Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የወጪ ንግድ ፖሊሲያችን አገርን የሚጠቅምና ሕገወጥነትን የሚነቅል ሆኖ እንደ አዲስ ሊቀረጽ ይገባል!

ኢትዮጵያ ያልተቋረጠ የውጭ ምንዛሪ ችግር ውስጥ እንድትገባ ካደረጓት የተለያዩ ምክንያቶች አንዱና ዋናው የውጪ ንግዳችን በሚፈለገው መጠን አለማደግ ነው፡፡ ዕድገቱ በዔሊ ጉዞ የሚመሰል ነው፡፡ ምዕተ ዓመታት ባስቆጠረው የኢትዮጵያ ታሪክ ዓመታዊ የወጪ ንግዳችንን ገቢ አምስት ቢሊዮን ዶላር እንኳን ማድረስ አልተቻለም፡፡ አንድም ዓመት በታቀደው ልክ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ተገኝቶ አያውቅም፡፡ በአንፃሩ ከወጪ ንግዳችን በአራት እጅ በሚልቅ ወጪ ገቢ ምርቶችን እናስገባለን፡፡

የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለአገራችን የዋጋ ንረት መባባስ ለሕገወጥ ንግድና መስፋፋት ምክንያት መሆኑም መዘንጋት የለበትም፡፡ የአገራችንን ኢኮኖሚ ዕድገት የተገደበ ያደረገው መሠረታዊ ምክንያትና ችግር የውጭ ምንዛሪ እጥረት መሆኑ አይካድም፡፡ 

ይህ የውጭ ምንዛሪ ደግሞ በዋናነት መገኘት ያለበት ከወጪ ንግድ ገቢ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የወጪ ንግዳችን በሚፈለገው ደረጃ ሊያድግ አልቻለም፡፡ ዘርፉ ከሌላው የቢዝነስ ዘርፍ ሁሉ የበለጠ ድጋፍ የሚደረግለት የመሆኑን ያህል ውጤት አመርቂ ሊሆን አልቻለም፡፡ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ረሃብ በማስታገስ ረገድ የሚገባውን አስተዋፅኦ ማድረግ አልቻለም፡፡ 

ዘርፉን ለመደገፍ ተብሎ የብር የመግዛት አቅምን በተደጋጋሚ በማዳከም የተተገበሩ ፖሊሲዎች ያስገኙት ውጤት አይታይም፡፡ ጭራሽ የወጪ ንግድ ዘርፉን ለመደገፍ የተተገበሩ ፖሊሲዎች ኢኮኖሚ ውስጥ ሌላ ችግር እስከመፍጠር ደርሰዋል ብሎ በድፍረት መናገር እንችላለን፡፡ 

ለወጪ ንግድ ዕድገት ተብሎ የብርን የመግዛት አቅም በተደጋጋሚ የማዳከም ውሳኔ ተፈጻሚ ቢደረግም በዚህ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ ይገኛል ተብሎ የታሰበው ውጤት የውኃ ሽታ ሆኗል። አንዳንድ የመንግሥት አሠራሮችና መመርያዎች ደግሞ ከወጪ ንግድ ሊገኝ ይችል የነበረውን ጥቅም እያሳጡ መሆናቸው ይታያል።

ከዘመናት በኋላ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ የተገኘበት የቡና ምርት በተፈለገው መጠን ዕድገቱ ሊቀጥል ያልቻለው የዓለም የቡና ዋጋ ስለወደቀ ብቻ ሳይሆን የቡና የወጪ ንግድን የተመለከቱ አንዳንድ የአሠራር ማሻሻያዎችና መመሪያዎች በፈጠሩት ችግር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የወጪ ንግድ ገቢ በተፈለገው ደረጃ ላለማደጉ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም እንደ ቡና ያሉ ምርቶች በተሻለ ዋጋ የተሻለ ገበያ እንዲያገኙ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተተገበሩ ያሉ አሠራሮች እንቅፋት መሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡ በአስገዳጅነት በማዕከላዊ ገበያ በኩል ብቻ እንዲገበያይ ሲደረግ የነበረ ቡና በተለያዩ አማራጮች ወደ ውጭ ይላክ መባሉ ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን አንዳንድ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ ይህ ችግር በቡና ግብይት ውስጥ ሕገወጥ አሠራሮች እንዲያቆጠቁጡ ምክንያት እየሆነም ነው፡፡ በተለያዩ አማራጮች ቡና ይገበያይ መባሉ ለበጎ ታስቦ ቢሆንም ውጤቱ ግን ያን እያሳየ ነው ማለት አይቻልም፡፡ አሠራሩ ለሕገወጥ ንግድ በር እየከፈተ ነው፡፡ የመንግሥትን ግብር ለመሰወር የተመቻቸ ስለመሆኑም እየተነገረ መምጣቱ የወጪ ንግድን ችግር በእንቅርታት ላይ ጆሮ ደግፍ እያደረገው ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ በጥልቀትና በጥንቃቄ ሊፈተሽ ይገባል፡፡

እንዲህ ያለው አሠራር ለአገራችን የወጪ ንግድ አንድ ችግር እየሆነ የመጣ ጉዳይ ሲሆን፣ ከቡና ባሻገር ሌሎች የአገሪቱ የወጪ ንግድ ምርቶችም የሚጠበቅባቸውን ያህል ዕድገት ሊያሳዩ ያልቻሉበት ምክንያት የወጪ ንግድ ፖሊሲያችንና ሥራውን ለማሳለጥ የሚተገበሩ መመርያዎች ደካማ ከመሆናቸው ጋር ሊያያዝ ይችላል፡፡ 

ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ የአብዛኞቹ ምርቶች ዋጋ ጨምሮ ሳለ፣ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ምርቶች ዋጋ ወይም አገሪቱ ከውጭ ንግድ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንዴት ፈቅ ሳይል ባለበት ቆመ?

በዓለም ላይ የተፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ዋጋ እንዲጨምር አድርጎ ሳለ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢ ጭማሪ ወይም ዕድገት ያላሳየው የዓለም ገበያ ለኢትዮጵያ ምርቶች ብቻ የተለየ ዋጋ ሰጥቶ ነው የሚል ምክንያት መቼም ሊቀርብ አይቻልም፡፡ 

ሌላው ቀርቶ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች በሙሉ የአገር ውሰጥ የመሸጫ ዋጋቸው በከፍተኛ ደረጃ መጨመራቸው በግልጽ እየታየ ይህ ለውጥ የወጪ ንግድ ገቢው ላይ አለመታየቱ አጠቃላይ አሠራሩ ላይ ችግር ስለመኖሩ አያሳይም? በአገር ውስጥ ገበያ ዋጋቸው የተሰቀሉት የወጪ ንግድ ምርቶች ለውጭ ገበያ ሲቀርቡ እንደሌላው አገር ምርት ተመሳሳይ የሆነ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙት በኪሳራ እየሸጥናቸው በመሆኑ ነው? እነዚህ ጥያቄዎች መልስ ካላገኙ የአገራችንን የወጪ ንግድ ችግር መፍትሔ ለማምጣት ከባድ ይሆናል፡፡ ብዙ ማግኘት እየቻልን አሁንም እዚያው እንድንዳክር ያደርገናል፡፡ 

የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ችግሮች በዚህ ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ብዙ የወጪ ንግድ ምርቶቻችን በተለይ እንደ ማዕድንና የቀንድ ከብት ያሉ ምርቶች ሕገወጥ ገበያ የገነባንባቸው ናቸው፡፡ በሕጋዊ መንገድ ከሚላከው ይልቅ በኮንትሮባንድ የሚሻገረው የበለጠ መሆኑ ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ ለዚህ ችግር ሁነኛ መፍትሐ ያለመበጀት የወጪ ንግድ ምርቶች የሕገወጦች መጠቀሚያ ሆነው ቀጥለዋል፡፡ በእርግጥ ከፀጥታ ችግር አንፃር አንዳንድ የወጪ ንግድ ምርቶች የሚፈለገውን ያህል ለገበያ መቅረብ ባለመቻላቸው የሚያሳደረው ተፅዕኖ ቢኖርም በጥቅል ሲታይ ግን የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ችግር ዘርፉን ከሚመለከተው ፖሊሲ ደካማነት ጋር ማያያዝ ስህተት አይሆንም፡፡ በላኪነት ስም የሚፈጠሩ ውንብድናዎችን የሚገድብ ጥርት ያለ ፖሊሲና ሕግ ያለመኖር ከዚህም በኋላ ብዙ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል፡፡ ከወጪ ንግድ ልናሟላ የሚገባንን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘትም አንችልም፡፡ በየዓመቱ የታቀደውን ያህል ገቢ ላለመገኘቱ ምርቶቻችን ገበያ አጥተው ወይም ዋጋ ወድቆ ብቻ አይደለም። ይህ ቢሆን በኮንትሮባንድ የሚቸበቸቡት ምርቶች ባልኖሩ ነበር፡፡ ስለዚህ አጠቃላይ የወጪ ንግድ ፖሊሲያችን ሊፈተሽ ይገባል፡፡ በተለይ ይጠቅማሉ ተብለው ሥራ ላይ የዋሉ ለምሳሌ የቡና ግብይትን የተመለከቱ መመርያዎች ማንን ጠቀሙ? ምንስ ጉዳት አስከተሉ? ብሎ መጠየቅና የተሻለ መፍትሔ ማፈላለግ ያስፈልጋል፡፡ 

ሌላው ቀርቶ ለወጪ ንግድ የተሰጡ ማበረታቻዎች ምን ውጤት እንዳስገኙ ተፈትሾ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ማበረታቻ የሚሰጠው የተሻለ ውጤት ለማግኘት እስከሆነ ድረስ ውጤቱ ለውጥ ካላመጣ ማበረታቻው ትርጉም የለውም ማለት ነው፡፡ ውጤት የሚያመጣ ከሆነና እንደተባለው የውጭ ምንዛሪ ግኝትን አሳድጎ ከሆነም ተጨማሪ ማበረታቻ ቢሰጥ አግባብ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ይህ እየሆነ ነው? ወይ ካልን የምናገኘው ምላሽ የታሰበው ውጤት እንዳልተሳካ ነው። ስለዚህ የወጪ ንግድ ፖሊሲያችን አገርን ሊጠቅምና ሕገወጥነትን የማያበረታታ ሆኖ እንደ አዲስ ሊቀረጽ ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ተያያዥ ችግሮቹ ወደፊትም ይቀጥላሉ፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት