Wednesday, May 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትየአብዮቱ ያልተዘጉ ዶሴዎች

የአብዮቱ ያልተዘጉ ዶሴዎች

ቀን:

‹ዳኛው ማነው› ሒሳዊ ንባብ – ሐሳብና ምክንያታዊነት በዚያ ትውልድ የፖለቲካ ተዋስኦ

በአፈወርቅ ገ.

የያ ትውልድ የፖለቲካ ጅማሮ ቤሳ ዳራ

- Advertisement -

በኢትዮጵያ ታሪክ 1960ዎቹ አብዮታዊ ዘመን (Game Changer) ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በተለይም በፖለቲካው ረገድ የተካሄዱ እንቅስቃሴዎች ነበር ከተባለ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምህዳር ወደ አዲስና የተለየ ምዕራፍ ያሸጋገረ፣ አልነበረም ከተባለም አዲስ የፖለቲካ ምህዳር የፈጠረና ዘመን አይሽሬ አሻራ ጥሎ ያለፈ መሆኑን ብዙ ድርሳናቶች ተጽፈዋል፡፡ አብዮታዊው ዘመን የ66ቱን አብዮት ካፈነዳ ድፍን ሃምሳ ዓመት ሞልቶታል። ነገር ግን አብዮቱ ግማሽ ክፍለ ዘመን አስቆጥሩ፣ ሦስት ትውልድ አፈራርቆ አሁንም ድረስ በአገሪቱ የፖለቲካ ባህልና ተዋሶ ተፅዕኖው የጠነነ ሆኖ እንደቀጠለ እናገኘዋለን፡፡

በዚያ ነጥብ ቀያሪ አብዮታዊ ዘመን ግንባር ቀደም ተሳታፊ ከነበሩ፣ ጉልህ አስተዋጽኦ ከአደረጉና ትልቅ ሥፍራ ከሚሰጣቸው አካላት ‹የተማሪዎች ንቅናቄ› አንዱ ነበር፡፡ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሪነት በተማሪዎች ንቅናቄና የተማሪዎች ንቅናቄ በወለዳቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ የነበራቸው የዘመኑ አፍላ ወጣቶች፣ ወጣቶችና ጎልማሳዎች በተለመዱ ‹የ1960ዎቹ ትውልድ›፣ በአጭሩ ደግሞ ‹ያ-ትውልድ› በሚል የወል ስያሜ ይጠራሉ፡፡

‹የተማሪዎች ንቅናቄ› በአገር ውስጥም፣ ከአገር ውጭም በነበሩ ተማሪዎችና መምህራን እየተመራ በኢትዮጵያ ዘውዳዊ ሥርዓት እንዲያከትም፣ ንጉሣዊ አገዛዝ እንዲያበቃ፣ ሕዝባዊ መንግሥት እንዲመሠርት በተደረገው ትግል የማይተካ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በድኅረ ዘውዳዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክም አዲስ የፖለቲካ ምኅዳር ለመትከል፣ የፓርቲ ፖለቲካ ለማስረፅ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማስፈን የተማሪዎች ንቅናቄ የመሩ፣ ያስተባበሩ፣ የተሳተፉ የፖለቲካ ድርጅት በመመሥረት የፓርቲ ፖለቲካን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ አስተዋውቀዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም የያ ትውልድ ‹የተማሪዎች ንቅናቄ› ወደ ፖለቲካ ፓርቲ ትግል ከፍ ብሏል፡፡

ከእነዚህ ቀደምት የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ ኢሕአፓ በ1967 (የኢትዮጵያ ሕዝቦች አርነት ድርጅት ኢሕአድ፣ 1964 ዓ.ም.) ተመሥርቷል፡፡ በመቀጠልም መኢሶን (መላው የኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ)፣ ወዝ ሊግና ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ተቋቁመው የፖለቲካ ትግሉን ተቀላቅለዋል፡፡ አቢዮቱን ተከትሎ ከንጉሡ ሥልጣን ነጥቆ በእጁ ያስገባውና አገሪቱን በጊዜያዊነት በመንግሥትነት የሚመራት ወታደራዊ መንግሥት ደርግ በሚባል ኮሚቴ ነበር አገሪቱን የሚመራው፡፡ ደርግ ገና የፓርቲ ቅርፅ አልነበረውም፣ ኢሠፓ የተመሠረተው ሁሉን ፓርቲዎች አባልቶና በልቶ ከጨረሰ ከአሥር ዓመት በኋላ በ1977 ዓ.ም. ነበር፡፡

ከተማሪዎች ንቅናቄ አብራክ የተገኙትን የፖለቲካ ፓርቲዎች የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመተከል፣ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ለማቆም፣ የመድበለ ፓርቲን ፈለግ ለመከተል ጥረት ቢያደርጉም ከወታደራዊ መንግሥት ጋር፣ እርስ በርሳቸውም መስፍን ወልደ ማርያም (ፕሮፌሰር) እንደሚሉት ‹‹ለሥልጣን በመጎምጀት፣ የሥልጣን ሽሚያ ውስጥ በመግባታቸው››፣ የአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሃዲዱን ስቶ አንድ ትውልድን መንገድ ላይ ባሰቀረ የእርስ በርስ መጠፋፋት፣ ‹የቀይና ነጭ ሽብር› ጥቁር ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡፡ ያ ትውልድ ‹‹ቅብዝብዝና ሥልጣን ፈላጊ በመሆናቸው ብቻ ራሳቸውን በጫሩት እሳት ራሳቸው ጠፉ፡፡ የእሳት ራት ሆኑ፤›› የሚል ትችት እንዳለ አምባሳደር ታደለች ኃይለ ሚካኤል ይገልጻሉ፡፡

እንዲህ ዓይነት የ ያትውልድን ተጋድሎ የሚዘክሩ፣ የ1960ዎቹን የፓለቲካ እንቅስቃሴ የሚተርኩ፣ የተማሪውን ንቅናቄ የሚያወሱ በርካታ መጻሕፍት በራሳቸው በየ ያትውልድ መሪዎች፣ አባላት በተለይም ከደርግ መንግሥት መገርሰስ (1983 ዓ.ም.) ማግሥት ጀምሩ እንደ እንጉዳይ ነበር የፈሉት፡፡ ላለፉት አምስት አሠርት ዓመታትም ያለማቋረጥ ለንባብ እየበቁ ያሉ መጻሕፍትን የያትውልድን ‘ገድል’ ወደ ስንክሳርነት (Encyclopedia) ሊያበቁት ምንም አልቀራቸው። ‹‹የ ያትውልድ ታሪክ ተጽፎ የማያልቅ፣ መጽሐፍት የማይበቃው ሆኗል፤›› ቢባል ማጋነን አይሆንም። እስከ ዛሬ የተጻፈው የመጽሐፍት ብዛትና ስብስብ ያለማጋነን ራሱን ችሉ መካከለኛ ቤተ መጽሐፍ ሳይወጣው አይቀርም። የያ ትውልድ፣ የያ ዘመን ታሪክ ይህን ያህል ተከትቦም፣ ከሦስት ተከታታይ ትውልድ በላይ ሆኖትም ‹‹ገና ዝንቡ እሽ አልተባለም›› የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ። ብዙዎች ‹‹ለመሆኑ የአንድ ትውልድ ያውም የአብዮታዊ ዘመን ‘ገድለ’ን በስንት መጽሐፍት ሊካተት ይችላል?›› ብለው ይጠይቃሉ። ‘ዳኛው ማነው’ ከማያባራው በያ ትውልድ ዙሪያ ከተጻፉ መጻሕፍት መካከል በቅርብ ዓመታት ለንባብ የበቃ መጽሐፍ ነው፡፡

ትንሺ ስለ‘ዳኛው ማነው’ መጽሐፍ

‘ዳኛው ማነው’ የ1960ዎቹን ዓ.ም. የተማሪዎችን እንቅስቃሴ፣ የያትውልድ የፖለቲካ ትግል ታሪክ በተለይም የኢሕአፓ የፖለቲካ ትግል ላይ የሚያጠነጥን በ2012 ዓ.ም. ለንባብ የበቃ መጽሐፍ ነው፡፡ ‘የብርሃነ መስቀል ረዳና የታደለች ኃይለ ሚካኤል ሕይወት በኢሕአፓ የትግል ታሪክ’ የሚል ንዑስ ርዕስ የተሰጠው ‘ዳኛው ማነው’ ከ‹አራት አሥርታት ዓመታት› ዝግጅት በኋላ በኢሕአፓ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ በነበራቸው፣ በራሳቸው አገላለጽ “ተዓምር ሊባል በሚችል” በሕይወት የተረፉት፣ አሥራ ሁለት ዓመት ከአምስት ወራት እስራት በኋላ በ1983 ዓ.ም. በተፈቱት አምባሳደር ታደለች ኃይለ ሚካኤል የተጻፈ ነው፡፡

በወቅቱ የፖለቲከኛ እስረኛ የነበሩ ታሳሪዎች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ፣ ችሎት ሳይሰየም እስከ ሞት ቅጣት የሚወሰድባቸውን ዕርምጃ የተመለከቱት ‹‹ለመሆኑ ለዚህ ሁሉ ፍርድ የሚሰጠው ዳኛው ማነው?›› የሚለውን በአዕምሯቸው ሲጉላላ የነበረን ጥያቄ በመወሰድ፣ ‹‹ዳኛው ማነው››ን የመጽሐፋቸውን አርዕስት እንዳደረጉት በመቅድሙ ላይ ገለጸዋል፡፡

የዳኛው ማነው መጽሐፍ ዋናኛ ዓላማ በመጽሐፉ መቅድም ላይ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

፩) ብርሃነ መስቀልን መዘከር እግረ መንገድም፣ የራሳቸውን የትግልና የግል ሕይወት እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን ያለፉበትን ውጣ ውረድ መዳሰስ፣

፪) በወቅቱ የነበረውን ትልቅ ምሥል ማለትም ለሰብዓዊ መብትና የሐሳብ ልዕልና የተደረገን ትግል ማሳየት፣

፫) የማኅበራዊ ፍትሕ ሰፍኖ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በእኩልነት፣ በነፃነት፣ ክብራቸው የሚጠበቅበትን የአስተዳደር ሥርዓት ለመመሥራት የተከፈለን ዋጋ ማሳየት ናቸው፡፡

እነዚህ ዓላማዎችም በአራት ክፍሎች በ21 ምዕራፎች ተቀንብበው በወጉ ተዘርዝረው፣ ተብራርተው፣ በውብ ቋንቋ፣ ፍሰቱን በጠበቀ አተራረክ፣ የግርጌ ማስታወሻዎችን፣ ፎቶዎች፣ አባሪዎችና መጠቆም አካቶ ቀርበዋል፡፡ ክፍልም፣ ምዕራፍም ያልተሰጠው የክፍሎችና ምዕራፎች ቀጣይ የሆነው ‹እንደ መውጫ›› ድኅረ ቃል የተካተተ ሲሆን ማጠቃለያ መልዕክት በማስተላለፍ በ425 ገጾች ‹ዳኛው ማነው› ተቋጭቷል፡፡

‹እንደ መውጫ› የ1960ዎቹን ዓ.ም. የያ ትውልድን፣ የተማሪዎች ንቅናቄን፣ የሦስቱ አውራ ፖለቲካ ድርጅቶች፣ በተለይ ደግሞ የድርጅታቸው ኢሕአፓ ‹ገድል› በአሁናዊ የፖለቲካ ተዋስኦ እንዴት መታየት እንዳለበት፣ የቀደመው የፖለቲካ ተዋስኦ ምን እንዳበረከተ፣ ምን ትምህርት መወሰድ እንዳለበት፣ ጠቅለል ያለ ሐሳብና አስተያየት የቀረበበት ክፍል ነው፡፡ በራስ ዳኝነት በመሠልጠን፣ በወቃሽ ዳኝነት በተማሪዎች ንቅናቄ ላይ ፍርደ ገምድልነትን በመስጠት መስዋዕት የሆኑ ወጣቶች ገድል ከማራከስ ባለፈ ‹‹እንደ አገር ከታሪካችን ሒደት አግባብነት ያለው ትምህርት እንዳንወስድ ደንቃራ የሆነብንን፣ እግር ከወርች አስሮ የያዘንንስ ምንድን ይሆን? ብለን መመርመር፣ ካሳለፍነው የትግል ውጣ ውረድ ጠንካራውን ከደካማው፣ መጥፎውን ከጥሩው አበጥረን በማውጣት በድፍረት ልንወያይ ይገባል፤›› የሚሉ መልዕክቶች ጸሐፊው አሥፍረዋል፡፡

‹‹በሰከን መንፈስ፣ ዕውቀትና ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ውይይትና መደማመጥ ግድ ይላል፣ ብሔራዊ ተግባቦት (ብሔራዊ መግባባት) ለመፍጠር መትጋት ያስፈልጋል፣ የመደማመጥ ችግራችን መፍትሔያችን ወደ ኃይል ዕርምጃ እንዲያጋድለ አድርጓል፤›› የሚሉ ጥቅል አስተያየቶችን፣ ‹‹እንደ መውጫ›› ላይ ተካተዋል፡፡ በተለይ ሐሳብን አስመልክተው ያቀረቡት አስተያየት ሚዛን የሚደፋ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

የአንድ ግለሰብ የሐሳብ ልዕልና አለመቀበል፣ ቢያንስ ለማስተናገድ አለመሞከር ከስህተቶች በላይ ነው፡፡ ስህተትን አግዝፎ በአስተሳሰብ ላይ የነበረን ልዩነት ወደ ሰብዕና በማውረድ በማንነት፣ በብሔር፣ በጎሳና በሃይማኖት በማተኮር ከስህተት በላይ ስህተት በመፈጸም ምንም ትምህርት ሆነ ዳኝነት ሊያገኝ ወደ የማይቻልበት የቁልቁለት ጉዞ እየሄድን ነው፡፡

አንድ ሐሳብ ተነስቶ ከሌላ ሐሳብ ጋር ሲፋጭ ነው በአስተሳሰብ ከፍታ የሚገኘው፡፡ አስተሳሰብ ደግሞ ድንበር የለውም፡፡ የተማሪዎችም ሆነ የምሁሩ፣ የደራሲውም ሆነ የገጣሚው አስተሳሰብ በሚሰነዘርበት ጊዜ ሐሳብ እንጂ ጦር የሚያማዝዝ መሆን የለበትም፡፡ ሐሳብን በሐሳብ መርታት እንጂ ማፈን መፍትሔ አያመጣም፡፡ የታፈነም ጊዜውን ጠብቆ መፈንዳቱ አይቀርም፡፡ ሐሳብን መፍራት አላዋቂነት ነው፡፡

ይህን ሒሳዊ ንባብ ለማዘጋጀት ትልቁን አስተዋጽኦ ያበረከተው ይኼው የታደለች ሐሳብ ነው፡፡ የአገራችን የፖለቲካ ተዋስኦ ከፖለቲካ ኮሙዩኒኬሽን (Political Communication)፣ ከሚዲያና ጋዜጠኝነት በተለይም ከመግለጽ ነፃነት (Freedom of Expression)፣ ከንግግር ነፃነት (Freedom of Speech) እና ከፕሬስ ነፃነት (Press Freedom) አንፃር ለመገምገም በግሌ ብዙ ጥረቶችን አደርግ ስለነበር፣ እስካሁኑ ትውልድ የተዛመተውን የያ ትውልድን የፖለቲካ ተዋስኦ በእነዚሁ ዕሳቤዎችና ነፃነቶች ከ‹‹ዳኛው ማነው›› አንፃር ሒሳዊ ቅኝት ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮልኛል፡፡

እዚህ ላይ አንባቢያን ልብ እንዲሉልኝ የምፈልገው ነገር ይህ ቁንፅል ሒሳዊ ንባብ ‹‹የያ ትውልድን ገድል ለማራከስ›› አሊያም ‹‹የቀደመውን የፖለቲካ ተዋስኦ የትውልዱ መጨቃጨቂያ እንዳይሆን የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፤›› ሲሉ አምባሳደር ታደለች መጽሐፋቸውን የዘጉበትን የተማፅኖ ዓረፍተ ነገር በመጋፋትም እንዳልሆነ ከወዲሁ ማሳወቅ እወዳለሁ፡፡ ይልቁንም ጸሐፊዋ በመጽሐፉ መውጫ ላይ ‹‹ምን እናድርግ?›› ሲሉ ያቀረቡትን ጥሪ በመቀበል ጉድለቶችን ለመሙላት ባለኝ መረዳት ልክ እንደ አቅሜ ሐሳቦችን ለማውጣት በማለም መሆኑ ይያዝልኝ፡፡    

ሐሳብና ምክንያታዊነት በያ ትውልድ የፖለቲካ ተዋስኦ

እዚህ ላይ አምርረንና ደፈር ብለን በ1960ዎቹ ዓ.ም. የተደረገውን የፓርቲ ፖለቲካ፣ የፖለቲካ ድርጅት እንቅስቃሴ በታደለች ቋንቋ ‘የፖለቲካ ተዋስኦ’ (Political Discourse) በተመለከተ ሊነሱ የሚገቡ ጥያቄዎችን ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ዕውን የያ ትውልድ የፓርቲ ፖለቲካ ትግል ሐሳብ የወለደው፣ ምክንያታዊነት የሚመራው፣ ለግልጽ ውይይትና ንግግር የሚገዛ፣ የሐሳብ ልዕልና ላይ መሠረቱን የጣለ፣ የትግል ሥልቱም ፍፁም ሰላማዊ ትግል ነበር ያካሄደው? ተገፍቶስ ነው ወደ ትጥቅ ትግል የገባው?›› ይህ ጥያቄ በጥቂት ቁንጮ አመራሮች ላይ ብቻ ተወስኖ የቀረበ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በወቅቱ ገፊ ተገፊም፣ አሳዳጅም ተሳዳጅም ለነበሩ ሁሉ በጥቅል የተሰነዘረ ጥያቄ ነው፡፡

እንደ እኔ መልሱ “አይደለም!” ነው። ምክንያት የምላቸውን ከማቅረቤ በፊት ግን አሁንም አንድ ነገር ግልጽ ላድርግ፡፡ በወቅቱ የነበረው የተማሪዎች ንቅናቄ ያደረገው የፖለቲካ ትግልና የተማሪዎች ንቅናቄ የወለዳቸው የፓርቲ ፖለቲካ ትግሎች ተለይተው ሊታዩ ይገባል የሚል አቋም አለኝ፡፡

የተማሪዎች ንቅናቄ ፍፁም ሰላማዊ የትግል ሥልት ነበር ያራመደው፡፡ ተሜ ሐሳብን ታጥቆ፣ መፈክር አንግቦ፣ መፈክሩን እያሰማ ሰላማዊ ሠልፍ የሚወጣ፣ ባህል ማዕከል እየተሰባሰበ ንጉሡና ባለሟሎቻቸው በእንግድነት በተገኙበት በግጥም ተቃውሞውን የሚያሰማ፣ ‹ታገል (ትግላችን)› ብሎ በሰየማት መጽሔት ሐሳቡን እያሰፈረ፣ ባስ ሲልበት ትምህርት የማቆም አድማ እየመታ ነበር የንጉሡን ሥርዓት በመቃወም፣ ዘውዳዊው አገዛዝ እንዲወገድ ውጤታማ ትግል ያደረገው፡፡ ከድኅረ ዘውዳዊ አገዛዝ የተማሪው ንቅናቄ ወደ የተደራጀ፣ የነቃ፣ የታጠቀ የፓርቲ ፖለቲካ ትግል ያስፈልጋል በሚል ሲሸጋገር ግን ፍፁም ሰላማዊ የነበረውን ሐሳብና ምክንያት የሚመራውን በድርጅቶች ተወስኖ ሌላ መልክ ሊይዝ ችሏል፡፡ ይህ ሒሳዊ ንባብ የሚያነጣጥረው የተማሪዎች ንቃናቄ ላይ አይደለም፣ ተማሪዎች የእኔ በሚሉት የፖለቲካ ድርጅት ታቅፈውና ተጠልለው ባደረጉት የፓርቲ ፖለቲካ ትግል ላይ ነው፡፡ የአብዮቱ አንድ ዶሴ የሆነውን የያ ትውልድ የፓርቲ ፖለቲካ ትግል በመምዘዝ ‹‹ከዳኛው ማነው›› አንፃር ሒሳዊ ቅኝት ለማድረግ እሞክራለሁ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመሠራረትከሰላማዊ ትግል ፈለግ መውጣትየብዙኃን ድርጅቶችን (የዴሞክራሲ ተቋማት) የነበራቸው ግንኙነት እንደ ማንፀሪያ በመጠቀም ሂሳዊ ንባብ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡   

የፖለቲካ ፓርቲዎች አመሠራረት “የአልጄሪያውና የአውሮፓው ቡድን ቅራኔ” 

በ1960ዎቹ ዓ.ም. የተደረገው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምሥረታ ‘ተፈጥሯዊ’ ሒደቱን ጠብቆ አልነበረም ከተማሪዎች ንቅናቄ አብራክ ተወልዶ እንዲደራጁ የተደረጉት፡፡ የኢትዮጵያ የተማሪዎች ንቅናቄ በፖለቲካ ፓርቲ ድርጅት አለመወከሉ በአልጄሪያ ከከተሙ ከመላው ዓለም የመጡ የነፃነት ንቅናቄዎች ጋር ለሚያደርገው ውይይት ያሳደረበትን አሉታዊ ተፅዕኖ ትምህርት በመውሰድ ነበር የተደራጀ የፖለቲካ ኃይል፣ የፖለቲካ የፓርቲ ምሥረታ የግድ የሆነው፡፡ ይሁን እንጂ ድርጅት ምሥረታ፣ (የፖለቲካ ፓርቲ ምሥረታ) በአገር ቤት የነበረውን የተማሪዎች ንቅናቄን የመሩ ወደ አልጄሪያ በስደት የገቡ ‘የአልጄሪያው ቡድን’ የሚባለውና በአውሮፓ የነበረውን የተማሪዎችን ንቃናቄ ሲመሩ የነበሩ ‘የአውሮፓው ቡድን’ መካከል የድርጅት ምሥረታ ላይ መግባባት አልተቻለም፡፡ ይህም በተማሪዎች ንቅናቄ ቀጣይ ጉዞ ላይ የአልጄሪያውና የአውሮፓው ቡድን ቅራኔ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል፡፡ ቅራኔውም ተራ ቅራኔ ሳይሆን “የሁለት ትውልድ ቅራኔ” መልክ ያለው ነበር፡፡

እንግዲህ ይህን የመሰለ ከፍተኛ ቅራኔ በወጉ ሳይፈቱ፣ ቢያንስ ወደ ‘አንድ ትውልድ ቅራኔዎች’ ዝቅ እንዲል የረባ ውይይትና ክርክር ሳያደርጉ፣ እንዲያውም እርስ በርስ እየተናቆሩ፣ እየተማሙ፣ አሉባልታ እያነፈሱ ቅራኔዎቻቸው ይበልጡኑ እንደተካረሩ ነበር ወደ የፖለቲካ ድርጅት መመሥረት ያመሩት፡፡ እነዚሁ የተቃቃሩ ቡድኖችም ኢሕአፓ፣ መኢሶንና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች በማቋቋም የግል የፖለቲካ ትግላቸውን በየፊናቸው ቀጥለዋል፡፡ የኋላ ኋላ በመሀላቸው የነበረው ቅራኔ ወደ የ‹‹ለሁለተኛ ደረጃ ቅራኔያዎች›› አድጎ አንደኛው ሌላኛውን እስከ ማሳደድ፣ እርሰ በርስ እስከ መገዳደል እንዲበቁ አድርጓቸዋል፡፡

በበኩሌ ምን ልብ ወለድ ቢሆን የያ ትውልድን ‹ገድል› ከሚወሱ መጻሕፍት የሆነውን ሁሉ በአንፃራዊ ገለልተኝነት ፍንትው አድርጎ የሚያሳየኝ የ ያትውልድ አባል የነበረው የደራሲ አዳም ረታ ሥራዎች ቀዳሚ ምርጫዬ ናቸው። ‘ይወስዳል መንገድ፣ ያመጣል መንገድ’፣ ‘እቴሜቴ የሎሚ ሽታ’፣ ‘መረቅ’ እና ‘የስንብት ቀለማት’ በዋናነት የያ ትውልድን፣ የአብዮቱን ዘመን ‘ሩካቤ ፖለቲካ’ (የፖለቲካ ተራካቦ) ከእነ መንፈሱ፣ ከእነ ጅምሱ እንደ መስታወት ወለል አድርገው የሚያሳዩኝ የአዳም ሥራዎች ናቸው።

ዴቪድ ሸልድ በ‹Reality Hunger: A Manifesto› መጽሐፉ በልብ ወለድና ኢልብ ወለድ ያለውን ድንበር የጣሰበት ሐሳብ በመግዛት ለኢ ልብወለዱ ‹ዳኛው ማነው› ከልብ ወለዱ ‹የስንብት ቀለማት› አንድ ማሳያ ልምዘዝ፡፡ አዳም ረታ የያ ትውልድ ወካይ መሪ ገጸ ባህሪ አድርጎ በሳለው ምኒልክ በኩል ያ ትውልድ የሚያወራውን፣ የሚወራለትን ያህል ‹‹በነጠረ ሐሳብ፣ በጠራ መስመር፣ ዓላማና ግቡን ለይቶ ይንቀሳቀስ ነበር፤›› የሚባለውን ትርክት ፉርሽ በሚያደርግ መልኩ ይህን ይለናል፡፡

ምናልባት በትክክል ምን እንደሚፈልግ፣ የሚፈልገውንም ነገር በምን ዓይነት መንገድ እንደሚያገኝ ያልገባው ትውልድ ውስጥ ነበርኩ፡፡ ወይም [በትክክል] ምን እንደሚፈልግ ያወቀ፣ ግን በምን ዓይነት መንገድ መፈለግ እንዳለበት ያልተረዳ ትውልድ ውስጥ ነበርኩ፡፡ ወይም ምን እንደሚፈልግ ያወቀ ግን ከማን ጋር እንደሚፈልግ ያልገባው ትውልድ ውስጥ ነበርኩ፡፡

እርግጥ አዳም ከኅልዮ መጽሔት (2007)ዓ.ም. ጋር ባደረገው ዘለግ ያለ ቃለ መጠይቅ «[ያ ትውልድ] ‹የተታለለ ትውልድ› ነበር፣ ነገር ግን ተታለልኩ ብሎ ማንም አይነግርህም፤» የሚል መረር ያለ አስተያየትም ሰጥቷል። አዳም ረታ አባል የነበረበትን የያ ትውልድን የፖለቲካ ተዋስኦ በተመሳሳይ በእቴሜቴ ሎሚ ሽታ መጽሐፉም በመስኮት ገረሱ በኩል፣ ‘የእና[ቸ]ንፋለን–እና[ሸ]ንፋለን’ የነበረውን የፖለቲካ አታካሮ በመንቀስ በኃይለኛ ቃላት እንዲህ ሲል ይወረፋቸው፡-

በዚያ ጊዜ የሚሠራውን ፖለቲካ ስሙን ‹መቸሻቸሽ› ብሎት ነበር፡፡ ‹ቸ› እና ‹ሸ› በተባሉ ሆሄያት (እናቸንፋለን–እናሸንፋለን) እንደሚጋጩት ዓይነት፡፡ አንዳንዴ የግራኞች የቁጩ ልፊያ ይለዋል፡፡ አንድ ተመሳሳይ ሐሳብ አሠልፈው ግን እርስ በርስ የሚደባደቡትን ቡድኖች የሚጠራበት ስም ነው፡፡ ግለሰቦችን ደግሞ ‹ችሹዎች› ይላቸዋል፡፡

ዕውቀትን ሳይሆን፣ ሴራና ስም ማጥፋትን ንቃትና ‘ስማርትነት’ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ መረጃ ማሰባሰቢያ ሥልታቸው ኅቡና ስለላ ነው፡፡ ሳይንሳዊ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ትክክለኛው በግልጽ፣ ምስክር አይን ሥር በመረጃ የቆመ ሳይንስ ለቀጣፊ ምላሳቸው ይከብዳቸዋል፡፡

የሐሳብ ጥራትና ተጨባጭ ልዩነት ሲጠፋ ጅሎች በተራ ሆሄ ይጣላሉ፡፡ እጃቸው ላይ የሚቀረው ሊደነቁበት የሚፈልጉት ተራ ሞት ነው፡፡ ይኼን ከርካሳ ነገር ትግል እንድንልላቸውና እንደ መለካም ነገር በታሪክ እንድንመዘግብላቸው ይፈልጋሉ፡፡ ሱሚ ነው፡፡ በሚያዋጣችሁ በዚያው በፊንታችሁ ቀጥሉ፡፡ ቢያውቁም ባያውቁም ለኢትዮጵያ ከባድ መቃብር በመቆፈር ላይ ናቸው፡፡ የምንገባበት ግን ሁላችን ነን፡፡ ከቴም ሥር ነቀል አይ መቸሻቸሽ፡፡  

ይህን በመሰለ ውዥንብር፣ በተምታታ ዕይታ፣ ባልጠራ ዕሳቤ፣ ባልዳበረ አስተሳሰብ ውስጥ ሆነው ነበር የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅት መሥርተው በፓርቲ ፖለቲካ የውስጥም፣ የውጭም ግንኙነት ሲናጡ ያማሩት፡፡ ጊዜ ሰጠው ስክን ብለው ባለማሰባቸው፣ ቅራኔያቸውን መፍታት ባለመቻላቸው ሁለት የፖለቲካ ድርጅት መሠረቱ እንጂ፣ የኢሕአፓና የመኢሶን የፖለቲካ ርዕዮት ዓለም ይህ ነው የሚባል አንድ እንኳን መሠረታዊ ልዩነት ያልነበረው፣ ይልቁንም በተወራራሽና ተዛማጅ ፕሮግራሞች የሚተሳሰሩ የአንድ ሁለት፣ የሁለት አንድ ርዕዮተ ዓለም ነው የነበራቸው፡፡ እንዲያውም ብርሃነ መስቀል ‹‹መኢሶን ከእኛ [ከኢሕአፓ] ጋር የሚመሳሰል የፖለቲካ ፕሮግራም ስላለው እንደ ጠላት ልንቆጥረው አይገባም›› ብለሃል በሚል ነበር ክስ የተመሠረተበት፡፡ ኢሕአፓና መኢሶን ደርግን በተመለከተ እንጂ ልዩነታቸው ለሁለት ፓርቲነት ቀርቶ በአንድ ፓርቲ ለመደራጀትም ያን ያህል ቁመናው አልነበራቸውም፡፡

ፍራንሲስ ካሱማ (2000) ለዶክትሬቴ ማሟያቸው ‹ፕሬስና የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ በአፍሪካ› (The Press and Multiparty Politics in Africa) ባካሄዱት ምርምር፣ ይህን ሐሳብ የሚያጠናክር የጥናት ግኝት አሥፍረዋል፡፡ ‹‹አፍሪካ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ ሊባሉ የሚችሉ ፓርቲዎች የሉም፣ አንጃዎች ነው ያሉት፡፡ አንጃዎች ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲ መሆን አይችሉም (ትርጉም በእኔ)፡፡››

ልብ ብሎ ፍራንሲስ ካሱማ በጥናቱ ያካተቷቸው በ1990ዎች ዓ.ም. (1980ዎች) ዓ.ም. የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ነው፡፡ ምንም እንኳን በጥናቱ ባይካተቱም ኢሕአዴግንና መሰል ፓርቲዎችን የሚመለከት ነበር፡፡ ጌታቸውና ብርሃነ መስቀል (ሀ እና ለ) በአንደኝነት ተፈርጀው በክሊኩ ከፓርቲው ቢባረሩም፣ ኢሕአፓም ሆነ መኢሶን ለአንጃ እንጂ ለፖለቲካ ፓርቲ ቅርበት አልነበራቸውም፡፡ ደርግም ቢሆን በኋላ ኢሠፓን ሲመሠርት የፖለቲካ ፓርቲ መሰለ እንጂ ኮሚቴ ቢሆንም ለአንጃ የቀረበ ነበር፡፡

ከዚህ አንፃር ከገመገምነው ከወታደራዊ አብዮታዊ ደርግ በኋላ ኢሠፓ አምባገነናዊና አፋኝ መንግሥት ከነበረው በሐሳብና ምክንያታዊነት በቅጡ ያልታሸ የፖለቲካ ፈለግ የኢሕአፓ፣ የመኢሶንና የሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ሐሳብ የሠለጠነበት፣ ምክንያታዊ የነበረው እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ ይህም ልዩነቱ ደርግ ከወታደራዊ ሥርዓት የተነሳ፣ ኢሕአፓ፣ መኢሶንና ሌሎች ፓርቲዎች ደግሞ ከተማሪዎች ንቅናቄ የተነሱ መሆናቸው ነበር፡፡

በጠቅላላው የፓርቲ ፖለቲካ ከላይ እንደተገለጸው በሐሳብ ፍጭት፣ በተራዘመ ውይይትና ሙግት ሳይደገፍ በአጭር ተመልካችነት መመሥረታቸው ውጫዊ ከሆነው ፍፁም ጨካኝና ፍርደ ገምድል የወታደራዊው መንግሥት ዳኝነት ባሻገር፣ በሒደት በውስጣቸው የተፈጠረውን ልዩነት መፍታት ተስኖት የፖለቲካ ፓርቲዎች ዛለቂ ሳይሆኑ በአጭር ተቀጭተው እንዲቀሩ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል፡፡ ከአብዮቱ ማግሥት እስካሁን ድረስ ገዥ ፓርቲ፣ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች እየተባሉ ለስሙ ይጠሩ እንጂ ለአቅመ ፖለቲካ ፓርቲነት ያልደረሱ፣ በተግባር የአንጃነት ባህሪን የተላበሱ፣ የመድበለ ፖለቲካ ሥርዓት የማይመጥኑ ሆነው እናገኛቸዋለም።

ከሰላማዊ ትግል ፈለግ መውጣት “የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ያሸንፋል”

ኢሕአፓ፣ መኢሶና ሌሎች ፓርቲዎች በተማሪዎች ንቅናቄ የተንፀባረቀውን ‹‹የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ያሸንፋል›› በሚል የወል መፈክር በመመራት፣ በተለይ የታጠቀውን ደርግ ለማግደርደርና ‹የታጠቀ› የሚለውን ለማሟላት ሰላማዊ የፖለቲካ ሥልት በመተው ወደ ‹ጠመንጃ ነካሽነት፣ አፍሙዝ አምላኪነት፣ ወታደራዊ ኃይል ሙጥኝ ማለት፤›› ተሻግረው ነበር፡፡ ኢሕአፓ በግልጽ ወታደራዊ ክንፍ አደራጅቶ በገጠር ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ በከተማም በተለይ በአዲስ አበባ የህቡዕ የትጥቅ ትግል ያደርግ ነበር፡፡ ኢሕአፓ ውስጥ ለተፈጠረው ልዩነት ቀዳሚው ምክንያት ይኸው የትጥቅ ትግል በምን መልኩ ይካሄድ የሚለው ጉዳይ ነበር፡፡

ኢሕአፓም ሆነ መኢሶን ይህንን ፍላጎታቸውን ለማሳካት በየፊናቸው አገሪቱን ከሚመራት ወታደራዊ መንግሥት ጋር በትብብር ለመሥራት መሯሯጥ ሲጀምሩ ነበር ከሰላማዊ ትግል መንገድ ያፈነገጡት፡፡ በተለይ ሥልጣን በእጁ ካስገባውና ከሚቆጣጠረው አገሪቱንም ከሚያስተዳድረው አብዮታዊ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ደርግ ጋር ለመሥራት፣ ቁንጮ ከሚባሉት ተራማጁን እየመረጡ የውስጥ መስመር በመዘርጋት የየግል እንቅስቃሴዎችን ያደርጉ ነበር፡፡ መኢሶን ደግሞ ደርግ የጠራውን የኅብረት ጥሪ በመቀበል በይፋ ከደርግ ጋር ቤተ መንግሥት ተጠቃሎ ገብቶ ነበር፡፡

ኢሕአፓ (በዘርዑ ክኸሸንና በተስፋዬ ደበሳይ) በኩል የወቅቱ ተራማጅ የደርግ ሊቀመንበር ከነበሩት ተፈሪ በንቲ ጋር የውስጥ ለውስጥ ሚስጥራዊ ግንኙነት ሲያደርጉ ቢቆዩም፣ በደርግ ዕርምጃ ሲወሰድባቸው ግንኙነቱ ተቋርጧል፡፡ ደርግም ‹‹ለምሳ ያሰቡንን ቁርስ አደረግናቸው›› በማለት ‹‹አብዮቱም ከመከላከል ወደ ማጥቃት›› መለወጡን በማወጅ ኢሕአፓን ወደ መምታት ተመልሷል፡፡

ይህ የሚያሳየው በፖለቲካ ድርጅት ትግል ለማድረግ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲመሠረቱ፣ በተለይ ኢሕአፓ የትግል መስመራቸውን ‹ሰላማዊ ትግል አሊያም የትጥቅ ትግል› ለማድረግ ከጅምሩ ተስማምተው አለመጀመራቸውን የሚያመላክት ነው፡፡ በተለይ የኢሕአፓ እንቅስቃሴ ሲቀዘቅዝ ሰላማዊ፣ ሲሞቅ የትጥቅ ትግልን ያራምድ የነበረ ሲሆን የማታ ማታ ይህ ሥልቱ ፓርቲው ከሁለት አንድ ያጣ አድርጎታል፡፡ ኢሕአፓ ከተሰነጠቀ በኋላ ‹ክሊኩ› በከተማ የትጥቅ ትግል፣ የእርምት ቡድኑ ደግሞ አዳነች እንደጻፈችው መርሐ ቤቴ ላይ ‘ዱር ቤቴ’ ብለው ወደ ትጥቅ ትግል ገብተው ነበር፡፡

መኢሶን ሰላማዊ ትግልን ሙጥኝ ያለና እንደ ኢሕአፓ ወታደራዊ ክንፍ ያላደራጀ ቢሆንም፣ ‹ሒሳዊ ድጋፍ› በሚል ከወታደራዊ መንግሥት ደርግ ጋር በመሥራት ወታደራዊን ኃይል ለማዘዝና ለመምራት ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ የቀይ ሽብር፣ የአዲስ አበባን አሰሳ እንደ ነገዴ ጎበዜ ያሉ የመኢሶን አመራሮች ሲመሩት ነበር፡፡ ደርግ ‹‹የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ያሸንፋል፤›› የሚለውን መፈክር ከመኢሶን በመውረስ ይጠቀምበት የነበረ ሲሆን፣ በአስተማማኝነት የታጠቀ ወታደራዊ ኃይል ስለነበረው የነቁና የተደራጁ ግን ደግሞ ያልታጠቁትን ፓርቲዎች ቅርጥፍ አድርጎ በመብላት እንዲከስሙ አድርጓል፡፡ የታጠቀው አሸንፏል!  

የብዙኃን ድርጅቶችን (የዴሞክራሲ ተቋማት) የነበራቸው ግንኙነት

ደርግ፣ መኢሶንም ሆነ ኢሕአፓ በወቅቱ የነበሩ የብዙኃን ድርጅቶችን (የዴሞክራሲ ተቋማትን) በየራሳቸው ተፅዕኖ ሥር ለማድረግ ሁሉም ትንቅንቅ የጀመሩበት ጊዜ ነበር 1960ዎች፡፡ እነሱ (ፓርቲዎች) የሚቆጣጠሯቸው ካልሆነ በስተቀር እንደ ሕዝብ ቤቶች ሆኑ ወጣቶች፣ ላባደሮች ሆኑ መምህራን ነፃ ሆነው እንዲደራጁ ማናቸውም አልፈቀዱም፡፡ በተፈጠረው ልዩነት ምክንያት መወያየት ሆነ መቻቻል ጠፍቶ፣ በሐሳባቸው የተለያዩትን የብዙኃን ድርጅቶች አባላት በጠላትነት መፈረጅ የተጀመረበት ጊዜ ነበር፡፡

በ1968 ዓ.ም. የተመሠረተው የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር አንድ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር ከተመሠረተ በኋላ በሕዝብ ድርጅት ጽሕፈት ቤት (ደርግ የመሠረተው መኢሶን በበላይነት የሚቆጣጠረው ነበር) ሥር ሆኖ ይደራጅ ወይስ ራሱን ችሎ በነፃነት የማንም የፖለቲካ ድርጅት ተቀጥላ ሳይሆን ይቋቋም የሚለው መከራከሪያ ነበር፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሴቶች ማኅበራት የመኢሶንና የኢሕአፓ ደጋፊዎች በሚል ተከፋፍለዋል፡፡ ‹‹የአመራሩን ቦታ የሚይዙት ‹ማርክሲዚም ሌኒኒዝም› የተቀበሉ ሴቶች ብቻ ናቸው›› የሚለው አንቀጽ በማኅበሩ መተዳደሪያ ሕገ ደንብ ተካቶ ነበር (አብዮታዊ ዴሞክራሲን የተቀበለ፣ መደመርን የተቀበለ የዚያ ዘመን ክፉ ውርስ መሆናቸው ልብ ያለው ልብ ይለዋል)፡፡    

ሌላው ማሳያ ሚዲያዎች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ 1960ዎቹ ‹የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ወርቃማ ዘመን› ተብሎ ይጠራል፡፡ በተለይ ከ1966 እስከ 1968 ዓ.ም. በአዲስ ዘመን፣ በኢትዮጵያን ሔራልድ የተለያዩ ጽሑፎችን ያለ ልዩነት፣ ያለ አድልኦ ሁሉንም የተማሪዎች ንቅናቄ ጉምቱ መሪዎችን፣ በኋላም የፖለቲካ ፓርቲ አመራር የሆኑትን ሐሳባቸውን በማስተናገድ ስለለውጡም ሆነ የአብዮት እንቅስቃሴ የሠለጠነ ሙግት ተደርጎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ቀስ በቀስ ደርግ የኅትመት ሚዲያውን በተለይ ደግሞ የብሮድካስት ሚዲያውን (የኢትዮጵያን ሬዲዮና ቴሌቪዥን) ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ወደ ፕሮፓጋንዳ መንዣ መሣሪያነት ቀይሯቸዋል፡፡

ተስፋ ሰጪ አጀማመር የነበራቸው ሚዲያዎችን ደርግ በጥርነፋ ወደ ፍፁም የፕሮፓጋንዳ ልሳንነት እንዲቀይራቸው የፓርቲዎች ሚና መዘንጋት የለበትም፡፡ ለአብነት እንኳን ብርሃነ መስቀል በፓርቲው ከቀረበበት አንዱ ክስ ለፓርቲው ሳያሳውቅ የአዲስ ዘመን አርታኢ የነበረውን ብርሃኑ ዘሪሁንን በማሳመን በአዲስ ዘመን ርዕሰ አንቀጽ ላይ፣ የራሱን ጽሑፍ የጋዜጣው (የመንግሥት) አቋም በማስመሰል እንዲወጣ በማድረጉ ነበር፡፡ ብርሃነ መስቀል በሰጠው ግለ ሒስ ማድረጉን ለፓርቲው አምኗል፡፡ የብርሃነ መስቀል ድርጊት (ሌሎችም ይኖራሉ) ለአምባገነኑ ደርግ የማስጠንቀቂያ ደውል ሆኖለት ከዚያ በኋላ ሚዲያዎች ‹ማርክሲዝም ሌኒኒዝም› በተቀበሉ፣ የኢሠፓ አባል በሆኑ ታማኝ ካድሬዎች እንዲመሩ በማድረግ የፕሮፓጋንዳ መንዣ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በተማሪዎች ንቅናቄ የምትቆምለት፣ የምትወግንለት የፖለቲካ ድርጅት ያልነበራት የታገል መጽሔት የፓርቲ ምሥረታን ተከትሎ የየፓርቲው ልሳን ለማድረግ በነበረው ሽኩቻ የቀድሞ የሐሳብ መድረክነት ጥንካሬዋን ይዛ መቀጠል ሳትችል ቀርታለች፡፡

ፓርቲዎች በመሠረቷቸው የፓርቲ ልሳን ሚዲያዎች ይወጡ የነበሩ የፕሮፓጋንዳ ጽሑፎች በብሽሽቅ፣ በስድብና በጥላቻ የታጨቁ፣ በጠላትነት መፈራረጅ የበዛበት እንጂ በሐሳብ ላይ የተመረኮዘና ለሥልጡን የፓርቲ ፖለቲካ የሚደረግ ጤናማ ሙግት አልነበረም፡፡ ‹‹አሻጥረኛ ነጋዴ፣ አድሃሪ ፊውዳል፣ አናርኪስት፣ ፈርጣጭ፣ ገንጣይ፣ አስገንጣይ፣ ጠመንጃ ነካሾች (ፎካይስቶች)፣ ወዘተ.›› አንዱ ለአንደኛው የሚሰጠው ለፖለቲካ ፋይዳ የሌላቸው ስሞች ነበሩ፡፡ ደርግም ይኼንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በቁጥጥሩ ሥር የነበሩ የሕዝብ ሚዲያዎችን በጠቅላላ ለፕሮፓጋንዳ መሣሪያነት በማዋል፣ ‹‹ነፃ ዕርምጃ የተወሰደባቸው፣ የተደመሰሱ›› እያለ በግፍ የሚረሽናቸውን ስም ዝርዝር በሬዲዮና በቴሌቪዥን በውድቅት ሌሊት ሳይቀር ‹‹የፍየል ወጠጤ ልቡ ያበጠበት ና እንዋጋ ብሎ ለነብር ላከበት››ን እያዘፈነ፣ ለሕዝቡ እንዲሠራጭ በማድረግ ሞገዱን በሙሉ ቀይ ደም አለበሰው፡፡   

ወራሪው ጣሊያ በአምስት ዓመት (ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም.) ቆይታው የቅኝ ግዛቱን ለማፅናት ካደረገው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በኋላ ትልቁ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የተመዘገበው በዚሁ የደርግ፣ የኢሕአፓና የመኢሶን የሚዲያ ግብግብ ነበር፡፡ ሁሉም ያደርጉት የነበረው ፕሮፓጋንዳ ከፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ እጅጉን ያፈነገጠ ነበር፡፡ የፕሮፓጋዳ ዘመቻ ሰለባ የነበረው የያ ትውልድ ‹‹የደም ህዋሳቶቹ ሦስት ሆነው ነበር ቀይ፣ ነጭና ጥላቻ፡፡ በፕሮፓጋንዳ ሦስተኛ ተፈጥሮ ተሰጠው፤›› ሲል አዳም ረታ በ‹ይወስዳል መንገድ፣ ያመጣል መንገድ› መጽሐፉ ገልጾታል፡፡ የዚህ ቅጥ ያጣና መረን የለቀቀ የፕሮፓጋንዳ ጥዝጠዛ በደም መራኮትን አስከተለ፡፡

ዛሬ ሚዲያዎቻችን በልቅ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ለዜጎች ደኅንነት፣ ለአገር ህልውና ሥጋት የሆኑት የያ ትውልድ ክፉ ውርስ ተጣብቷቸው ነው፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚዲያን ሚና በፕሮፓጋንዳነት እንዲወሰን በማድረጋቸው ሚዲያው ሊጫወተው የሚችለውን የሐሳብ መድረክነት፣ የሰከነ ውይይት መድረክነት ከኢትዮጵያ ሚዲያ ታሪክ እንደ ተወርዋሪ ኮኮብ ብልጭ ብሎ ድርግም እንዲል የበኩላቸውን አሉታዊ ሚና ተጫውተዋል፡፡

ፓርቲዎች በሴቶች ማኅበር፣ በሕዝብ ሚዲያዎችና በሌሎች የሕዝብ ድርጅቶች ያራምዱት የነበረ የቁጥጥር ፍላጎትና ሽኩቻ የዴሞክራሲ ተቋማት በፖለቲካ ወገንተኝነት እንዲታጠሩ፣ በድርጅት ፍላጎት እንዲወሰኑ ያደረገ ክፉ ውርስ ሆኖ ዛሬም የረቡ የዴሞክራሲ ተቋማት የሉንም፡፡      

ከላይ ያ ትውልድ በፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራጅቶ ይከውነው የነበረውን የፓርቲ ፖለቲካ ትግል እንዴት ባለ የፖለቲካ ተዋስኦ ሲያካሂድ እንደነበር ከሞላ ጎደል ከተቀመጡት ሦስት ማንፃሪያዎች አንፃር ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ በዚህ ምልከታ መሠረት የ1960ዎቹ ዓ.ም. የፖለቲካው ተዋስኦ ‹ከሐሳብና ምክንያታዊነት› የራቀ እንደነበር መረዳት ይቻላል፡፡ ታደለች ‹እንደ መውጫ› ላይ በዝርዝር እንዳስቀመጠችው የያትውልድ የፖለቲካ ተዋስኦ ለሐሳብ ልዕልና ቦታ የሌለው፣ ሐሳብን በሐሳብ ሳይሆን ሐሳብን በአፈሙዝ የሚገጥም፣ ሐሳብ እንደ ጦር የሚፈራ እንደነበር የሚያረጋግጡ ማሳያዎች ናቸው፡፡ የያ ትውልድ የፖለቲካ ተዋስኦ በ‹ሐሳብ-ጠል› የፖለቲካ ባህል ነበር የተራመደው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ ታደለች ሁሉ በውይይት፣ በንግግር፣ በሐሳብና ምክንያታዊነት የፖለቲካ ልዩነቶች እንዲፈቱ በፖለቲካው ንቁ ተሳታፊ የሆኑ ጉምቱ ፖለቲከኞችን ጭምር በርካቶች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የሚያቀነቅኑ፣ የሚወተውቱት ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹በጥይት ከመታኮስ በመረጃ መላኮስ የላቀ ጠቀሜታ አለው፡፡ በኃይል አጥቅቶ የበላይ ከመሆን በሐሳብ አሳምኖ አጋዥ መፍጠር ይበጃል፤›› ሲሉ የሚመክሩት ሽብሩ ተድላ (ፕሮፌሰር) ናቸው፡፡

ከቀደመው ጊዜ በተለየ በሕገ መንግሥት ደረጃ የተቀመጡ መብቶችና አስቻይ ሁኔታዎች ባሉበት አሁን ያሉት ፓርቲዎች በደርግ፣ ኢሕአፓና መኢሶን መንገድ ነው የፖለቲካ ተዋሶዎአቸው የተቃኘው፡፡ በቀድሞና በአሁን ፓርቲዎቻችን መካከል ይህ ነው የሚባል የፖለቲካ ተዋስኦ የለም ለማለት ያስደፍራል፡፡ ዛሬም የነቃውና የተደራጀውን የሚያሸንፈው ‘ባንክና ታንክ’ የታጠቀው ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የፖለቲካ ቋንቋችን ከሐሳብና ከምክንያታዊነት የራቀ እንዲሆን ያደረገው ‘ምቹ መደላደል ማጣት፣ የአስቻይ ከባቢ አለመኖር’ ከመሆን ያለፈ ያደርገዋል፡፡ ለሐሳብ ጠል ፖለቲካችን ከሌላ ማዕዘንም መፍትሔ ማፈላለግ ይጠይቃል፡፡

የአገራችንን ፖለቲካ ተዋስኦ እንደሚከታተልና እንደሚያነብ፣ በጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን (አስ)ተማሪ እንደሆነና የሚዲያው እንቅስቃሴ በቅርብ እንደሚከታተል ግለሰብ፣ ከአብዮቱ ዘመን እስካሁን ላለው የተዛነፈ የፖለቲካ ተዋስኦ ዋና ምክንያት የሆነው ሐሳብን ለመግለጽ ነፃነት፣ ለንግግር ነፃነትና ለፕሬስ ነፃነት ያለን ግንዛቤ እንደ ዜጋ፣ እንደ ማኅበረሰብ፣ እንደ ልሂቅም፣ እንደ ፖለቲከኛም፣ ወዘተ. ያልዳበረ መሆኑን ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እነዚህ ነፃነቶች የሰብዓዊ መብት ከመሆናቸው በላይ ጥብቅና የዳበረ ልምድ ይጠይቃሉ፡፡ ቪታሊ ማልኪን (Vitaly Malkin) ‹‹የንግግር ነፃነት የምንማረው፣ ከራሳችን ዓውድ ጋር የምናላምደው፣ ሁሌም ልናዳብረው የሚገባ ማኅበረሰብ ሠራሽ መብት ነው (ትርጉም የእኔ)›› ሲል ይበይነዋል፡፡ ማልኪን የንግግር ነፃነትን እንደ ማንኛውም የሕይወት ክህሎት ጊዜ ሰጥተን ልንማረው፣ ልናዳብረው የሚገባ ክህሎት አድርገን መውሰድ እንዳለብን በአፅንኦት ያሳስባል፡፡

ኢትዮጵያውያን በሐሳብ እጥረት ብዙም የማንታማ እንደሆነ በብዙኃኑ ደረጃ ስምምነት አለ፡፡ ለአገራችን፣ ለሕዝባችን የሚበጁ ምጡቅ አሳቢዎች አሉን፡፡ በሌላ አማርኛ ትልቁ ዕጦት ሐሳብና የአሳቢ አለመኖር አይደለም፡፡ የጎደለን ሐሳባችን በዳበረ የንግግር ነፃነት ክህሎታችን ተጠቅመን መግባባት፣ መተጋገዝ አለመቻላችን ነው፡፡ እንደ ምሳሌ ከዳኛው ማነው መጽሐፍ ልጥቀስ፡፡

ታደለች ለብርሃነ መስቀልና ለተስፋዬ ደበሳይ፣ ‹‹እኔ እኮ [ዘርዑን] በአካል አላውቀወም ያልኳቸው ጊዜ» ይኼን አሉኝ ብላ የጻፈችው ይህን ህፀፅ ወለል አድርጎ ነው የሚያሳየው። ‹‹አይ ተይው፣ ሴቶች ሊያስተውሉት የሚችል ዓይነት ሰው አይደለም፤›› በማለት ሁለቱም በአንድነት መልሰውልኛል በሚል ቃል በቃል በመጽሐፉ ሰፍሯል።

ወረድ ብሎም ተስፋዬ ደበሳይ ስለዘርዑ ክኸሸን አለኝ ያለችው በዚሁ መልኩ በመጽሐፉ ቀርቧል፡፡

አለባበሱ የአዳኝ ይመስላል። አንድ ትልቅ የቆዳ ጃኬት አለው። አውልቆት አያውቅም። ለአነጋገሩም ሆነ ለአካሄዱ ብዙ ደንታ የለውም። ፈረንጆች ‹‹Rough›› (ሥርዓት አልባ፣ ባለጌ) የሚሉት ዓይነት ሰው ነው።

‹‹ካለፈው ትምህርት እንውሰድ፣ በውይይትና በንግግር ሐሳብና ምክንያታዊነትን ዋስ በማድረግ የፖለቲካ ተዋስኦዎችን እንግራ፤›› የሚል ምክረ ሐሳብ ያዘለ፣ ለትውልድ በሚሻገር መጽሐፍ፣ ከ40 ዓመት በኋላ ህያው ምስክር በሆኑ እንስት በተጻፈ መጽሐፍ ይኼን የመሰለ አገላለጽ መጠቀም የሌላ ሳይሆን የንግግር ነፃነት ክህሎት ድህነትን የሚያሳይ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ በታደለች ብቻ ሳይሆን መሰል የያ ትውልድ አባላት የሚንፀባረቅ ከላይ ከላይ ‹ሐሳብና ምክንያታዊነት› የፖለቲካ ሰባኪነት ‹ሐሳብና ምክንያታዊነት› የነገሠበት የፖለቲካ ተዋጽኦ አራምዳለሁ የሚሉ ለምድ ለባሽ የሐሳብ አምባገነን አገሪቱ ላይ እንዲሠለጥን በር ከፍቶ፣ የአገሪቱን ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎታል፡፡ በቅጡ ያልዘጋናቸው፣ ብይንና ዳኝነት ያላገኙ የአብዮቱ ዶሴዎች አሁን ለተዘፈቅንበት፣ ለምንዳክርበት ሐሳብ ጠልና ኢምክንያታዊ ስሜታዊነት የሚጋልበው የፖለቲካ ተዋስኦ እርሾ፣ ቅኝትና መስመር ሆነው እያገለገሉ እንዳሉ የአደባባይ ሚስጥር ነው። እናም አዲስ ሥርዓት በአሮጌ ተዋስኦ አይመሠረትምና የአፈጁ የአብዮቱ ዶሴዎችን ዳኝነት እንስጣቸው! እንዝጋቸው! አዲስ ዶሴ ለአዲስ ሥርዓት እንክፈት!   

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...

እኛ ኢትዮጵያውያን ከየት መጥተን ወዴት እየሄድን ነው?

በአሰፋ አደፍርስ ኢትዮጵያውያን ከየትም እንምጣ ከየት እስከ 1445 ዓ.ም. እስላማዊና...

የሳባ መንደር

ሼባ ግሩፕ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሼባ/ሳባ የጉዞ ወኪል...

የበጀት እጥረት የፈተነው የአኅጉሩ የባህል ዘርፍ

የአፍሪካ አገሮች ቢያንስ ከበጀታቸው አንድ ፐርሰንቱን ለባህል ዘርፍ መዋል...