሡ ላይ እንዲሸፍት አደረገው። ልጅ ጋረድ የካሳ አብሮ አደግ  ነበር። ካሳ ንጉሥ ሲሆን በደጃዝማች ማዕረግ የወገራ ገዥ አድርጎ ሾሞትም ነበር። እሱ አይመጥነኝም ብሎ ለመሸፈት አሴረ እንጂ።

አፄ ቴዎድሮስ ይህንን ሲሰሙ አዘኑ። ራሴ ነኝ ሄጄ የምቀጣው ብለው ጦር ሲያደራጁ ምሽታቸው ተዋበች ሞቱ።

“እስቲ ጠይቁልኝ እርቃ ሳትሄድ፣

እቴጌ ተዋበች ሚስት ‘ናት ገረድ”

በማለት ከባድ ሐዘናቸውን ለሙሾ ተቀባዩ ለቀስተኛ የገለጹት ያኔ ነው። እናት፣ ሚስትና ገረድ አጡ። እንደ እናት ማን ይሳሳላቸው? እንደ ሚስት ማን ደጋፊና መካሪ ይሁናቸው? እንደ ገረድስ (ሁሉን አቀፍ የምግብ ባለሙያ) ማን ጣት የሚያስቆረጥም ምግብ አዘጋጅቶ ይመግባቸው?

ሐዘናቸውን ሳይጨርሱ በትካዜ ውስጥ ሆነው፣ መካሪ አጥተው ጋረድን ለመውጋት ከገብርዬ፣ ከአለሜና ከሊቀ መኳስ ቤል (የኢትዮጵያዊነት ዜግነት ተሰጥቶት  ኢትዮጵያዊት አግብቶ፣  ሃይማኖቱን ኦርቶዶክስ አድርጎ የሚኖር በአፄው ማዕረግ የተሰጠው እንግሊዛዊ) ጋራ ዘመቱ።

ከጋረድ ጦር ጋር ያደረጉት ፍልሚያ በእጅጉ ከባድ ነበር። ጋረድ ንጉሡን ለመግደል ተቃርቦ ነበር። ንጉሡ ላይ ከመተኮሱ በፊት ሊቀ መኳስ ቤል በሽጉጥ ከፈረሱ ላይ ጣለው። ቤልንም የጋረድ ወንድም በጦር ወግቶ ገደለው። የጋረድ ወንድምን አፄ ቴዎድሮስ በሽጉጣቸው ቀልበው ከፈረሱ ላይ ተፈናጥሮ ድንጋይ ላይ እንዲከሰከስ አደረጉት።

በሊቀ መኳስ ቤል መሞት የተበሳጩት ንጉሥ አንድም ሰው እንዳያመልጥና ምሕረትም እንዳይደረግለት ጦራቸውን አዘዙ።

ከጦርነቱ በኋላ መሰሪው  አክሊሉ ሸሽቶ ገዳም ገባ። ከዕፎይታ  በኋላ በአንድ ደብር ላይ አንካሴውን ይዞ፣ ሰንሰለት በወገቡ ታጥቆ ባህታዊ መስሎ በንግሥ በዓል ላይ ተገኘ። “በአፄው ሰበብ ምዕመናን በቂ ሃይማኖታዊ ሥርዓት እንዳይፈጽሙ ተደርጓል። በአንድ ደብር  ከአምስት በላይ ካህን አያስፈልግም በማለት ንጉሡ በሃይማኖታችን ጣልቃ ገብተዋል።  እንግዲህ ልጆቻችሁን ማን ያስተምር? ፍትሃት ማን ይፍታ? ማንስ ስለሃይማኖት ያስተምር? ንጉሡ ፀረ ሃይማኖት ናቸው…” ብሎ ሰበከ።

በዚህ መሰሪ ቅስቀሳ የጎንደር ሕዝብ በአፄው ላይ ሸፈተ፣ አፄ ቴዎድሮስም እጅግ ተናደዱ። ምሕረተ ቢስና ጨካኝ ዕርምጃ በአማፅያኑ ላይ ወሰዱ። የጎንደር ከተማ ቤቶች ተቃጠሉ። ዘግናኝ ዕልቂትም ተፈጠረ። አፄውም በሁኔታው አዘኑ፡፡ ለዚህ ከሆነ ፈጣሪ የፈጠራቸው፣ ባይፈጥራቸው እንደሚሻል በቁጭት ለፈጣሪ ተናገሩ። ከዚያ በኋላ ብዙም አልሰነበቱም። በወራሪው በእንግሊዝ ጦር አሳዳጅነት መቅደላ አፋፍ ላይ ሽጉጣቸውን ጠጥተው ሞቱ።

 “መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ፣

 የሴቱን አላውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ፣

 ገደልን እንዳይሉ ሞተው አገኟቸው፣

 ማረክን እንዳይሉ ሰው የለ በእጃቸው፣

ምን አሉ እንግሊዞች ሲገቡ አገራቸው?”

ከላይ የጻፍኩትን ሐሳብ ያገኘሁት በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ከሚሰጠው ጋዜጠኛና ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ “የቴዎድሮስ ዕንባ” ከተሰኘ አጭር ልቦለድ ነው። በነገራችን ላይ ብርሃኑ ዘሪሁን የበርካታ ሥራዎች ባለቤት ሲሆን፣ ደጎስ ያሉ በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት የታተሙ ሁለት የአጭር ልቦለድ ስብስብ ወይም መድብሎች አሉት። “መድብል አንድ እና ሁለት” ተብለው የታተሙ። ወጣቶች ፈልገው ያነቧቸው  ዘንድ እጋብዛቸዋለሁ (በበኩሌ ከታሪክ የተገነዘብኳቸውንና ከብርሃኑ ዘሪሁን ቀደምት ሥራ “መድበል አንድ” ያነበብኩትን አካፍያችኋለሁ)፡፡

እርግጥ ነው የአፄ ቴዎድሮስ  ኢትዮጵያን ታላቅ የማድረግ ጥረት፣ በወቅቱ በነበረው  ሕዝብ ንቃተ ህሊና ዝቅተኛነትና ከግል ጥቅማቸው ውጪ የሕዝብ ጥቅም ጉዳያቸው ባልሆነ የዘመኑ  መሣፍንቶችና ባለሥልጣናት ስግብግብነት ከሽፏል።

እነዚህ ባለሥልጣናት “ሥልጣን የጥቅም ማግኛ መሣሪያ ብቻ ነው” ብለው የሚያምኑና “ሹመት ለመብላት እንጂ ለማብላት እንዳልተፈጠረ” አበክረው የሚሰብኩ ነበሩ። የአገርና የሕዝብን ታላቅ መሆን ሳይሆን የራሳቸውንና የዘመድ አዝማዶቻቸውን ጥቅም  በሥልጣን ስም ለማስጠበቅና ለማስከበር የተሠለፉ ነበሩና የታላቁ ባለራዕይ መሪን ሕልም አጨናግፈዋል።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...